በኢትዮጵያ ከሚጠቀሱ የመንግሥት ችግሮች መካከል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሥራቸው ስለሚያስተዳድሯቸው ይዞታዎች በጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን የታገዘ መረጃ አለመኖር ተጠቃሹ ነው፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታዎችን መለየት፣ መቀየስ፣ ካርታ አዘጋጅቶ መመዝገብ፣ እንዲሁም የካርታ ዝግጅት በማከናወን የመረጃ ቋት ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ይገለጻል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የተስተካከለ የመንግሥት የመሬት ይዞታ አስተዳደር መገለጫው መሬት በአግባቡ የመጠቀም መብት፣ ክለላ፣ ገደብ፣ እንዲሁም የመሬት ይዞታው ወሰንና ልኬትን የተመለከቱ መረጃዎች ተሟልቶና ትክክለኛነቱ ተረጋግጦ የተመዘገበ ከሆነ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት በቅድሚያ የመንግሥት መሬት ይዞታ መለየትና መብትን ማረጋገጥ ሥራ መከናወን ይኖርበታል ይላሉ፡፡
ይህም ሥራ በአገሪቱ በሚገኙ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማትና የመንግሥት ልማት የመሬት ይዞታዎች በልኬት በማረጋገጥ ሒደት መከናወን ያለበት በመሆኑ፣ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል ግብዓትና በጀት በታቀደው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ ያለበት በመሆኑ በፕሮጀክት መልክ መሠራት ያለበት እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
በዚህም መሠረት መንግሥት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ በደንብ ቁጥር 431/2018 መሠረት የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ከተቋቋመ አንድ ዓመት የሆነው ሲሆን፣ ወደ ሥራ ከገባ ግን አምስት ወራትን ያስቆጠረ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም በዋነኝነት የፌዴራል መንግሥት፣ እንዲሁም ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች የያዙዋቸውን ይዞታዎች መረጃቸውን በመጠንም በልኬትም ለመሬት ልማት ማፕ አድርጎ ወደ ሥራ ለማስገባት የተቋቋመ መሥሪያ ቤት ነው የሚሉት ወ/ሪት ሌንሳ መኮንን የፌዴራል መንግሥት የመሬት ባንክና የልማት ትብብር ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡
ይህም ተቋም የመጀመርያው ሥራው አድርጎ የወሰደው መረጃዎችን መሰብሰብ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ከኮርፖሬሽኑ በተገኘው ይዞታና ተያያዥ መረጃዎች መሠረት በአገሪቱ ውስጥ የተለዩት 384 ቁራሽ መሬቶች 106.72 ኪሎ ሜትር ካሬ ስፋት ያላቸው ይዞታዎች ስለመኖራቸው እንደሚገመትና የመጀመርያ በሆነው በዚህ ፕሮጀክት ትግበራ ሒደት ወቅትም የማጥራትና የማስተካከል ሥራ እንደሚኖር ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክቱ ባለቤት የፌዴራል የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን በመተግበር ሒደት በበላይነት የሚመራውና የሚቆጣጠረው ጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እንደሆነ ታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የፌዴራል መንግሥት የመሬት ባንክና የልማት ትብብር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሌንሳና የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ቱሉ በሻ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በመግባቢያ ስምምነቱ ወቅትም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ ተገኝተዋል፡፡
አብርሃም (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሆነውን መሬት በቴክኖሎጂ በመጠቀም ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚውም ረገድ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል ሥራ በጋራ ለመሥራት እየተፈራረምንበት ያለነው መግባቢያ ሰነድ ነው በማለት፣ እሱን መሠረት አድርገንም በፍጥነትም ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ሲስተሙን ገንብተን የምናስረክብ ይሆናል ብለዋል፡፡
የጂኦ ስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ቡድንም በዕለቱ ከመሬት ምዝገባ ጋር ተያይዞ የሚጠቀማቸውን ቴክኖሎጂዎችና መረጃዎች ኤግዚቢት አድርገዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ ከ43 በመቶ በላይ የአገሪቱን ክፍሎች በአየር ፎቶ ግራፍ በማንሳት መሸፈን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የከፍታ መረጃዎችም ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ባለሙያዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የማጥራትና የማስተካከል ሥራ የሚካሄድባቸው ይዞታዎች ቁጥር እንደየሁኔታው በመለየት በአጠቃላይ 384 ይዞታዎችን ከአራት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ለማከናወን እንደታቀደ ወ/ሪት ሌንሳ ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ እንዲህ አጠር ያለ ጊዜ ይጠይቃል ብለን ያሰብነው ለተለያዩ ዓላማዎች እንዲውሉ ተብለው ማፒንግ ሥራዎች ቀድሞውኑ የተሠሩ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ በማፒንግ ወቅት የሚገኙትን ባዶ መሬቶችም ወደ ልማት ቀጥታ እንደሚያስገቡም ወ/ሪት ሌንሳ ገልጸዋል፡፡