Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የኮረና ቫይረስ ሥርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር የተሰጠ ማብራሪያ

ዓርብ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ግለሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ይፋ ተደረጓል፡፡ ግለሰቡ የ48 ዓመት ጎልማሳና የጃፓን ዜጋ መሆኑን፣ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቡርኪናፋሶ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱንና አስቀድሞ በተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ተገቢው የሕክምና ክትትል እየተደረገለት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ከበሽተኛው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦችም ተለይተው ክትትል የማድረጉ ሥራ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ግለሰቡ የከፋ ጤንነት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ፣ ይህ ዓይነቱም የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ የተጀመረውን ዕርምጃ እንዲጠናከር እንጂ፣ መደናገጥ መፍጠር እንደሌለበት የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡ መደናገጥና አጉል ፍራቻ ከበሽታው እኩል አደገኛ ሊሆን እንደሚችል፣ በዚህ በሽታ የሚያዘው አብዛኛው ሰው ቀላል ሕመም ከያዘው በኋላ እንደሚድን፣ ነገር ግን ዕድሜያቸው የገፋ ወይም ተጨማሪ በሽታ ባላቸው ሰዎች ላይ ሕመሙ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ነው የተመለከተው፡፡ የኮረና ቫይረስን በተመለከተ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ታደሰ ገብረማርያም እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡   

ጥያቄ የግለሰቡ አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስላል? ከየት ነው የተነሳው? ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ከሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር ኤባ፡– የግለሰቡ የጉዞ ታሪክ እንደሚያሳየው ከጃፓን ነው የተነሳው፡፡ ፌብሩዋሪ 23 ወይም የካቲት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ቡርኪናፋሶ የነበረና ማርች 4 ወይም የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ ባለን መረጃ መሠረት ወደ ግል ጤና ተቋም ሄዶ ነው የተመረመረው፡፡ ከተቋማቱ ጋር ቅንጅታዊ አሠራር ስላለን በደረሰን ጥቆማ መሠረት፣ ፈጣን ምላሽ በሚሰጠው ግብረ ኃይል የሚያስፈልገውን ምርመራና ክትትል ካደረገ በኋላ ለይቶ ማቆያ ጣቢያ ውስጥ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ በሽታው ሊገኝ የተቻለው ናሙናው በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተሠራ በኋላ ነው፡፡

ጥያቄግለሰቡ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ትንሽ ቆይታ ነበረው፡፡ ከዚህ አንፃር ክትትሉ ምን ይመስል ነበር? ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?

ዶ/ር ኤባ፡– አንድ መንገደኛ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ መጀመርያ የእኛ የመከላከል ምላሽ ሒደቶች የሚያተኩሩት በሽተኛውን መመለስ ላይ አይደለም፡፡ ማናቸውም አገሮች ይህንን ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ስለዚህ በመጀመርያ ቅንጅታዊ አሠራሩ የሚያተኩረው አንድ የተጠረጠረ ሰው ሲመጣ፣ ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቶ መሠራጨቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሳይደርስ መቆጣጠር ነው፡፡ ይህንንም ሥራ ለማከናወን የሚያስችል አቅም መገንባት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ነው ይህንን መንገደኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ልንይዘው የቻልነው፡፡ በዚህም የተለያዩ ዓይነት ንክኪዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሽታን ከመቆጣጠር አንፃር ማንም አገር የሚከተለው ራሱን የቻለ አካሄድ አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ የጉዞ ታሪኩ ከመጣ ጊዜም ጀምሮ ያለው ሒደት የሚታይበትና የሚገመገምበት አግባብ አለ፡፡ በዚያ አግባብ መሠረት እንቅስቃሴው በሚገባ ከተጠና በኋላ በቆይታው ወቅት ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች የማግኘት፣ የመከታተል ሒደቱ ተከናወነ፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው ከ25 በላይ የሚጠጉ ሰዎች በኢንስቲትዩቱ ክትትል ውስጥ ሲኖሩ፣ ይህም ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ለመግለጽ አወዳለሁ፡፡

ጥያቄ፡ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያዋስኗት ድንበሮች አሉ፡፡ ድንበሮቹ በየብስ የሚያገናኙ ናቸው፡፡  ከዚህ አኳያ በየብስ መተላለፊያ መንገዶች ያለው የቅኝት ሥራ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ኤባ፡– በየሳምንቱ በምንሰጠው መግለጫ ላይ፣ እንዲሁም በኢንስቲትዩና በጤና ሚኒስቴር ድረ ገጻችን ላይ ይህንን በተመለከተ የምናስቀምጣቸው መልዕክቶች አሉ፡፡ አሁን የምንነጋገርባቸው 30 ያህል የየብስ መተላለፊያዎች በዚህ ስክሪኒንግ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ ጋር የሚያገናኙ አብዛኞቹ ኬላዎች በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በፌዴራል ወይም በማዕከል ብቻ የሚሠራ ሳይሆን ከክልሎች ጋር በቅንጅት የሚሠራ ነው፡፡

ጥያቄ፡ግለሰቡ በኤርፖርት የሙቀት መለያን እንዴት ሊያልፍ ቻለ?

ዶ/ር ኤባ፡– በአየር መንገዳችን የሚመጡ ወይም በኤርፖርት የሚያልፉ መንገደኞች የሚለኩት ሙቀታቸውን ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም መንገደኛ የመቁት መጠኑ ከተወሰነ በታች ከሆነ ሁኔታውን ለይቶ ማወቅ አይቻልም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው መንገደኛው ከቡርኪና ፋሶ ነው የመጣው፡፡ ቡርኪናፋሶ ደግሞ በቅርቡ ነው ኮረና ቫይረስ መገኘቱን ይፋ ያደረገችው፡፡ እስከ በቅርብ ጊዜ በነበረው መረጃ ወደ ሁለት ሰዎች ናቸው እንደተጠቁ በሪፖርት የተረጋገጠው፡፡ ስለዚህ በተለይ ለሁለት ሳምንት ለክትትል የምናስቀምጣቸው በኮሮና ቫይረስ ከፍ ያለ ሪፖርት ካደረጉ አገሮች የመጡ መንገደኞችን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ መንገደኛ በማቆያ ውስጥ በክትትል ላይ ባይሆንም፣ በክትትል ውስጥ ያልገቡ መንገደኞችን ደግሞ የምንከታተልባቸውን አግባቦች በመመርኮዝ ነው ማኅበረሰቡ ውስጥ ሳይወሰን በቅርቡ ግለሰቡ ፖዘቲቭ መሆኑ ለማረጋገጥ የቻልነው፡፡

ጥያቄአቅምን የማጎልበት ሥራ እንዴት እየተከናወነ ነው? ማኅበረሰቡስ ምን ማድረግ አለበት?

ዶ/ር ኤባ፡– ይህንን በተለመከተ በየሳምንቱ በምንሰጠው መግለጫ ላይ አሳውቀናል፡፡ አብዛኞቻችሁ በመግለጫችን ላይ የተሳተፋችሁ ስለሆነ በሚገባ ልትረዱት ትችላላችሁ፡፡ አቅማችንን በየጊዜው እያጎለበትን ነው ያለነው፡፡ ይህም ከአገሪቱ አቅም ጋር ታሳቢ ተደርጎ የሚታይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን አንድ ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ሥራውን አቁሞ ለኮረና ቫይረስ ሕክምና ብቻ ዝግጁ እንዲሆን የተደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ እስከ 600 ግለሰቦችን የማከም አቅም ያለው ነው፡፡ በሌሎቹም አቅም የማጎልበት ሥራ በዚያው መጠን ቀጥሏል፡፡

ጥያቄተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? እንዴትስ መከላከል ይቻላል?

ዶ/ር ኤባ፡– በዚህ በሽታ መጠቃት ማለት ሞት ማለት አይደለም፡፡ የተለያዩ ሒደቶች አለው፡፡ እነዚህን ሒደቶች ካለፉ በኋላ ነው የሞት ምጣኔዎች ሊከሰቱ የሚችሉት፡፡ መጀመርያ ይህ በሽታ የሚያጠቃው የዕድሜ ክልላቸው በተለይ ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያንን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ 80 በመቶ ያህሉ በሽታን ከመከላከል አቅም ጋር ተዳምሮ በራሳቸው ከበሽታው የሚድኑበት አግባብ አለ፡፡ 20 በመቶ ናቸው የበሽታው ሕክምና የሚያስፈልጋቸው፡፡ ሌላው ሊሰመርበት የሚገባው ብዙ አገሮች በሽታውን ሪፖርት እያደረጉ ነው፡፡ አሁን በምንነጋገርበት ወቅት ከ134 በላይ አገሮች ይህንን በሽታ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ በሽታው በአጭር ርቀት ሳይሰፋ የሚያዝና የሚገኝ ከሆነ በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ከዚሀ አንፃር በሽተኞቹ በሕክምና ሙሉ ለሙሉ የሚድኑበት ሁኔታ አለ፡፡ ማኅበረሰባችን ውስጥ አንድ ኬዝ ወይም አንድ በሽተኛ ተገኘ ማለት፣ የማኅበረሰቡ ሁኔታ ትልቅ ችግር ነው ማለት እንዳልሆነ መረዳት ይገባል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚታወቀው አንድ ኬዝ ነው፡፡ ይህም ለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ነው ያለው፡፡ የጤንነት ሁኔታውም መልካም ነው፡፡ ማኅበረሰባችንም ሊወስዳቸው የሚገባ ጥንቃቄ ይኖራል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በበሽተኛው ከፍተኛ ሥጋት ሳይገባው በጣም ደግሞ በሽታውን ሳያሳንስ፣ ልክ እንደ ሥጋት መጠኑ ከመንግሥትና በተለይ ተአማኒ ከሆኑ አካላት የመረጃ መልዕክቶችን እየተከታተለ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ መጨባበጥ ከአንዱ ወደ ሌላው ለመተላለፍ ዕድል ይሰጣል፡፡ በተቻለ መጠን ሌሎች አማራጮችን መከተል፣ የበሽታውን ምልክት የሚያሳይ ግለሰብ በተለይ በበሽታው ከተጠቁ አገሮች የመጡ መሆናቸው ሲታወቅ ወይም ከመጡት ጋር ንክኪ ያለው ሰው መሆኑ ከታወቀ፣ በቀጥታ ለጤና ተቋማት በተገቢው መንገድ በፍጥነት ማሳወቅ፣ እንዲያውም በነፃ የስልክ መስመር 8335 ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውሳኔ ለመስጠት አጋዥ ይሆናል፡፡

ጥያቄ፡ግብዓት የማሟላትና ሥልጠና የመስጠት ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?

ዶ/ር ኤባ፡- ተጋላጭ ለሆኑ ማኅበረሰቦችና ለጤና ባለሙያዎች ሊያገለግሉ የሚችሉ ግብዓቶች የሚሟሉበት ሒደት እንደቀጠለ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደሰማችሁትም በአገር ውስጥ የፊት መሸፈኛ ጭምብል የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ወደ ውጭ አገር የሚያቀርቡትን ሽያጭ አቁመው፣ ሙሉ ምርታቸውን  በአገር ውስጥ እንዲያቀርቡ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ከሥልጠናም አንፃር ሥልጠናው የአየር መንገድ ሠራተኞችን፣ የበረራ አስተናጋጆችን፣ የፀጥታ ሠራተኞችንና የኤምግሬሽን ባለሙያዎችን ያካተተ ነው፡፡ ከ2,500 በላይ የሆቴል ቤት ባለሙያዎችን፣ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ የተለያዩ የሙያ ማኅበራትን፣ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ያካተተ ሥልጠና በየጊዜ እየተሰጠ ነው ያለው፡፡

ጥያቄ፡- በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው ናሙናው የት ነው የሚመረመረው? የቴስቲንግ ኪት እጥረት ገጥሟችኋል?

ዶ/ር ኤባ፡- የምርመራውና የማረጋገጫው ሥራ የሚከናወነው እዚህ ነው፡፡ የኮረና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ በዓለም ላይ ትልቅ ውስንነት አለ፡፡ ምናልባት አሜሪካ  ውስጥ የተከሰተው ማሳያ ሊሆን የሚቻል ይመስለኛል፡፡ አሜሪካ ትልቅ አገር ናት፡፡ ትልቅ የኢንዱስትሪ ባለቤት አገር ናት፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ትልቅ ችግር በነበራት ወቅት በቂ የሆነ ቴስቲንግ ኪት በአገር ውስጥ እንዳልነበር መገናኛ ብዙኃን በሰፊው ይዘግቡ ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ አዳጋች የሚያደርገው የመመርመሪያ ሪኤጀንት ወይም ኪት ለገበያ አልቀረበም፡፡ ስለዚህ የተወሰኑ አካላት እያመረቱ በአሜሪካ ሲዲሲ በኩል የምናገኘው ድጋፎች ናቸው፡፡ የቻይና መንግሥትንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የምናገኛቸውን ውስን የመመርመሪያ ኪቶችን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር በጥንቃቄ ሥራዎቻችን እያከናወንን ነው ያለነው፡፡ ነገር ግን እንደ በሽታው ስፋት ባለፉት ጊዜያት የተሠሩ ጥሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በክልሎች ያቋቋምናቸው የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን አቅም የማጎልበትና በተቻለ መጠን ይህ ምርመራ እንዲሰጥ መንገድ እየተሠራ ነው ያለው፡፡

ጥያቄ፡– በቦሌ ኤርፖርት የሚደረገው ክትትል ምን እንደሚመስል ብታብራሩልን?

ዶ/ር ሊያ፡- በሽታውን ለመለየት በኤርፖርት የምንሠራቸው ሥራዎች ቢኖሩም፣ አንድ ሕመሙን ይዞት የሚመጣ ሰው የምንለይባቸው በአብዛኛው ጊዜ የተለያዩ አካሄዶች አሉ፡፡ አንደኛው በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ አገሮች የሚመጡ ሰዎች የሚሞሉት ፎርም አለ፡፡ በዚህም ፎርም በመጠቀም ክትትል ይደረግላቸዋል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ከ120 በላይ የሆኑ አገሮች በበሽታው ተይዘዋል፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ይህንን ዓይነት ክትትል አናደርግም፡፡ ክትትል የምናደርገው ከፍተኛ የበሽታው ቁጥር ያለባቸው አገሮች ላይ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት በአሀኑ ጊዜ ከስምንት በሚበልጡ አገሮች ላይ ክትትል እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ውጪ ያሉትን ደግሞ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥትና የግል ተቋማት እንዲከታተሉ ይደረጋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን አስፈላጊ የሆነ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከፍተኛ የበሽታ ቁጥር ከነበረባቸው አገሮች ጋር የጉዞ ታሪክ ያላቸውና የበሽታው ምልክት የታየችባቸው ካገኙ፣ ለኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወዲያውኑ እንዲያሳውቁ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ይህም ታካሚ በዚህ መንገድ ነው ሊገኝ የቻለው፡፡

ጥያቄ፡- በለይቶ ማቆያ ማዕከል የባለሙያዎች አቅም የማጎልበት ሥራ ምን ይመስላል? በየመድኃኒት ቤቱ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እጥረት ተከስቷል? ከምን የመጣ ነው?

ዶ/ር ሊያ፡- የባለሙያዎችን ሥልጠና በተመለከተ በመላው ማዕከሉ ውስጥ የሚከናወነው፣ ሥራ ለዚህ ሲባል ሥልጠና በተሰጠው ባለሙያው ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ የጤና ተቋማትም ውስጥ በሽታው ሊገኝ እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህም የተነሳ በበርካታ የጤና ተቋማት ሥልጠናው እንደቀጠለ ነው፡፡ የማስክ ጉዳይ ግን አንድ የማሳስበው ነገር፣ ይህ በሽታ ስለተከሰተ ሰው ማስክ ማድረግ አለበት ማለት አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስክ እጥረት ተከስቷል፡፡ ማስክ ማድረግ ደግሞ የራሱ የሆነ ጉዳትም እንዳለው ብዙ መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡ ማስክ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሰዎች በዚህ በሽታ የተረጋገጡ ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውም ዓይነት ጉንፋን መሰል፣ ሳልና ትኩሳት ያላቸው ሰዎች እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች በተጨማሪም በቤትም ሆነ በሕክምና ተቋም አገልግሎት ድጋፍ የሚሰጡ ሰዎች ማስክ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ለመከላከል ሲባል ሁሉም ሰው ማስክ ማድረግ አለበት የሚል ግንዛቤ ትክክል አይደለም፡፡

ጥያቄ፡- ቫይረሱን ለመከላከል ኅብረተሰቡ ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት? ወደፊትስ ምን ዓይነት ዕርምጃ ሊወሰድ ታስቧል?

ዶ/ር ሊያ፡- አሁን  አንድ ኬዝ ያገኘንበት ወይም ያወቅንበት ደረጃ ላይ ነን፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የተለያዩ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ አሁን ግን በጣም የሚጨናነቁ ቦታዎች ላይ በተቻለ መጠን አለመገኘት አንዱ የሚመከር ጉዳይ ነው፡፡ በአውቶብሶች፣ በሌሎችም የሕዝብ ትራንስፖርቶች መስኮቶች እንዲከፈቱ፣ የአየር ቬንትሌሽኖች እንዲኖሩ ግድ ይላል፡፡ የተጨናነቁ አውቶብሶችና ሌሎች ትራንስፖርቶች ከመጠቀም ይልቅ በተቻለ መጠን በእግራችን መሄድ ይመረጣል፡፡ የጉንፋን ስሜትና ትኩሳት ያለባቸው ሰዎች ትልልቅ ወደ ስብሰባዎች፣ ወደ ሥራና ወደ ትምህርት ቤት ባይሄዱ ይመከራል፡፡ ከዚህ ውጩ አሁን የሚወሰድ ዕርምጃ የለም፡፡ ነገር ግን በሒደት የሚያስፈልጉ ነገሮች ካሉ እናሳውቃለን፡፡

ጥያቄ፡- ቫይረሱን ለመከላከል ምን ያህል በጀት ተመድቧል?

ዶ/ር ሊያ፡- ለዚህ ሥራ ከመንግሥት 300 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ ይህም በቂ ስለማይሆን ተጨማሪ በጀት የመጨመሩ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ በተጨማሪ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተጨማሪ በጀት ለማግኘት እየተሠራ ነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...