በየካ ተራራ በ40 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ሊካሄድ የታሰበው የሪል ስቴት ልማት ነዋሪዎችን ከማፈናቀል አልፎ የደን ምንጠራን ያስከትላል የሚሉ ቅሬታዎች መነሳታቸው ያስከተለውን ጫና ተከትሎ፣ የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት በወረዳ አመራሮች የሪል ስቴት ኩባንያውና እንዲነሱ የተነገራቸው ነዋሪዎች ለውይይት መጠራታቸው ተሰማ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት አስተዳደር ‹‹ለተነሺዎች›› በሚል አመልካች ለውይይት መጠራታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡ በሪል ስቴት አልሚው ብርሃን ጎሕና በ‹‹ተነሺ›› ነዋሪዎቹ መካከል የሚደረገው ውይይት ለሰኞ መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት 7፡30 ሰዓት ቀጠሮ እንደተያዘለት ሲገለጽ፣ በወረዳ አምስት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በግንባር ተገኝተው እንዲወያዩ የሚጠይቅ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ ተነሺዎች ተብለው በአስተዳደሩ ደብዳቤ መጠቀሳቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር ከሳምንት በፊት ባቀረበው ዘገባ፣ በየካ ተራራ በ40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሊካሄድ በተሳበው የሪል ስቴት ፕሮጀክት ሳቢያ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው 17 ነዋሪዎች እንዲነሱ መጠየቃቸው ተገልጾ ነበር፡፡ ከእነዚህ ነዋሪዎች በተጨማሪ ከሰሞኑ 11 ያህል ካርታ ወይም የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው ነዋሪዎችም እንዲነሱ በተናጠል ጥያቄ ሲቀርብላቸው እንደ ሰነበቱ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
ብርሃን ጎሕ የተሰኘው የሪል ስቴት ኩባንያ በየካ ተራራ ላይ የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ ፈቃድ ያገኘውና የይዞታ ማረጋገጫ የተሰጠው፣ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ እንደነበር ይናገራል፡፡
ነዋሪዎች በበኩላቸው ሕጋዊ ይዞታቸው ላይ ይህ ፕሮጀክት መምጣቱ አግባብ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውም በካርታ ላይ ካርታ ደርቦ ከመስጠት ባሻገር፣ በአረንጓዴ ሥፍራነት የተከለለ አካባቢን ለቤቶች ግንባታ እንዲውል መፍቀድ አግባብ እንዳልሆነ፣ የደን ይዞታው ሲመነጠር የጎርፍ አደጋ እንደሚያስፋፋ በመግለጽ ጭምር በፕሮጀክቱ ላይ ተቃውሞ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ የሪል ስቴት ኩባንያው ሊያለማው የተዘጋጀው አካባቢ የአዲስ አበባ ሳንባ እንደሆነ የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በአንድ በኩል ዛፎች ይተከሉ እየተባለ በሌላ በኩል እንደዚህ ዓይነት ደን የመመንጠር አደጋ ሲጋረጥበት ማየት ያሳዝናል ብለዋል፡፡
ሪል ስቴት አልሚው በበኩሉ ከአካባቢው ለሚነሱ ነዋሪዎች የካሳ ክፍያ መፈጸሙን፣ የደን ምንጠራ ሳይሆን ባህር ዛፎችን ብቻ እንደሚያነሳ በመግለጽ ይከራከራል፡፡
በዚህ ሁሉ መሀል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመገናኛ ብዙኃን በተለይም ሪፖርተር ላቀረባቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለቱም ባሻገር፣ ‹‹ምንም ዓይነት መረጃ አትስጡ ተብለናል፤›› የሚሉ ምላሾች ለሚዲያ አካላት እየተሰጣቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹም በስልክ ምላሽ መስጠት እንደማይፈልጉ በመግለጽ ጭምር የሚዲያውን ጥያቄ በሩቁ እያሉት ነው፡፡