Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጎማ ኦዲት የሚደረግበት ሥርዓት የሚያበጅ ሕግ ለፓርላማ ቀረበ

ለክልሎች የሚሰጥ የበጀት ድጎማ ኦዲት የሚደረግበት ሥርዓት የሚያበጅ ሕግ ለፓርላማ ቀረበ

ቀን:

የፌዴራል መንግሥት በየዓመቱ ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጎማ፣ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ኦዲት ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

የሕግ ሰነዱ የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የወጣ የነጠላ ኦዲት ረቂቅ አዋጅ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ አዋጁ ያስፈለገበትን ምክንያትና ፋይዳ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ማክሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ አቅርበዋል።

የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጋፍ ኦዲት የማድረግ ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 94(2) እንደተሰጠው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ክልሎች የራሳቸውን በጀት ኦዲት የማድረግ ሥልጣን እንዳላቸው አፈ ጉባዔው በሰጡት ማብራሪያ አስታውሰዋል።

የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጎማ በሥራ ላይ መዋሉን የመቆጣጠር ሕጋዊ ኃላፊነቱን ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌና ከክልሎች መብት ጋር በተጣጣመ መንገድ ለማከናወን የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ፣ ረቂቅ አዋጁ ለምክር ቤቱ መቅረቡን አስረድተዋል።

የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የወጣ የነጠላ ኦዲት አዋጅ በሚል ስያሜ ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የአገሪቱ ሀብት በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ መዋሉን ለመቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ፣ የቁጥጥር ሥርዓቱ የጊዜ ብክነትና ድግግሞሽን በማስቀረት እንዲፈጸም የሚያስችል እንደሆነ አፈ ጉባዔው ተናግረዋል።

ከክልሎች ሥልጣን ጋር ተያይዞ በተነሳ ውዝግብ ሳቢያ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ ኦዲት ማድረግ ካቆመ በርከት ያሉ ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በ2008 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ በፓርላማ የፀደቀው በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ተቋሙ ክልሎችን ኦዲት የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱ የሚደነግገው አንቀጽ እንዲወጣ ተደርጓል።

ይሁን እንጂ በ2011 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በድጋሚ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ደግሞ፣ ተቋሙ ክልሎችን ኦዲት የማድረግ ሥልጣን እንዳለው የሚደነግግ አንቀጽ ተካቶበት ፀድቋል።

መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ የቀረበው የነጠላ ኦዲት አዋጅ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በራሱ፣ እንዲሁም ከክልል የኦዲት ቢሮዎች ጋር በመተባበር ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ለታለመለት ሥራ መዋሉን ለማረጋገጥ፣ ክልሎቹ ኦዲት የሚደረጉበትንና የፌዴራል ዋና ኦዲተርም ይህንን የሚያረጋግጥበት ሥርዓት የሚያበጅ ነው።

ረቂቅ አዋጁ ለምክር ቤቱ በቀረበበት በዚህ ስብሰባ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ከምክር ቤቱ አባላት የተነሳ ባይሆንም፣ ረቂቁ ለዝርዝር ዕይታ ለመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት፣ እንዲሁም በተባባሪነት ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...