ዘመናዊ ሆስፒታልና ምቹ የአረጋውያን መኖሪያ ሕንፃ ለማሠራት የተነሳው መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም 102 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ማዕከሉ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው፣ መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት የተገኙ የተለያዩ ተቋማት በካሽ (እጅ በእጅ) እና ቃል በገቡት 102 ሚሊዮን ብር የሕንፃው 10 በመቶ ወጪ ይሸፈናል፡፡
መቄዶንያ የሚያሠራው ሕንፃ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ሲሆን ባለ 2 ቤዝመንት ግራውንድ ፕላስ 11 (2B+G+11) የሆነ ዘመናዊ ሆስፒታልና ምቹ የአረጋውያን መኖሪያ ሕንፃ ከነቴራሱ 15 ወለሎች ያሉትና 3,600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡
ማዕከሉ ምንም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን በተለይም ደግሞ ራሳቸውን ችለው መፀዳዳት፣ መመገብና መንቀሳቀስ የማይችሉ ከ2000 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡