ለተመሳሳይ ሥራ እኩል ደመወዝ ክፍያ 7.9 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ በጀቱ ተካቷል
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለዘንድሮው በጀት ዓመት ተጨማሪ 27.89 ቢሊዮን ብር እንዲፀድቅለት ያቀረበውን ረቂቅ የበጀት አዋጅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶበት በዝርዝር እንዲታይ ለቋሚ ኮሚቴ መራ።
የመንፈቅ እረፍቱን አጠናቆ ወደ መደበኛ ሥራው ማክሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. የተመለሰው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በዚሁ ዕለት ከቀረቡለት አጀንዳዎች መካከል አንዱ የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ነበር፡፡ ተጨማሪ በጀቱ ያስፈለገበት ምክንያትም መንግሥት የጀመረውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማስቀጠል፣ ለተመሳሳይ ሥራ እኩል ደመወዝ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመክፈልና ለሴፍቲኔት አገልግሎት ወጪዎች ለማዋል መሆኑ ተገልጿል።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ከቀረበው የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ውስጥ ትልቁ ድርሻ ለኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ የሚውል ነው።
ለዚህም ሲባል ከቀረበው አጠቃላይ ተጨማሪ በጀት ውስጥ 18 ቢሊዮን ብር፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አሁን ከገጠሙት ተግዳሮቶች የሚላቀቅበትን የፖሊሲ ዕርምጃዎች ተግባራዊ በማድረግ ወደ ጤናማ ጉዞ ተመልሶ ዕድገቱ ቀጣይ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የደመወዝ ምጣኔ ሥርዓት እንዲኖር መንግሥት ለተመሳሳይ ዕኩል ደረጃ ላላቸው የሥራ ዓይነቶች እኩል ደመወዝ ለመክፈል፣ 7.9 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ በጀት ውስጥ ተካትቶ መቅረቡን ጠቁመዋል። የተቀረው ሁለት ቢሊዮን ብር ደግሞ ለሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የሚውል ነው።
ለቀረበው ተጨማሪ በጀት የገቢ ምንጭ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ዘንድሮ ከታክስ ይሰበሰባል ተብሎ ከተያዘው ተጨማሪ 20 ቢሊዮን ብር ገቢ ዋነኛው ሲሆን፣ ከውጭ አጋሮች የሚገኝ 7.9 ቢሊዮን ብር የቀጥታ በጀት ድጋፍና ዕርዳታ ሌላኛው የገቢ ምንጭ መሆኑ በረቂቁ ተመልክቷል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ለሁለተኛው አገር አቀፍ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ኃይጂን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ፣ እንዲሁም ለደብረ ማርቆስ ሞጣ የመንገድ ሥራ ማሻሻያና ማሳደጊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ፣ ከዚሁ ተቋም የተደረጉትን የብድር ስምምነቶች እንዲያፀድቅ ቀርቦለታል።
ለሁለተኛው አገር አቀፍ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ከሳዑዲ ልማት ፈንድ የተገኘው ብድር 240 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ግን ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ መሆኑ ተገልጿል። ለደብረ ማርቆስ ሞጣ መንገድ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከሳዑዲ ልማት ፈንድ የተገኘው ብድር ደግሞ 86 ሚሊዮን ዶላር ነው።
በተጨማሪም ለአዳማ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ የልቀት ማዕከል ማቋቋሚያ፣ ከኮሪያ ኢሞፖርት ኤክስፖርት ባንክ ጋር የተደረገ የብድር ስምምነት ለምክር ቤቱ ቀርቧል። ሁሉም የብደር ስምምነቶች የዕፎይታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመታት ውስጥ የሚከፈሉ እንደሆኑና ከአገሪቱ የውጭ ብድር ፖሊሲ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸው ተገልጿል።
ምክር ቤቱ የተጨማሪ በጀትና የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆቹን ለዝርዝር ዕይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።