ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመንገድ፣ የመኖርያ ቤትና ሌሎችም ግንባታዎች በየጊዜው ይካሄዳሉ፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አካባቢዎችም የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ደግሞ በስፋት ትኩረት ከተሰጠው ይጠቀሳል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ መንገዶችና ሌሎች በስፋት መገንባት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ መሠረታዊ የሚባሉና የሰው ልጅ አኗኗርን የሚያቀሉ ብሎም ለመንፈስ ዕርካታን የሚሰጡ ውበቶች ተሟልተው አይገኙም፡፡ ከግንባታ ባሻገር ቤትን ከሚያስውቡ ቁሳቁሶች አንዱ የቤት ውስጥ ዕቃ ነው፡፡ ከእንጨት የሚሠሩ አልጋዎች፣ ወንበሮች በርና መስኮት ቁምሳጥንም ሆነ ሌሎች የእንጨትና የሌሎች ቁሳቁሶች ውጤቶች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ቁሳቁሶች በአነስተኛና ጥቃቅን ብሎም በትልቅ ፋብሪካ ደረጃ በማምረት ለገበያ የሚያቀርቡ በርካታ ድርጅቶችም ተቋቁመዋል፡፡ ሆኖም የተለያዩ የቤት ቁሳቁስ ምርት (ፈርኒቸር) አቅራቢ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ቢኖሩም ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዳያቀርቡና ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ብዙ ማነቆዎች ይገጥማቸዋል ችግሩን ለመቅረፍ በኢንዱስትሪው የተሰማሩ ድርጅቶችን በመሰባሰብ ማኅበር መሥርተዋል፡፡ ማኅበሩ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዙሪያ የማኅበሩ ጸሐፊ የሆኑትን ወ/ሮ ትህትና ሙሉሸዋ ለገሰን ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ ምን ያህል ጊዜ ሆነው?
ወ/ሮ ትህትና፡– ማኅበሩ በእግሩ እንዲቆም ለሦስት ዓመታት ያህል ጥረት አድርገናል፡፡ ነገር ግን በስያሜ ምክንያት ሕጋዊ ሰውነቱን ወዲያው ለማግኘት አልቻለም፡፡ ፈርኒቸር በብረት የሚሠሩ ነገሮችንም ስለሚያካትት በአማርኛ አቻ ፈቺ አልተገኘለትም ነበር፡፡ የእንጨት ሥራ ውጤት ከተባለ ደግሞ ሌላውን ስለሚገድብ ሲያከራክረንና ሲያወያየን ቆይቶ ፈርኒቸር የሚለው ስያሜ ላይ ሁሉም ሊስማማ በመቻሉ እንደ ማኅበር ሥራውን ከጀመረ ስምንት ወራት ሆኖታል፡፡ በዚህ ስምንት ወራት ውስጥ የማኅበርን ጥቅም እንድንረዳ ዕድል ሰጥቶናል፡፡ ከዚህም ባለፈ እርስ በርስ ያለንን ልምድና ክህሎት እንድናይ ረድቶናል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን ያህል አባላት አፈራችሁ?
ወ/ሮ ትህትና፡– በመጀመሪያ እንቅስቃሴ የጀመርነው አምስት ሆነን ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከ17 በላይ ሆነናል፡፡ ለመነሻ ካፒታል ሁሉም 10,000 ብር በማዋጣት ነበር የተጀመረው፡፡ ከዚህ በኋላ በጣም ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ ፈርኒቸር የሚለው ስያሜ አማርኛ አይደለም በሚል ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ጊዜ መውሰዱ አቀዛቅዞን ነበር፡፡ ማኅበሩ የተመሠረተው ደግሞ በ13 ፊርማዎች ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ብዙዎች በዚህ ዘርፍ ተሰማርተዋል፡፡ የእናንተ ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ በዘርፉ ያሉትን በሙሉ ወደ ማኅበር ለማስገባት አላሰባችሁም?
ወ/ሮ ትህትና፡– የማኅበሩ መመሥረት ዓላማ በዘርፉ የሚሠሩ ድርጅቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ የልምድና የቴክኖሎጂ ልውውጥ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በማኅበሩ ላሉ አባላት ዋስትና ጭምር ለመሆን ነው፡፡ የዘርፉ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ማኅበር በመሆኑ ብዙና ተሰሚነት እንዲኖረን በዛ ማለት ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም አባላት የመጨመር ሥራ ይኖረናል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ የሁለተኛው የፈርኒቸርና ቤተ ውበት ዓውደ ርዕይ ተደርጓል፡፡ በዚህ አንደ ማኅበር ምን የተጠቀማችሁት ነገር አለ? በኮሮና ቫይረስ ምክንያትም ብዙ የውጭ አገር አምራቾች አልተሳተፉም፡፡ በዚህስ ምን አጥታችኋል?
ወ/ሮ ትህትና፡– ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀነው ዓውደ ርዕይ የመጀመሪያውን የሚደግፍ ነበር፡፡ እንደ ተሳታፊም እንደ ማኅበርም፣ ማኅበሩን የማያውቁ እንዲያውቁት ዕድል ሰጥቷል፡፡ ዓውደ ርዕዩ ኢንዱስትሪው እንዲያድግና እንዲጎለብት ዕድል የሚፈጥር ቢሆንም የጠበቅነውን ያህል ጎብኚ አናገኝም ብለን ሰግተን ነበር፡፡ በዓለም ሥጋት በሆነ በኖቭል ኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከውጭ የሚመጡ ኩባንያዎች ቀርተውብናለ፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የሚመረቱ የፈርኒቸር ውጤቶች እንዲታዩ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ይኼ እዚህ ይሠራል? የሚሉ ብዙ ሰዎች አጋጥመውናል፡፡ የፈርኒቸር ውጤት ገዝቶ ለመምጣት ጊዜው የማይመች በመሆኑም እዚህ ያሉት የገበያ ዕድል አግኝተዋል፡፡ ጎብኚዎችና ደንበኞች ማን ምን ይሠራል? አገር ውስጥ ምን ዓይነት ፈርኒቸር ይመረታል የሚለውን እንዲያዩ ዕድል ሰጥቷል፡፡ በተለይም አዳዲስ የፈርኒቸር ውጤቶችን ስንመለከት አገር ውስጥ መሠራቱን ማመን የሚያቅታቸው ደንበኞችን ተመልክተናል፡፡ አንዳንዴ ችግሮችም ዕድሎች ይፈጥራሉ፡፡ አገር ውስጥ ያካሄድነው የፈርኒቸር ዓውደ ርዕይ ሰው ከአገር ባለመውጣቱ አገሬ ውስጥ ምን አለ ብሎ እንዲያይ አግዟል፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ መድረኮች ዘርፉ መድረስ ካለበት ደረጃ አልደረሰም ሲባል ይሰማል፡፡ ማኅበሩ ይኼን ከማገዝና ከማጎልበት አንፃር ምን ይሠራል?
ወ/ሮ ትህትና፡– እንደ ዓላማ ብለን የያዝነው ከውጭ አገር የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ በጥራትና በቴክኖሎጂ በተመረቱ ውጤቶች መተካት ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ስኬታማና ውጤታማ የሆኑትም በጊዜ ሒደት ነው፡፡ እኛም ቀስ በቀስ ቢሆን ጥራቱን የጠበቀ በዓለም ተወዳዳሪና ተፈላጊ ምርቶችን ማምረት እንችላለን፡፡ እንደ አገር የሚያኮራ ሥራ የሚሠሩ አምራቾች ይኖራሉ፡፡ ምርቶቹን በመሸጫ ቦታዎች ብቻ ከማሳየት ባለፈ ማኅበረሰቡ አንድ ቦታ ሆኖለት እንዲያውቅ ማድረገ ይገባል፡፡ አምራች ብለን ሁሉም በየቦታው ቢሠራ ምንም ዋጋ አይኖረውም፡፡ ልንጠነክር የምንችለው በጋራ ስንሠራ ነው፡፡ ለአንድ ሰው የማይቻለውን በብዙዎች ይሳካል በሚል እምነት ነው፡፡
ሪፖርተር፡– በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ማግኘት ይከብዳል ይባላል፡፡ የተማረና የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማግኘት የማኅበሩ ዕገዛ የቱን ያህል ነው?
ወ/ሮ ትህትና፡- በዋነኛነት ከትምህር ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር ነው፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩበት መሣሪያ ሥራ ላይ ከሚያገኙት መሣሪያ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ አንዳንዱም በቴክኖሎጂ የረቀቀ ይሆንባቸዋል፡፡ በድሮ ጊዜ በገቡ ማሽነሪዎች የተማሩ ልጆች ሲወጡ የሚያገኙትን ማሸነሪ ከትምህርት ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር በዘርፉ ለሚሠለጥኑ ባለሙያዎች በቴክኖሎጂ የተሻሉ ማሽነሪዎች ላይ ልምድ እንዲያገኙና እንዳይደነጋገሩ መርዳት ትልቁ የማኅበሩ ዓላማ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ በየመንግሥት ቢሮዎች የዕቃ ግዢ ሲኖር የሚፈጠረው የማጭበርበረ ወንጀል ለመግታት ማኅበሩ ትልቅ ሥራ ለመሥራት እተዘጋጀ ነው፡፡ ሕጋዊ ያልሆነ የግብይት መስመሮችን ከማፅዳት ባሻገር ለዘርፉ ማደግ ማነቆ የሆኑት ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት ሌላው ዓላማችን ነው፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ፣ በመካከለኛና ከፍተኛ አምራቾች መካከል የእርስ በርስ ትስስር መፍጠር ትልቁ ግባችን ሲሆን፣ አንዱ ለሌላው ዓብዓት አቅራቢ እንዲሆን የንግድ ሰንሰለት በመፍጠር ለመሥራት አስበናል፡፡ በዚህ የንግድ ሰንሰለት አንዱ ለሌላው አስፈላጊ ከመሆን በበለጠ ዕድገታቸውን የተያያዘ ስለሚያደርገው በመረዳዳትና በመተጋገዝ መርህ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ያስችለናል፡፡
ሪፖርተር፡- በፈርኒቸር አምራቾች የሚሠሩ አዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች እንዳሉ በዓውደ ርዕዩ ለማየት ችለናል፡፡ ማኅበሩ የፈጠራ ባለቤትነትን ከመጠበቅ አንፃር ምን ይሠራል?
ወ/ሮ ትህትና፡– በባለቤትነት መብት በኩል ብዙ ጊዜ የሚሰማው የሙዚቃ የፊልምና ሌሎች ዘርፎች ላይ ነው፡፡ በፈርኒቸር በኩል ይህንን ለማስጠበቅና ለማስመዝገብ ሕጉ ሊጠብቅና ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ሁለተኛ እርስ በርስ ልንተማመን ይገባል፡፡ ይኼ የእገሌ ዲዛይን ነው ተብሎ እንዲመዘገብለትና እንዲታወቅለት መሥራት ይጠበቃል፡፡ እንደ ማኅበር እንደ ዓላማ አድርገን ባንይዘውም፣ አሁን ጊዜው ነው ብለን እናምናለን፡፡ በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚፈተኑበት ጉዳይ በመሆኑ ወደኛ ዘርፍ መምጣቱ አይቀሬ በመሆኑ የምንሠራበት ይሆናል፡፡ ለዲዛይን (ንድፍ) ትልቅ ቦታ ልንሰጠው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ አዲስ ፈጠራ ለመሥራት ብዙ ዓውደ ርዕይዮችን ማዘጋጀት ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ኮፒ ለማድረግ ሳይሆን አዲስ ፈጠራ ለመሥራት ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ውጤት ማሳያ ስለሚሆን ነው፡፡ አዲስ ነገሮች መፍጠር ወይም የነበረውን ማሻሻል የሚቻለው በዓውደ ርዕይ የመተያየት ዕድልን በመፍጠር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዓውደ ርዕዩ ብዙ የውጭ አገሮች አምራቾች ቢቀሩም የተወሰኑ ግን ተሳትፈዋል፡፡ የእናንተን ሥራ ሲያዩ ምን ዓይነት አስተያየት ነበራቸው?
ወ/ሮ ትህትና፡– አብዛኛው ከውጭ አስመጥታችሁ ነው? እያሉ ሲጠይቁን ነበር፡፡ ትልቅ ነገር ያየሁት ነገር ቢኖር ይኼ ከውጭ የገባ ነው ሲባሉ ደስተኛ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን እዚሁ የተመረተ ነው ሲባል አይ ከውጭ የገባው ይሻላል የሚሉ አሉ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ጥራቱን ያልጠበቀ አጨራረስ ስለሚሆንባቸው ነበር፡፡ ይኼ ጎብኚዎች የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ብዙ የተሻሻለ ነገር ስለቀረበ ብዙዎች የተደነቁበት ዓውደ ርዕይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በፈርኒቸር ዘርፍ ምን ዓይነት ችግሮች አሉ?
ወ/ሮ ትህትና፡– በዘርፉ ትልቁ ችግር ግብዓት የሚሆኑ ነገሮች ከውጭ የሚገቡ መሆናቸው ነው፡፡ ቦታና ብዙ ገንዘብ የሚፈልግ ሥራ መሆኑም ዋነኛው ችግሮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ያለው ድርጅት በቀላሉ ሊሠራ ይችላል፡፡ ነገር ግን ፈጠራና ሐሳብ ኖሯቸው የቦታና የገንዘብ ችግር የሚያጋጥማቸው ብዙ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መንግሥት ግብዓት የሚያመርቱ ድርጅቶችን ወደ አገር ውስጥ ቢያስገባ ለአምራቾችም ሆነ ለአገሪቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ሊያስብበት የሚገባ ዘርፍ ነው፡፡ ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር ጋር ያለን ግንኙነት ጥሩ ነው፡፡ ጥያቄ ሲኖረንም የሚሰማ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ከዚህም በበለጠ የፖሊሲ ቀረፃ ሲኖር እኛን ያሳትፋሉ፡፡ ነገር ግን እንደ መንግሥት ፖሊሲ ሲቀረፅ ብቻ ሳይሆን፣ ዘርፉ እንዲያድግ ከተፈለገ ለፈርኒቸር ማምረቻ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ኢንዱስትሪውን ለማገዝ ከተፈለገ ከቀረጥ ነፃ መሆን አለበት፡፡ ኢንዱስትሪው የሚሻሻለው በፖሊሲ ነው፡፡ ፖሊሲው የተመቻቸለት ኢንዱስትሪ ሁሉ እያደገ እንደሆነ ሌሎች ዘርፎችን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡