የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የ59 ዓመት እንግሊዛዊት ዲፕሎማት በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መሆናቸው መረጋገጡን አስታወቀ፡፡
እንግሊዛዊቷ ዲፕሎማት ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ መቼ እንደመጡ ባይታወቅም፣ ሰኞ መጋቢት 7 ቀን ካረፉበት ሆቴል በተደረገ ጥቆማ መሠረት በክፍላቸው ተገልለው እንዲቆዩ በማድረግ፣ በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ የናሙና ውጤት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ስድስት ደርሷል፡፡
ከግለሰቧ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየትና የክትትል ሥራው መጠናከሩን፣ በአሁኑ ጊዜም ግለሰቧ በለይቶ የሕክምና መስጫ ማዕከል የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው አስቀድሞ ከተረጋገጠባቸው አምስት ሰዎች ጋር የቅርብ ንኪኪ ያላቸውን 992 ሰዎች፣ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በሰጠው ወቅታዊ መግለጫው እንዳስታወቀው፣ 992 ሰዎች ለ14 ቀናት የጤና ክትትሉን የሚያደርጉት ባሉበት ቦታ ነው፡፡
የኢንስቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ እንዳብራሩት፣ በአሁኑ ወቅት 1,285 የሚሆኑት ደግሞ ለ14 ቀናት የጤና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው ጤንነታቸው በመረጋገጡ የጤና ክትትላቸው ተቋርጧል፡፡
የበሽታውን ተመሳሳይ ምልክቶች በማሳየታቸውና ከመጀመሪያው ታማሚ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ጨምሮ፣ በአሁኑ ወቅት 113 ተጠርጣሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በለይቶ መቆያ ማዕከል እንዲቆዩና የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ 74 ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡ 34 ተጠርጣሪዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው አምስቱ ታማሚዎች በለይቶ ማቆያ የሕክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ በጥሩ ጤንነትም ይገኛሉ፡፡
መንግሥት ኅብረተሰቡ የሚሳተፍባቸውን እንደ ትምህርት ቤቶች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ስብሰባዎችን ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ በማድረግ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታትና ለመቆጣጠር በርካታ ዕርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይም የበሽታውን ምልክት ያሳዩ ወይም ተጠርጣሪዎች ተብለው በለይቶ ማቆያ አካባቢ የሚቆዩ ግለሰቦች ነፃ መሆናቸው ቢረጋገጥም፣ የማግለል ባህሪዎችን እንዳይከሰቱ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግና ስለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምንነትና የመከላከያ መንገዶች በጥልቀት ሊረዳ የሚገባ መሆኑን አሳስበዋል፡፡