Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየድሉ ትውስታ

የድሉ ትውስታ

ቀን:

በተመስገን ተጋፋው

“የካራማራ ድል ኢትዮጵያውን ለአገራቸው ሉዓላዊነት ያላቸውን ቀናዒነት ቀፎው እንደተነካ ንብ በኅብረት በመቆም ገልጸውታል፡፡ ለሰንደቃቸው ያላቸውን ልባዊ ፍቅር ውድ የሆነውን የሕይወት መስዋዕነት በመክፈል በደማቅ የደም ቀለም ጽፈውታል፡፡ ለዘመናት የተገመደው የማይጠበስ አንድነታቸውን በደም ፍሳሻቸውና በአጥንት ፍላጫቸው በድጋሚ በፅኑ መሠረት ላይ ገንብተውታል፡፡”

ይህ ኢትዮጵያ በ1970 ዓ.ም. የካቲት 26 ቀን በወራሪው የሶማሊያ ጦር ላይ ድል የተቀዳጀችበት 42ኛ ዓመት የካቲት 26 እና 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በተከበረበት ወቅት ድሉን በሚዘክረው መሰናዶ ላይ ከተስተጋቡት ኃይለ ቃሎች አንዱ ነው፡፡

‹‹ታላቋ ሶማሊያ›› ቅዠት የተለከፉት የሶማሊያ መሪዎች እነዚያድ ባሬ በምሥራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሜትር ድረስ ዘልቀው ተቆጣጥረው ነበር፡፡ መደበኛውና ሕዝባዊው ሠራዊት በወሰዱት አጸፋ የሶማሊያ ጦር በጅግጅጋ ካራማራ ተደምስሷል፡፡  የዚህን ታላቅ ድል ገድል በዕለተ ቀኑ በአዲስ አበባ ትግላችን ሐውልት ሥር፣ በኢትዮጵያና ኩባ ወዳጅነት ፓርክ እንዲሁም እሑድ የካቲት 29 በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ የቀድሞ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታና በዓውደ ውጊያው የዋሉ የቀድሞ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

ለገድሉ ክብር በተዘጋጀው ጽሑፍ እንደተገለጸው፣ በምሥራቅ 700 ኪሎ ሜትር፣ በደቡብ 300 ኪሎ ሜትር ጣልቃ በመግባት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቷን በኃይል የተቆጣጠረችውን ሶማሊያን ለማስወገድ ከተፈጸሙት ተዘርዝረው ከማያልቁ የሠራዊቱ ጀብዶች መካከል ለአብነት ያህል፣ የሐረር አካዴሚና የበረራ ትምህርት ጥምር ምሩቅ የሆኑ የአዲስ አበባው ፍሬ የአየር ኃይሉ ነብር ጀግናው ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ በF5-E ጀታቸው አማካይነት በአየር ላይ ውጊያ አምስት የሶማሊያ ሚግ 21 ጀቶችን በመምታት ከአየር ወደ መሬት አራግፈዋቸዋል፡፡ 

የድሉ ትውስታ

 

ጄኔራል ለገሰ በጠላት ተይዘው ለ11 ዓመታት በሶማሊያ እስር ቤቶች የስቃይ ሕይወት አሳልፈው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ለወደር የለሽ የጀግንነት ሥራቸውም በጊዜው የአገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ የሆነው የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የጀግና ሜዳይ ተሸልመዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ሌላው ጀግና የእናት አገር ጥሪ ሰምቶ በለጋ ዕድሜው ከቀድሞ ወለጋ  ክፍለ አገር አሶሳ አውራጃ ቤጊ ወረዳ የመጣው ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ነው፡፡  ሻለቃ ባሻ አሊ በኡሸሪፍ ግንባር ሦስት የጠላት ታንኮችን በእጅ ቦምብ በማቃጠል በግንባሩ ለነበረው ድል ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡ ለዚህም ሥራው የላቀ የጀብድ ሜዳይ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአራቱም ማዕዘናት የብሔርና የሃይማኖት አጥር ሳያግደው በጠነከረ የአንድነት መንፈስ በመላበስ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ ነው ይህንን ታላቅ ድል ማስመዝገብ የተቻለው ይላል የሚለው ዝክረ ነገሩ፣ ለድሉ ዕውንነት ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪም የኩባውያን፣ የሩሲያውያንና የደቡብ የመን ሠራዊት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለውበታል፡፡

የካራማራ ድል መዳረሻ

‹‹ሆ ብሎ ተነሳ ሠራዊቱ

ጉዞ ጀመረ እየዘመረ

አቀበቱን ጋራ ቁልቁለት

ወጣ ወረደ ሠራዊቱ

አገሬ መመኪያ ክብሬ

አትደፈርም እናት አገሬ… ›› እያለ እየዘመረ፣ እየፎከረ የካቲት 23 ቀን 1970 ዓ.ም. የዓድዋ ድል ዕለት የኢትዮጵያ ጦር በጭናቅሰንና በቆሬ በኩል ወደ ጅግጅጋ አቅጣጫ የተጠናከረ ቅንጅታዊ የጎህ ማጥቃት ዘመቻ ከፈተ፡፡ የሶማሊያ ጦርም ጥቃት ይመጣብኛል ብሎ ባልጠበቀው አቅጣጫ በመዋጋቱ ተደናገጠ፡፡ ጅግጅጋንም ላለመልቀቅ ተሟሟተ፡፡ ሶማሊያ በዚህ መደናገጥ ውስጥ እያለች ከጀልዴሳ ግንባር ሌላ ጥቃት ተከፈተባት፡፡ የሶማሊያም ሠራዊት ጅግጅጋን ከለቀቀ ትልቅ የሞራል ውድቀት እንደሚገጥመው ያውቃል፡፡ በመሆኑም ከጅግጅጋ በስተ ምዕራብ በኩል ባለው ካራማራ ተራራ ላይ ማዘዣ ጣቢያውን በመሥራት በከፍተኛ ደረጃ ተከላከለ፡፡ ሆኖም በለስ አልቀናውም፡፡

ጥቃቱ በሁሉም ግንባር የተከፈተ በመሆኑ አጋዥ ሠራዊት ከየትም ማንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ በውጤቱም የካቲት 26 ረፋድ ላይ በካራማራ ከባድ ሽንፈት ተጎነጨ፡፡ በውጤቱም ከሞትና መቁሰል የተረፈው የጠላት ሠራዊት መሣሪያውን እያንጠባጠበ ጅግጅጋን በመልቀቅ ወደ ሐርጌሳ መስመር አፈገፈገ፡፡

እሑድ የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. ላይ በአካባቢው የነበረ ሠራዊት ወድቃና ተዋርዳ የነበረችውን ሰንደቅ ዓላማ መልሶ ከፍ አድርጎ በክብር ሰቀለ፡፡ የካቲት 27 ቀን ንጋት ላይ የኢትዮጵያ ሠራዊት የጅግጅጋ ከተማን ተቆጣጠረ፡፡

የኢትዮጵያና ኩባ ጥምር ጦር በቆላው ምድር ላይ በመገስገስ በጄልዴሳ ግንባር የተከማቸውን የሶማሊያ ጦር ለሦስት ተከታታይ ቀናት በመውጋት ደመሰሰው፡፡ የካቲት 30 ጥምር ጦሩ ግዳጁን በማጠቃለል ከኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር በስተደቡብ ያሉ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ፡፡

ከሐረር የተንቀሳቀሰው ጦር ደግሞ በሰሜን በኩል ግዳጁን በቀላሉ በመፈጸም ኮምቦልቻን አልፎ እስከ ኤጀርሳ ጎሮ ድረስ ገስግሷል፡፡ በሐረር በስተደቡብ የተንቀሳቀሰው ጦር ግን ከሶማሊያ ሠራዊት ከፍተኛ መከላከል ገጥሞታል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የካቲት 29 ቀን ፊዲስ ከተማን የተቆጣጠረው ከባድ መስዋዕትነት ከከፈለ በኋላ ነው፡፡ በባሌና በነገሌ ቦረና ግንባር የተሠለፈው ጦር ግን ጠንካራ መከላከል ሳይገጥመው እስከ ሶማሊያ ጠረፍ ድረስ እየገሰገሰ ከተሞችን ሁሉ በቀላሉ ለመቆጣጠር ችሏል፡፡

ከአራት አሠርታት በፊት የተገኘው አኩሪ ድል በትውልድ ሲታሰብ እንዲኖር ለማድረግ ብሔራዊ በዓል ሆኖ በየዓመቱ መከበር አለበት የሚሉት የኢትዮጵያና የኩባ የወዳጅነት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበበ አያሌው ናቸው፡፡ የካራማራ ድል በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...