Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ ምርቶችን ለኢትዮጵያ ማቅረብ ለሚችሉ የውጭ ድርጅቶች ውስን ጨረታ ሊወጣ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ ተጠቅመው በመንግሥት የሚፈለጉ ሸቀጦችንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለኢትዮጵያ ማቅረብ የሚችሉ የውጭ ድርጅቶችን ለመለየት ውስን ጨረታ ሊወጣ ነው።

ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንዳመለከተው፣ መንግሥት ይህንን ውስን ጨረታ በማውጣት ልምድና የፋይናንስ አቅሙ ያላቸው የውጭ ድርጅቶችን በመለየት፣ መሠረታዊ ሸቀጦችንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ወደፊት በሚከፈል ስምምነት እንዲያቀርቡ ማድረግ አስፈልጎታል።

ይህም አገሪቱ ለጊዜው የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቋቋም ታስቦ የተቀመጠ አቅጣጫ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ውሳኔውን ያሳላፈው የኢንቨስትመንት ቦርድ ነው፡፡

ውሳኔውን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አሠራር ላይ ለማዋልና ለማስፈጸም በተዋረድ ተሳታፊ የሚሆኑ የመንግሥት ተቋማት እንዲለዩና የሥራ ድርሻቸውን የተመለከተ መመርያ ወጥቶ ኃላፊነት እንዲወስዱ ደግሞ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሰሞኑን አቅጣጫ ማስቀመጡ ታውቋል።

በዚህም መሠረት የገንዘብ ሚኒስቴር መመርያ እንዲያወጣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ ተላልፎለታል። የገንዘብ ሚኒስቴር መመርያ ከማውጣት በተጨማሪ፣ ከውጭ የሚቀርቡት ምርቶች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን የመለየትና መጠናቸውን የመወሰን ኃላፊነት እንደተሰጠው፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ በወ/ ደሚቱ ሐምቢሳ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ያስረዳል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከላይ ከተሰጠው ኃላፊነት በተጨማሪ፣ ከውጭ መግባት ያለባቸውን ሸቀጦችና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በመለየትና መጠናቸውን መወሰን ይጠበቅበታል።

የሚለዩትን ሸቀጦችና ግብዓቶች ለማቅረብ የሚፈልጉ የውጭ ድርጅቶች የፍላጎት መግለጫ እንዲያቀርቡ ጥሪማድረግ፣ አጭር የአቅራቢዎች የማወዳደሪያ መጠየቂያ በማዘጋጀትና በማወዳደር አሸናፊውን ለይቶ ውል የማዋዋል ኃላፊነትም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ መንገድ ተለይተው አሸናፊ የሚሆኑት የውጭ ድርጅቶች የራሳቸውን የውጭ ምንዛሪ ተጠቅመው ሸቀጦችንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ ካስገቡ በኋላ፣ በሚገቡት ውል መሠረት መንግሥት ወደፊት በውጭ ምንዛሪ ከፍያ እንደሚፈጽምላቸው መረጃው ያስረዳል።

በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ግብዓቶችንና መሠረታዊ ሸቀጦችን በአብዛኛው የሚያቀርቡት የመንግሥት ተቋማት ናቸው። ጥራት ያለው ቆዳና ጥጥ በኢንዱስትሪ ግብዓትነት ከሚቀርቡት መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ስንዴና የምግብ ዘይትን ጨምሮ በርካታ ሸቀጦች ከውጭ እየገቡ እንደሆነ ይታወቃል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች