ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ከታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ጋር ለመነጋገር የሚያስችላትን አዲስ የውይይት ሰነድ እንዳዘጋጀች፣ ሰነዱም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ታወቀ።
በአዲስ ይዘት የተዘጋጀው የድርድር ሰነድ በኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን፣ በብሔራዊ የባለሙያዎች መማክርት፣ ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ የሕግና የውኃ ምሕንድስና ባለሙያዎች፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሙያዎች በጋራ መረቀቁን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የድርድር ሰነድ ለግብፅና ለሱዳን ብቻ እንደሚቀርብ፣ ነገር ግን በሦስቱ አገሮች ስምምነት መሠረት ሌሎች አጋሮች በድርድሩ ሚና እንዲኖራቸውም ክፍት መደረጉን ከመረጃው መረዳት ተችሏል።
የተዘጋጀው አዲስ ሰነድ የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ ድርድር የማታደርግባቸውን ጉዳዮች ለይቶ ማስቀመጡንና የኢትዮጵያን የማያወላዳ አቋም የያዘ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በግድቡም ሆነ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን ጥቅም የሚያስከብርና አሳልፎ የማይሰጥ እንደሆነ፣ የታችኞቹ የተፋሰስ አገሮችን ተጠቃሚነትም በዓለም አቀፍ መርሆች መሠረት የሚያረጋግጥ፣ በሦስቱ አገሮች መካከል ትብብርና መልካም ግንኙነትን የሚያሰፍን እንደሆነ ምንጮች አክለዋል።
በዚህ ሰነድ መነሻነት በሚደረገው ድርድር የሚመነጨው የመፍትሔ ሐሳብ ምን መምሰል እንደሚገባው፣ አመላካቾችንም ያስቀመጠ እንደሆነም ምንጮች አስረድተዋል።
ሰነዱን መነሻ በማድረግ የሚደረገውን ድርድር ለሦስቱም አገሮች ቅርብ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት እንዲመራ በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን የገለጹት ምንጮች፣ መንግሥት ይህንን ዕውን ለማድረግ እየጣረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ እንዲያደራድሩ ኢትዮጵያ የጠየቀች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ይህንኑ የመንግሥታቸውን ፍላጎት ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም። በዚህ ወቅት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ፕሬዚዳንት ራማፎዛ ይህንኑ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት በወቅቱ እንደተናገሩት የኢትዮጵያን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር መነጋገራቸውን፣ ከእሳቸውም በጎ ምላሽ እንዳገኙ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ራማፎዛ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሆነው ለአንድ ዓመት እንዲያገለግሉ በቅርቡ መመረጣቸው ይታወሳል። ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ አኅጉር ያሉ የፖለቲካ ቀውሶችንና ግጭቶቸን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ የገለጹ ሲሆን፣ የሊቢያን ቀውስ ኃያላን አገሮች ጣልቃ ገብተው እያባባሱት እንደሆነ በማውሳት ጉዳዩን ለአፍሪካውያን እንዲተውት አሳስበው ነበር።
ግብፅ በአሁኑ ወቅት የዓረብ አገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ አብረዋት እንዲቆሙ ሰፊ የማግባባት ሥራ ላይ መጠመዷን መረጃዎች ያመለክታሉ። የግብፅ የዘመቻ አካል መሆኑ በይፋ ባይረጋገጥም፣ ጀርመን የአውሮፓ ኅብረት አጋሮቿን በማስተባበር ለግብፅ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ፣ ግብፅ ደግሞ ለኢትዮጵያ ካሳ እንድትከፍል አዲስ የድርድር ሐሳብ ይዛ መቅረቧ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን ከማስገረም አልፎ አስቆጥቷል፡፡ አሜሪካ ድርድር ለማመቻቸት ብላ ቀጥታ ጣልቃ በመግባቷ ኢትዮጵያ ከድርድሩ ማፈግፈጓ አይዘነጋም፡፡