Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ በስምንት ወራት ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት አከናወነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ የ26.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 528,899 ቶን ምርቶችን እንዳገበያየ አስታወቀ፡፡

ምርት ገበያው ከሐምሌ 2011 ዓ.ም. እስከ የካቲት 2012 ዓ.ም. ባሉት ስምንት ወራት ውስጥ ያከናወናቸው የግብይት እንቅስቃሴዎች በዋጋ ደረጃ ከዕቅዱ የ11 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ከመጠን አንፃር በስምንት ወራት ውስጥ የተገበያየው የምርት መጠን ከዕቅዱ አንፃር ሲታይ የአንድ በመቶ ብቻ ብልጫ እንዳሳየ ታውቋል፡፡

በስምንት ወራት 202,248 ቶን ቡና በ15.7 ቢሊዮን ብር፣ 186,474 ቶን ሰሊጥ በስምንት ቢሊዮን ብር፣ 62 ሺሕ ቶን አኩሪ አተር በ894 ሚሊዮን ብር፣ 43 ሺሕ ቶን ማሾ 1.1 ቢሊዮን ብር፣ 33 ሺሕ ቶን ነጭ ቦሎቄ በ691 ቢሊዮን ብር፣ 2,602 ቶን ቀይ ቦሎቄ በ38 ሚሊዮን ብር ግብይታቸው እንደተፈጸመም ገልጸዋል፡፡ በስምንት ወራት ምርት ገበያው ካገበያየው ምርት ውስጥ በግብይት መጠን ቡና 38 በመቶ ድርሻ ነበረው፣ ሰሊጥ 35 በመቶ፣ አኩሪ አተር 12 በመቶ ድርሻ ነበራቸው ብሏል፡፡ በግብይት ዋጋ ቡና 59 በመቶ፣ ሰሊጥ 30 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በየካቲት 2012 ዓ.ም. በነበሩት 20 የግብይት ቀናት 35,901 ቶን ሰሊጥ፣ 25,354 ቶን ቡና፣ 21,254 አኩሪ አተር፣ 7,881 ነጭና ቀይ ቦሎቄ፣ 6,992 አረንጓዴ ማሾ፣ በአጠቃላይ 97,382 ቶን ምርት በ4.42 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ገልጸዋል፡፡  

በየካቲት ወር ግብይት 35,901 ቶን ሰሊጥ በ1.52 ቢሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ይህም 37 በመቶ የግብይት መጠንና 34 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ በወሩ ከተገበያዩ ምርቶች ቀዳሚውን ቦታ መያዙን አመልክቷል፡፡ በወሩ ከተገበያየው የሰሊጥ ምርት ውስጥ ሁመራ/ጎንደር ሰሊጥ በ78 በመቶ የግብይት መጠንና በ79 በመቶ የግብይት ዋጋ ትልቁን ድርሻ እንደያዘም ይኸው የምርት ገበያው መረጃ አመልክቷል፡፡

የቡና ግብይት በየካቲት ወር ከሰሊጥ ያነሰ የነበረ ሲሆን፣ በወሩ 25,354 ቶን ከሁሉም የቡና ዓይነቶች ለግብይት ቀርቦ በ2.28 ቢሊዮን  ብር ተገበያይቷል፡፡ ለውጭ ገበያ የቀረበ ቡና 60 በመቶ የግብይት  መጠንና 57 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ የመጀመርያውን ደረጃ የያዘ ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የቀረበ ቡናና ስፔሻሊቲ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡

የየካቲት ወር የአኩሪ አተር የግብይት ሁኔታን የሚያሳው መረጃ ደግሞ 21,254 ቶን አኩሪ አተር ለግብይት ቀርቦ በ274 ሚሊዮን ብር መገበያየቱን ይጠቁማል፡፡  በወሩ ከቀረበው የአኩሪ አተር ምርት  የጎጃም አኩሪ አተር በመጠንና በዋጋ 83 በመቶ በማስመዝገብ የመጀመርያውን ደረጃ ይዟል፡፡ በተጨማሪም 6,992 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ185 ሚሊዮን ብር፣ 7,881 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ161 ሚሊዮን ብር ግብይታቸው ተፈጽሟል፡፡ ከዚህም ውስጥ 6,426 ቶን ነጭ ድቡልቡል ቦሎቄ በ142 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም 1,455 ቶን ቀይ ቦሎቄ በ20 ሚሊዮን ብር እንደተገበያየም ተገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቡና፣ በጥራጥሬና ቅባት እህል አቅራቢነትና ላኪነት ለተሰማሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ብቻ የሚሳተፉበት አሥር የአባልነት ወንበሮችን ለኅብረት ሥራ ማኅበራት በግልጽ ጨረታ ለሽያጭ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ ምርት ገበያው ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ባወጣው የጨረታ ማስታወቂያ፣ ‹‹እያደገ ባለው የዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ አካል በመሆን አባሎቻቸውን ጥቅም በማሳደግ ለአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በጨረታው እንዲሳተፉ ምርት ገበያው ይጋብዛል፤›› ብሏል፡፡

ምርት ገበያው ከሌላ ጊዜ በተለየ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ብቻ እንዲጫረቱ ለምን ፈቀደ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የምርት ገበያው የኮርፖሬት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ተስፋዬ፣ ‹‹ይህ የሆነው በምክንያት ነው፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ብቻ እንዲሳተፉ ያደረግንበት ዋና ምክንያት በምርት ገበያው ውስጥ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሳትፎን ማሳደግ በማስፈለጉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

 ‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበራት በምርት ገበያው ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ ከ347 የምርት ገበያው አባላት ውስጥ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ብዛት 33 ብቻ ነው፤›› ያሉት አቶ ነፃነት፣ የማኅበራቱን ቁጥር ከፍ ለማድረግ አሥር የአባልነት መቀመጫዎችን በጨረታ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻ ማቅረቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ታምኖበት የተወሰደ ዕርምጃ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

አንድ የኅብረት ሥራ አባል ሆነ ማለት በሥሩ ብዙ ሺሕ አባል አርሶ አደሮች ስላሉ ለእነዚህን አርሶ አደሮች መድረስ ስለሚያስችል እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ሥር ያሉት በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ከማድረግም በላይ ለዘመናዊ ግብይቱ ማደግ ዕገዛ ይኖቸዋል ተብሏል፡፡ አርሶ አደሩ በቀጥታ ከመሸጥ ባሻገር በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል መሳተፉ የበለጠ ተጠቃሚ  ያደርጉታል፡፡ እንዲሁም ከትርፍ ጭምር የሚከፍሏቸው በመሆኑ፣ ተቀሜታው ሰፊ እንደሚሆን አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት በቀጥታ ወደ ውጭ ምርት የመላክ ዕድል ያላቸው በመሆኑም፣ ከዚህ በኃላ ተጨማሪ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ወደ ምርት ገበያ እንዲገባ የሚያስችል ሥራዎች እንደሚኖሩም ከአቶ ነፃነት ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ጨረታው መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም.  የሚከፈት መሆኑም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች