በቁምላቸው አበበ ይማም
የዛሬዎቹ የዓለማችን ፍርድ ቤቶች ችሎቶች የበርካታ ሺሕ ዓመታት ሒደታዊ ለውጥ ውጤት ናቸው፡፡ የሕግ ታሪክ ከባቢሎን እስከ ፋርስ፣ ከግሪክ እስከ ሮማና እስከ ፈረንሣይ፣ ከግብፅ እስከ ኢትዮጵያ ያካለለ ነው፡፡ ከታላቁ መጽሐፍ፣ ከቅዱስ ቁርዓን፣ ከባህላዊና ከሃይማኖታዊ ዳኝነቶች ተቀድቶ የተቀመረ ነው፡፡ በአገራችንም የመጀመርያው ሕገ መንግሥት እስተረቀቀበት 1923 ዓ.ም.፣ በእንግሊዝ ዕገዛ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ተሰየሙበት፣ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ሕጎችን ከፈረንሣይና ከሌሎች አገሮች አምጥተን እስክናነብር፣ በፍትሐ ነገሥትና በባህላዊ ሽምግልና ነበር የምንዳኘው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት፣ የአየር መንገድ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የባንክ፣ የአውራ ጎዳና፣ ወዘተ. ድርጅቶች ቀደምት መሥራቾች የውጭ አገር ዜጎች እንደነበሩ ሁሉ፣ የአገራችን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት እንግሊዛዊ እንደነበር ይወሳል፡፡
በፍርድ ቤቶች ፍትሕ ሲከበር፣ ሲዛባና ሲጓደል አጋጥሞን ያውቃል፡፡ በችሎት አዳራሽ የበዳይና የተበዳይ ወገኖች ለፀብ ሲገባበዙ፣ አንዱ በሌላው ላይ ከንፈሩን ሲነክስ፣ ዓይኑን ሲያጉረጠርጥ አይተናል፡፡ የሟች ወገኖች በፍርድ ቤት ውሳኔ ተደስተው ችሎቱን በዕልልታ ሲያቀልጡት፣ በተቃራኒው የገዳይ ወገኖች ችሎቱን በዋይታ ሲያደባልቁት ታዝበናል፡፡ ተከሳሾች በማዕከላዊና በፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ስም የተፈጸመባቸውን ግፍ፣ ሥቃይ፣ ልብሳቸውንና ሱሪያቸውን አውልቀው ሰንበራቸውን፣ የተኮላሸ ብልታቸውን ለችሎቱ ሲያሳዩ የተበዳይ ወገኖችና ታዛቢዎች በዕንባ ሲራጩ ተመልክተናል፡፡
ተጠርጣሪዎች ስማቸው ሲጠራ አቤት ባለማለትና ከመቀመጫቸው ባለመነሳት፣ ችሎቱን ወይም ዳኞቹን ገለልተኛ አይደለህም ብለው ሲቃወሙ ዓይተናል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱን ነፃነት ሲሞግቱ ታዝበናል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ከችሎት አደባባይ የተነፈጉትን ፍትሕ በእጃቸው ሊቀዳጁ ሲሞክሩ፣ ሌሎች ፍትሕን ከችሎት አደባባይ በላይ ከፈጣሪ ሲለማመኑ ተመልክተናል፡፡ በአገራችን ከጥቂት ዓመታት በፊት በሐዋሳ በአንድ ጠበቃ ላይ ከተፈጸመ ግድያ በቀር የተለመደ ባይሆንም በኮሎምቢያ፣ በሜክሲኮ፣ በኤልሳቫዶርና በሌሎች አገሮች ጠበቆችና ዳኞች ሲታገቱና ሲገደሉ በቴሌቪዥን ዓይተናል፡፡
በፈጠራው ዓለም ችሎትም በዊሊያም ሼክስፔየር “የቬኑስ ነጋዴ” ሻይሎክ፣ ከአራጣ ተበዳሪው መቀመጫ ሙዳ ሥጋ ለመቁረጥ ሲቋምጥ አንብበናል፡፡
እ.ኤ.አ. ጥቅምት 4 ቀን 2019 በዩናይትድ ስቴትስ ዳላስ ከሚገኙ ፍርድ ቤቶች በአንዱ የሆነው ግን በአግራሞትና በአድናቆት እጅን በአፍ ያስጫነ ታዳሚውን፣ ተከሳሹን፣ ዳኛዋን ሳይቀር በዕንባ ያራጨ፣ በቴሌቪዥን፣ በዩቲዩብ የተመለከቱትን ሚሊዮኖችን ሳይቀር ያስለቀሰና የይቅርታን ጥጋ ያመላከተ ነበር፡፡
የሟች ታናሽ ወንድም ቦታም ጅን ከተቀመጠበት የምስክር ሳጥን ድንገት ልብን በሚሰብር ድምፅ ዕንባ ያቀረሩ ዓይኖቹን ወደ ዕለቱ ዳኛ ወርውሮ፣ በእዚያ ችሎትም ሆነ በሌሎች ፍርድ ቤቶች ተጠይቆ የማያውቅ እንግዳ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹ክብርት ዳኛ! ይፈቀድ አይፈቀድ አላውቅም፡፡ የወንድሜን ገዳይ አምበርን አቅፌ ይቅርታ እንዳደረግሁላት እንድነግራት እባክዎ ይፍቀዱልኝ!?›› ሲል ዳኛዋ ያልጠበቁትና ስሜታቸውን የነካ ጥያቄ ስለነበር፣ ዕንባቸውን በመሃረባቸው እየጠረጉ ዝም ሲሉት ዓይን ዓይናቸውን እያየ አንጀትን በሚበላ ለሆሳስ እንደገና “እባክዎ. . .!?›› ሲል ይማፀናቸዋል፡፡ ዳኛዋም በመጨረሻ ይሁንታቸውን ሰጡት፡፡
አምበር ከተከሳሽ ሳጥን ተነስታ ቦታም ከምስክሮች ሳጥን ተነስቶ ከዳኛዋ፣ ከታዳሚው፣ ከዓለም ካሜራ ፊት ለዓመታት ተነፋፍቆ እንደተገናኘ ፍቅረኛ ተቃቀፉ፡፡ በሳግ ስቅስቅ ብለው ተላቀሱ፡፡ ይኼን ከስንት አንድ የሚያጋጥም የችሎት ውሎ መደበኛና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለመላው ዩናይትድ ስቴትስ አዳረሱት፡፡ ነጭ አክራሪ፣ ለዘብተኛ፣ ኢንዲያንስ፣ ጥቁር፣ ስፓኒክ፣ ብላክ ፓንተር፣ ብላክ ላይፍ ማተር፣ ዴሞክራት፣ ሪፐብሊካን፣ ቲ ፓርቲ፣ ኬ ኬ ኬ. . . ሳይለይ፡፡ ቦታም በእቅፉ ሥር ሆና ስቅስቅ ብላ በፀፀት የምታነባውን የታላቅ ወንድሙን ገዳይ፣ ‹‹እንደ ሰው እወድሻለሁ፣ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እንዲደርስብሽ አልፈልግም፤›› ሲል አደመጡት፡፡ ዓለም ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ተመለከተው፡፡ ችሎቱ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የዋይታ ቤት ይመስል በለቅሶ ተሞላ፡፡
የወንድማችንን፣ የእህታችንን፣ የአባታችንን፣ የእናታችንን፣ የምንወዳትን፣ የምንወደውን፣ የቅርብ ቤተሰቦቻችንን ገዳይ ለዚያውም ተመጣጣኝ ፍርድ ባልተሰጠበት ችሎትና ሚዲያ ፊት ይቅር ማለት፣ ለዚያውም ገዳይን አቅፎ ማፅናናትን ለአፍታ በምናባችን ስናንሰላስለው ተምኔታዊ ከአዕምሮ በላይ ቢሆንም፣ ከላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርኩት ዳላስ በዋለው በዚህ ታሪካዊ ችሎት ከሰውነት በገዘፈ ተክለ ሰብዕና ወጣቱ ቦታም ጅን ለዓለም ተገልጿል፡፡ ይህ የይቅርታ እጅ የተዘረጋው ገዳይ የታላቅ ወንድሙ መኖሪያ ቤቱ ድረስ ሄዳ ለፈጸመችው ግድያ፣ በአሥር ዓመት እስር ብቻ እንድትቀጣ ከተወሰነባት በኋላ ነው፡፡
ጂን ይኼን ሲያደርግ ነጭ ስለሆነች ነው ቅጣቱ የቀለለላት በሚል ቅሬታ፣ በችሎቱ አዳራሽ የሚሰማው ጉርምርምታም ጋብ አላለም ነበር፡፡ ስለዚህ የይቅርባይነት ጥግ የሰማሁት ከሲኤንኤን ጎምቱ ጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፑር ነው፡፡ የችሎቱን ውሎ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምሥል ዩቲዩብ ላይ ሰውነቴን እየወረረኝ ዕንባ እየተናነቀኝ ደግሜ ደጋግሜ ተመልክቸዋለሁ፡፡ ምነው ይኼ የይቅርባይነት መንፈስ አትላንቲክን በተዓምር ቀዝፎ ቀጣናውን አሳብሮ ኢትዮጵያን ባዳረሰ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ይቅርባይነትና ፍቅር ግዘፍ ነስቶ የሚዳሰስና የሚጨበጥ መሆኑን ነው የተገነዘብኩት፡፡ በሟች ወንድምና በገዳይ መካከል የተገነባው የቂም፣ የዘር፣ የቀለም፣ የመልክዓ አጥር ፈርሶ በዳላሱ ፍርድ ቤት ይቅርታና ፍቅር ሲነግሥ ስመለከት፣ በዚያ የተገኘሁ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡
ሰው የመሆን ሚስጥሩ የተገለጸበት ክስተት ከመሆኑ ባሻገር፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደ ፈጣሪ ፍፁም ፍቅር የተገለጸበት መለኮታዊ ክስተት ነው፡፡ ወጣቱ ቦታም ጅን ያለበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይቅርባይነትና ፍቅር ከፍ ብሏል፡፡ ጥላቻ፣ ልዩነትና ዘረኝነት አየሩንና መልክዓውን በተቆጣጠረበት ዓለም ይህን መሰል ይቅርታ ከሰማይ እንደ ወረደ መና ቢቆጠር ሊያስደንቀን አይገባም፡፡ የሟች ወንድም ቦታም ጅን ገና የ18 ዓመት ብላቴና እያለ ነው ይቅርባይነትን ኖሮ በተግባር ያሳየን፡፡ የልጅ አዋቂ ሆኖ የይቅርባይነትን ዓይነ ልቦና የገለጸልን፡፡ ብዙዎቻችን አይደለም በእሱ ዕድሜ በማምሻ ዕድሚያችን እንኳ ደፍረን “ይቅርታ!” ለማለት ይተናነቀናል፡፡
በፋና ቴሌቪዥን ከወላጅ እናቱ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ ተኮራርፎ በጥምቀት ሰሞን እንደታረቀ ስንሰማ ብዙዎቻችንን አስገርሞን ነበር፡፡ ቂምን፣ በቀልንና ጥላቻን እንደ ተሸከምን የምናልፍና ወደ መቃብር የምንወርድ መኖራችንን ስንረዳ እንፅናናለን፡፡ በወላጆቻችን፣ በእህት ወንድሞቻችን፣ በትዳር አጋሮቻችን፣ በልጆቻችን፣ በቅርብ ዘመዶቻችን፣ በአብሮ አደጎቻችን፣ በክፍል ጓደኞቻችን፣ በመምህራኖቻችን፣ ወዘተ. እንዳኮረፍን ቂም እንደያዝን ከእዚህ ዓለም በሞት እንለያለን፡፡ ባስ ሲልም ከራሳችን ጋር ሳይቀር እንደተጣላንና እንደተኳረፍን ወደማይቀርበት ዓለም እንሄዳለን፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ ከአምላካችንና ከተፈጥሮ ጋር እንደተጣላን ይቅር ሳንባባል እንሞታለን፡፡ ቦታም ጅን ግን ከእዚህ አልፎ የሚወደውን የታላቅ ወንድሙን ገዳይ ነው ይቅር ያላት፡፡
አንዳንዶቻችን ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም፣ ዩቲዩብ፣ ወዘተ. ላይ በተሰጠን አስተያየት መልስ ለመስጠት እንቅልፍ የምናጣ፣ የስድብ ውርጅብኝ የምናወርድ፣ ይህ አልበቃ ብሎን ጉድኝታችንን የምናቋርጥ (Unlike)፣ ከፍ ሲልም ጥርቅም አርገን የምንዘጋ (Block) ቂማችንን የምንወጣ ጉዶች ነን፡፡ በጥሞናና በሰከነ አዕምሮ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ልዩነትን የመፍታት ልምምድ የለንም፡፡ ፈልገ፣ ወደንና ፈቅደን ባላገኘነው ማንነት ሳይቀር የምንጣላ፣ ቂም የምንይዝና ለበቀል የምንነሳ ስንት ደመ ነፍሳውያን አለን፡፡ በቀደሙ ነገሥታት የተፈጸመን ስህተት በእዚህ ትውልድ ለማወራረድ የምንቀዠቀዥ ከንቱዎች ነን፡፡
ቦታም ጅን፣ ‹‹ይፈቀድ አይፈቀድ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የወንድሜን ገዳይ አቅፌ ይቅር እንድላት የተከበሩ ዳኛ ሊፈቅዱልኝ ይችላሉ!? እባክዎ!›› የሚለው ድምፅ ዛሬ ድረስ በእዝነ ህሊናዬ ይሰማኛል፡፡ የዕለቱ ዳኛ ታሚ ኬምፕ ባልጠበቁት ጥያቄ ግራ ተጋብተው ይሁን በጅን የይቅርባይነት ልብ ልባቸው ተነክቶ፣ ለደቂቃዎች ዝምታን ከመረጡ በኋላ ሲፈቅዱለት የሚያሳየውን ምሥል በመደነቅ ከመድገም በላይ ደጋግሜዋለሁ፡፡
የወንድሙ ገዳይ የዳላስ ፖሊስ ባልደረባ የነበረችው ነጯ አምበር ጉይገርም 911 ላይ ደውላ ከተናገረችው እንደ ተደመጠው፣ ‹‹ሥራ ውዬ ቤቴ እንደ ደረስኩ በሩ ተከፍቶ ጠበቀኝ፡፡ እኔም ሌባ የገባ ስለመሰለኝ ሽጉጤን አቀባብዬ ወደ ሳሎን ስዘልቅ እንግዳ ሰው ሶፋ ላይ ተቀምጦ ሳይ ደንግጬ ተኩሼ ገደልኩት፡፡ ወደ አዕምሮዬ ስመለስ ግን ለካ የገባሁት እኔ ቤት ሳይሆን በስህተት ሟች ቤት ነበር፤›› በማለቷ የገዳይን ሰንካላ ቃል አምኖ ለመቀበል አዳጋች ቢሆንም፣ በዚህ መንገድ የወንድሙን ሕይወት ለነጠቀች ፖሊስ ነው ጅን ይቅርታ ያደረገላት፡፡ ሌሎች የቤተሰቡ አባላትና የጥቁር መብት ተሟጋቾች ግን ገዳይ በአሥር ዓመት እስር ብቻ መታለፏን በመቃወም፣ ከፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት ቁጣቸውን በመፈክር እየገለጹ ነበር፡፡ አንተ፣ አንቺ ብትሆን/ኚ/ ታደርገዋለህ/ጊዋለሽ!?
ማጠቃለያ
የይቅርታና የፍቅር ተምሳሌት አባት ረቡኒ/አስተማሪ የሆነው የደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ትግል መሪና የነፃዋ ደቡብ አፍሪካ የመጀመርያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ (ማዲባ) እ.ኤ.አ. በ1995 ለንባብ በበቃው “Long Walk to Freedom” በተሰኘው ድንቅ ግለ ታሪክ መጽሐፉ፣ ‹‹ሁሉም ሰው ጥላቻን ተምሮ እንጂ ከእናቱ ማህፀን ይዞት አልተወለደም፡፡ ጥላቻን የተማረ አዕምሮ ደግሞ ፍቅርንና ዕርቅን መማር አይከብደውም፤›› እንዳለው፣ ጅን ፍቅርንና ይቅርታን ከእናቱ ማህፀን ይዞት አልተወለደም፡፡ ከፈጣሪውና ከእምነቱ ተምሮት እንጂ፡፡
እኛም ከጅን የይቅርታ ልብ ብዙ ብዙ መማር ማትረፍ እንችላለን፡፡ ጥላቻን ልዩነትን ባለፉት 50 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሊባል በሚችል ደረጃ ተጋትነው እንጂ፣ ከእናታችን ማህፀን ይዘነው አልተወለድንም፡፡ ከእናታችን ማህፀን ይዘነው ያልተወለድነውን ግን በአንድም ሆነ በሌላ የተማርነውን ጥላቻ፣ ልዩነትና ቂም በቀል ከአዕምሯችን ለመሰረዝና ለማጥፋት እንደ ጅን ካሉ ባለግዙፍ ተክለ ሰብዕና ባለፀጋዎች መማር እንችላለን፡፡ ከእነ ማንዴላ፣ ማህተመ ጋንዲ፣ ማርተን ሉተር ኪንግ ተዝቆ የማያልቅ የይቅርታ መዝገብም መማር ይቻላል፡፡
ጥላቻን ከመማር ይልቅ ፍቅርንና ይቅርባይነትን መማር ይቀላል፡፡ ምክንያቱም ፍቅርና ይቅርባይነት አምላካዊ ሲሆን፣ ጥላቻ ደግሞ ሰይጣናዊ ነው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ አምላኩ በአምሳሉ የፈጠረው ስለሆነ አዕምሮው ለፍቅርና ለይቅርታ ይቀርባል፡፡ ያደላል፡፡ ከጅን ይቅርባይነትን ያረጋገጥነው ይኼንኑ ነው፡፡ መቼም ስለፍቅርና ይቅርባይነት በተነሳ ቁጥር ከፈጣሪ ቀጥሎ ስሙ የሚወሳው ማንዴላ ነው፡፡
ከፍ ብዬ በጠቀስሁት መጽሐፉ ስለይቅርባይነት ከፍታና ኃያልነት፣
‹‹ይቅርባይነት ነፍስን አርነት ያወጣል፣ ፍርኃትን ያስወግዳል፤›› ሲል እማኝነቱንና ምስክርነቱን ገልጿል፡፡ ስለዚህ ይቅር በመባባል ነፍሳችንን ከባርነት ነፃ እናውጣ፡፡ በይቅርባይነት ቀይዶ አላላውስ ካለን የፍርኃት ቆፈን እንላቀቅ፡፡ ወገኖቼ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የበደልኳችሁና በዚህ ጋዜጣ በምጽፋቸው መጣጥፎች የተቀየማችሁ ብትኖሩ፣ ከእግራችሁ ሥር ወድቄ ይቅር እንድትሉኝ እለምናለሁ፡፡ እንዲሁም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የበደላችሁኝንም ከልብ ይቅር ብያለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡