Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የግብፅን ድብቅ ፍላጎት ማምከን የሚቻለው በጠንካራ ዲፕሎማሲና በፈጣን ዕርምጃ ነው

  የታላቁ የህዳሴ ግድብን ድርድር በታዛቢነት ለመርዳት በሚል ሰበብ ገብታ የስትራቴጂካዊ ፍላጎቷ መጠቀሚያ ለማድረግ የቃጣችው አሜሪካ ዕቅዷ ሲከሽፍ፣ አስተዛዛቢ ምክረ ሐሳብ ይዛ የቀረበችው ጀርመን ደግሞ ድርድሩን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመግፋት ተነስታለች፡፡ ከቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ ባለመላቀቅ የዓባይን ውኃ ለመቆጣጠር የምታሴረው ግብፅ ገመናዋ በተደጋጋሚ ይፋ ቢደረግም፣ አሁንም ኢትዮጵያን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለመወጠር በጀርመን በኩል የጎን ውጋት እየሆነች ነው፡፡ አሜሪካ ‹‹የዕብድ ገላጋይ ዱላ ያቀብላል›› እንደሚባለው ያላንዳች ኃፍረት ለግብፅ መወገኗን ባወጣችው መግለጫ ራሷን አጋልጣ፣ በአፍሪካ አኅጉር ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የውኃ ጦርነት ለመቀስቀስ የሚያስችል ክህደት ፈጽማለች፡፡ ጀርመን ደግሞ የአሜሪካ ሙከራ አልተሳካም በሚል ሰበብ በውጭ ኃይሎች የሚደረግ ድርድር ውዝግቡን ስለማያስቆም፣ ጀርመንና የአውሮፓ አጋሮቿ ለግብፅ የፋይናንስ ድጋፍ አድርገው ግብፅ ደግሞ ለኢትዮጵያ ካሳ እንድትከፍል ቢደረግ በማለት አዲስ አስገራሚ ሐሳብ ይዛ ብቅ ብላለች፡፡ ይህ የጀርመን አስገራሚ ሐሳብ ሁለቱ አገሮች ጦርነት ቢያስነሱና ቀውሱ ቢበረታ፣ አውሮፓ በስደተኞች እንዳትጥለቀለቅ የሚል ሥጋትም አለው፡፡ ከፍትሐዊና ከምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ በማፈንገጥ ግብፅ ኢትዮጵያን ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ እየተፈታተነች ነው፡፡ ይህንን የግብፅ ድብቅና ሴረኛ አካሄድ በጠንካራ ዲፕሎማሲና ብቃት ባለው ድርድር ማምከን የግድ ነው፡፡

  ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲውን ዘርፍ ብቃት ባላቸውና የዘመኑን አስተሳሰብ በሚገባ በሚረዱ ባለሙያዎች ማጠናከር አለባት፡፡ የዲፕሎማሲው ዘርፍ ብቃት የሌላቸውና ከፖለቲካ ሹምነት የተገለሉ ግለሰቦች መጦሪያ ወይም መጣያ መሆን የለበትም፡፡ በሙስና፣ በአቅም ማነስና በጥቅም ቡድንተኝነት ግለሰቦችን ዲፕሎማሲው ዘርፍ ውስጥ መሰግሰግ አገርን አቅም አልባ ማድረግ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አላስፈላጊ ድርጊት ኢትዮጵያ ብዙ የተጎዳች መሆኑ አየታወቀ፣ አሁንም አክሳሪው ድርጊት መቀጠሉ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል መረዳት ይገባል፡፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የሚታሙት በቋንቋ ክህሎት ማነስና በዲፕሎማሲ ጥበብ አለመካን ነው፡፡ ምንም እንኳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጪ ዲፕሎማቶች እየታዩ ቢሆንም፣ የዚያኑ ያህል ግን ተስፋ አስቆራጭ ግለሰቦች ሲሾሙ ማየት ያስገርማል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት በተቻለ ፍጥነት ራሱን ያርም፡፡ በመስኩ የተካኑ ባለሙያዎችን በማፈላለግ ምክረ ሐሳብ ይቀበል፡፡ የግብፅ ዲፕሎማቶች በተሾሙባቸው አገሮች የእያንዳንዱን ፖለቲከኛና ሹመኛ ቢሮ እያንኳኩ፣ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ጥረት ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ግብፅ ለአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲዋ ማስፈጸሚያ ሁነኛ መሣሪያ ስትሆን፣ በምትኩ ጥቅሟ እንዲከበርላት ጠንክራ በመሥራቷ ነው በህዳሴ ግድብ ድርድር ድጋፏን ያገኘችው፡፡ ኢትዮጵያም በአካባቢው ተሰሚነት ያላት አገር እንደ መሆኗ መጠን፣ እጅን አጣጥፎ ‹እውነት ያለው እኛ ዘንድ ነው› ማለት አያዋጣም፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መጠንከርና በበሳል ዲፕሎማሲ ልቆ መገኘት የግድ ነው፡፡ አቅም ያለው ተደራዳሪ መሆን የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባላት እስካሁን ባከናወኗቸው ተግባራት ሊመሠገኑ ይገባል፡፡ በቡድን መሪው አማካይነት በተደጋጋሚ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች የግብፅን ተደራዳሪዎች በሚገባ ገትረው መያዝ ችለዋል፡፡ ከማን ጋር እየተደራደሩ እንደሆነ በሚገባ በማወቃቸውም ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ችለዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ መንግሥት ይህንን ቡድን በሚገባ ማጠናከር አለበት፡፡ በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ የውኃና የጂኦ ፖለቲካ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ የተጠናከረ የመከራከሪያ ሰነድ፣ እንዲሁም የመደራደሪያ የስምምነት ረቂቅ ድረስ ማዘጋጀት መቻል አለበት፡፡ ከእነዚህ ባለሙያዎችና ዲፕሎማቶች በተጨማሪ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታ የተቸራቸው የሕግ ባለሙያዎችን ወሳኝ በሚባሉ አገሮች በማሰማራት ከፍተኛ የማግባባት ሥራ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በዓለም የተመሠከረላቸው የውጭ አማካሪ ድርጅቶችን በመቅጠር ጭምር የማግባባት ሥራው መጠናከር አለበት፡፡ እያንዳንዷን የግብፅ ዕርምጃ ከመከተል ባለፈ፣ ቀድሞ በመሄድ ሴራዋን ማክሸፍ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ለባለሙያዎችና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምክረ ሐሳብ ላላቸው ኢትዮጵያዊያን በራቸውን መክፈት ይኖርባቸዋል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ዳር ማድረስ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ተግባር እንደሆነ ታውቆ፣ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ አስተዋጽኦቸውን የሚያበረክቱበት ምኅዳር መከፈት ይኖርበታል፡፡ በተለመደው ችላ ባይነት፣ መዘናጋትና መጠባበቅ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ እንቅልፍ የሚነሳ ከፍተኛ ጥረት ያስፈልጋል፡፡

  በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ኢትዮጵያ በግብፅ የደረሰባት የዘመኑ ፈተና ብቻ ሳይሆን፣ ከግንባታው በፊት በነበሩ የተለያዩ መንግሥታት ወቅት ከፍተኛ በደሎች ተፈጽመውባታል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የነበረው ችግር ከግብፅ ጋር በእኩል ደረጃ መመጣጠን አለመቻል ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ ሲበሰር የነበረው የሕዝቡ የዘመናት የቁጭት ስሜት መቼም አይረሳም፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ፕሮጀክት ለመሆኑ የጋራ መግባባት በመፈጠሩ፣ በውጭ በተቃውሞ የነበሩ ኃይሎች ሳይቀሩ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ተሳስተው እንኳ በግድቡ ላይ ነቀፌታ ሲሰነዝሩ ቢታዩም፣ አሁን ግን ስህተታቸውን አርመው የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ ይህ አጠር ያለ ምሳሌ የሚያሳየው ኢትዮጵያዊያን ግድቡን እንደ ብሔራዊ ምልክታቸው እንደሚቆጥሩት ነው፡፡ መንግሥት ለአሜሪካ አደራዳሪነት ይሁንታ ሰጥቶ የተፈጸመውን ክህደት በማስተዋል፣ ከመጨረሻው ስብሰባ ቀርቶ አገራዊ ምክክር ማድረጉ ከስህተቱ ለመማሩ እንደ ማሳያ ይቆጠራል፡፡ አሁን ግን ይህንን ብሔራዊ ፕሮጀክት ዳር ለማድረስ በጠንካራ መሠረት ላይ መቆም ይኖርበታል፡፡ በሳልና ጠንካራ ዲፕሎማቶች፣ የተካኑ የውኃና የጂኦ ፖለቲካ ባለሙያዎች፣ አሉ የተባሉ የሕግ ባለሙያዎችና ሊጠቅሙ የሚችሉ የተለያዩ ዘርፎች ልሂቃንን ለዚህ ዓላማ ማሠለፍ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ግብፅ አንዱ አልሳካ ሲላት ሌላ ግንባር እየፈጠረች በገዛ ራሷ ዛቢያ ውስጥ ስታሽከረክረን የምትጎዳው አገራችን ናት፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግና በሞራላዊ አስተሳሰብ ብቻ ስንተማመን፣ ራሳችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከተለያዩ ጫናዎች የማላቀቅ ኃላፊነት እንዳለብን መገንዘብ አለብን፡፡ መንግሥትም ልማዳዊውንና ኋላቀሩን አሠራር በመሻር፣ ለዘመኑ የሚመጥን ተግባር ለማከናወን ብርቱና ንቁ ይሁን፡፡ ጥንካሬ የሚገኘው በዚህ መንገድ ነው፡፡

  በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው ከብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ አገሮች ከሌሎች ጋር በሚኖሯቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የሚያሰሉት ጥቅሞቻቸውን ነው፡፡ ይህ በየትም ሥፍራ የሚያጋጥምና መሆንም ያለበት ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ መስተጋብር ውስጥ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ በማተኮር መንቀሳቀስም ብልህነት ነው፡፡ የዓረብ ሊግ አባል አገሮች ለግብፅ ሲወግኑ ጥቅማቸውን አስልተው ነው፡፡ እነ እከሌ ለምን ከግብፅ ጋር አበሩ ተብሎ ቁዘማ ውስጥ መግባት ሞኝነት ነው፡፡ ይልቁንም 55 አባል አገሮች ያሉትን የአፍሪካ ኅብረት መጠቀምና መብትን ማስከበር የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ይረዳል፡፡ ግብፅ የአሜሪካ ድርድር አለመሳካት ሲያሳስባት የዓረብ ሊግ ድጋፍን በመጠየቅ ሳትቆጠብ፣ ጀርመንን ጎትታ ወደ ድርድር ለማምጣት ጥረት ማድረጓን አለመጠርጠር የዋህነት ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ በዙሪያው ሆነው የሚያማክሩት በሙሉ የግብፅን ፍጥነትና ተለዋዋጭነት በአርምሞ ከመመልከት ይልቅ፣ የአፍሪካ ኅብረትንና የዓባይ ተፋሰስ የራስጌ አገሮችን ለማንቀሳቀስ ይፍጠኑ፡፡ አዝጋሚው ዲፕሎማሲና ቀርፋፋው ቢሮክራሲ ለዘመናት ከተጣባው ድብርት ይላቀቅ፡፡ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን በፍትሐዊነት መጠቀም የምትችለው በሚያንቀላፋ አሠራር ሳይሆን፣ እጅግ በጣም ፈጣንና ቅጽበታዊ ውሳኔ ሰጪነትን በመካን ነው፡፡ የግብፅን ድብቅ ፍላጎት ማምከን የሚቻለው በዚህ ቁመና ላይ በመገኘት ብቻ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...