Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚሳተፉ የውጭ ደርጅቶች ላይ ጫና ለመፍጠር የተጠራው የግብፅ ፓርላማ...

በህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚሳተፉ የውጭ ደርጅቶች ላይ ጫና ለመፍጠር የተጠራው የግብፅ ፓርላማ በኮሮና ምክንያት ሳይሰበሰብ ቀረ

ቀን:

የተለመደው የሚዲያ ጦርነት ኢትዮጵያን እንደማያሳስባት ተገለጸ

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፏቸውን አቋርጠው እንዲወጡ የተጠራው የግብፅ ፓርላማ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ስብሰባ፣ በኮሮና ቫይረስ ሥጋት ሳይካሄድ ቀረ።

የግብፅ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በህዳሴ ግድቡ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ለማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. መጥራቱን፣ የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበው ነበር። የውጭ ጉዳይ ኮሚቴው ሊቀመንበር እንደገለጹት፣ የኮሚቴው ስብሰባ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ የሚሳተፉ የውጭ ድርጅቶች ጥለው እንዲወጡ የግብፅ መንግሥት ማድረግ ያለበትን ጫና በተመለከተ መምከር የስብሰባው አጀንዳ ነበር።

አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊ ግን የግብፅ ፓርላማም ሆነ የግብፅ መንግሥት ግድቡን በተመለከተ ከሚጠቀሙባቸው ቴክኒኮች መካከል አንዱ፣ በሚዲያ ዘመቻ ሥጋት የመፍጠር መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህ የሚዲያ ዘመቻ እንደማያሳስብና ተግባራዊ መሆን የማይችል ነው ሲሉም አጣጥለውታል።

 በህዳሴ ግድብ የሚሳተፉ ኩባንያዎች በግብፅም በተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚሳተፉ ስለሆኑ፣ ውላቸው እንዲቋረጥና ወደፊት እነዚህ ኩባንያዎች ምንም ዓይነት ፕሮጀክት በግብፅ እንዳያገኙ ማድረግ እንደሚገኝበት ከግብፅ በኩል ተሰምቷል።

በተጨማሪም የዓለም ባንክና ሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች እነዚህ ኩባንያዎች እንዳይሳተፉ ለማድረግ፣ የግብፅ መንግሥት ከገንዘብ ተቋማቱ ጋር እንዲነጋገር ማድረግ የሚለውም ይገኝበታል።

ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ በግብፅ በመስፋፋቱ ምክንያት፣ የተጠራውን አስቸኳይ ስብሰባ ማካሄድ እንዳልተቻለና ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉን የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የግብፅ ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ዕቅድን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊ ይህ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

 ግብፆች ለማድረግ የማይፈልጉት ነገር እንደሌለ የተናገሩት እኚህ ኃላፊ፣ አሁን ያሰቡትን ድርጊት ለመፈጸም አቅቷቸው እንጂ ግድቡ ሲጀመርም የጣሊያኑን ኩባንያ ሳሊኒን ለማስወጣት ያላደረጉት ሙከራ እንዳልነበር ገልጸዋል።

ከሳሊኒ ውጪ በግድቡ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ዋነኞቹ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሥር በንዑስ ተቋራጭነት ላለፉት ዓመታት ሲሳተፉ እንደነበር፣ ግብፅ እነዚህ ኩባንያዎችን ማስወጣት ብትችል ኖሮ ቀደም ባሉት ዓመታት ይሳካላት እንደነበር ኃላፊው ጠቁመዋል።

የግብፅ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ሙከራዎችን የሚያደርገው በድብቅ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ‹‹ኩባንያዎቹን ማስወጣት እንደማይቻል ሲያውቁት፣ ቢያንስ በሚዲያ ሥጋት እንፍጠር ብለው የለቀቁት መረጃ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል።

ሜቴክ ከግድቡ እንዲወጣ በመደረጉ ምክንያት በሥሩ ንዑስ ተቋራጭ የነበሩ ኩባንያዎች፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የኃይድሮ ስቲል ስትራክቸር ሥራዎችን እንዲረከቡ መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል። የእነዚህ ኩባንያዎች ውል በፕሮጀክት ምዕራፍ የታሰረ መሆኑን፣ ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ኩባንያዎች እንዲጨመሩ በማድረግ በጥቅሉ በግድቡ ግንባታ ከተለያዩ ሰባት አገሮች የተወጣጡ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ መደረጉን አክለዋል።

ይህ የሆነበት ምክንያት እንዳለው የተናገሩት ኃላፊው፣ አንደኛው ምክንያት ግብፅ በግድቡ ግንባታ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ላይ የምታደርሰውን ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ አስቸጋሪ ማድረግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ የሚገኙት ኩባንያዎች ከቻይና፣ ከአሜሪካ፣ ከጣሊያን፣ ከጀርመንና ከፈረንሣይ የተውጣጡ መሆናቸውን ያወሱት ኃላፊው፣ ከኩባንያዎቹ በተጨማሪ የእነዚህ አገሮች መንግሥታት በኢትዮጵያ ጥቅም ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል እንደዚህ ዓይነት ሴራዎች መንግሥታት በሚስጥር የሚፈጽሟቸው እንጂ፣ ፓርላማ በይፋ መክሮበት በመንግሥት ተግባራዊ የሚደረግ ተራ ነገር አለመሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች በግድቡ ግንባታ ላይ ከሚሳተፉ ኩባንያዎች ጋር በጣም በቅርበት እየሠሩ መሆናቸውን፣ የገንዘብ ክፍያ ጥያቄም ሆነ ሌሎች ችግሮች እንዳይኖሩባቸው በየጊዜው እየተገናኘ እንደሚመካከር ገልጸዋል። ከእነዚህ ኩባንያዎች ጋር አዲስ ውል ከታሰረ ጀምሮም ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ መፈጸሙን ኃላፊው አረጋግጠዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...