Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሚፈናቀሉ የአገር ቅርሶች

የሚፈናቀሉ የአገር ቅርሶች

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ከከተሞች መስፋፋት ወይም ለልማት በሚል ምክንያት በማወቅም ሆነ ባለ ማወቅ ብዙ ታሪክ ያላቸው የአደባባይ ቅርሶች ፈርሰዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 የሚገኘው በቅርስነት የተመዘገበው የፊታውራሪ አምዴ አበረ ካሳ መኖሪያ ቤት ከዘጠና ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ትዕዛዝ መፍረሱ የቅርብ ጊዜ ትውስታና ብዙዎችን ያበገነና ያስቆጨ ተግባር ነው፡፡

ቅርስ የበፊት አባቶች የአኗኗር ሥልት፣ ዘይቤ፣ ከማሳየት ባሻገር አገሪቱ የነበረችበትን የሥልጣኔ ደረጃ የሚያመለክትና ሥልጣኔ የሚተላለፍበት መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የቅርስ ዕጦት ወይም ድርቅ እንደሌለባት ብዙ ማሳያዎች ያሏት አገርና በቅርስ ደረጃ ከዓለም በግንባር ቀደም ከሚጠቀሱ መካከል ናት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁን እንጂ መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር ለቅርሶቹ በሚሰጣቸው የተለያየ አመለካከት ምክንያት አንዳንዶች ሲፈርሱ ግማሾቹ ኖረው እንደሌሉ ሲታዩ ቆይተዋል፡፡

ለዚህም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ‹‹ትግላችን›› ሐውልት ነው፡፡ ከካራማራ ድል ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሐውልት በአዳዲስ የመንግሥት ፖለቲካዊ ትርክት ምክንያት ተጋርዶ ሳይታይ ቆይቷል፡፡ እንደ ምሳሌነት የትግላችን ሐውልት ተነሳ እንጂ ብዙ ቅርሶችን የያዙ ሐውልቶች የነበራቸውን ክብር አጥተው መቅረታቸው ብዙዎች የሚቆጩበት ጉዳይ ሆኗል፡፡

የሚፈናቀሉ የአገር ቅርሶች

ፋሽስት ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ወረራ በፈጸመበት ጊዜ ለቀድሞው የመንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ወራሪው ግፍ እየፈጸመ መሆኑን በወቅቱ የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ለማኅበሩ አቤት ቢሉም ተሰሚነታቸው እምብዛም እንደነበረ በታሪክ ይነገራል፡፡

በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጎን ከተሰለፉ ሜክሲኮ ስትሆን፣ ይህን ታሪካዊ እውነታ ይታወስ ዘንድ በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ አበባ ላይ ‹‹ሜክሲኮ አደባባይ›› የተሠራ ሲሆን፣ በሜክሲኮም ‹‹ኢትዮጵያ ፕላዛ›› የባቡር መዳረሻ በሚል ስያሜ ተሠርቷል፡፡

ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በታሪክ ይታወስ ዘንድ በአዲስ አበባ የተሠራው የትውስታ ቅርስ መፍረሱ ተገቢነት የሌለው መሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡

በ1950 ዓ.ም. ማይጨው አደባባይ ይባል የነበረው ሜክሲኮ አደባባይ ሲባል የቆመው ኪነ ቅርፅ (ሐውልት)፣ ከ53 ዓመታት በኋላ በ2003 ዓ.ም. በመንገድ ማስፋፊያ ስም ፈርሷል፡፡ ይሁን እንጂ መፍረሱን ተከትሎ ቁጭታቸውን ከመግለጽ ባሻገር ከስብርባሪዎች መካከል የተወሰነው በመያዝ ሐውልቱን ዳግም እውን ለማድረግ የጣሩት ቀራፂው በቀለ መኰንን ናቸው፡፡

በአለ የሥነ ጥበባትና ዲዛይን ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ተመልሶ የተሠራው የሜክሲኮ አደባባይ ፍራሽ ሐውልትን በቀራፂ በቀለ መኰንን፣ በተማሪዎችና በአስተማሪዎች ትብብር ታንፆ ዳግም ተከስቷል፡፡

ቀራፂው አደባባዩ ለምን ፈረሰ ሳይሆን፣ የአፈራረሱ ሁናቴ እጅግ የሚያበሳጭና ያልተገባ ቢሆንም፣ አሁን የተሠራው ሐውልት ግን ያለፈውን ታሪክ እንደወደመ ከማሳየት በተጨማሪ በሰው ሐሳብ ውስጥ ብቻ እንዳይኖር፣ ቅርስ እንዳይጠፋ ወይም እንዳይረሳ ለማድረግ የታለመ ነው ብለዋል፡፡

በፈረሰውና ከፊሉ ፈጠራ ታክሎበት ዳግም በቆመው የሜክሲኮ አደባባይ ሐውልት ዙሪያ በአለ ሥነ ጥበባትና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዓርብ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት ተደርጓል፡፡

ቀራፂ በቀለ ‹‹ትልቅ ነገር ስለተሠራ ሳይሆን ትንሽ ነገር ሠርተን ትልቅ ነገር ለማሳሰብ ተብሎ የተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በጊዜው አደባባዩ ሲፈርስ ‹‹ሰው ለአገሩ ሲሞት አይተው ቅርሶች ለልማት ሞቱ›› የሚል ጽሑፍ መጻፋቸው የሚያስታውሱት ቀራፂ በቀለ፣ በጊዜው አሳዛኝ የነበረው ለምን ፈረስ ሳይሆን እንደ ጠላት ቅርስ መውደሙ አሳዛኝ ድርጊት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ ስለ ጉዳይ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ መጻፋቸው ገልጸው፣ ትውስታው (ቅርሱ) በዚህ መልኩ እንድናስበውና እንድናስታውሰው መደረጉ እጅግ ደስ የሚያሰኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የሕግ ባለሙያ የሆኑት እኚህ ግለሰብ ቅርስ በየትኛው የግንባታ ሥርዓትም ሆነ የዓለም አቀፍ የግንባታ ሕግና ሥርዓት ቅርስ የማፍረስ ሕግ እንደሌለ አስረድተው፣ ድርጊቱ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ብለዋል፡፡

አክለው በአገሪቱ ያለው የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እንደ ሌሎቹ የአዲስ አበባ ቅርሶች ይኼኛውም ቅርስ ተብሎ የተቀመጠ ቢሆንም አልተፈጸሙም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ብቻ ሳይሆን ሜክሲኮ የነበረውንም የስም ለውጥና የቦታዎች በመፍረስ በሁለቱም አገሮች ያሉ ታሪክ አላዋቂዎች የፈጸሙት ድርጊት እጅግ አሳዛኝ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ከፋሺስት ጣሊያን እንድትላቀቅ ካገዟት አምስት አገሮች አንዷ ሜክሲኮ ናት የሚሉት ቀራፂ በቀለ፣ በአገሪቱ ብቸኛ ውብ ፋውንቴን እሱ እንደነበረ አስታውሰው በሜክሲኮ የመሬት መንቀጥቀጥ በገጠማት ጊዜ አምስት ሺሕ ዶላር በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጊዜ ዕገዛ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የሁለቱ አገር ታሪካዊ ግንኙነት በሁለቱም አገር ያለው ታሪካዊ ሥፍራ እንደማይረባ ቁስ መጣሉ ታሪካዊ ስህተት እንደተሠራ አስተያየታቸውን ለግሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን ዕዝራ አባተ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ቅርሰን ልክ እንደተፈናቃይ ቢታሰብ በዕድገት ስም የተፈናቀሉ ቅርሶች ማለት ያስችላል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

ዕድለኛ ሆኖ ከሦስቱ አንዱ ሙሉ አካሉ በመገኘቱ የጠፉትን እንድናስታውስና እንዲታሰብ ሆኗል የሚሉት ዕዝራ (ዶ/ር)፣ በዚህም ድሮ የነበረውን የቅንጦትና የድሎት ቦታ ቢያጣም እንኳን ጥሩ እጅ ላይ የወደቀ ተፈናቃይ ቅርስ የሚያስብል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል በሁለቱም አገሮች ነዋሪዎች ዘንድ እስከ አሁን በሜክሲኮ አደባባይና በኢትዮጵያ አደበባይ ስያሜ የሚጠራ ሲሆን፣ ይህም በሰዎች ህሊና የሚገኝ ቅርስ ነገር ግን በመሬት ላይ የማይገኝ እንደሆነ ተገዷል የሚል ሐሳብ ተሰጥቷል፡፡

በሐሳብ ደረጃ የተነሳው ቅርስ ሜክሲኮ አደባባይ ይሁን እንጂ ታሪክ፣ ባለቤት እያላቸው እንደሌላቸው ጥሻ ተጥለው ያሉ ቅርሶችን እንዲታወሱ የተደረገበት ውይይት ነው፡፡

በተለያዩ ጊዜ የሚሾሙ አዳዲስ መሪዎች የየራሳቸውን ታሪክና ሐሳብ፣ ዝንባሌ ይዘው ስለሚመጡ የነበረው ቅርስ የሚወድምበት ተግባር አገር ከታሪክና ከቅርስ መማርና ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...