Wednesday, June 19, 2024

የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የመረጃ ልውውጡን ማዘመን ያስፈልጋል!

የኮሮና ቫይረስ በመላው ዓለም እየተስፋፋ ባለበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ ከዓለም የጤና ድርጅትና ከሚመለከታቸው የጤና አጠባበቅ አካላት የሚለቀቁ መረጃዎችን በአንክሮ መከታተል ችላ የማይባል ነው፡፡ በመረጃዎቹ ላይ በመመርኮዝ በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት የሚያወጧቸው መመርያዎችም ሥርጭቱን ለመግታት ይጠቅማሉ፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ መረጃዎችና ትንተናዎች ለማኅበረሰቦች በፍጥነት መድረስ አለባቸው፡፡ ማኅበረሰቦችም በተቻለ መጠን ምንጫቸው የማይታወቁ መረጃዎች ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ፣ የሚመለከታቸው አካላት መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለጥንቃቄ የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ብሎ በአግባቡ መንቀሳቀስ ሲቻል፣ አላስፈላጊ ሥጋቶችና ፍርኃቶች ይወገዳሉ፡፡ በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመቀነስና በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ይመከራል፡፡ በርካታ ሰዎች የሚገኙባቸው ሥፍራዎች አለመገኘት፣ አካላዊ ንክኪን ማስወገድ፣ ከአካባቢ ራቅ የሚሉ ሥፍራዎች የሚደረጉ ጉዞዎችን መግታት፣ በቫይረሱ የሚጠረጠሩ ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄዱ መርዳት፣ የግል ንፅህናን መጠበቅ፣ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ፣ ተዓማኒነት የጎደላቸው አጓጉል ድርጊቶች ማስወገድና የመሳሰሉት አስፈላጊ ተግባራት ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሐሰተኛ መረጃዎችን ከማሠራጨት መታቀብ፣ ቫይረሱን በተመለከተ የተጋነኑም ሆኑ የሚያጣጥሉ መረጃዎችን አለመቀበልና ለአድልኦና ለማግለል የሚያበረታቱ ድርጊቶችን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚረዱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ግልጽና አሳታፊ የሐሳብ ልውውጦች አስፈላጊ በመሆናቸው፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመረጃ ልውውጡን ማዘመን አስፈላጊ ነው፡፡ የሚጠቅመውም ይኼ ነው፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን በመከታተልና ሪፖርት በማድረግ በሚታወቀው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ሪፖርት መሠረት፣ በመላው ዓለም 182,400 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 7,100 ያህሉ ሞተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በቻይና ከነበረው የሞት መጠን ከቻይና ውጪ መመዝገቡን፣ እንዲሁም ጣሊያንና ስፔን በጣም መጎዳታቸው ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያና በርካታ አገሮች ትምህርት ቤቶችን፣ አላስፈላጊ ስብሰባዎችንና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያቆሙ፣ በአውሮፓ ግን ሚሊዮኖች ከቤታቸው እንዳይወጡ ተገደዋል፡፡ እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት መካከል በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው፣ የሕክምና ዕርዳታ አግኝተው መዳናቸው ይታወቃል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለም የጤና ሥጋት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ በሚመለከታቸው አካላት የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ በማድረግ መከላከል እንደሚቻል መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት ውጤታማ የሆኑ ሥራዎች ላይ መሰማራት ብቻ ነው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መረጃ ያላቸው ሁሉ ማኅበረሰቡን በአርዓያነት ትክክለኛውን የመፍትሔ መንገድ ማመላከት አለባቸው፡፡ መስማት ለተሳናቸው ወገኖች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት በመስጠት ዕገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አዛውንቶችና አቅመ ደካሞች በቫይረሱ እንዳይያዙ መርዳትም እንዲሁ፡፡ የመረጃ እጥረት ያለባቸው ወገኖች ካሉም በየደረጃው የሚገኙ አካላት ማገዝ አለባቸው፡፡ የመረጃ ልውውጡ በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግ ነው ለመፍትሔ መትጋት የሚቻለው፡፡

የመረጃ ልውውጡ ሊያካትታቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ማኅበረሰቡን ለሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት የሚያጋልጡ፣ የመድኃኒት ርጭት እናደርጋለን በማለት የሚዘርፉና ጉዳት የሚያስከትሉ የተለያዩ ድርጊቶችን የሚፈጽሙትን ተባብሮ ማጋለጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ የግለሰቦችን እምነት እንደ ደካማ ጎን በመቁጠር የሚያጭበረብሩ፣ የመከላከያ ዘዴዎችን በሐሰተኛ ወሬ አቅጣጫ የሚያስቱ፣ የሚያዘናጉና ያልተገባ ድርጊት የሚያስፈጽሙትንም ጭምር በንቃት መከታተል ተገቢ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ከአንድ ግለሰብ ጀምሮ ወደ ብዙ ሰዎች ሊዳረስ ስለሚችል፣ የማኅበረሰቡ ሙሉ ትኩረት መሆን ያለበት በትክክለኛው መንገድ የሚተላለፉ መረጃዎች ላይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ድህነት የበረታባት አገር ውስጥ ሕዝቡ በማይመቹ የመኖሪያ አካባቢዎች ተፋፍጎ ስለሚኖር፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ በጣም ኋላቀር በመሆናቸው መጓጓዣዎች ስለሚጨናነቁ፣ በቂ የንፁህ ውኃ አቅርቦት ስለሌለ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል በየጊዜው ስለሚቆራረጥ፣ የቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገድ ከሚታሰበው በላይ ብዙ የሚቀረው በመሆኑ፣ የመሠረታዊ ንፅህና አጠባበቅ ደረጃው በጣም የወረደ ስለሆነ፣ የሰላምታ ሥርዓቱ ለቫይረሱ ሥርጭት አመቺ ስለሆነና በአጠቃላይ የአኗኗር ሁኔታው አጋላጭ ስለሆነ ይህንን አሳሳቢ ወቅት በብልኃት ማሳለፍ ያስፈልጋል፡፡ መረዳዳቱና መተሳሰቡ እንዳለ ሆኖ ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ራስንም ሆነ ማኅበረሰቡን ማጋለጥ አይገባም፡፡ ይልቁንም ወቅታዊና ትኩስ አስተማማኝ መረጃዎችን በጋራ እየተጋሩ፣ ይህንን ከባድ ጊዜ ማሳለፍ የተሻለ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በበቂ መረጃ ቫይረሱን መግታት ካልተቻለ፣ መጪው ጊዜ ከበድ ሊል ይችላል፡፡

መንግሥት ለጊዜው ትምህርት ቤቶችን መዝጋቱ፣ ስብሰባዎችን ማገዱ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረጉ፣ ወዘተ መልካም ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ የተለያዩ ማኅበራት፣ የግል ድርጅቶች፣ ድግሶችና የመሳሰሉ ዝግጅቶች ያሉባቸው ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሙዚቃ፣ የቴአትር፣ የፊልምና የመሳሰሉት አዘጋጆች በሙሉ ለጊዜው ሰዎችን በማሰባሰብ ለሥርጭቱ መባባስ ምክንያት ባይሆኑ ይሻላል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ ከውጭ ከመጡ ግለሰቦች ቫይረሱ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ቁጥጥር የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለዚህም በቦሌ ኤርፖርትም ሆነ በተለያዩ የየብስ መግቢያዎች የሚያደርገውን ቁጥጥር በማጠናከር፣ ተጠርጣሪዎችን ወደ ልየታ ማዕከል በፍጥነት እንዲገቡ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በመግቢያ በሮች ላይ በሚፈጠር መዘናጋት ምክንያት በአንድ ሰው ብቻ በርካቶች ሊጠቁ ይችላሉ፡፡ ማኅበረሰቡም የሳል፣ የትኩሳትና መሰል ምልክቶች የሚታዩባቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ያለ ይሉኝታ በማስታወቅ ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ በመገለል ፍራቻ ምክንያት የሚደበቁ ካሉም በፍጥነት ሪፖርት ማድረግ ይገባል፡፡ ማኅበረሰቡ በሰከነ መንገድ መረጃ ሲለዋወጥና ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ ሲያደርግ፣ ሥርጭቱን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በሚገባ ያግዛል፡፡ ይህ ዕውን መሆን የሚችለው ግን የመረጃ ልውውጥ ባህሉ ሲጎለብት መሆኑን መገንዘብ የግድ ይሆናል፡፡

ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የመጣ ይመስል ተገቢ ያልሆኑ መረጃዎችን መልቀቅ፣ አርዓያነት ያላቸውን ተግባራት ማንኳሰስ፣ ማኅበረሰቡን ማታለልና ማዘናጋት፣ ያልተገባ እላፊ ጥቅም ፍለጋ ነውረኛ ድርጊቶችን መፈጸም፣ የፖለቲካ ቁርሾን ማባባስ፣ ለማግለልና ለመድልኦ የሚረዱ ቅስቀሳዎችን ማድረግ፣ ቫይረሱን ከመጠን በላይ በማጋነን የምፅዓት ቀን የደረሰ ማስመሰል፣ በጣም በማቃለልም ተረት ማስመሰልና የመሳሰሉት ድርጊቶች አያስፈልጉም፡፡ በእንዲህ ዓይነት ድርጊቶች የተለከፉ ወገኖች ቢቻል በምክርና በመገሰፅ፣ ካልተቻለ ደግሞ ለሕግ በማቅረብ ማስቆም ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጠቃሚ ሐሳቦችን መለዋወጥ፣ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ፣ የተጓደሉ ነገሮች ሲያጋጥሙ መጠቆም፣ ለጥንቃቄ የሚረዱ አዳዲስ መረጃዎችን ማካፈል፣ ወዘተ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት ሊወስዳቸው ይገባል የሚባሉ አስፈላጊ ዕርምጃዎች ሲዘገዩ፣ በመገናኛ ብዙኃን በግልጽ ማሳሰብ የግድ ነው፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተዛባ መረጃ የሚያሠራጩትንም ማጋለጥ እንዲሁ፡፡ እግረ መንገድንም ይህ አጋጣሚ ወደፊት ለሚኖሩ መስተጋብሮች ጥሩ መንደርደሪያ እንዲሆን፣ የውይይትና የሐሳብ ልውጥጥ ባህልን ማዳበር ይቻላል፡፡ እንደተለመደው ለመረጃ በር መዝጋትና የማኅበረሰቡን የማወቅ መብት መጋፋት አደጋ አለው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የመረጃ ልውውጥ ሲኖር፣ የኮሮና ቫይረስን ሥጭት ለመግታት ይቻላል፡፡ ለዚህም ሲባል የመረጃ ልውውጡን ማዘመን ያስፈልጋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...