Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሮና ቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ትኩሳቶች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑ ከታወጀ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ከአንታርክቲካ በቀር ሁሉንም አኅጉራት አዳርሷል፡፡ በኢትዮጵያም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ብዛት ወደ ስድስት አሻቅቧል፡፡ ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙም ይፋ ተደርጓል፡፡ የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው ናሙናቸው ተወስዶ ውጤታቸው የሚጠበቅና በጥርጣሬ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ በርካቶች ይገኛሉ፡፡ ከስድስቱ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ከ900 በላይ ሰዎች ምርመራ እየተደረገላቸው ነው፡፡

የቫይረሱ ሰደድ ዓለምን በከፍተኛ ፍጥነት እያዳረሰ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን እያስከተለ የሚገኘው ኮሮና ቫይረስ፣ ለወትሮው ችግሮች የተበተቡትን የገበያ ሥርዓት የበለጠ አስቸጋሪ እያደረገው መምጣቱን ከሰሞኑ የታዩ ሥነ ምግባር የጎደላቸው አጉራ ዘለል ድርጊቶች ይመሰክራሉ፡፡

የቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ይፋ ከተደረገበት ቅጽበት ጀምሮ በሽታውን ለመከላከል የሚያገለግሉ ዕቃዎች ዋጋ አልቀመስ ብሏል፡፡ የምግብ ሸቀጦችም ላይ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ነው፡፡ የቁሳቁሶቹ አቅርቦትም ሆነ ተብሎ በሚመስል አኳኋን እጥረት እየታየበት ነው፡፡ ሸማቹም ባደረበት ሥጋት ሳቢያ በተጋነነ ዋጋ በሠልፍ ሲሸምት ታይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን አጋጣሚውን በመጠቀም ገበያውን ያዛቡ አካላትን ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል እንዳቋቋሙ የገለጹት ወዲያው ነበር፡፡ ምርቶችን ባልተገባ ዋጋ ሲሸጡ የተገኙ 83 መደብሮች አሽገዋል፡፡ ለወትሮው በአምስት ብር የሚሸጠውን የአፍ መሸፈኛ (ማክስ)  በ500 ብር ለመሸጥ ማስታወቂያ ሲያስነግር የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል፡፡

በኮሮና ሰበብ የተፈጠረው ሕገወጥ የንግድ ሥራ በጊዜ ካልተገታ ከበሽታው መዛመትና መስፋፋት ጋር አደገኛነቱ አያጠያይቅም፡፡ አንዳንዶች የኮሮና አጋጣሚን ተገን በማድረግ የተፈጠረው ድባብ፣ በነሐሴ ለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫም አመላካች ስለመሆኑ ጭምር ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ የከፋ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ሊያስከትል እንደሚችል ይታመናል፡፡

በዚህ ዙሪያ ላይ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁና ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ያስከትላል፡፡ ይሁን እንጂ ተፅዕኖውን ለመቀነስ የሚረዱ የመፍትሔ ዕርምጃዎች እንደሚኖሩም ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ ኮሮና ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳትና ከዚህም በኋላ ሊኖር የሚችለውን ሥጋት በማብራራት አስተያየት የሰጡ አንድ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ፣ የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ እያስከተለና በእያንዳንዱ አገር ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መምጣቱን በመግለጽ ይጀምራሉ፡፡ ‹‹ዝርዝር ጉዳዮችን ትተን፣ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ በግልጽ ከሚያሳዩን አንዱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ማሳየቱ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ቅናሹ ሊጠቅማቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የነዳጅ ዋጋው መቀነስ የሚያሳው የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዙን፣ በቂ ምርት አለመመረቱን በመሆኑ፣ ‹‹በገቢ ንግድ ወጪ ላይ የተወሰነ ተጠቃሚነት ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሌም አዎንታዊ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ የለብንም፤›› በማለት ባለሙያው ያሳስባሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ከውጭ የሚገቡ የምግብ ምርቶች መኖራቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተጣራ የምግብ ሸቀጥ ከሚያስገቡ አገሮች ተርታ ትፈርጃለች፡፡ የምርት መቀነስ በዓለም ከተከሰተም የምግብ ምርቶች ዋጋ እንዲጨምር ሊያስገድድ ይችላል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ፣ ዱቄትና፣ ሌሎች ምግብ ነክ ምርቶችን የምታስገባ በመሆኑ እነዚህ ምርቶች ላይ ተፅዕኖ ሊያርፍ ይችላል፡፡

በአንፃሩ ከላኪዎች ሥጋት በተቃረነ መልኩ የወጪ ንግድ ላይ የተወሰነ አዎንታዊ ለውጥ ሊያሳይ ይችላል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ የዚህም ለውጥ ብዙ የሚያስወራ እንደማይሆን ይጠቅሳሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከወጪ ንግዱ ይልቅ ገቢው ከፍተኛ በመሆኑና ምግብ ነክ ሸቀጦች ከውጭ በብዛት ስለሚገቡ፣ የምግብ ዋጋ ንረት ላይ ተዕኖ ያሳርፋል ብለው ያምናሉ፡፡  

ከውጫዊ ተፅዕኖዎች ጋር በተያያዘ ሌሎችም የሚጠበቁ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እንዳሉ ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ የጉዞ ገደብና እንቅስቃሴ እየቀነሰ መምጣት፣ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ተቋማት ገቢን ይቀንሳል፡፡ ሌላው የሚያሠጋው ተፅዕኖ የውጭ ሐዋላ ላይ ሊደርስ የሚችለው ቅናሽ ነው፡፡

የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ከሚያስገኘው ጊዜያዊ ጠቀሜታ ይልቅ፣ የምርት እጥረት የሚፈጥረው ተፅዕኖ በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለውን ገበያ እንደሚጎዳው እየተገለጸ ነው፡፡ ሌላው የዓለም ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተፅዕኖ ውስጥ መውደቁን እያሳየ ያለው፣ በዓለም ደረጃ የስቶክ ገበያ ላይ የሚታየው መዋዠቅና የዋጋ መቀነስ ነው፡፡

የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የእስያ ስቶክ ገበያ ዋጋ እያሸቆለቆለ የመሄዱ ችግርና ገፈቱ እዚያው ይቆማል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ በሁሉም አገሮች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ እየታየ ነው፡፡ ይህ መሆኑም የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ አኳያ ሲታይ የውጭ ኢንቨስትመንት ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ምልክቶቹ እየታዩ እንደመጡም  የኢኮኖሚ ባለሙያው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው የውጭ ሐዋላ ገቢ ሊቀንስ ስለሚችልባቸው መንገዶች ሲያብራሩም፣ የንግድ ሥራቸው የተቀዛቀዘባቸው ኩባንያዎች ሠራተኞች ሊቀንሱ እንደሚችሉ ሥጋት ከመፈጠሩ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ቫይረሱ በተከሰተባቸው አገሮች ውስጥ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ‹‹ዜሮ ኮንትራት›› በሚባለው የቅጥር ሥርዓት ውስጥ የሚቀጠሩ በመሆናቸው፣ ኩባንያዎቹ የሠራተኛ ቅነሳ ሲያደርጉ ግንባር ቀደም ዕርምጃቸው በዜሮ ኮንትራት የተቀጠሩት ላይ የሚያነጣጥር በመሆኑ፣ ቀላል የማይባሉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሥራ ገበታቸው ይቀነሳሉ የሚል ግምት አለ፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ወደ ኢትዮጵያ ይላክ የነበረው የውጭ ሐዋላ ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል ተብሎ ተሠግቷል፡፡

ሌላው ኮሮና ቫይረስ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ገቢ ላይ የሚታይ ነው፡፡ በርካታ ስብሰባዎች ከወዲሁ እየተሰረዙ በመሆኑ፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ገቢ ይቀንሳል፡፡ ይህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ በበሽታው መዛመት ሳቢያ በኢትዮጵያ እንዲካሄዱ ከታሰቡ ኮንፈረንሶች መካከል የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም መሰረዙ እየተነገረ ነው፡፡

የትራንስፖርት ዘርፍም ተፅዕኖ ከሚያርፍባቸው የኢኮኖሚ መስኮች አንዱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፣ እንቅስቃሴዎች ሲገደቡ የአገልግሎት ዘርፉ ጫና ውስጥ እንደሚወድቅ ግልጽ ነው፡፡ ሆቴል፣ ሬስቶራንትና ልዩ ልዩ ሕዝብ የሚገለገልባቸው የመዝናኛ ዝግጅቶች ይስተጓጎላሉ፡፡ ሰዎች በበሽታው ሥጋት ሳቢያ በየቤታቸው እንዲቆዩ ሲገደዱ ገቢያቸውም ይቀንሳል፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱ የመንግሥት በጀት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ መንግሥት የበሽታውን ሥርጭት ለመግታትና ለመከላከል ተጨማሪ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ ለአሁኑ እንኳ የ500 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡ እየገለጸ ነው፡፡ የቫይረሱ መዛመት እየተባባሰ ከሄደም የሚመደበው በጀት እየጨመረ መሄዱ ስለማይቀር፣ በአገሪቱ ላይ የበጀት ጫና ያሳድራል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡ መንግሥት የሚኖርበት ጫና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

በአንፃሩ መንግሥት ለሁለት ሳምንታት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችና ዝግጅቶች፣ እንዲሁም ስፖርታዊ ክንውኖች እንዳይካሄዱ በመወሰኑ፣ ሊደርስ የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ከመነቀስ ባሻገር ሊጋጥም የሚችለውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ የሚያስችል ዕርምጃ እንደሆነ ኢኮኖሚስቱ ይገልጻሉ፡፡

‹‹መንግሥት ይህንን አድርጓል፡፡ ኅብረተሰቡም በተባለው መሠረት ራሱን ከጠበቀ ኢኮኖሚው ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅዕኖ መቀነስ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የኮሮና ቫይረስ መግባቱ ከተነገረ ጀምሮ፣ በሽታው እንዳይዛመት ለመከላከል በሚያግዙ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ለውጦች ከመታየታቸውም በላይ ምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ለውጥና እጥረት መከሰቱ በተለያየ መንገድ እየታየ ነው፡፡  

ይህንን ለመከላከል መንግሥት ምርት የሚሸሽጉ ነጋዴዎች እስካሁን ከተከሰተውም የባሰ እጥረት እንዳያስከትሉ፣ ማቅረብ በሚችልባቸው መንገዶች ማቅረብ ሲጀመር የዋጋ መናር ሊረግብ እንደሚችል፣ እጥረቱም ሊስተካከል እንደሚችል የኢኮኖሚስቱ እምነት ነው፡፡ ሸማቹ በበሽታው ሥጋት ምክንያት ያደረበትን የምግብ ምርቶች እጥረት ሥጋት ለመቅረፍ፣ መንግሥት መሠረታዊ ምርቶችን በሚገባ ማቅረብና መቆጣጠር ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡ መንግሥት የሕዝቡን መተማመን ለመፍጠር በዕርዳታም ሆነ በሌላ መንገድ ምርቶችን ማቅረብ ከቻለ በተወሰነ መልኩ ዋጋው እንደሚያረጋጋ ይጠበቃል፡፡

ነጋዴው ከደበቀው ባሻገር ግን እውነተኛ የምርት እጥረት ካለ ግን ይህን ማስተካከሉ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ሥጋት አለ፡፡ ይህም ሆኖ በሥጋትና በፍርኃት ውጥረት የተነሳ አላስፈላጊ የሸመታ እንቅስቃሴ ከተፈጠረ፣ ገበያውንም ኢኮኖሚውንም የሚረብሽ ክስተት እየተበራከተ ሊሄድ ስለሚችል መንግሥት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ምክር ቀርቦለታል፡፡

ይህም ሆኖ በዓለም ደረጃ የሚከሰቱና ኢትዮጵያም ሆነ መንግሥት ምንም ሊያርጓቸው የማይችሉ ክስተቶች በመኖራቸው የእነዚህን ጫና መቀነስ ስለሚቻልበት መንገድ መንግሥት ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚጠበቅበትም ባለሙያው ያምናሉ፡፡ ‹‹የዓለም የምግብ ዋጋ ከጨመረ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ለጊዜው ወጪያችንን በመቀነስ ጫናውን ለመቀነስ የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡ ይህም ቫይረሱን ቀድመን መከላከል መቻል ነው፡፡ ቀድመን ቫይረሱን መከላከል ከቻልን ቶሎ የሚድኑም ሰዎች ስለሚኖሩ በዚህ መጠቀም እንችላለን፤›› የሚል አመለካከት አላቸው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሆቴልና የግሮሰሪ ባለቤቶች እንደጠቀሱት፣ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ በፈጠረው ጫና ሳቢያ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ የተጠቃሚዎች ቁጥር በመቀነስ ላይ ይገኛል፡፡ ፆመ ሁዳዴም ገበያቸውን አቀዛቅዞታል፡፡ በዚህ መካከል ብቅ ያለው የኮሮና ቫይረስ ሥጋት ጭራሹን ገበያቸውን እያዳከመው እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ሐሳብ የሚጋሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፣ እንዲህ ባለው ጊዜ የገበያ መቀዛቀዝ መከሰቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉት ሁሉ ሆቴሎችና መሰል ድርጅቶችም ሊዘጉ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ያጣቀሱት በሌሎች አገሮች የተወሰዱ ዕርምጃዎች እዚህም ሊመጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡ በዚህ ወቅት መታሰብ ያለበት ጊዜያዊ ገበያ መታጣቱ ሳይሆን፣ ዘላቂታዊ ችግሩ ነው ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች