Saturday, June 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የህዳሴው ግድብ የአንድነታችን አዲስ ምልክት

በታፈረ ህሉፍ ዓለሜ (ኢንጂነር)

ክፍል ፩

ህዳሴ የኢትዮጵያውን ጽንሰ ሐሳብ ነው

ውኃ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ዋና የልማት ማሳለጫ መሣሪያም ነው፡፡ ኢነርጂ ደግሞ ብቸኛ የልማት ኃይል ነው፡፡ ግድብ ሁለቱንም በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ መሠረተ ልማት ነው፡፡ የውኃ ክምችታቸውና የኢነርጂ አቅርቦታቸው ከሕዝባቸው ቁጥር አንፃር ከፍተኛ የሆኑት አገሮች ሁሉ ያደጉ ናቸው፡፡ የውኃ ክምችትና የኢነርጂ መጠን ከአንዲት አገር ኢኮኖሚያዊ ጂዲፒ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት ኃይላት ግን በሬና ማገዶ ሲሆኑ የልማት ዋነኛ ማሳለጫ ደግሞ በቀጥታ ከደመናዎች የሚወርደው ዝናብ ነው፡፡ ይህን መቀየር ነው ዕድገት ማለት፡፡ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ትላልቅ ግድቦች የአገር ምልክት እስከ መሆን የሚመለኩበት ዋናው ምክንያት ይኼው ሁለትዮሽ ትሩፋታቸው ብቻ አይደለም፣ ትሩፋቱ ለቀጣይ ብዙ ትውልዶች የሚሻገር መሆኑም ጭምር እንጂ፡፡ ይኼን የተገነዘቡ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃዋሃርላል ኔህሩ “ታላላቅ ግድቦች የዘመናዊቷ ህንድ ቤተመቅደሶች ናቸው” ብለው ነበር፡፡

በዘመናዊ የአገሮች ታሪክ ውስጥ መሪዎች ታላላቅ ግድቦችን ለብሔራዊ ማንነትና ለአገር ፍቅር ግንባታ ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ ነው፡፡ የህዳሴው ግድብ ለሺሕ ዓመታት ሲያወዛግብ ከኖረው ከታሪካዊው የዓባይ ወንዝ ላይ መገንባቱ በራሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ታሪካዊና ሞራላዊ ትርጉም አለው፡፡ “አገር ግንባታ” ላይ የሚኖረው ፋይዳም የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በእርግጥ ዓባይን እንደተራ ወንዝ ብቻ መውሰድ ስህተት ነው፡፡ ዓባይ ከሥልጣኔ መፈጠር ጋር፣ ዓባይ ከመጀመሪያዋ የሰዎች ግዛት መፈጠር ጋር፣ ዓባይ ከራሷ ከኢትዮጵያ መፈጠር ጋር፣ ዓባይ ከኢትዮጵያውያን ፍልስፍና ጋር፣ ዓባይ ከቋንቋዎቻችን ይዘት ጋር፣ ዓባይ ከኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና ጋር፣ ወዘተ በጥልቁ የተሳሰረ ነው፡፡ ህዳሴ እየተገነባ ያለው በዚህ ወንዝ ላይ ነው፡፡

ህዳሴ ከሥር መሠረቱ የራሳችን የኢትዮጵያውያን ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ከነገሥታቱ ዓባይን የመጥለፍ ሙከራ ይጀምራል፣ አፄ ኃይለ ሥላሴ በ“ኮርብስ ኦፍ ኢንጂነርስ” በኩል ሞክረዋል፣ ደርግም በአገር ውስጥ ውጥንቅጥ በዝቶ ባይሳከለት እንጂ አስቧል፣ በታሪክ አጋጣሚ ኢሕአዴግ ህዳሴን ከዲዛይን እስከ ግንባታ ማሳካት ችሏል፡፡ ህዳሴን የጀመረም ሆነ የጨረሰ ተመሳሳይ አገራዊ ገድል እንደፈጸሙ ቢያንስ ለቀጣይ ክፍለ ዘመናት ህያው ገድል ሆኖ ይተረክላቸዋል፡፡ ህዳሴ አሁን ያለው ትውልድ ለቀጣይ ለስድስት ትውልዶች የሚሰጣቸው ስጦታ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ ዘመን መገኘቴ ዕድለኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ዓባይ ላይ የገነባነው ቁሳቁስ ሳይሆን ኃይል ነው፣ የሕይወት ውኃ ነው፣ ሞራል ነው፣ ታሪክ ነው፣ የአገር ፍቅር ነው፣ ተሻጋሪ ሀብት ነው፣ የሀብቶች መጠቀሚያ መሣሪያ ነው፣ የእውቀት ክምችት ነው፣ ከዚህ በኋላ እልፍ ህዳሴዎች ይገነባሉ፡፡ እንደ አጠቃላይ ህዳሴ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ህልቆ ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ካደረጉት ትንሽዬ ጥረት ጋር የሚያያዝ ቢያንስ ለክፍለ ዘመናት የሚቆይ ታላቅ አገራዊ ምልክት ነው፡፡

ከውጭ በኩል ስናየው፣ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በአንድ ወገን ውሳኔ ብቻ ዓለም አቀፍ ወንዝ ላይ እንደመገንባቱ ሥጋትና ተስፋ ማሳደሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች የውኃ እጥረትና አጠቃላይ የሕዝባቸው ኑሮ ላይ ያጋጥማል በሚል ሥጋት መኖሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ተፈጥሮ አወዛጋቢ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ቀጣናዊውን በልማት ማስተሳሰሩ ላይ ግን ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አያጠያይቅም፡፡ ታላቁ ህዳሴ በሁሉም የልማት ግንባሮች ማለትም በማኅበራዊ፣ በከባቢያዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዕድገቶች ላይ እምርታ የማስገኘት ታላቅ አቅም ያለው ፕሮጀክት እንደሚሆን በቀላሉ ማስላት ይቻላል፡፡ በቀጣናው የትብብር ሐውልት የመሆን ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡         

ህዳሴን ለአገር ውስጥ ጊዜያዊ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ለመጠቀም የሞከሩት ግን በደንብ ይፈሩ፣ በታሪክ ውስጥ ይሸማቀቁ፣ እኔ ግን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ይቅር ብያቸዋለሁ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የትላልቅ ግድቦች የግንባታ ታሪክ ሳያውቁ ፀጉር ሲሰነጥቁ ሰምቻለሁ፣ ያጠፋውን ከመቅጣት በዘለለ ህዳሴው የሚታሰብበት ባህሪያት ለመለወጥ መሞከር ግን ታሪካዊ ስህተት ነውና እነሱም ይፀፀቱ፡፡     

አሁን ሌላ ትኩሳት እየተነሳ ነው፡፡ በእርግጥ ግድቡንና የግድቡ ዲፕሎማሲ ለማስተዳደር የተሞከረበት መንገድ ስህተት ነበር፡፡ ስምምነቶቹ በትክክል ከተቀረጹ ሁለት ምዕራፍ ይኖራቸዋል፡፡ የህዳሴ ግድብ የውኃ መሙላት መርሐ ግብር ላይ የሚደረግ ስምምነትና ውኃ የመሙላት ተግባር ከተጠናቀቀ በኋላ በሚኖረው የናይል ተፋሰስ ሥርዓት ላይ የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ የመጀመሪያው ቶሎ መጠናቀቅ ይችላል አለበትም፡፡ ሁለተኛው ግን እስከ ቀጣይ አምስትና አሥር ዓመታት ድረስ መቆየት የሚችልና የሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች ተሳትፎን የሚፈልግ ነው፡፡ የዋሽንግተኑ ድርድር ግን ሁለቱንም በአንድ ላይ በማጠፍ አንድ ስምምነት የማድረግ እጅግ አደገኛ ሙከራ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ በራሳቸው ተነሳሽነት የተሰባሰቡ፣ ድርድሩ ላይ ከፍተኛ ሙያዊ ሚና ያበረከቱ፣ በእያንዳንዷ የድርድር ምዕራፍ ላይ ሞዴል እየሠሩ የድርድሩን ቴክኒክ በአሸናፊነት ያጠናቀቁት ኢትዮጵያውን መሐንዲሶች ሌላኛው የኢትዮጵያዊነት ችካል አኑረዋልና ማመስገን ያስፈልጋል፡፡    

አዲሱ ድርድር

በናይል ተፋሰስ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለድርድር መቀመጥ የጀመሩት 2005 ዓ.ም. ላይ ከህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ 2007 ዓ.ም. በመሪ ሐሳብ ደረጃ ስምምነት ላይ ደረሱና ዲፕሎማሲያዊ ድርድር ተጀመረ፡፡ በያዝነው ዓመት 2012 ዓ.ም. ውስጥ ደግሞ ሒደቱ ታጥፎ ዲፕሎማሲያዊው ድርድሩ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ በሦስተኛ ወገን አሳላጭነት ዋሽንግተን ላይ የሚከናወን ድርድር ሆኗል፡፡

የድርድሩ ይዘት ሁለት ምዕራፎች አሉት፡፡ አንደኛው የህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላል መርሐ ግብር ላይ የሚደረግ ድርድር ሲሆን ወደ ጊዜያዊ ስትራቴጂ የስምምነት ማዕቀፍ የሚያድግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከውኃ አሞላል መርሐ ግብር መጠናቀቅ በኋላ ናይል ተፋሰስ ላይ በሚፈጠር “አዲስ ዓይነት የተፋሰስ ሥርዓት” ዙሪያ የሚያተኩር ሆኖ ወደ ዘላቂ የስምምነት ማዕቀፍ የሚያድግ ነው፡፡ ሁለቱም ድርድሮች ሁለት ግዙፍ ተለዋዋጮች (variables) ያላቸው ሲሆን እነዚም የህዳሴ ግድብና የአስዋን ግድብ ናቸው፡፡ የዋሽንግተን ድርድር ሁለቱም ታሳቢ ስምምነቶች ወደ አንድ ማዕቀፍ ለማምጣት የሚደረግ የግብፅ ጥረት ሆኖ አጠቃላይ የህዳሴ ግድብ ሕጋዊ ባለቤትነት መጋራትና የናይል ተፋሰስ ጉዳይ እ.ኤ.አ. የ1959 የናይል ስምምነት ላይ ማጽናት ነው፡፡ የመጀመሪያው ስምምነት ቶሎ መጠናቀቅ ይችላል አለበትም፡፡ ሁለተኛው ግን እስከ ቀጣይ አምስትና አሥር ዓመታት ድረስ መቆየት የሚችልና የሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች ተሳትፎን የሚፈልግ ቋሚ ማዕቀፍ ነው፡፡

ሀ) የህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላል፣ ምዕራፍ አንድ

ግብፆች ከ2011 ዓ.ም. ወዲህ የሚያቀርቡት የውኃ አሞላል ስትራቴጂ መሠረት፣ የመጀመሪያው 3.0 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከግድቡ የታችኞቹ ተርባይኖች በታች ይጠራቀማል፡፡ እነዚህ ሁለት ተርባይኖች ለማንቀሳቀስ ግን 1.5 ቢሊዮን ኪዩዩቢክ ሜትር ውኃ ተጨማሪ መሞላት አለበት፡፡ ይህ በድምሩ 4.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን በአማካይ በ20 ቀናት ውስጥ የሚጠራቀም ውኃ ነው፡፡ ቀጣይ ውኃ የመሙላት ርዕሰ ጉዳይ የሚነሳው ግን ከአንድ ድፍን ዓመት በኋላ ነው፡፡ የኛው የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በክረምት የዝናብ ወራት (ከ60 ቀናት በላይ) ግድቡ እንደሚሞላ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ይህ በገንዘብ ተነፃፃሪነት ቢቀመጥ፣ ህዳሴን ከባንክ አካውንት የሚነፃፀር ሆኖ የሚጠራቀመው ግን ገንዘብ ሳይሆን ውኃ ይሆናል፡፡ 4.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ማለት ለዚህ ባንክ አካውንት መክፈቻ ብቻ የገባ ዋጋ ነው፡፡ የ74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ሥራ ብንሠራም አካውንቱ ከመክፈት በዘለለ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባ ገንዘብ ማግኘት አንችልም፡፡ በመጀመሪያው ዓመት የሚመጡ ተጨማሪ ፍሰቶች ሁሉ በሁለቱ ተርባይኖች የሙከራ ተግባር ላይ የሚውሉ ሆነው በግድቡ ውስጥ የመጠራቀም ዕድል ግን የላቸውም፡፡

በሁለተኛው ዓመት ደግሞ ኢትዮጵያ 13.7 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ታስቀርና የህዳሴ ሐይቅ ከባህር ጠለል በላይ ወደ 595 ሜትር ከፍ ይላል፡፡ ይህ ቀሪዎቹ ተርባይኖች የሚሞከሩበት ከፍታ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ የህዳሴው አካውንት መያዝ ከሚገባው የገንዘብ መጠን 24 በመቶ ብቻ ወደ ኢኮኖሚው መቀላቀል ዕድል ቢኖረውም ወደ አስዋን የሚገባው የናይል ፍሰት በአማካይ ከ31 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ካነሰ የህዳሴው የውኃ ክምችት ይለቀቅና ኢትዮጵያ ከህዳሴው የምታገኘው ጥቅም ተመልሶ ወደ ስድስት በመቶ ይወርዳል፡፡ 

ቀሪው የግድቡ አካል ማለትም ከ595 እስከ 640 ሜትር ድረስ ያለው የውኃ ክምችት ታሪካዊው የግብፁ 55.75 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃን ይመለከታል፡፡ ኢትዮጵያ ህዳሴውን እስከ 640 ሜትር ድረስ በሙሉ አቅም ለመሙላት የሆነ ተዓምራዊ የጎርፍ አጋጣሚ መጠበቅ አለባት ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የቅኝ ግዛቱ የናይል ስምምነት ወደ ተግባር መምጣት የሚጀምረው፡፡  

የግብጹ 55.75 ቢሊዮን ውኃ እስከተጠበቀ ድረስ ግድቡ እስኪሞላ ድረስ ውኃን የመያዝ ሒደት እንደ አለቃቀቁና አያያዙ ፍጥነት ከአምስት እስከ አሥር ዓመት እንደሚወሰድ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተለቀቁ የግብፃውያን ጥናታዊ ዶክመንቶች ይጠቁማሉ፡፡ ግብፃውያኑ ለድርድር ዋሽንግተን ድረስ ይዘውት የቀረቡት ግን ከዚህም አልፎ እስከ 20 ዓመታት የሚለጠጥ ነው፡፡

ህዳሴ ግድብን ከባንክ አካውንት ጋር ለማነፃፀር፣ ህዳሴ እየሞላ እያለ የጥቁር ዓባይ ፍሰት እንደ ገቢ ገንዘብ ብንወስደው ግማሹ በህዳሴ አካውንት ይጠራቀማል፡፡ ከዚህ ተቀማጭ ገንዘብ ላይም በሙሊት ሒደቱ በማንኛውም ጊዜ ኢትዮጵያ ኃይል ለማመንጨትና በተመሳሳይ ጊዜም የታችኛው ተፋሰስ አገሮች የውኃ ፍላጎት ለማሟላት ትለቀዋለች ማለት ነው፡፡ ከህዳሴ ግድብ የውኃ ክምችት ላይ ቀንሶ ለታችኞቹ አገሮች መልቀቅ ማለት የገንዘብ አወጣጥህ ሳይለወጥ ተቀማጭ ገንዘብህ ላይ ቀንሰህ ለሌላ መስጠት እንደ ማለት ነው፡፡

በግብፃውያን ጥናታዊ ሥራዎች መሠረት፣ ከድርቅ ጋር በተያያዘ የህዳሴ ግድብ የሚለቀው የመጨረሻው አነስተኛው የውኃ መጠን የ28 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዓመታዊ ፍሰት የሚተገበርበት የአሞላል ስትራቴጂ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያውያን በኩል ህዳሴ ግድብ እጅግ ጉልህ የሆነ የገንዘብ መስዋዕትነት የሚፈልግ ግዙፍና ውስብስብ የኢንጂነሪንግ ፕሮጀክት ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ግድቡ ውኃ መሙላት ሲጀምር ክብር ሊሰማን፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በተቻለ ፍጥነት ለማግኘት ልንጓጓ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የዓባይ ፍሰት ከተለመደው በታች ወርዶ ዜሮ ቢደርስም ለኛ ላያስጨንቀን ይችላል፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ከመድረሱ በፊት ነው ከግብፆች ጋር መተሳሰብና መተባበር የሚገባን፡፡    

ለ) የህዳሴው የውኃ አሞላል መርሐ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ምዕራፍ 2

የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በዓመታት ውስጥ ከባህር ጠለል በላይ 640 ሜትር ከፍታ ላይ ከደረሰ በኋላ፣ የህዳሴው ሐይቅ የውኃ መጠን ከአማካይ ዓመታዊ የውኃ ግብዓት እንዳያልፍ የሚቆጣጠር ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ይህ ማዕቀፍ እንደየሁኔታው ከህዳሴው ውኃ እንዲለቀቅም የሚያስገደድ ይሆናል፡፡

የግብፆች ፍላጎት ህዳሴ 1,600 ሜጋዋት ድረስ ዝቅ ያለ ኃይል ብቻ እንዲያመነጭ ዒላማ ያደረገ ነው፡፡ ይህ አኃዝ ከአማካዩ እጅግ በታች ነው፡፡ ግድቡ ዝቅተኛው የውኃ ክምችት (Base Load) የሚሉት ላይ ብቻ እንዲሠራ ማድረግ እንደማለት ነው፡፡ በከፍተኛ የጎርፍ ዓመታት ውስጥ (ሦስት ወራት ብቻ) ኢትዮጵያ በህዳሴ በኩል የበለጠ ውኃ በማሳለፍ የበለጠ ኃይል ታመነጫለች እንጂ ውኃውን አጠራቅማ እንደአስፈላጊነቱ የምትጠቀምበት ዕድል እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከአማካይ በታች ዝቅ ባሉት የፍሰት ዓመታት ውስጥ ግን በህዳሴ በኩል የሚለቀቀው ውኃ እየቀነሰ ስለሚሄድ ግድቡ በመጨረሻው ዝቅተኛ ደረጃ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡

ሌላው የማይዋጥ ነገር፣ ኃይል የማመንጨቱ ሒደት በጥንቃቄ ከያዘችው ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ15,000 ጊጋዋት ሰዓት ኤሌክትሪክሲቲ በመሸጥ ኢኮኖሚዋን መደጎም ትችላለች የሚለው ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው የግብፆችም ጨምሮ የውጮቹ ጥናታዊ ሥራዎች ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት ዓመቱን ሙሉ 1,736 ሜጋዋት ኃይል በየሰዓቱ ያመነጫል ከሚል መነሻ የመጣ ነው፡፡ የህዳሴው ሥራ አስኪያጅ ከጥቂት ወራት በፊት ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫም ከዚህ ጋር ተቀራራቢ የሆነ 16,153 ጊጋዋት ሰዓት የሚል አኃዝ ይገኝበታል፡፡ በዓመት 16,153 ጊጋዋት ሰዓት ማለት በየሰዓቱ 1,860 ሜጋ ዋት ዓመቱን ሙሉ ማመንጨት መቻል ማለት ነው፡፡ የህዳሴው ዓመታዊ ኃይል የማመንጨት አቅም ግን ከዚህ ቢያንስ ከእጥፍ በላይ ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ ከፍተኛ የኃይል ማመንጨት ዕቅዳችን ከግብፅ የውኃ ፍላጎት መቀነስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ እየነገሩን ነው፡፡ የግብፅ የውኃ ፍላጎት ይቀንሳል ተብሎ የሚታሰብበት አጋጣሚ ደግሞ መቼም አይመጣም፡፡   

በድርቅ ወቅት የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ለማገዝ የህዳሴው ውኃ መጠቀም ለኢትዮጵያ ዋጋ ያስከፍላታል፣ ይህ ዋጋ በኢነርጂ መቀነስ ይገለጻል፡፡ የኔ ጥያቄ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በዚህ ላይ መደራደር ይገባቸዋል ወይ? ቢደራደሩስ ኢትዮጵያ የምትጠይቀው ማካካሻ ከሚቀንሰው የኢነርጂ መጠን ጋር ብቻ መያያዝ አለበት ወይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የውኃ የመልቀቅ ስምምነት ለኢትዮጵያ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍላት አጠያያቂ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ወደታችኛው ተፋሰስ ውኃ በመልቀቅ የግድቡ መሥሪያ የመጨረሻው ዝቅተኛ ነጥብ (565 ሜትር) ድረስ ወርዶ እንዲሠራ ማድረግ እንዳለበት ነው ግብፆች ከ2011 ዓ.ም. ክረምት ጀምረው የሚያቀርበት የስምምነት ሞዴል፡፡ ከዚህ ነጥብ በታች ያለው የውኃ ክምችት ግን መጠቀም የማይቻል ሙት ክምችት (Dead Storage) ነው፡፡       

በዚህ ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ ለታችኞቹ አገሮች መልቀቅ የምትችለው ትልቁ መጠን በምትለቅበት ጊዜ ለአጭር ጊዜ ኃይል ማመንጨት ትችላለች፡፡ ይህ ግን ለረጅም ጊዜ እጅግ ዝቅተኛ ኃይል ማመንጨት የሚቻለውን ዋጋ የሚያሳጣ መፍትሔ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማግኘት የሚገባን ኢነርጂ ማጣት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ መታየት መቻል አለበት፡፡ 

የህዳሴ ግድብ ትሩፋቱ ለኢትዮጵያ እንዲሆን ለታችኞቹ አገሮች ደግሞ ሥጋት እንዳይሆን ብቻ ነበር ስምምነቱ የሚያስፈልገው፡፡ ግብፅ የምትፈልገው ድርድር ግን የ1959 የናይል ስምምነት ካስጠበቀች በኋላ የታችኞቹ አገሮች ከህዳሴ የሚያገኙትን ጥቅም ከፍ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ይህ ማለት የህዳሴ ትሩፋት ለጋራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ ሥጋት አምጪ በመሆኗ ለራሷ ከሚገባት አብዛኛው ጥቅም አሳልፋ እንድትሰጥ ነው፣ ቅጣት መሆኑ ነው፡፡            

ሐ) የትብብር አይቀሬነት

በእርግጥ ህዳሴ ተጠናቅቆ ግድቡ ውኃ ከሞላ በኋላ በታሪክ ያልነበረ አዲስ ዓይነት ድንበር አቋራጭ የተፋሰስ ሥርዓት ይፈጠራል፡፡ በድንበር በማይዋሰኑ በተለያዩ ሁለት አገሮችና በአንድ ወንዝ ላይ የዓመታት የውኃ ክምችትን የተሸከሙ ሁለት ግድቦች (ህዳሴና አስዋን) የሚገኙበት ውስብስብ ተፋሰስም ይሆናል፡፡ ይህ ተፋሰስ አሁን ላይ የትብብርም ሆነ በጋራ የመሥራት አዝማሚያ ባልተጀመረበት ሁኔታ፣ ድርድሩ ከእጃችን ወጥቶ በሦስተኛ ወገን የራስ ፍላጎት ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ያም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩን እንደ አዲስ ለማየት እየሞከረ መሆኑ አውቀናል፡፡ የናይል ውኃ ተጠቃሚነት በሱዳንና በግብፅ ብቻ የተወሰነ የነበረ መሆንና እነዚህ አገሮች ደግሞ በዓለም የመጨረሻው ከፍተኛ የውኃ እጥረት ያለበት የዓለም ክልል ላይ የሚገኙ መሆናቸው የውስብስብነቱ አካል ነው፡፡

እየጨመረ የመጣው የሕዝብ ብዛትና እየጨመረ የመጣው የዕድገት ፍላጎት የውኃም ሆነ የኢነርጂ እጥረቱ በእጅጉ ያባብሰዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢነርጂ እንጂ ለመስኖ የመጠቀም ዕቅድ ባለመኖሩ አንዴ ውኃ ከያዘ በኋላ ከውኃ እጥረት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግኑኝነት የለውም፡፡ ያም ሆኖ የህዳሴ ግድብ ተገባዶ አገልግሎት ሲጀምር የታችኛው የተፋሰስ ሥርዓት በእጅጉ ይለወጣል፡፡ የናይል ፍሰት እንዴት ማስተዳደር እንደሚገባ ለመወሰን ተጠቃሚው ማኅበረሰብ የወንዙን የአፈሳስ ጽንሰ ሐሳብ እንደገና ለመቅረጽም ይገደዳል፡፡

የናይል የውኃ ሥርዓት የማይገመቱ የአየር ንብረት ሁኔታዎች በመኖራቸው የወደፊት ሁኔታ ለመተንበይ በተፈጥሮው አዳጋች ነው፡፡ ይህ እስካሁን ያልተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች አሁናዊን ስለሚያስቀድሙ፣ ግልጽ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ችላ ስለሚሉና በጥርጣሬ እየተሰቃዩ የመኖር ልማድ ስላላቸው፡፡ በተለይ የውኃ እጥረት መታየት ከጀመረ ወይም የጥርጣሬው እውነታ ምልክቶች መታየት ከጀመሩ የጋራ መፍትሔ ለማምጣት ወደ ሳይንስ ከማተኮር ይልቅ የፖለቲካ ወሬ ላይ የመጠመድ ሁኔታ እያየለ ይሄድና አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡   

የናይል ተፋሰስን እንደ ሥርዓት ሲታይ፣ ህዳሴ ግድብ ለአጠቃላይ ተፋሰሱ የጠሩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች የማስገኘት አቅሙ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ለነዚህ ጥቅሞች እውቅና የሚሰጥ አካል የለም፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ከትርፍ ይልቅ ኪሳራ የማስላት ዝንባሌያቸው ከፍተኛ በመሆኑና ተጨማሪ ጥቅም ለማግኘት የማያመች ስለሚመስላቸው፡፡ ተጨማሪ ጥቅም ለማሳደድ መጭውን ችግር ሳይቆጣጠሩት ይቀሩና የባሰ አስጊ ሁኔታ የመፈጠር እድሉ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያና ለግብፅ ሕዝቦች የሚያጋጥም ይሆናል፡፡ ከህዳሴው ሙሌት በኋላ በመጀመሪያው ምዕራፍ መልካም የፍሰት ሁኔታ ላይ ይደሰቱ ይሆናል፣ በቀጣይ ሊመጣ የሚችልና ማስወገድ የማይቻለውን የመጀመሪያ ድርቅ ላይ ቀድሞ ካልተዘጋጁ ግን ጥፋቱ ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይችላል፡፡ 

ከህዳሴው መገንባት ጋር ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ከመቼውም በላይ በዓባይ ተፈጥሮ ይተሳሰራሉ፡፡ ያም ሀኖ ግብፆች የእውነት ሥጋት አለባቸው፡፡ ይህን ሥጋት ልንጋራላቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የሰው ልጆች ውኃን የማጣት ሥጋት “ጥንተ ተፈጥሯዊ” መሠረት አለው ብለው ያምናሉ፡፡ በሺሕ ዓመታት ውስጥም ይኼው ሥጋት እየበረታና እየሰረፀ መጣ ይላሉ፣ ምክንያቱም ለሰው ልጆች ሕይወት ውኃ ወሳኝ ነውና፡፡ የዚህ “ጥንተ ተፈጥሯዊ” የማጣት ፍርኃት በአንዱ መንደር ከታየ በፍጥነት ወደሌላው መንደር ሊዛመት ይችላል፡፡ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ሥነ ልቦና እኛ ኢትዮጵያውያን አናውቀውም፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የውኃ ማጣት ፍርኃት በዘረመል የመተላለፍ መነሻም የለውም፡፡ ግብፃውያን ግን ይኼንን ጥንተ ተፈጥሯዊ መሠረት ያለው ማኅበረሰባዊ ውኃን የማጣት ሥጋታቸው ዓለም እንዲረዳላቸው ይሻሉ፡፡ በበኩሌ ተረድቼላቸዋለሁ፡፡

በተፋሰሱ አገሮች ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ዙሪያ በርከት ያሉ ጥናቶች ተደርገዋል፣ የትብብር አስፈላጊነትም በተደጋጋሚ ተጠቁሟል፡፡ የዚህ ተፋሰሳዊ ትብብር ሥጋቶችና ትሩፋቶችም ተጠቁመዋል፣ ወደ አንድ የስምምነት ማዕቀፍ ለማምጣት እየተሞከረ ባለበት ሦስተኛ ወገን የራሱ ፍላጎት ይዞ ስለገባበት ሥጋት ላይ መውደቃችን እውነት ሆኗል፡፡ 

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቅ መቃረቡ ጋር ተያይዞ፡

፩. ማኅበራዊ ቀውስ የሚፈጥሩ አደገኛ ሁኔታዎች የሚባሉት ምን ምን  ናቸው?

፪. የውኃ እጥረት ወይም ድርቅ የሚባለው የናይል ፍሰት ስንት ሲደርስ ነው?

፫. የውኃ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ወቅት ምን መደረግ አለበት?

፬. በህዳሴው የውኃ አሞላል ዙሪያ የሚደረግ ስምምነት ይዘቱ ምን መምሰል አለበት?

፭. የግድቡ ውኃ የመሙላት ሒደት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ታላላቅ ግድቦች (ህዳሴና አስዋን) የተቀናጀ አሠራር ውጤታማ ለማድረግና በሦስቱም አገሮች ሥጋቶችን ለመቀነስ እንዴት ዓይነት የትብብር ማዕቀፍ ይቀረፅ? ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ መፈለግ የድርድሩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ይመስለኛል፡፡

ከላይ ከአንድ አስከ አራት የተገለጹ ነጥቦች ላይ ከሦስቱ አገሮች ውጭ አጠቃላይ የናይል ተፋሰስ አገሮችን ላይመለከት ይችላል፡፡ አምስተኛው ነጥብ ላይ ግን መላው የናይል ተፋሰስ አገሮችን ይመለከታል፡፡ አምስቱም ነጥቦች ወደ ስምምነት ማዕቀፍ ሲያድጉ በዋነኝነት በሦስት ከፋፍሎ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡

  1. በቅርቡ የሚጀምረው የግድቡ ውኃ አሞላል በምን ያህል ጊዜ ይጠናቀቅ የሚለው ስምምነት ያስፈልገዋል፡፡
  2. በግድቡ “የውኃ አሞላል ሒደት ወቅት” ድርቅ ቢያጋጥም፣ ሊያጋጥም የሚችለውን የውኃ እጥረት ችግር እንዴት ይመራ የሚለው ስምምነት ያስፈልገዋል፡፡   
  3. ግድቡ “ውኃ ከሞላ በኋላ” በናይል ወንዝ ላይ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ የሚደረግበት አዲስ ዓይነት የተፋሰስ ሥርዓት ይፈጠራል፣ ይህን “አዲስ ዓይነት ሥርዓት” አገሮቹ እንዴት ያስተዳድሩት የሚለው ስምምነት ቢያስፈልገውም የሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች መስማማትን ይጠይቃል፡፡
  4. ይህ “አዲሱ የተፋሰስ ሥርዓት” ከጀመረ በኋላ የድርቅ ዘመን ቢመጣ ከድርቁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የውኃ እጥረት አደጋን ለመጋራት የውኃ አጠቃቀማችን እንዴት ይሁን የሚለውም ስምምነት ይፈልጋል፡፡ ይህም የሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች መስማማትን የሚጠይቅ ነው፡፡

ከላይ የተገለጹት ሒደቶች መቼ ጀምረው መቼ እንደሚጠናቀቁ በትክክል ማስቀመጥ ሊከብድ ስለሚችል በጊዜ መስመር ላይ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ እዚህ ላይ ድርቅ የማጋጠም ዕድል በሚጠቀስበት ጊዜ ለአንዳንዶች እንደ ሟርት ሊመስል ይችላል፡፡ የግብፆችና ሱዳኖች ጥያቄ ግን ሳይንሳዊና ተገቢ ነው፡፡ በናይል ተፋሰስ ዙሪያ እንዲህ ዓይነት የማይጠበቁና በተወሰነ የጊዜ ቆይታ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰት ድርቅ መኖሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የውኃ ሥርዓት (Hydrologic) ተለዋዋጭነት በእጅጉ እየጨመረ ይገኛል፡፡  

ከላይ በተጠቀሱ በእያንዳንዱ አምስት ሁኔታዎች፣ የህዳሴ ግድብ ሐይቅ አገልግሎት አሰጣጥ ከሱዳን፣ ከኢትዮጵያና ከግብፅ አንፃር መታየት ስለሚገባው በሥጋቶቹና በትሩፋቶቹ ዙሪያ ውይይትና ድርድር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሥጋቶቹም ሆነ ትሩፋቶቹ በዝርዝር ማየት ከቻሉ ብቻ ነው ሚዛናዊ ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድላቸው የሚጨምረው፡፡

አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ በመጀመሪያ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ እንደነበረው ዲፕሎማሲያዊ ድርድር ብቻ በቂ ነበር፡፡ አሁን ሦስተኛ ወገን ገብቶበታል፡፡ ሥጋቶቹ ሙሉ በሙሉ ለግብፅና ለሱዳን ሰጥተው ትሩፋቶቹ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትተው የሥጋት ምንጭ ደግሞ ኢትዮጵያን አድርገው የሚያደርጉት ድርድር ነው እየተካሄደ የነበረው፡፡ ሁለቱም አደራዳሪዎች (ዩኤስ አሜሪካና የዓለም ባንክ) የተመረጡት በአንድ ወገን ብቻ መሆኑ በራሱ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡

መ) የስምምነቱ ይዘት ላይ

የመጀመሪያው፣ ከድርቅ ጋር የተያያዘ ስምምነት ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ለሚደርሰው ድርቅም ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡ “የድርቅ ማካካሻ” በሚል የቀረበው የስምምነት ሰነድ የኢትዮጵያን በድርቅ መመታት ተፈጥሯዊ እውነታ የዘነጋ እንደሆነ ስምምነቱ ሚዛናዊ የመሆን ዕድሉ ያቀጭጨዋል፡፡

ሁለተኛው ከድርቅ ማካካሻ ጋር በተያያዘ በግድብ የተከማቸ ውኃን የማይመለከት ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ግድብ ውስጥ የገባ ውኃ ማለት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማጀት ውስጥ የገባ ሀብት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከማጀታቸው አውጥተው ለግብፆች የድርቅ ድጎማ የሚያደርጉበት አንዳች አመክንዮ ያለ አይመስለኝም፡፡ ድርቅን የሚቀንስ ግድብ ሠራን እንጂ ድርቅ አምጪ ግድብ አልሠራንም፡፡ አገርን ቋሚ ባለዕዳ ማድረግ ሌላ ጣጣ ያመጣብናል እንጂ መፍትሔ የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ በታሪክ ውስጥም አንገት የሚያስደፋ ስለሆነ ፈጽሞ ባይታሰብ መልካም ነው፡፡

ሦስተኛ ግድቡ ሥራ ከጀመረ በኋላ ግብፅና ሱዳን በዓመት እያንዳንዳቸው ከ4.9 እስከ 5.6 ቢሊዮን ዶላር ከመስኖ ግብርናና ከመሠረተ ልማት ብቻ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙ በአያሌ ጥናቶች ላይ ተጠቁሟል፡፡ ግድቡን ስንገነባ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍና ብድር በሌለበት በራሳችን ሀብት መሆኑም ይታወቃል፡፡ እዚህ ላይ ከሁለቱ አገሮች የምናወራርደው ማካካሻ መፈለጋችን ምክንያታዊ በመሆኑ ስምምነቱ ውስጥ አነሰም በዛም የፕሮጀክት ዋጋ ማካካስን ታሳቢ ካልተደረገ ስምምነቱ ሚዛናዊ የመሆን ዕድሉን እጅግ ያቀጭጨዋል፡፡

አራተኛ ግድቡን የመሙላት ጊዜ በተራዘመ ቁጥር ኢትዮጵያ ከግድቡ ማግኘት ያለባት ጥቅም ስለምታጣ መጎዳቷ የማይቀር ነው፡፡ ስምምነቱ ይኼንንም ሊጨምር ይገባል ማለት ነው፡፡ ከግድቡ የአሞላል መዘግየት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ጉዳት ለሦስቱም አገሮች መካፈል አለበት፡፡ አለያ ግን የስምምነቱ ሚዛናዊነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ አይቀሬ ነው፡፡

አምስተኛማንኛውም ማካካሻ፣ የተፋሰሱን ፍሰት ለመጨመር የኢትዮጵያ ገበሬዎች ከሚያደርጉት ተፋሰስ አቀፍ የአፈርና ደን ልማት ጋር መገናኘት የለበትም፡፡ ምክንያቱም የተፋሰስና የተራራ ልማት አገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚፈልግ ትልቅ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ራሱን የቻለ ሌላ ስምምነት የሚፈልግ በመሆኑ፡፡ በመሆኑም ስምምነቱ ሚዛናዊ እንዲሆን ቀጣይ የፍሰት ማሻሻያን ባይመለከት፡፡ 

ስድስተኛ፣ ከማንኛውም ዓይነት ስምምነት ጋር በተያያዘ የህዳሴ ግድብ የማመንጨት ዓመታዊ አማካይ አቅም 1,570 ሜጋዋት ሳይሆን ቢያንስ ከ3,200 ሜጋዋት በላይ መሆኑን የሚያሳዩ አማካይ የፍሰት መረጃዎች ስላሉ ወደ ስምምነት ከመተርጎሙ በፊት እንደገና ቢፈተሽ (እንደ አዲስ ዳታ ቢወሰድ)፡፡

ሰባተኛሁለቱም ስምምነቶች ማለትም የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል ስትራቴጂ ስምምነትና ከተሞላ በኋላ የሚኖረው የተፋሰስ አጠቃቀም ስምምነት መጽናት የሚጀምሩበት ጊዜ ቢያንስ በሁለት ዓመት ቢለያዩ፣ ከተሞላ በኋላ ለሚኖረው የተፋሰስ አጠቃቀም ስምምነት አስተማማኝ የድርድር ሜዳ ማግኘት ያስችላልና፡፡                

ይቀጥላል

ከአዘጋጁ፡ ጸሐፊው ሳይንሳዊ ነክ ጽሑፎች ጸሐፊና የምሕንድስና አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles