የዓለም ሴቶች ቀን ቃቄ ውርድወትን በመዘከር በወልቂጤ ተከብሯል
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ችግሮች በድል እንድትወጣና በብልሀት እንድትሻገር ያስቻሉ በርካታ የቀደሙ ሴቶችን በመከተል የአሁኑ ትውልድ ሴቶችም ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና ነጥቀው እንዲያወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡
የዓለም ሴቶች ቀን አስመልክቶ ከ154 ዓመታት በፊት የሴቶች መብት ይከበር ዘንድ የተሟገተችውን የቃቄ ውርድወትን በመዘከር የካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በወልቂጤ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በቀደምት ጊዜ ከገጠሟት ችግሮች ለማውጣት የአብርሃና አፅብሃ እናት ንግሥት አህዋ፣ እነ እቴጌ ምንትዋብ፣ እቴጌ ጣይቱና ዘውዲቱ በብልሃት የተሞላ ምክርና ውሳኔ ያሳልፉ እንደነበር አስታውሰው፣ ኢትዮጵያን ከአደጋ መዘው እንዳወጧትና እንዳሻገሩዋት ቀደምት ሴቶች፣ ሴቶችም በአገሪቱ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ ከመሪዎቻቸው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው መሥራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
በተደጋጋሚ ስለሴቶች ጭቆና ብቻ ስለሚወራ እንጂ በተለያዩ ዘመናት ላይ የነበሩ ሴቶች ለሴቶች መብት መከበርም ሆነ አገርን ለማቅናት የጀርባ አጥንት ሆነው ትልቅ ጫና መጫወታቸውን ያወሱት ሚኒስትሯ፣ ሴቶች አቅጣጫ መጠቆም ለባሎችና ልጆች መምከር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹የቃቄ ውርድወት፣ የጣይቱ፣ የዘውዲቱና የንግሥት እሌኒ ልጆች ከሆንን ኢትዮጵያን ከገጠማት ችግር ነጥቀን ማውጣት አለብን፣ የቀደሙትን እናቶቻችንን ታሪክ የምንደግምበት ጊዜም አሁን ነው፤›› ብለዋል፡፡
የቃቄ ውርድወት ከ154 ዓመታት በፊት የሴቶች መብት ይከበር ዘንድ የተሟገተች ኢትዮጵያዊት በመሆኗ ‹‹እንኳን ለ154ኛው የሴቶች ቀን አደረሳችሁ›› ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት ሒሩት (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የራሷ ታሪክ ያላት 44 ዓመት ሳይሆን ከ154 ዓመት በፊትም ለሴቶች መብት የታገለች ሴት እንደነበረች ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሴቶች የሴትነት ባህላቸውና ሰብዕናቸው ባይኖር ኖሮ ምን ዓይነት ዓለም ይኖር ነበር? ሲሉ በመጠየቅም እናት ከወለደች በኋላ ልጆቿን በአካልም፣ በሥነ ምግባርም፣ በማሳደግ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ጀግና ወንድ ጀርባ ያላትን ሚና ከፊት በማውጣት ያላትን ሚና አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ሁሌም ከውጭ የተገኘውን ብቻ ሳይሆን የራስ የሆነውን ሀብት እንዘክር በማለት፣ በዓለም ለ109ኛ በኢትዮጵያ ለ44ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሴቶች ቀን የቃቄ ውርድወትን ታሪክ በመዘከር እንዲከበር መደረጉን የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ ተናግረዋል፡፡ የቃቄ ውርድወት ትምህርት ባልነበረበት፣ ሕገ መንግሥት ባልተደነገገበት፣ የጨለማ ቀን ሴቶች ነፃነት እንዲያገኙ ዛሬ በተለይ ለተደነገጉ የሴት መብቶች መከበር ቀድማ አሻራ ያሳረፈች ጥቁር ኢትዮጵያዊት ነች ብለዋል፡፡
ሴቶች ከፍ ብለው በማይናገሩበት ሰዓት በሴት ላይ የተጣለውን አንቂት (እርግማን) እንዲነሳና ከአሥር ያላነሱ የሴት መብቶች እንዲከበሩ የጠየቀች ሴት ናት፡፡
ካነሳቻቸው የመብት ጥያቄዎች ሴቶች ለማያውቁት ወንድ እንዳይዳሩ፣ በፍርድ ሒደት ሥርዓት አብረው ሽንጎ እንዲቀመጡ፣ ባላቸውን መፍታት ከፈለጉ እንዲፈቱ የሚሉት ከጠየቀቻቸው የመብት ጥያቄዎች መካከል ናቸው፡፡
ይህች ሴት በዚያን ዘመን ለመብት ተሟጋችና አሸናፊ ከነበረች አሁን ላይ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ታሪክ ለማስተላለፍ፣ በዚያ ዘመን ልዕለ ኃያላን አገሮች ያልደፈሩትን የመብት ጥያቄ የደፈረችዋን ሴት ታሪክ ከቴአትር ባለፈ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ እንደሚገባ ወ/ሮ መሠረት ተናግረዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበርና ከጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ጋር ባዘጋጀው መድረክ የቃቄ ውርድወት በዓለም እንድትታወቅ የተወለደችበትን በዞኑ የሚገኘውን የምሁር አክሊል ወረዳ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እንደሚሠራ ተነግሯል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የወልቂጤ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር እያስገነባ የሚገኘውን ባለስምንት ወለል የንግድ ማዕከል በቃቄ ውርድወት ስም ሰይሟል፡፡
31,800,000 ብር ይፈጃል የተባለውን የንግድ ማዕከል በቃቄ ውርድወት የተሰየመው ሴቶች በየትኛውም ዘርፍ ተሰማርተው ከሠሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ከውርድወት ታሪክ መማር እንደሚቻል ለማሳየት መሆኑን የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ እንግዳዬ እሸቴ ተናግረዋል፡፡
ከማኅበሩ ቁጠባ፣ ከተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ በማግኘትና የባንክ ብድር ተጠቃሚ በመሆን የሚገባው ሕንፃ የሴቶች ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የወጣቶችና ሕፃናት መዝናኛና ሌሎችንም አገልግሎቶች የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል፡፡
ማኅበሩ ለግንባታ የሚሆነው 3,000 ካሬ ሜትር ብቻ እንደተፈቀደለት ያስታወቀ ሲሆን፣ አሁን እጁ ላይ በገባው ከፊል ሥፍራ ላይ ግንባታውን አስጀምሯል፡፡
ሕንፃው ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሴት ነጋዴዎች የመነገጃ ቦታ ችግርን ይቀርፋልም ተብሏል፡፡ የወልቂጤ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር በ1992 ዓ.ም. ቢመሠረትም በገጠመው ችግር ምክንያት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው ከ2004 ዓ.ም. ወዲህ ነው፡፡