Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበማክስ አውሮፕላን ላይ የተከሰቱ የቴክኒክ ግድፈቶችን የምርመራ ሪፖርት አመለከተ

በማክስ አውሮፕላን ላይ የተከሰቱ የቴክኒክ ግድፈቶችን የምርመራ ሪፖርት አመለከተ

ቀን:

አደጋው የደረሰበት አንደኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ ውሏል

እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ኬንያ በማቅናት ላይ እንዳለ በገጠመው ድንገተኛ አደጋ ቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ የወደቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ላይ የቀረበው የምርመራ ሪፖርት፣ በአውሮፕላኑ ላይ የታዩ በርካታ የቴክኒክ ግድፈቶችን አመለከተ፡፡

ተጠሪነቱ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር የሆነው የአደጋ ምርመራ ቢሮ ለአንድ ዓመት ሲያካሂድ የቆየውን የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ጊዜያዊ ሪፖርት፣ በሚኒስቴሩ አማካይነት ሰኞ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ 

ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአውሮፕላን አደጋና የአደጋ አጋጣሚ ምርመራ እንዴት መካሄድ እንዳለበት የሚገልጸው አንቀጽ 13፣ የአውሮፕላን አደጋ በተከሰተ በ30 ቀናት ውስጥ የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርት መውጣት እንዳለበት፣ እንዲሁም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዋናው ሪፖርት ይፋ መደረግ እንዳለበት ይገልጻል፡፡

የአውሮፕላን አደጋ ምርመራን በመሪነት ማከናወን ያለበት አደጋው የደረሰበት አገር በመሆኑ፣ የአደጋ ምርመራ ቢሮ በበረራ ቁጥር ET 302 ላይ የተከሰተውን አደጋ በቀዳሚነት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርቱን በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ሕግ መሠረት፣ በ30 ቀናት ውስጥ መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ 

የአደጋ ምርመራ ቢሮው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቴክኒክ አማካሪነት፣ የአሜሪካ ናሽናል ትራንስፖርት ሴፍቲ ቦርድ የአውሮፕላኑን አምራች አገር በመወከል፣ የፈረንሣይ ቢኢኤ የበረራ መረጃ ቋትና የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል መቅረፅ ድምፅ (በተለምዶ ጥቁር ሳጥን የሚባለውን) መሣሪያዎች መረጃ በመገልበጥና በመተንተን በአደጋ ምርመራ ሥራው ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ሪፖርቱ መውጣት የነበረበት ቢሆንም፣ ቀሪ ሥራዎች በመኖራቸው የአደጋ ምርመራ ቢሮ ጊዜያዊ ሪፖርት ለማውጣት ተገዷል፡፡

በአምድዬ አያሌው ፈንታ (ኮሎኔል) የሚመራው የአደጋ ምርመራ ቢሮ ያወጣው ጊዜያዊ ሪፖርት በ130 ገጾች ተቀነባብሮ የቀረበ ነው፡፡ ሪፖርቱ ለስድስት ደቂቃ ያህል በአየር ላይ ስለቆየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢ737 ማክስ 8 አውሮፕላን አነሳስ፣ የገጠመውን ፈተና፣ የአውሮፕላኑን ይዘትና ታሪክ፣ የአብራሪዎቹን ትምህርትና ሥልጠና በዝርዝር ይዟል፡፡

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በሰላም መነሳቱን፣ ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስተግራ በኩል የሚገኘው ‘አንግል ኦፍ አታክ’ በመባል የሚታወቀው የበረራ መረጃ መሣሪያ የተሳሳተ መረጃ በማንበቡ ምክንያት፣ ‘ኖዝ ዳይቭ ትሪም’ የሚባለው አውሮፕላኑን ወደ ታች የሚመልሰው መሣሪያ በራሱ ትዕዛዝ መሥራት መጀመሩ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ይህን ተከትሎ የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያው በተከታታይ አውሮፕላኑን ወደ መሬት መድፈቁን ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይልና የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት በፈልጎ ማዳን ሥራ ላይ መሠማራታቸውን፣ አውሮፕላኑ የወደቀበት ሥፍራ ኢጆሬ በተባለ አካባቢ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

አንድ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ሥራ የመረጃ ማሰባሰብ፣ ትንተና፣ መደምደሚያና ምክረ ሐሳብ የማቅረብ የሥራ ክፍሎችን አካቶ የያዘ ነው፡፡ ጊዜያዊ ሪፖርቱ የትንተና ሥራ በመካሄድ ላይ መሆኑንና በዋናው ሪፖርት ላይ እንደሚካተት ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ሪፖርቱ በመደምደሚያው ላይ ዘርዘር ያሉ ግኝቶች አሥፍሯል፡፡

አደጋ የደረሰበት ቢ737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንደነበረው፣ በሲቪል አቪዬሽን ደንብና አሠራር መሠረት የተጠገነ እንደነበርና ከበረራ ET 302 በፊት የሚታወቅ የቴክኒክ እክል እንዳልነበረበት ይገልጻል፡፡

አብራሪዎች ከቢ737 NG አውሮፕላን ወደ 737 ማክስ አውሮፕላን ሽግግር በሚያደርጉበት ወቅት፣ በአምራች ኩባንያው የተሰጠው የሥልጠና መርሐ ግብር በቂ ሆኖ እንዳልተገኘ ይጠቁማል፡፡ ኤምካስ የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያ ‘አንግል ኦፍ አታክ’ በተባለ መሣሪያ በሚያቀርብለት መረጃ ብቻ ተመሥርቶ መሥራቱ፣ የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያውን ለስህተት እንደሚያጋልጠው በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በምክረ ሐሳቡ ላይ ኤምካስ የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ በአንድ መሣሪያ መረጃ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ከሚሠራ በሁለት መሣሪያዎች መረጃ ቢታገዝ፣ ወይም የመጠባበቂያ መሣሪያ ቢበጅለት የሚል ሐሳብ ተቀምጧል፡፡

አብራሪዎች ከቢ737 ወደ 737 ማክስ አውሮፕላን ሽግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የሚሰጠው ሥልጠና፣ የምሥለ በረራ ሥልጠና እንዲያካትት የሚሉና የመሳሰሉ ምክረ ሐሳቦች ተጠቁመዋል፡፡

በአደጋው የስምንት የአውሮፕላኑ ሠራተኞች (ሁለት አብራሪዎች፣ አምስት የበረራ አስተናጋጆችና አንድ የበረራ ደኅንነት ሠራተኛ) እና የ149 መንገደኞች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡ የመጨረሻው የአደጋ ምርመራ ሪፖርት በጥቂት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢ737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ የደረሰበት አንደኛ ዓመት፣ እንዲሁም በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ መንገደኞች መታሰቢያ የተለያዩ ዝግጅቶች ተከናውነዋል፡፡

እሑድ የካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. አደጋው በተከሰተበት ሥፍራ የአካባቢው ነዋሪዎችና ካህናት በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ መንገደኞችን በፀሎት ያሰቡ ሲሆን፣ ማክሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የሟች ቤተሰቦች አደጋው በተከሰተበት አዳዲ መንደር በመገኘት ሙት ዓመት አውጥተዋል፡፡ የአየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማኅበር ማክሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በማኅበሩ ቅጥር ግቢ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...