Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኧረ ምን ይሻለናል?!

ኧረ ምን ይሻለናል?!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

መቋሰልን የሚያፈልቁና ሊያፈልቁ የሚችሉ ቀዳዳዎችን ዛሬም አልዘጋንም፡፡ መዝጋት ቀርቶ መኖራቸውን የትኞቹ መሆናቸውን ገና አላወቅነውም፡፡ ስሜቶቻችንንም ገና አላስታረቅንም፡፡ መልሰን መላልሰን የመናቆር ወጥመዶች ውስጥ መግባታችንና ከዚያ አልወጣ ያልንበት ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ በየዕለቱ የምንሰማቸውና የምናስመዘግባቸው የሚቆረቁሩና የሚገርሙም ዜናዎች ምንጭ ይኼው ነው፡፡

አንድ ላይ ገጥመን በሁነኛ የህልውና ጉዳዮቻችን ላይ እንደ ልብ በመሆን፣ የመንግሥትም ሕግን የማስከበርና የሕዝብ ደኅንነትን የመጠበቅ አቅም እንዲጠናከር ማገዝ፣ ኢትዮጵያን ለሁሉም የምትደላ ዴሞክራሲያዊት ፌዴራላዊት አገር አድርጎ የመገንባቱን (በአንፃራዊነት) የረዥም ጊዜ ግብ መዳረሻ ወይም መነሻ የሆነውን ዴሞክራሲን የማደላደል ሥራ ላይ መረባረብ፣ በተለይ በዚህ የለውጥና የሽግግር ወቅት የሞት ሽረት ሥራችን መሆን አለበት፡፡

ግን አሁንም በክፍልፋይነት በተሟሸ አዕምሮ ከሚያስብ ቅርቃር ውስጥ አልወጣንም፡፡ በብሔር በተሰባሰበ ፓርቲ መግዛትና በብሔረሰብ ባለቤትነት ላይ የተመሠረተ የአገር አከፋፈል የፌዴራሊዝም፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትና ነፃነት ሌላው ስማችንና ስያሜያችን ነው፡፡ በዚህና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች ለእኩልነት መብት የሕግ ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ የሰጠው አንቀጽ 25፣ እንዲሁም በየትም የአገሪቱ ቦታ ተዘዋውሮ የመሥራትና ቤት ንብረት የማፍራት መብት (አንቀጽ 32) ከይስሙላ ያለፈ ዋጋ አጡ፡፡  የዚህ ምክንያት ብሔርተኛ ፖለቲካዊ አስተዳደራዊ አደረጃጀትና ብሔረተኛ አስተሳሰብ የእኩልነት መብትን በአገር ውስጥ ተዘዋውሮ የመኖርን ነፃነት መዳፈር በቀጥታ ስለሚፈቅድ ነው፡፡ የተጠቀሱት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች መረገጥና መረምረም የሚጀምሩት ሕዝብን የአንድ አካባቢ፣ የአንድ ክልል ባለቤትና ባይተዋር አድርጎ ስለሚከፋፍል ነው፡፡ እስካሁን ባለው ልምድ 27 ዓመታት ሙሉ በተቋቋመው አሠራር፣ ክልሎች በይዞታቸው ውስጥ ባለቤትነት የማይመለከታቸውን ማኅበረሰቦች ወደ ፖለቲካ ሥልጣን የመውጣት ዕድልንም ሆነ የሥራ ዕድልን ይገድቡ ዘንድ ነፃ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል፡፡ አንዳንዶችማ እንዲያውም በክልላዊ ሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ይኼንኑ የመብትና የነፃነት አንጓላይነት እንዲሠፍር አድርገዋል፡፡

ዋናውና ገዥው መመዘኛ ብሔረሰባዊ ባለቤትነትና ባለርስትነት ሆኖ ስለተመረቀ፣ የቁጥር ብልጫ ኖረም አልኖረ እኩልነትና ዴሞክራሲ ከይስሙላ ያለፈ መሠረት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ይህን የመሰለ የሥር የመሠረት ሥርዓታዊ ማኅፀን ያለው የመብት መንጓለልም፣ የቅሬታና የንቁሪያ ምንጭ መሆኑ አይቋረጥም፡፡ አመለካከት በብሔርተኛነት ተውጧልና የአስተዳደሮችንና የአውታራት አደረጃጀት በብሔረሰባዊ ባለቤትነት ዕይታ ይመራ ስለተባለ፣ ፍትሕና ሕግ አስከባሪነት ሁሉ ለአድልኦ ተጋለጠ፡፡ ለ27 ዓመታት ያጎለበትነውና ለዚያን ያህል ጊዜም ለአምባገነንነት ጉልበት ሆኖ የኖረው ከፋፋይነት፣ ግለሰቦችን ሲያያቸው የኖረው በብሔረሰብ ኮረጆዋቸው ውስጥ መድቦ ስለሆነ ግለሰባዊነታቸውን ሲያይ የብሔረሰብ ኮሮጇቸውን ሳይዘነጋ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የብሔረሰብ አባላት ከተለያዩ ግለሶቦች ጋር አፍ እላፊ ሲነጋገሩና አምባጓሮ ሲገቡ፣ ፀባቸውን በግለሰባዊነት ብቻ ዓይቶ ለማለፍ አይሆንለትም፡፡ ፀባቸውን ብሔረሰባዊ አድርጎ ለመተርጎም ይፈጥናል፡፡

የእንዲህ ዓይነቱ የአስተሳሰብ ምሰሶ ወገኔ በሌላ ወገን ተበደለ/ተጠቃ ብሎ ስለሚጀምር የበደል ግንኙነቱ ቢቋረጥም፣ ወገንተኝነቱ ወይም ብሔርተኝነቱ ከቀጠለ የድሮን እያነሳ ከማፍተልተል ወይም የብሔር ክብር/ጥቅም የነካ አዲስ በደል መሰል ነገር በመብራት ከመፈለግ አይቦዝንም፡፡ የተለያየ ብሔረሰባዊ አመጣጥ ባላቸው ግለሰቦች መካከል የሚደረጉ ፀቦችና አፍ እላፊ ንግግሮች መላ ብሔረሰብን የመዳፈር ትርጉም በቀላሉ የሚሰጣቸውም ብሔርተኝነት ለሚሻው ተጠቃን፣ ተነካን ባይነት ማገዶ መሆን ስለሚችሉ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የአመለካከትና የአደረጃጀት ሥርዓቱ ራሱ በአንድ የአፍ እላፊ ምላስ ብሔረሰባዊ ፀብ ለማቀጣጠል የሚያስችል ባልቦላ፣ ለእያንዳንዱ ጎጠኛ ግለሰብ ያስታጥቀዋል፡፡ የኅብረተሰብ ሰላም ያንን ያህል መጫወቻ ለመሆን ይጋለጣል፡፡

የግለሰቦች ፀብና የቃላት ምልልስ የብሔረሰቦች መነካካት፣ የእነሱ ጉዳይ ተደርጎ ለመተርጎም ዕድል እስካገኘ ድረስም መሸካከርንና መናቆርን እንዳመረትን እንኖራለን፡፡ አንድ ብሔርተኛ ቡድን ሕዝቤ ከሚለው ብሔረሰብ ጋር ዝምድናውን የሚቋጥረው፣ በድፍኑ ብሔረሰቡን ከሌላው ለይቶ ማተኮሪያው በማድረግ፣ በማሞገሥና ጥቃትህን እየታገልኩ ነው፣ ለጥቅም የቆምኩልህ ጠበቃህ ነኝ በማለት ላይ እንደ መሆኑ፣ በብሔርተኛ ቡድኑ የተማረኩ የብሔረሰቡ አባላት የቡድኑን ገመና በክፋት አዕምሮ ለማየትና ለማጋለጥ ይቸገራሉ፡፡ ጎጠኛ ቡድኑም ባለው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ መርሐ ግብርና ተግባሩ ተቀባይነቱ የሚሠፈርበት ግፊት ስለሌለ፣ ገመናውን እያፀዳ ወደፊት የሚራመድበት ዕድል ደካማ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ገመናን ከማየትና ከማሳየት ይልቅ፣ ራስን በመሸንገል ማለትም የቡድኑን ጥፋት በሌላ ላይ በማላከክ ወይም በብሔረሰብ ላይ ለደረሰ ችግር ማሳበቢያ በመፈለግ፣ ቡድኑ ላይ የሚደረግ ነቀፋንና ውንጀላን ሁሉ በብሔረሰቡ ላይ የተሰነዘረ አድርጎ በመውሰድ ይጠመዳሉ፡፡ ወጥመዱ ሀ ብሎ የሚጀምረው ገና በጎጠኝነት ራስን ከሌላው ለይቶ መንቀሳቀስ ሲጀመር ነው፡፡

ብሔርተኝነት የብሔረሰብን መገፋትና መበደል ቢያይም፣ ከሌላው ጋር ትግል አዛምዶ በመታገል ፈንታ ለብቻ ራስን የለየ ትግል ውስጥ መግባት ተነጥሎ የመጠቃት ጥፋት መሆኑን ማስተዋል ትልቅ ችግሩ ነው፡፡ ለብቻ በመጮሄ፣ ለብቻ ትጥቅ ትግል ውስጥ በመግባቴ ሕዝቤ ተለይቶ እንዲጠቃ አጋልጫለሁ፣ ስቃዩም ትግሉም እንዲራዘም አድርጌያሁ ብሎ ጥፋትን ማመንና ወደ ኅብረ ብሔራዊ መንገድ መግባት፣ በኢትዮጵያ የብሔርተኛ ትግል ውስጥ ጉልህ ሆኖ የኖረ ችግርና ገመና ነው፡፡ ብሔርተኝነት በ1983 ዓ.ም. ድል ከተቀዳጀ ወዲህ በተቋቋመ አንጓ ላይ የብሔርተኛ አገዛዝ ራሴንም ብሔረሰቤንም በጥላቻ፣ በቅያሜ አስጠመድኩ በማለት ጥፋት የማመንና ኃላፊነት የመቀበል፣ እንዲሁም የመታረምን ጉዳይ ዛሬም የሞት ያህል የሚሸሽ ነው፡፡ ለትግራይ ወገኖቻችን መጠመድ መዘዝ የሆነው ሕወሓታዊ የበላይ ገዥነትና ሀብት አግበስባሽነት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሳለ፣ ከሕወሓት ውስጥ ይቅርና ያለ ኃጢያቱ ጥላቻ ከተረፈው ትግራዊ በኩልም ይህንን የድርጅቱን መዘዘኝነት ፊት ለፊት አውጥቶ የመኮነን ደፋር እንቅስቃሴ ገና፣ በጣም ገና ነው፡፡ አሁን ከለውጡ በኋላ ደግሞ ሌሎች ‹‹ቅድሚያ›› የሚሰጣቸው ጉዳዮች ጣልቃ እየገቡ በቀጠሮ እያደረ ነው፡፡

በየትኛውም ብሔረሰብ ውስጥ ሕግ ጣሾችና የመብት ጥቃት አድራሾች ይከሰታሉ፡፡ ለምሳሌ ኦነግ በሰላም በር አገር ውስጥ ከገባ በኋላ በኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች ውስጥ በጠመንጃ አማካይነት አሁንም ድረስ የሚካሄደው አማሽነት፣ ፈጣን መንግሥታዊ ዕርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኦነግ ወይም የኦነግ አንጃ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ዕይታ፣ ለኦሮሞ ብሔር የቆመና የታገለ ተደርጎ ሲቆጠር እንደ መኖሩ ቡድኑ በዚህ ዝና ውስጥ ተሸጉጦ በአተራማሽነት የሚያደርሰው በደል ከሚያስከትለው ፖለቲካዊ ጫና ይልቅ፣ በኦነግ ወይም በአንጃው ላይ ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ በኦሮሞ ታጋዮች ላይ ዛሬም እንደ ትናንቱ የመንግሥት ጥይትና ካቴና ቀጠለ የሚል ጫጫታ የበለጠ እየሆነ ይመጣል፡፡

ኦሮሚያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ብለው ትግሉን በተቀላቀሉ ቡድን/ቡድኖች አማካይነት የተፈጠረው ችግር እያስመረረና ይዞታ ማስፋት የሚባል ነገርም መጥቶ፣ የኦሮሚያና የፌዴራል መንግሥት የበረታ ዕርምጃ መውሰድ ውስጥ ሲገቡ በብሔርተኝነት ዘንድ ከሁሉ ቀድሞ የታየው ነገር ሰላማዊ ትድድርን አናግተው፣ በዜጎች ላይ ወንጀል የፈጸሙ ለፍርድ የመቅረባቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ ከፍትሕ ይበልጥ፣ ከፍትሕ ይልቅ ብሔርተኝነትን ያብከነከነው፣ ኦሮሚያን የሚያስተዳድረው ኦዴፓ ወይም ብልፅግና ኦሮሚያ ለኦሮሞ የቆመ ድርጀት ሆኖ ወይም ነኝ እያለ፣ ኦነግም ለኦሮሚያ ሲታገል የኖረ የኦሮሞ ድርጅት ሆኖ እንዴት ለኦሮሞ የቆሙ የብሔሩ ልጆች እርስ በርስ ይዋጋሉ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ተጠያቂነትና ሕግ ማስበር ይህን ያህል ሲጎሳቆልና ገደል ሲገባ ይታያል፡፡ አመፅ ድረስ የሄደ በደልና ተጠያቂነት በብሔር ታጋይነት ውለታና ዝና ውስጥ ተሽሞንሙኖ ‹‹ነፃ መውጣት›› ድረስ ሊያመልጥና ሊሸለም ይችላል፡፡ ለብሔርህ ጥቅም የደማሁና የተሰዋሁ ባይነት በደል፣ ግፍና ዘረፋ ከሌላ ብሔር ብቻ የሚመጣና የብሔር ልጅ በገዛ ብሔሩ ላይ የማያደርገው የሚያስመስል ብዥታም ይፈጥራል፡፡ እንዲያም አድርጎ ዓይንን ይጋርዳል፡፡ ለዚህ ዓይነት ብዥታ የኦሮሞ ሕዝብ ከኦነግ ጋር ባለው ታሪካዊ ቁርኝት የተጋለጠ መሆኑን ያስተዋለ ሰው፣ የትግራይም ሕዝብ ከሕወሓት ጋር ባለው የታሪክ ትስስር ያለበትን ፈተና ማጤን አይከብደውም፡፡

ለትግራይ ሰው ቢያንስ ቢያንስ በቀዝቃዛ ስሜት መታየት ዳፋ ወይም ምክንያት የሆነው የሕወሓት መጠመድ የመጣው ከትግሬነት አይደለም፡፡ በብሔር መሰባሰብን ምርኩዝ አድርጎ ሥልጣን ላይ የወጣ ሕወሓታዊ ቡድን ሥልጣንን የሰነገና የሀብት መመጥመጫ መሣሪያ ከማድረጉ መመንጨቱን አገር ያውቃል፡፡

እንደ ምንም ብሎ እነሆ መጋቢት ላይ ሁለተኛ ዓመቱ ውስጥ የገባውን፣ ደንበር ገተር እያለም ቢሆን የቀጠለውን ይህን የዴሞክራሲ ለውጡን በዋናነት የሚመራው የዶ/ር ዓብይ የኦሮሞ ቡድንም፣ ከአሁን አሁን እዚህ ወይም እዚያኛው ወይም ሌላው አደጋ ውስጥ ይገባ ይሆን የሚል ሥጋት ፍራቻና ሰቀቀን ጋር ሲያላጋን ቆይቷል፡፡ በአክራሪ ብሔርተኞችና በሥልጣን ጥመኞች ተጠልፎና ተንሸራትቶ ሕወሓት የገባበት ወጥመድ ውስጥ ይገባ ይሆን አንዱ ፍራቻ ነበር፡፡ ወይም ጥርጣሬና ተቃውሞ ይህን ቡድን አዋክቦት፣ ቡድኑ አፈናን የሥልጣን ማስቀጠያ ዋና መሣሪያ ወደ ማድረግ ይዞርና ታሪክ ራሱን ይደግማል ብለንም ሠግተናል፡፡ ከአክራሪ ብሔርተኞች አደጋ ለማምለጥ ዋስትናው ከመላ ሕዝብ ድጋፍ ጋር የዴሞክራሲ ለውጡን ማንደርደርና በአስቸኳይ የብሔርተኛ አደረጃጀት ቆዳውን ገፍፎ ኅብረ ብሔራዊ ቅልቅል ውስጥ መግባት መሆኑ ቢታወቅም፣ ከዚህም አኳያ ኦዴፓ ብዙ ቡድኖችን ይዞ ወደ ውህድ ፓርቲነት ለመሸጋገር መቁረጡ ዴሞክረሲያዊ ሁኔታዎችን የማበልፀግ ሥራ ከመቀጠሉ ጋር ተደምሮ፣ ብልፅግና የሚባል ፓርቲ መመሥረቱ/ተመሠረተ መባሉ የተሻለ አቅጣጫ ቢያመለክትም፣ የተፈራውን ሥጋት ለጊዜው መሸሽ/መሻገር የቻልነው የበለጠና የከፋ ሥጋትና አደጋ ውስጥ ገብተን ነው፡፡ ዛሬ የለውጡ ሥጋቶች ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር የሚጠናወቱት የቀኝ ክንፍ አድኃሪያን ሳይሆኑ አክራሪ ብሔርተኞች ናቸው፡፡

የምርጫ ዘመቻ ቅስቃው ወይም ‹‹የምረጡኝ ዘመቻ ጊዜ››ው የሚጀምረው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2012 ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ገና ግንቦት 21 ቀን ቢሆንም (ነሐሴ 18 ድረስ ይዘልቃል)፣ ጥቅምት ውስጥ የጀመረው ቅድመ ዘመቻና ቅስቀሳ ግን የሚያሳየውና እያስፈራራው የሚናገረው፣ ለውጡን የሚመራው የዶ/ር ዓብይ አህመድ ቡድንና መንግሥት ቁርጠኛና ጠንቀኛ ተጠናዋቾች የኦሮሞ ብሔርተኛ ቡድኖች መሆናቸውን ነው፡፡

ጭፍን ጥላቻና ጥቃት ውስጥ የከተተን ያሳለፍነው ሩብ ምዕት ዓመት ብሔርተኛ አገዛዝ፣ አደረጃጀትና ፖለቲካ ሲያነክተን የኖረው ብቻውን አይደለም፡፡ የቁርጥራጭ የብሔርተኛ አመለካከት የአፀፋ ምላሽ ሆኖ ተጠናክሮ የመጣው የ‹‹አንድነት››፣ የ‹‹ኅብረ ብሔራዊነት›› ኃይልም ዳፋ አለ፡፡ ከአደገኛነታቸው አኳያ ሁለቱም አይተናነሱም፡፡ ስለከፋፋይና ቁርጥራጭ ብሔርተኛነት ከላይ በሰፊው የገለጽኩ ይመስኛል፡፡ የሚቀረን ነገር ቢኖር ስለሌላኛው አንድ ሁለት ነገር ማለት ነው፡፡ የአንድነት ወይም የኅብረ ብሔራዊነት ኃይል የሚባለው በከፋ ገጽታው ከግዛት ሒሳብ በስተቀር፣ የብሔር ብሔረሰብ መብት የማይገባው የትምክህትና የድንቁርና ጎራ ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊነት ዛሬ ለኢትዮጵያ አንድነት መቆም ከማለት የበለጠ ትርጉም የለውም፡፡

ዶ/ር ዓብይ ሲመጡ ጀምሮ ያነገቡት በዕርቅ የመተቃቀፍ፣ ወገንተኛ ባልሆኑ አውታሮች ላይ ዴሞክራሲን የመገንባት፣ ብሔረሰባዊ ማንነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር የማግባባት፣ እንደ አገር ህልውናን በሚወስኑ የቀጣናችንና የአኅጉራችን አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የማተኮር ነገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፈነጠቀው መልካም ዕድል በኖቤል ሽልማቱ ልክና መጠን ብቻ የሚሠፈር አይደለም፡፡ ይህ የአገርን ህልውና የሚወስን ዕድል ተጨባጭ እንዲሆን፣ ገልጀጅ ሲል በብልኃት ነቅነቅ እያደረጉ ወደፊት ማስኬድ የዴሞክራቶች ኃላፊነት ነው፡፡ የጎደለንም ያጎደለንም ይኼው ይመስለኛል፡፡ ዴሞክራቶች ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ወይ? ከማለት በላይ ዕውን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዴሞክራቶች አሉ ወይ? ማለት ድረስ መሄድም ይቻላል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አንድነት›› ላይም ሆነ ብሔር/ክልል ላይ ዓይንና ልባቸው የተሰካ ፖለቲከኞች ገና ገንታራነታቸውን አላላሉም፡፡ ግልጽና ሥውር አቋሞቻቸውም ሆኑ ድርጊቶቻቸው የሕዝብን ጥቅም የተመረኮዙ ናቸው ወይ ብለው መጠየቅን የመሰለ ጨዋነት ላይ ገና አልደረሱም፡፡ አድሏዊነት፣ ቁርሾን፣ ጥላቻንና መወንጃጀልን ወደ ጎን አኑረው በኢትዮጵያ ውስጥ የዚህንም የዚያንም አካባቢ ሕዝብ አስተያየት፣ ኪሳራና ትርፉን፣ ዕጦትና ብሶቱን፣ ጭንቀትና ሥጋቱን፣ ምኞትና ፀሎቱን ከማዳመጥ አልተነሱም፡፡ አዳምጠውም ልዩነቱንና ተመሳሳይነቱን በየፈርጁ ለመሰደር አልተንደረደሩም፡፡ እዚህ ሥራና መንገድ ውስጥ ቢገቡና የእነሱን ፖለቲካ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ቢያገናዝቡ የቅሌታቸውን፣ የሁላችንንም ቅሌት አበዛዝና ምንነት ለራሳቸውም ለሁላችንም ያሳያሉ፡፡ እስኪ አንዳንድ ጥያቄዎችን እያነሳን እንጠያየቅ፡፡

ከሶማሌላንድና ከጂቡቲ ጋር የተጠላለፈ ትርምስ መፍጠር የሚሻ ሕዝብ አለ? የአማራ ክልልዝብ እርስ በርስ መናጨት የትግራይዝብ ፀሎት ነው? ሕወሓቶች ከአገውና ከቅማንት የበቀለ ‹‹ሳተላይት›› ቡድን ስላበጁ የትግራይዝብ ይጠቀማል? የአገውና የቅማንትዝብ መብቶችስ ከሕወሓት መሻረክን ከአዴፓ ጋር መናቆርን ይፈልጋሉ? ባለፈ ታሪክና በእነ ምኒልክ ጉዳይ መተካተክና አምባጓሮ መክፈት ስለተመላለሰ፣ ስለተደጋገመ ሰዎች በጭካኔ ስለተገዳደሉና ብዙ ንብረት በእሳት ስለተበላ አንጀቱ ቅቤ የሚጠጣ ሕዝብ አለ? ለብቻዬ ብሮጥ ሰላምና ዕድገቴም ይሮጣል ብሎ የሚያምን የትኛው ሕዝብ ነው? ወይስ ተስማምቶ አንድ ላይ መሮጥ የሁሉም ጉጉት ነው? ከአሁን አሁን ምን ይመጣ ይሆን ከሚል የሥጋት ኑሮ መገላገልን (የደኅንነትና የፀጥታ ዋስትና ማግኘትን) በአሁኗ ሰዓት የማይማፀንስ የትኛው ሕዝብ ነው? የኦሮሚያዝብ ሆነ የሲዳማ፣ የሐረር ሆነ የድሬዳዋ ሕዝብ የሥራፍራዎች ጥቃት ስለወረናባቸው፣ በማያባራ ግርግር ጎብኚና ከፋች ከሩቅ ስለሸሸ፣ ልጆቻችን ሥራና እንጀራ ይወጣላቸዋል ብሎ ያምናል? በአጠቃላይ በድህነትና በውርደት ከሚፈደፍድ የአፈና ኑሮ ከመላቀቅ የበለጠ ሌላ አጀንዳ ያለው የትኛው ሕዝብ ነው? የየትኛው ክልል ወይም ብሔረሰብ የቤተሰብ ሕግ ነውአበደ› ወይምጨርቁን ጣለ› ሳይባል በይነ ብሔረሰባዊ ጋብቻ ይከልከል ወይም ይፍረስ የሚለው?

 እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሳቸውን ራሳ በራሳ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡ የውስጥ ሰላማችን ቀጣናዊ ሰላማችንን ይወስናል፡፡ የውስጥ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሰላማችን መበላሸትና አለመበላሽት ግብፅን ነገረኛም ሰላማዊም የማድረግ ተፅዕኖ አለው፡፡ በዴሞክራሲ መብቶችንና ግስጋሴን የመቀዳጀት ዕድላችን፣ ተግባብተንና ተጋግዘን የሽግግሩን ጊዜ ማቃናትን ይጠይቀናል፡፡ ከመበታተንና ከደም ጎርፍ ሕዝቦቻችንን ማትረፍ የምንችለውም ይህንን ወሳኝ ተግባር ከተወጣን ነው፡፡ አቋማችንና አረማመዳችን ለዚህ ቁልፍ የሕዝቦች ጉዳይ ምን እየፈየደ እንደሆን ልባችንን ከፍተን እናስተውል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...