Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጃፓናዊው የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር የኢትዮጵያን የምርት ጥራት ማሻሻል እንደሚገባ ይመክራሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በደን ጥበቃና ተጠቃሚነት ላይ አዲስ አሠራር መከተል ይገባል ብለዋል

ከኮቤ ዩኒቨርሲቲ በመምጣት ለሁለት ቀናት ገለጻ የሰጡት የዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ባለሙያ ኬጂሮ ኦትሱካ (ፕሮፌሰር) በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንቅስቀሴዎች፣ እስካሁን ሲተገበር ከቆየው የአመራረት ሥርዓት በመሻገር በምርት ጥራት ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ላለፉት አሥር ዓመታት ያህል የጃፓን የማኔጅመንት ፍልስፍና የሆነው ካይዘን ሲተገበር ቢቆይም፣ ያመጣው ለውጥ ከመሠረታዊ የወጪ ቅነሳ አልዘለለም፡፡ በዚህ የሚስማሙት ኦትሱካ (ፕሮፌሰር)፣ ይህን አካሄድ መቀየር እንደሚገባ፣ ምርታማትን ከማሳደግ ባሻገር ጥራት ላይ ያተኮረ የምርት ሥርዓት ማስፈን እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ የካይዘን ኢንስቲትዩት ማቋቋምን ጨምሮ በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የዘለቀ የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠና መሰጠት ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ግንባር ቀደም በመሆን በካይዘን ሥርዓተ ትምህርት እስከ ዶክትሬት ዲግሪ እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በምርት ጥራትም ሆነ በአምራችነት ብቃት ላይ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የታየው ለውጥ አዝጋሚ ከመሆኑም አልፎ የታሰበው ዘላቂ ለውጥና ውጤታማነት ብዙም አልታየም፡፡ በዚህ አባባል በከፊል እንደሚስማሙ የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ፣ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያደርሳት የሚችለውን ወይም አድቫንስድ ካይዘን የተሰኘውን ሥርዓት መተግበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ካይዘን ዘለቄታዊ ምርታማነትና ጥራትን ለማስፈን ያልተቋረጠ የለውጥ ሥርዓትን የሚያቀነቅን የማኔጅመንት ፍልስና ነው፡፡ ይህንን ሥርዓት ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ካስቻሉ ጅምሮች መካከል ፕሮፌሰሩ ከኢትዮጵያ ምሁራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የነበራቸው ግንኙነት አስተዋጽኦ እንደነበረው ይገልጻሉ፡፡

የአቶ መለስ የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጽሑፍ

ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት ከቀድሞው የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረአብ (ነፍስኄር) ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸው ያስታወሱት ኦትሱካ (ፕሮፌሰር)፣ ከአቶ ነዋይም ባሻገር የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊንም ለማወቅና በኢንዱስትሪ መስክ ሐሳብ ለመለዋወጥ የቻሉባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት አብራርተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ከፖሊሲ ጉዳዮች አልፎ ወደ የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጽሑፍን እስከማማከር ያመራበት አጋጣሚም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን ሳሉ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለመሥራት መነሳታቸውን ያደነቁት ኦትሱካ (ፕሮፌሰር)፣ አቶ መለስ የጻፉትን የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ረቂቅ ጽሑፍ የማየትና ማስተካከያ ሐሳቦችን አክለው እንደመለሱላቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥረታቸው ገፍተውበት እስከ መጨረሻው አለማድረሳቸው ከምን መነሻ እንደሆነ እንደማያውቁ ይገልጻሉ፡፡  

የማሟያ ጽሑፉ ርዕስም ሆነ ጽሑፉ ለየትኛው ዩኒቨርሲቲ እንደተዘጋጀ እንደማያስታውሱ የሚገልጹት ኦትሱካ (ፕሮፌሰር)፣ ይሁን እንጂ በእንግሊዝ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለማግኘት በማሰብ የጻፉት እንደነበር በደምሳሳው ይገልጻሉ፡፡ ጽሑፉ የደቡብ እስያ አገሮችን ተሞክሮ መነሻ ያደረገ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲን ለኢትዮጵያም እንዲሠራ የሚተነትን ጽሑፍ እንደነበር እንጂ የጽሑፉ ርዕስ ምን እንደነበር አያስታውሱም፡፡ 

ይህ እንግዲህ በአብዛኛው የካይዘን ትግበራን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ በተደረገ ምክክር መነሻነት የነበረ ግንኙነት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ካይዘን እንዲተዋወቅ ሐሳባቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንዳቀረቡላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በሐሳቡ ተስማምተውበት በኢትዮጵያ የካይዘን ኢንስቲትዩት እንዲመሠረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሲተገበር ከቆየው ካይዘን ባሻገር መሄድ አለባችሁ የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ የተፈጥሮ ሀብትን በመንከባከብ ረገድ እስካሁን የነበሩ አሠራሮች እንዲቀየሩም ጠይቀዋል፡፡ የተራቆቱ አካባቢዎችን በአረንጓዴ ልማት በማሻሻል የደን ተጠቃሚነትን ማስፋት ይገባል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ በትግራይ ክልል ከሁለት ዓመታት በፊት ማካሄድ ስለጀመሩት ጥናት አብራርተዋል፡፡ የደን ጥበቃን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግና በደን አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ገቢ ለማሳደግ በማኅበር ከሚደረግ የደን ጥበቃና አስተዳደር ሥርዓት ይልቅ ግለሰቦችን ማዕከል ያደረገ የደን አስተዳደር መከተል ብሎም የጥቅማ ጥቅም ድጋፍ መስጠት ውጤታማ እንደሚያደርግ የኢኮኖሚ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵ ብቻም ሳይሆን በዓለም ደረጃ የደን ጥበቃና ክብካቤ ላይ ሲተገበሩ የቆዩ አሠራሮች ችግር አለባቸው በማለት እንደ ዓለም ባንክ፣ የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅትና ሌሎችም ለደን ጥበቃ የሚከተሉትን አሠራር ይተቹታል፡፡ ‹‹የተሳሳተና ለደን ጥበቃም ሆነ ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ዕርባና የሌለው›› ሥርዓት በማለት አጣጥለውታል፡፡

ከዚህ ይልቅ የግለሰቦችን የደንና የመሬት ተጠቃሚነት መብት የሚያረጋግጥ ሥርዓትን በማስፋፋት፣ ዜጎች የደን ልማት ላይ እንዲሳተፉ ብሎም ደኑን ጥቅም ላይ በማዋል እንዲጠቀሙ ማድረግ የሚቻልባቸውን መንገዶች ማስፈን እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ ከማኅበረሰብ አቀፍ የደን ጥበቃ ሥርዓት ይልቅ፣ ግለሰብ ተኮር የደን ልማት ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች