Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቃቄ ውርደወት ሙግት

የቃቄ ውርደወት ሙግት

ቀን:

ሴቶች ከማኅበራዊውም ሆነ ከኢኮኖሚው እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አስሮ የያዛቸውን የወንዶች የበላይነት፣ ወደ እኩልነት ለመቀየር መታገል ከጀመሩ ምዕት ተቆጥሯል፡፡ ለሴቶች እኩልነት ተጋድሎ ያደረጉ አብዛኞቹ ሴቶች ከባህር ማዶ ሲሆኑ፣ ዓለምም ከቀዳሚዎቹ የሴት መብት ተሟጋቾች ተርታ ካስቀመጣቸው ውስጥ ሉሲ ስቶን፣ ሱዛን ቢ አንቶኒ፣ ማቲድላ ጆይስሊንና አቢ ኬሊ ፎስተር ይጠቀሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ እንደ እነዚህ ምዕራባውያን የሴት መብት ተሟጋቾች ዕውቅና አታግኝ እንጂ ለሴት መብት መከበር ደፍራ የተሟገተችው የቃቄ ውርድወት ትጠቀሳለች፡፡ እሷ ሙግት የገጠመችበት ወቅት ሴቶች ከፍ ብለው የማይናገሩበት፣ ወንዶቻቸው ብቻ የሚሏቸውን ሰምተው መፈጸም ግዴታቸው የነበረበት፣ የፈለጉትን ለመምረጥ፣ አደባባይ ለመውጣትም ሆነ ፍርድ ለመቀመጥ የማይችሉበት የነበረ ቢሆንም፣ ታሪኳ እንደ ምዕራባውያኑ ተሟጋቾች በየመረጃ ቋቱ ገብቶና በተለያየ ቋንቋ ተተርጉሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያየው ዕድል አልተፈጠረም፡፡

በአገር ውስጥ በተለይ ከዓመታት በፊት በብሔራዊ ቴአትር ሲቀርብ የነበረውና በበጀት እጥረት ምክንያት የተቋረጠው የቃቄ ውርደወት የመድረክ ቴአትር ግን የማየት ዕድሉ ለነበረው ግንዛቤ ፈጥሯል፡፡ የደራሲ እንዳለ ጌታ ‹‹እምቢታ›› መጽሐፍም ለታሪኩ መገለጥ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚህ ባለፈ በጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ፣ በዞኑ ስለሚገኙ መስህቦች ባጠናቀረው መጽሐፉ ካካተተው በስተቀር፣ ከ154 ዓመት በፊት የሴቶች መብት እንዲከበር ትሟገት ስለበረችው የቃቄ ውርደወት እምብዛም ግንዛቤ የሚፈጥር መድረክ የለም፡፡ ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የተካተቱ መብቶችን ቀድማ ያነሳች ሴት ብትሆንም፣ ዕውቅናዋ በዓለም አቀፍ መድረክ የናኘ አይደለም፡፡

የቃቄ ውርደወት ሙግት

 

44ኛው የዓለም ሴቶች ቀን የካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲከበር፣ ይህች ሴት በወልቂጤ በተዘጋጀ መድረክ የተዘከረች ሲሆን፣ በዓለም እንድትታወቅ እንደሚሠራ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ካሰው (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በወልቂጤ ከተማ ሲከበር ያገኘናቸው በጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የባህል ባለሙያ አቶ መንግሥቱ አበራ እንደነገሩን፣ የቃቄ ውርድወት አሁን ላይ ሴቶች የሚያነሷቸውን፣ በሕጎች የተካተቱትንም ያልተካተቱትንም ጥያቄዎች ቀድማ አደባባይ ያወጣች ነበረች፡፡

የቃቄ ውርድወት ለሴቶች መብት መከበር ምን አነሳሳት?

በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ አንቂት (እርግማን) የሚባል ባህል ነበር፡፡ ይህ በሕጋዊ መንገድ ጋብቻ የፈጸመች አንዲት ሴት፣ በሕጋዊ መንገድ ከባሏ ጋር ፍቺ ሳትፈፅም ሌላ ጋብቻ እንዳትመሠርት የሚከለክል ባህላዊርዓት ነው፡፡ በባለቤቷ ወይም ባለቤቷ ከሌለ በባለቤቷ  ወላጆችና ቤተሰቦች ለሷና ለቤተሰቦቿግልፅ ‹‹ ስርጥ የህር¦›› ‹‹ሂጂ ተፈተሻል ነፃ ነሽ›› ተብሎ ሦስት ጊዜ ካልተነገረ፣ ሴቷ ከአንቂት ነፃ አትሆንም፡፡

ይህ ደግሞ ባል በሥራ ምክንያት ወጥቶ ለዓመታት ቢቆይ እንኳን ሴቷን አስሮ የሚያስቀር ነው፡፡ የሴቷ በብቸኝነት መቀመጥ ግን ከቁብ የሚገባ አጀንዳ አልነበረም፡፡ ይህን ጉዳይ የሚያየው የአንቂት ዳኝነትም ለወንዶች ያደላ እንደነበር ይነገራል፡፡

ባደረገችው ሙግት በወቅቱ ከአንቂት ነፃ የሆነችው የቃቄ ወርድወት፣ ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ የተዳረችው ለታዋቂው የእዣ ጀግና ለአጋዝ ፉርችየ ላምቢየ ነበር፡፡ ሆኖም የብዙ ሚስቶች ባል መሆኑን ስትሰማ በኋላም ብቻዋን የምታድርባቸውሊቶች ሲበዛ የወንዶች ቅጥ ያጣ ነፃነት ያብሰለስላት ጀመር፡፡

ወርድወት ወንዶች የፈለጋቸውን ያህል ሚስት ሲያገቡ፣ ሴቷ ባንድ ባል የምትታሰረው ለምንድነው? ስትል ጠየቀች፡፡ ወንዶች በአንድ ሚስት ይወሰኑ! እንቢ የሚሉ ከሆነ ደግሞ ለሴቷም ከአንድ በላይ ማግባት ሊፈቀድላት ይገባል በማለትም አደባባይ ወጣች፡፡

በጉራጌ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶችን በአደባባይ መሰብሰብ የሚከለክለውን ባህላዊርዓት ጥሳ ሴቶችን አደባባይ የሰበሰበችው ዛሬ ላይ ወትዋች (Activist) እንደምንላቸው የቃቄ ወርድወት፣ የብዙዎቹን ሴቶች ቀልብ በመግዛቷ ብዙ ተከታይ አፍርታለች፡፡ ይህንን አዲስና በሴቶች ያልተለመደ ጥያቄ አንግባ ወደ አደባባይ መውጣቷ የየቤተ ጉራጌውን ሴት ልብ ስላሞቀው በአደባባይ የሚሰበሰቡ ሴቶች ቁጥር እጅግ ስለበዛና በብዙዎች ላይ አግራሞት ስለፈጠረ የኧጆካ ሸንጎ (ባህላዊ የፍርድ ሸንጎ) ዓብይ መነጋገሪያ ሆነ፡፡

የቃቄ ውርደወት ሙግት

በውርድወት ወትዋችነት አንድ ወንድ ለአንድ ሴት ብቻ ይሁን፣ አይሆንም ካላችሁ እኛም ሴቶች ከአንድ ወንድ በላይ እንድናገባ ይፈቀድልን የሚል ጥያቄም በሴቶቹ ተነስቷል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተሰብ ሕግ ላይ የሰፈረው የአንድ ወንድ አንድ ሴት ጋብቻ  የቃቄ ውርድወት በዘመኗ ካነሳቻቸው ጥያቄዎች አንዱ ነበር፡፡

የትኛዋም ሴት ከባሏ ጋር በትዳር ለመቀጠል ካልፈለገች ‹‹ከአንተ ጋር በቃኝ ፍታኝ›› ስትለው የመፍታት መብቷ ሊረጋገጥ ይገባል የሚለውም የቃቄ ውርድወት ካነሳቻቸው ከአሥር በላይ የመብት ጥያቄዎች ሌላው ነው፡፡

እንደዛሬው ሴቶች አደባባይ ወጥተው መሰብሰብ፣ ድጋፍና ተቃውሞ መግለጥ በማይችሉበት በዛ ዘመን፣ ሴቶች እንደ ወንዶቹ ጀፎሮ (አደባባይ) ወጥተው በአካባቢያቸው ጉዳይ ላይ የመምከር ነፃነት እንዲኖራቸው ውርድወት ጠይቃ ነበር፡፡

በጉዳዩ ላይ የመከረው የኧጆካ ሸንጎም ወንድ በአንድ ሚስት ይወሰን የሚለው ጥያቄ ፈፅሞ የማይቻል መሆኑን፣ ለሴቶቹም ከአንድ በላይ ባል ይፈቀድ የሚለውም በባህልም በታሪክም የሌለ መሆኑና ፍቺ መፈፀም ያለበት በሴቶችም ጥያቄ መሆን አለበት በማለት የተነሳው ጥያቄ የሚያስከትለው አደጋ ከባድ ነው በማለት ወንዱ በየቤቱ የኃይልርምጃ በመውሰድ ሚስቱን ከስብሰባ እንዲያስቀር ተወሰነ፡፡

ሸንጎው ይህንን ሲወስን፣ የአድማው አስተባባሪና መሪ ወርድወት ዳግም ሴቶች ይዛ ወደ አደባባይ እንዳትወጣ እሷ ላይ የተጣለው አንቂት ይነሳላት ተባለ፡፡

ውርድወት ሌሎች ሴቶች አደባባይ ወጥተው ያልተለመደ ተግባር እንዲፈፅሙ ከማነሳሳት እንድትታቀብ፤ በሌሎች ትዳር ጣልቃ እንዳትገባ ሸንጎው ቃል አስገባት፡፡ ‹አንቺን ጉዳይ ወስነናል› ያለው ሸንጎ፣ አንቺ አንቂት አይኑርብሽ፣ የፈቀድሽውን አግቢ በፈቀድሽ ጊዜ ፍቺ እንዳላትም በዞኑ የተዘጋጀው የቃቄ ውርድወት ታሪክ ያስረዳል፡፡

ቃቄ የመጀመርያ ትዳሯን ከፈታች በኋላ ሌላ አግብታ እንደነበርና ጥቂት እንደኖረች በወንዶች ልቅ ነፃነትና ገደብ የለሽ መብት ውስጧ ባለመደሰቱ ሁለተኛ ባሏን ፈትታ ወደ እነሞር ቤተጉራጌ መጓዟን ታሪኳ ያስረዳል፡፡   

በሴቶች ላይ ሲፈፀም የነበረውን የዘመናት በደል ለማስቀረትና ከወንዶች እኩል የመብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ ራዕይ ሰንቃ የተነሳችው ውርድወት፣ በወቅቱ ባይሳካለትም፣ እሷ ግን በየትኛውም ወቅት የመረጠችውን ወንድ ማግባትና መፍታት ችላ ነበር፡፡

የቃቄ ውርድወት የጋብቻ መብትን ብቻ አልነበረም ያነሳችው፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ በሚሰጠውና ሴቶችን ያገል በነበረው የዶካ ሸንጎ፤ ሴቶች እኩል ሊቀመጡ ይገባል ስትል ጠይቃ እንደነበርም አቶ መንግሥቱ ነግረውናል፡፡

በጆካ ሥርዓት (የፍርድ ሒደት) ሴቶች ከወንዶች እኩል ተቀምጠው ‹‹ይህ ትክክል ነው ወይም አይደለም›› ብለው የመወሰን መብት አልነበራቸውም፡፡ በወንዶች ብቻ በሚሰጠው ዳኝነትም ሴቶች የበደል ተቀባይ ነበሩ፡፡ ውሳኔ የመሰጠት መብትም አልነበራቸውም፡፡

የዞኑ የባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ፣ የውርድወት ጥያቄ ለዛሬው ሕገ መንግሥት መሠረት ነው ይላሉ፡፡ እሷ እምብዛም አትታወቅ እንጂ ቀድማ ያነሳቻቸው ጥያቄዎች በብዙ ዓለም አቀፍም ሆነ ብብሔራዊ ሕጎች ውስጥ ተካተው የሚገኙም ናቸው፡፡

የዓድዋ ተጓዡና አመቻቹ አርቲስት ያሬድ ሹመቴ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር በነበረው ቆይታ፣ በገጠር ሴቶች ላይ ካሉ ጫናዎች አንዱ ብሎ የታዘበውና አሁንም ያልተቀረፈው ችግር፤ ውርድወት ከ154 ዓመት በፊት ያነሳችው ጥያቄ ነበር፡፡

አርቲስት ያሬድ እንደሚለው፣ በዓድዋ ጉዞ በየገጠሩ ከታዘባቸው ገጠመኞች አንዱ፣ ሴቶች ቢጫ ጀሪካን በጀርባቸው ተሸክመው ውኃ ፍለጋ መማሰናቸውን ነው፡፡ ወንዶች ጀሪካኖቻቸውን በአህያ ጭነው ሲጓዙ፣ ከባድና ሩቅ መንገዶችን በበቅሎ ጭምር ሲነጉዱ፣ ሴቶች እምብዛም ለዚህ አልታደሉም፡፡

ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ባህል በቀላሉ ማስቀረት ባይቻልም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች አህዮችና በቅሎዎች የሴቶችን ሸክም ሲያቀሉ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም አብዛኛው ተጠቃሚዎች ወንዶች ናቸው፡፡

እንደ አቶ መንግሥቱ፣ ውርድወት ካየችው በመነሳት ከጠየቀቻቸው ጥያቄዎች ውስጥ ወንዶች በበቅሎ ቁጭ ብለው ሴቶች ከኋላ በእግር ለምን ይከተላሉ፣ ይህ መቀየር አለበት ሁላችንም ተጠቃሚ አንሁን የሚለውም ይገኝበታል፡፡

ከዘመኑ ቀድማ የተወለደች የምትባለው ውርድወት የተለያዩ የሴቶች እኩልነት ጥያቄዎች ስታነሳ ‹‹ባህል አበላሸች›› በሚልም ከወንዶች ወቀሳ ይገጥማት ነበር፡፡ ይህንን ወቀሳና ነቀፋ በመቋቋም፣ የወንድ የበላይነትን የሞገተችው ውርድወት፣ ያነሳቻቸው ጥያቄዎች ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር ውስጥ ሕጎች የተካተቱ ናቸው፡፡ ሆኖም ተፈጻሚነታቸው ላይ ዛሬም ጥያቄ ይነሳል፡፡

የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የክልልና ዞን የሴቶችና ሕፃናት ቢሮዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሴቶች ላይ የሚደርስ በደልና አድሎ ይቆም ዘንድ እየሠሩ ቢሆንም ችግሮች እምብዛም አልተፈቱም፡፡

ሴቶች ዛሬ ላይ በድብቅ ይገረዛሉ፡፡ ላልፈለጉት ሰው ያለ ዕድሜያቸው ይዳራሉ፡፡ አደባባይ ወጥተው የፈለጉትን እንዲጠይቁ መሠረት ከሚሆናቸው ትምህርት ያቋርጣሉ፡፡ በተለይ በገጠር የሚኖሩ ሴቶች ጫና የበዛ ነው፡፡

ከሰሜን ሸዋ አካባቢ ወጥታ በቤት ሠራተኝነት እንደምትሠራ የምትገልጸው ወጣት፣ የአካባቢዋ ሴቶች ባሎቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን አባቶቻቸውን በጣም እንደሚፈሩ ነግራናለች፡፡

እሷ እንደምትለው፣ አንዲት ሴት ለባሏ መልስ ከመለሰች ወይም እሱ ትክክል አይደለም ብሎ የሚያምንበትን ፈጽማ ከተገኘች በልምጭ ትገረፋለች፡፡ ሴት ልጅ በቀን ተኝታ ከተገኘችም ነውር ነው፣ ሊያስቀጣም ይችላል፡፡ አንዲት ሴት ፍም እሳት በእጇ ይዛ ከአንዱ ምድጃ ወደ አንዱ ካላደረገች ወይም የጋለ ዕቃ በጨርቅ ጠቅልላ ካነሳች ‹‹ምኗ ሴት ነው›› ትባላለች፡፡ ታዲያ ሴቶቹ ልጅ አዋቂ ሳይል ‹‹ምኗ ሴት ነው›› የሚለውን በመፍራት የሚጎዳቸውን ነገር ማድረግንም ለምደውታል፡፡

ከ80 በመቶው በላይ ሕዝቧ በገጠር ይኖራል በምትባለው ኢትዮጵይ፣ ሴቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከወንዶች ሲነፃፀሩ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ በትምህርት፣ በጤና ተደራሽነትም ሆነ የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ተጠቃሚነታቸው አናሳ ነው፡፡ በማኅበረሰባቸው ዘንድ ዝቅ ብለው መታየታቸውና እነሱም ይህንን መቀበላቸው እንዲሁም ከማኅበራዊ ትስስር አናሳነት ጋር ተያይዞ ሴቶች ለጉዳት የተጋለጡ ናቸው፡፡

በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ጉልበት በሚፈልገው የግብርና ሥራም መሳተፋቸው ቤት ውስጥ የሚሠሩት ጋር ተጨምሮ ሲደክሙ የሚውሉት ሴቶች፣ በየአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ዘንድ ይህንንም ያህል ልፋታቸው አይታወቅላቸውም፡፡ በራሷ በሴቷ ጭምር ለሷ የተሰጠ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ሴቶችን በትምህርትና በኢኮኖሚ በማበልፀግ ካሉባቸው ጫናዎች ማቃለል ቢቻልም፣ የተሄደው ርቀት ገና የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት አላረጋገጠም፡፡ በመሆኑም መንግሥት ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ አካላት ጭምር ለሴቶች መብት መከበር ጠንክረው ሊሠሩ ይገባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...