ዘውዳዊው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በደርግ የበታች ወታደሮች ዕርምጃ ሥልጣኑን ከተነጠቀበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማንነት፣ እንዲሁም የባህል መገለጫዎች ከሆኑ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የመሬትና የብሔር ጥያቄ ተጠቃሽ ነው፡፡
በተለይ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ጋር ወደ ሥልጣን የመጣው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት፣ የአገሪቱን ጭቁን ሕዝቦች የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ያስችላል ያለውን ‹‹የመሬት ለአራሹ›› አዋጅን በማወጅ፣ በጥቂት መሳፍንትና የቤተ ክርስቲያን ንብረትነት ተይዘው የነበሩ መሬቶችን ለጭቁኑ አርሶ አደር የመመለስና የማከፋፈል ሥራ ቢያከናውንም፣ የመሬት ጥያቄ በአገሪቱ አንገብጋቢው የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የማንነት ጥያቄዎች ማጠንጠኛ በመሆን መቋጫ ያላገኘ መሠረታዊ ጥያቄ እንደሆነ ዘልቋል፡፡
መሬት ባለው ተፈጥሮአዊ ባህሪይ ምክንያት በኢትዮጵያና በሌሎች መሰል አገሮች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማንነት ጉዳዮች የስበት ማዕከል ሆኖ ዘልቋል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ በእርሻ በሚተዳደርበት አገር፣ የመሬት ጉዳይ የኢኮኖሚያዊ ማዕከል ብቻ ሳይሆን ከመሬት ጋር የተያያዙ ማናቸውም ጉዳዮች የፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምንጭም ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገልጹ በርካታ ድርሳናት አሉ፡፡
በዚህ ማነፃፀሪያነት የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ ለሚመለከት መሬት ለዘመናት የፖለቲካ ሥልጣን ምንጭ፣ የፖለቲካ ሥልጣንን ለማጣትም ምክንያት በመሆን ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ወታደራዊ የደርግ ሥርዓት ንጉሡን ከሥልጣናቸው ካስወገደ በኋላ ከወሰዳቸው መሠታዊ ዕርምጃዎች መካከል የመሬት አዋጅ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በዚህ አዋጅ አማካይነትም የብዙዎቹን ይሁንታ የማግኘት ዕድል ከማግኘቱም በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢሕአፓ) የመሳሰሉ ዋነኛ ተቀናቃኞቹን ከሕዝብ በመነጠል፣ ለሕዝብ ‹‹ወገንተኝነት›› ያሳየበት አዋጅ መሆኑን የሚጠቅሱት በርካቶች ናቸው፡፡
የቅርብ ጊዜው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትኩሳትን ቢታይ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት፣ አገሪቱን ለአራት ዓመታት ሲንጣት የከረመው መነሻውን ኦሮሚያ ያደረገው ሕዝባዊ አመፅ ምንጩ ከዚሁ ከመሬት ጉዳይ ጋር የተያያዘ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
‹‹የኦሮሞ ተቃውሞ›› (Oromo Protest) የተሰኘው ሕዝባዊ አመፅ ከመላው የኦሮሚያ ከተሞች ከመሠራጨቱ በፊትና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው፣ የአመፁ መጀመርያ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ከተሞችን በጋራ ‹‹የማልማት›› ዕቅድ ያለው የማስተር ፕላን ጉዳይ መሆኑ፣ መሬት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን ምን ያህል ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው አመላካች ነው፡፡
መሠረታዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የማንነት መገለጫ የሆነውን የመሬት ጉዳይ ለማረቅ መንግሥታት የተለያዩ አቅጣጫዎችን የተከተሉ ሲሆን፣ በመሠረታዊነት የሚጠቀሰው ግን የተማሪዎችን እንቅስቃሴ ተከትሎ የታወጀው የመሬት ላራሹ አዋጅ 31/67 ነው፡፡
ይህ አዋጅ ወደ ሥራ ከገባ 45 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አዋጁ በፀደቀበት ወቅት አንግቦት የነበረው መሬትን የዜጎች የማድረግ ትልሙ ግን አሁንም ከ45 ዓመታት በኋላ መቋጫ ያገኘ ጉዳይ አይደለም የሚሉ በርካታ ወገኖች በአንድ ወገን፣ የለም አዋጁ በራሱ ሥር ነቀል በመሆኑ አሁን ለሚደረጉ መሠረታዊ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የማንነት ጥያቄዎች መጎልበት የራሱን ሚና ተጫውቷል የሚሉ ደግሞ በሌላ ወገን እየተሟገቱ አዋጁ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡
ይህ ዘመን ተሻጋሪ የመሬት ላራሹ አዋጅ መታወጁን 45ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ‹‹የአዋጁ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አሻራ›› የሚል ውይይት በአዲስ አበባ ሐሙስ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል፡፡
የስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ተቋም በሚያዘጋጀው ወርኃዊ ዓውደ ጥናት (Seminar) የዚህ ወር መርሐ ግብሩ በዚህ የመሬት ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን የመሬት፣ የሕዝብንና የመንግሥትን ግንኙነት ለመመርመርና ለመረዳት ያግዛል ተብሎ መዘጋጀቱን የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ ሃሌሉያ ሉሌ በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት ገልጸዋል፡፡
ከ45 ዓመታት በፊት ከታወጀው የመሬት አዋጅ አንፃር በአገሪቱ ያለው የመሬት ጉዳይ ምን ዓይነት ገጽታ አለው በሚለው ጉዳይ ለመወያየትና ምልከታቸውን ለማካፈል የአዋጁ አርቃቂዎች፣ የቀድሞ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራርና አባላት፣ የምጣኔ ሀብትና የማኅበራዊ ሳይንስ ተራማሪዎች በመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ነበሩ፡፡
በዓውደ ጥናቱ ላይ ከተካፈሉትና ምልከታቸውን ካጋሩት መካከል የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ አንዱ ነበሩ፡፡ አዋጁን ለማውጣት የተደረገውን አጠቃላይ ዝግጅት፣ ያስከተለውን ለውጥና አዋጁን ለመወሰን የነበረውን ከባድ ሁኔታ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ግብርና ዋነኛው የኢኮኖሚ መሣሪያ መሆኑን ያወሱት ኮሎኔል ፍሰሐ፣ በዚህ ዘርፍ የሚደረግ ማንኛውም የፖሊሲም ሆነ የፖለቲካ ውሳኔ ከመሬት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በማከልም የመሬት አዋጁ በሚታወጅበት ጊዜ 90 በመቶ የሚሆነው የአገሬው ዜጋ በእጁ የሚገኘው መሬት ከአምስት በመቶ የማይበልጥ መሆኑን በማስታወስ መሬት በመሳፍት አባላት፣ በቤተ ክርስትያኒቱ ቁጥጥር ሥር መሆኑ አዋጁን ለመተግበር ዋነኛ ገፊ ምክንያት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳን ለጭቁኖች ያደላ አዋጅ ማወጅ ጠቀሜታው ከፍተኛ ቢሆንም፣ አዋጁን ለማወጅና ለማስፈጸም ግን ከባድ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አዋጁን ወታደራዊው ሥርዓት ባይሆን ኖሮ ማንም ደፍሮ ያውጀዋል የሚል እምነት የሌላቸው መሆኑን ያወሱት ኮሎኔሉ፣ ደርግም ይህን አዋጅ ሊያውጅ የቻለው በዋነኛነት በሦስት ምክንያቶች መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡ እነኚህ በኮሎኔሉ የተጠቀሱት ምክንያቶች ደግሞ የደርግ አባላላት ወጣቶችና ወታደሮች መሆን፣ እንዲሁም ከአርሶ አደሩ አብራክ መገኘታቸው መሆኑን አውስተዋል፡፡
ሆኖም በወቅቱ ንጉሡን ከሥልጣን ለማውረድ ከተጨነቁትና ከፈሩት እኩል አዋጁን ማወጅና ተፈጻሚ ማድረግ፣ እንዲሁ አስጨናቂና ሰፊ ውሳኔ እንደነበር በትውስታ ገልጸዋል፡፡
ከ1966 ዓ.ም. አብዮት በፊት የነበረው የመሬት ሥርዓት የራሱ የሆነ የተለየ ባህሪይ የነበረው ሲሆን፣ በመሠረቱም በርስት ጉልት ግንኙነት ዙሪያ የተዋቀረ ነበር፡፡ በዚህም ምክያት መሬት በአብዛኛው የመሳፍንት፣ የባላባትና የቤተ ክርስቲያን በሚሉ መዋቅሮች የተከፋፈለ ነበር፡፡ ይህ የመሬት ሥርዓት በአገሪቱ አብዛኛውን ክፍል በሚሸፍነውና መተዳደሪያ መሬት ያለውን አርሶ አደሩን የሚያገል ከመሆኑም በላይ፣ የባለቤትነትም ሆነ የመጠቀም መብትን ዋስትና የማይሰጥ እንደነበር የሚገልጹ በርካታ ጸሐፍት አሉ፡፡
ከዚህ አንፃር የመሬት ላራሹ አዋጅ ቀደም ሲል የነበረውን የርስት ጉልት መዋቅራዊ ግንኙነት በመሻር፣ በአገሪቱ የመሬት ሥሪት ሥርዓት ላይ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ ነገር ግን አዋጁ እንዲሁ በቀላሉ ተግባር ላይ የዋለ እንዳልሆነ ኮሎኔል ፍሰሐ አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነበሩ ባላባቶችና መሳፍንቶች ባነሳሷቸው ገበሬዎች ሳቢያ የብዙ ዜጎች ሕይወት ማለፉን በመጥቀስ፣ አዋጁን ወደ ተፈጻሚነት ለማምጣት ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ሒደት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በተመሳሳይ አዋጁ በታወጀበት ወቅት የመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስትር የነበሩት አቶ ዘገየ አስፋው፣ አዋጁን ለማወጅ የነበሩትን ክርክሮች በማስተዋል የግል ምልከታቸውን በመርሐ ግብሩ ካጋሩት መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
በወቅቱ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ የተሟሟቀ ክርክር መደረጉን የሚያስታውሱት አቶ ዘገየ፣ የሕዝብን የመሬት ባለቤትነት ለማወጅ የወጣውን አዋጅ አስመልክቶ በተራማጁና በአድኃሪው መካከል የተካሄደው ክርክር በኢትዮጵያ ታሪክ ዋነኛው እንደሆነ አውስተዋል፡፡
የክርክሩን ሑደት ከመግለጽ ባለፈም በወቅቱ የነበሩት አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፣ ለአዋጁ መውጣት ዋነኛ ምክንያት እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
በተያያዘም አዋጁ በእርሻ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን በዋነኛነት ያማከለ እንደነበር በመግለጽ፣ ከዚያ ውጪ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማካተት ግን እየተሠራ እንደነበር በማስታወስ፣ ‹‹በአንድ አዋጅ አማካይነት የዚህችን አገር ችግር ሙሉ በሙሉ እንፈታለን ማለት አይቻልም፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ነገር ግን አዋጁ መሠረታዊ በሆነ መንገድ ለዘመናት በአገሪቱ የነበረውን ማኅበራዊ ግንኙነት መለወጥ የቻለ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በዚህ ሐሳብ የሚስማሙትና በኢትዮጵያ የመሬት ሥሪትና ይዞታ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቁትና በዚህ መስክ በርካታ መጻሕፍትና ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ የሚታወቁት ተመራማሪው አቶ ደሳለኝ ራህመቶ፣ አዋጁ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ይህ ሥር ነቀል ለውጥ በአገሪቱ ለዘመናት የነበረውን ባላባታዊ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያስወገደ ከመሆኑ መሆኑን ቢገልጹም፣ ነገር ግን ለዜጎች ሙሉ የመሬት ባለቤትነት መብት ከማጎናፀፍ አንፃር ክፍተት እንደነበረበትም አስታዋሰዋል፡፡
የመሬት ጥያቄ ከጥንት ጀምሮ የነበረና አሁንም የሚኖር መሆኑን የገለጹት አቶ ደሳለኝ፣ ሆኖም የጥያቄው ይዘትና ማዕቀፍ በየዘመኑ ተቀያያሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ አንፃር በደርግ ጊዜ የነበረው የመሬት አዋጅ መሠረቱ ማኅበራዊ ፍትሕ (Social Justice) እንደነበር በማውሳት፣ ይህ የማኅበራዊ ፍትሕ መሠረት ግን ብዙም መጓዝ እንዳልቻለና በራሱ በደርግ አማካይነት መጠለፉን አውስተዋል፡፡
‹‹በዚያን ጊዜ የተጨቆኑ ሕዝቦች አሉ፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ለተጨቆኑ ሕዝቦች መቆም አለብን ከሚል የተነሳ ነበር፡፡ ገበሬው መሬቱን በራሱ እንዲያርስና ማንም መጥቶ ያፈራውንም ሆነ መሬቱን እንዳይወስድበት የሚል ነበር፤›› በማለት አስታውሰው፣ ኋላ ላይ ግን መንግሥት ራሱ አርሶ አደሮችን በገበሬ ማኅበራት እንዲያርሱ ማድረጉና ያፈሩትንም በገበያ ዋጋ ሳይሆን፣ በራሱ ውሳኔ እንዲሸጡ ማድረጉ አዋጁን ስንኩል እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡
የመሬት ጥያቄ በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ ገጽታዎች ወይም መገለጫዎች እንደሚኖሩት የገለጹት አቶ ደሳለኝ፣ አሁን ያለው የአርሶ አደሩ ከመሬት ጋር የተያያዘ ጥያቄ ደግሞ እንደ ቀድሞ የባላባት ወይም የከበርቴ መኖር ሳይሆን፣ የመሬቱ መጠንና የመሳሰሉት ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የተገለጹትን አስተያየቶችና ማብራሪያዎች ተከትሎ የውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ሰንዝረዋል፡፡ በተለይ ግን የአዋጁ ወቅታዊ ጠቀሜታ ምንድነው? አዋጁ ከ45 ዓመታት በፊት የታወጀ ቢሆንም፣ አሁንም መሬት ዋነኛው የፖለቲካ ልሂቃን መነታሪኪያ አጀንዳ ከመሆኑ አንፃር ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው መቼ ነው? የሚሉት የበርካቶች ጥያቄዎች ነበር፡፡ መሬት የግል ቢሆንስ? መሬት ከሚገባው በላይ ተለጥጦ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል ይህን እንዴት ማስተካከል ይቻላል? የሚሉ ነጥቦችም ተነስተዋል፡፡
አዋጁ ከ45 ዓመታት በፊት መውጣቱን በማስታወስ በዚያው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትስስር ዓውድ መመልከት እንደሚገባ በመግለጽ፣ ‹‹አዋጁን አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ የምንገመግመው ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው›› ሲሉ ኮሎኔል ፍሰሐ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ በነበረው ውይይት ላይ ሐሳብ አቅራቢዎቹ በአብዛኛው ወደኋላ በመሄድ የመሬት ሥሪቱንና የአዋጁን ታሪካዊ ዳራ በማጉላት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች ደግሞ ከወቅታዊው የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ግንኙነት፣ እንዲሁም ማንነት አንፃር መሬት ምን ዓይነት ሚና አለው በማለት በመጠየቅ ያተኮሩ ነበሩ፡፡
ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚጦዘው የአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መዋቅር ዘላቂ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ፣ ያለፉትን አዋጆች አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ አዲስ ዓይነት አሠራር ማበጀት መልካም እንደሆነም ምክረ ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡
‹‹የባለፀጋ ቤት ትናንት ተዘረፈ፣ ዛሬ ዘብ አቁሙ ያለፈው አለፈ›› በማለት በምሳሌያዊ አነጋገር መልዕክት ያስተላለፉት የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ፍሰሐ ደስታ ሲሆኑ፣ በዚህ መሠረት የመሬትን ጉዳይ ወደኋላ እየሄድን የሙግት አውድማ ከማድረግ በመግባባትና በውይይት የዳበረ ሥርዓት በማበጀት እንዴት የአንድነት ማማ ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ፣ ለአገሪቱ ጠቃሚ ለዘርፉም ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ እንደሚሻል ግንዛቤ የተያዘበት ውይይት ነበር፡፡