Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በወለድ አልባ አገልገሎት 3.7 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ አሰባሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲቀርብ የሚፈቅደው ሕግ እንደወጣ አገልግሎቱን በማስጀመር ግንባር ቀደም በመሆን የነበረው የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በዚህ አገልግሎቱ የሚስተናገዱ ደንበኞቹን ከ350 ሺሕ በላይ ከማድረስ አልፎ ከ3.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወለድ አልባ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰቡን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ሐሙስ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሚያቀርብበትን የመጀመርያውን ቅርንጫፍ ሥራ ባስጀመረበት ወቅት እንደገለጸው፣ የወለድ አልባ አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ ቁጥር 356,337 ያህል ናቸው፡፡

 ባንኩ ወለድ አልባ አገልግሎትን ለማስፋፋት ባደረገው እንቅስቃሴ ውጤት ማስመዝገቡን የገለጸው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በዚሁ መስክ የሚተገበሩ አዳዲስ አገልግሎቶችንም እንደሚያስጀምር አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. እስከ ፌብሩዋሪ 29 ቀን 2020 ድረስ በወለድ አልባ አገልግሎቱ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 3.7 ቢሊዮን ብር ማስመዝገቡንና ለዚሁ ዘርፍ ያዋለው የብድር ክምችትም 2.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን የወለድ አልባ ቅርንጫፉ በተከፈተበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን ገልጸዋል፡፡

 ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት አትራፊ እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ባንኩ በ2011 ዓ.ም. ከዚሁ አገልግሎት 217 ሚሊዮን ብር ማትረፉን በአስረጂነት አቅርበዋል፡፡ ባንኩ ለራሱ ብቻም ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ወለድ አልባ አገልግሎትን መጀመሩ፣ ለሌሎች ባንኮችም መንገዱን እንደከፈተላቸው የሚጠቀስለት ተሞክሮ እንደሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ አቶ ተፈሪ እንደሚሉት፣ ‹‹ባንኩ በዘርፉ ፋና ወጊ ስለመሆኑ ታሪክ የማይረሳው ሀቅ ነው፡፡ ባንካችን በዚህ ዘርፍ ለሌሎች አቻ ባንኮች ጥሩ የዕውቀት ሽግግር በመሆን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ለአገልግሎቱ ተደራሽነት በጎ ሚና ተጫውቷል፡፡›› የወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ይረዳ ዘንድ አገልግሎቱ ራሱን በቻለ ቅርንጫፍ ደረጃ እንዲቀርብ የአገሪቱ የባንክ አዋጅና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ እንዲወጡ ለማስቻል ባንኩ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተነግሯል፡፡

የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አሰግድ ረጋሳ ባንኩ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ ረገድ ፈር ቀዳጅ ከመሆኑም ሌላ፣ ‹‹በአሁን ወቅት ሁሉም ባንካች የወለድ ነፃ የባንኪንግ አገልግሎት የጀመሩና እየጀመሩ ያሉ በመሆኑ፣ ባንካችን ከመነሻው ይዞት የተነሳው የባንክ አገልግሎትን ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተደራሽ የማድረግ ዓላማ በእጅጉ እየተሳካ መሆኑን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡ ባንካቸው በአጠቃላይ የባንክ አገልግሎቱ እያሳየ ካለው እመርታ ጎን ለጎን ራሱን በቻለ ቅርንጫፍ አገልግሎቱን ከመስጠትም በላይ ከፍ ብሎ ራሳቸውን የቻሉ ኢስላሚክ ባንኮች እንዲደረጁና መንግሥት የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣላቸው ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ የወለድ አልባ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፉን ሲያስመርቅ እንደገለጸው፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጨማሪ ደንበኞች ለማሰባሰብ አሁንም የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ነው፡፡ በእነዚህ ልዩ ቅርንጫፎችና በሁሉም ቅርንጫፎቻችን ከምንሰጣቸው መደበኛ የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቶት በተጨማሪ ሕፃናቶችን፣ ወጣቶችን፣ የተመለከቱ አገልግሎትን በማከል እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ አቶ አሰግድ በዚሁ ጉዳይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ በተለይ በሃይማኖታቸው ምክንያት የባንክ አገልግሎት በተገቢው ለማግኘት የተቸገሩትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ ለመመለስ ባንኩ የሸርዓ መርሆዎች ለኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ኅብረተሰቡን ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ እንዲህ ያለውን አገልግሎት ለመስጠት የቀድሞ የባንካችን ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ለተጫወቱት የመሪነት ከፍተኛ ሚና በባንኩ ኃላፊዎች በዕለቱ ተመሥግነዋል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ፈር ቀዳጅ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አሁንም በአገልግሎቱ ከግል ባንኮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ እንደቻሉ ተገልጿል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በመስኮት ደረጃ በመጀመር ቀዳሚ የሆነው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ በመክፈት ግን ከሌሎች ባንኮች ዘግይቶ የመጀመርያውን ቅርንጫፍ የከፈተው ባለፈው ሐሙስ ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ ቅርንጫፍ ሌላ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ተመሳሳይ አራት ቅርንጫፎን በመክፈት በአንድ ሳምንት አምስት ቅርንጫፎቹን በመክፈት ሥራ አስጀምሯል፡፡

በቢላል ቅርንጫፍ ምረቃ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄይላን ከድር (ዶ/ር) የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሺኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሡልጣን አማን ኤባ የተገኙ ሲሆን፣ የቅርንጫፉን መከፈት ለማብሰር የተዘጋጀውን ሪባን ከባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ቆርጠዋል፡፡

ባንኩ በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ ከሐሙስ ጀምሮ አስመርቆ ወደ ሥራ ያስገባቸው ቅርንጫፎች ቦሌ፣ አየር ጤና፣ ኮልፌ፣ መርካቶና ቤተል አካባቢ የሚገኙ ናቸው፡፡

እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ውስጥ በባሌ ሮቤ፣ በሻሸመኔ፣ ጅማ፣ አላባ ሰንበቴ፣ ዶዶላ፣ ድሬዳዋ ሐረርና አዳማ ከተሞች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎችን ሥራ ያስጀምራል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በአንድ ወር ውስጥ የሚከፈቱ መሆናቸው ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ባንኩ ከአጠቃላይ እንቅስቃሴ አንፃር የደረሰበትን ውጤት በተመለከተ፣ እስከ 2012 ሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ የተከፈለ ካፒታል ሦስት ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም 23.8 ቢሊዮን ብር፣ የሰጠው ብድር 20.4 ቢሊዮን ብር፣ የቅርንጫፎች ብዛት 280፣ የደንበኞች ቁጥር ከ1.6 ሚሊዮን በላይ እንደደረሰ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ የቋሚ ሠራተኛ ብዛት 3,974 ሺሕ የደረሰ ሲሆን፣ ዓመታዊ ትርፉም እ.ኤ.አ. ጁን 30 2019 ላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ፣ እንዲሁም ጠቅላላ ሀብቱ 32 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች