በታፈረ ህሉፍ ዓለሜ (ኢንጂነር)
ግድቡ የሚያመነጨው የኢነርጂ መጠን
ከጥቂት ወራት በፊት የፕሮጀክቱ አመራር ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ የግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅም ቀንሷል አልቀነሰም የሚል አካራካሪ አጀንዳ ተፈጥሮ ነበር፡፡ አሁን ድረስ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የሚከራከሩ ወገኖች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በእርግጥ የተወሰደው ዕርምጃ ግድቡ የሚገኝበት አካባቢ የዓባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ ገደቦችን መሠረት በማድረግ የምህንድስና ማስተካካያ ዕርምጃ ነበር፡፡ ግድቡ ላይ የተነሳው ጥያቄ “ከመጠን በላይ (Over-Siezed) ነው” የሚል ነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ዲዛይን የሠራው ድርጅት የጣሊያኑ ፔንትራጄሊ ሲሆን ሦስቱም ግልገል ግቤዎችን ጨምሮ ከአንድ መቶ ግድቦች በላይ የሠራ አንጋፋ ድርጅት ነው፡፡
አንድ ግድብ “ከመጠን በላይ” ነው ከተባለ አብዛኞቹ ተርባይኖች በአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የመዋል ዕድላቸው ዝቅተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንድ ባለ ብዙ ወለል ሕንፃ ለአንድ ግለሰብ እንደመገንባት ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ለጥቂት ወራት ሕንፃውን መሙላት የሚችሉ እንግዶች ይኖሩትና በአብዛኛው ጊዜ ግን የሕንፃው ክፍሎች ባዶ ይሆናሉ፡፡ ማመንጨት የሚቻለው የኃይል መጠን የሚወስኑት የግድቡ ርዝመትና የውኃው ተፈጥሯዊ ፍሰት ናቸው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ የግድቡ ዲዛይን የተሠራው ለከፍተኛ ፍሰት ይመስላል የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነበር፡፡ ይህ ከፍተኛ ፍሰት በዓመት ውስጥ ለሦስትና አራት ወራት ብቻ የሚስተዋል ነው፡፡ 17 ተርባይኖች 145 ሜትር ርዝመት ላለው ግድብና በዓመት ስምንት ወራት ሙሉ ዝቅተኛ ፍሰት ላለው ወንዝ በተወሰነ ደረጃ ብዙ ሊባል ይችላል፡፡ በእርግጥ ግድቡ የተሠራበት ዓላማ ኃይል ለማመንጫነት ብቻ ከሆነ ከፍተኛ ፍሰትን ተመሥርቶ የተሰላ የኃይል መጠንን ዒላማ ማድረግ ኢኮኖሚያዊ እሳቤ ላይኖረው ይችላል፡፡ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ግን ኃይል ማመንጨት ላይ የተወሰነ እንዳልሆነ ከመጀመሪያውም ይታወቃል፡፡
ከህዳሴ ግድብ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የሱዳኑ ሮሴይረስ ግድብ ዙሪያ በተገኙ መረጃዎች (Khartoum, Sudan; Ministry of Irrigation and Water Resources) መሠረት የዓባይ ወንዝ ዓመታዊ ፍሰት እ.ኤ.አ. 1985 ውስጥ በሰከንድ 6944 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር፣ 1995 ውስጥ በሰከንድ 5,208 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር፣ 2005 ውስጥ በሰከንድ 5,787 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነበር፡፡ የህዳሴ ግድብን ቁመት 145 ሜትር ወሰድን ግርድፍ ስሌት ብንሠራ የህዳሴ ኃይል የማመንጨት አቅም እስከ 8,000 ሜጋዋት ማድረስ እንደሚቻል ያሳያል፡፡ ሙሉ ዓመት ቀጣይነት ያለው የኃይል መጠን እንዲያመነጭ ግን ለአማካይ ፍሰት የተቀራረበ ቢሆን ይመረጣል፡፡ በመሆኑም ዲዛይኑ በልኩ ካልተሠራ የወንዙ ፍሰት በቀነሰ ቁጥር ኃይል ማመንጫው ለወራት በከፊል ሥራ ያቆማል፡፡ በእርግጥ ይህ በዲዛይን ጊዜ የሚታይ ነው፡፡
ህዳሴ ላይ በዲዛይኑ ጊዜ ለከፍተኛው የቀረበ የፍሰት መጠን መጠቀማቸው፣ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የሚከናወን ልማትን ታሳቢ በማድረግ “የፍሰት መጠኑን ማሻሻል ይቻላል” ከሚል መነሻ ሊሆን እንደሚችል ፍንጮች አሉ፡፡ በዚህ መሠረትም የህዳሴ ከፍተኛው የማመንጨት አቅሙ 6,450 ሜጋዋት እንደነበር ይታወቃል፡፡
ትንሽ ለማብራራት፣ አንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ ምን ያህል ኃይል እንደሚያመነጭ የሚወስነው በግድቡ ቁመትና በወንዙ አማካይ ዓመታዊ የፍሰት መጠን ነው፡፡ ኢንተርኔት ላይ የተገኙ ጥናታዊ ወረቀቶች፣ የዓባይ ወንዝ በዓመት ውስጥ የፍሰት መጠን በሰከንድ ከ1,500 እስከ 7,000 ኪዩቢክ ሜትር ሊደርስ እንደሚችል ያሳያሉ፡፡ በዚህ መሠረት በግርድፉ ቢሰላ 1,900 እስከ ከ8,500 ሜጋዋት ኃይል ድረስ በየወቅቱ እየወጣና እየወረደ ማመንጨት የሚችል ግድብ መሥራት ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም በከፍተኛው ኃይል የማመንጨት ገደብ ላይ በውኃ እጥረት ምክንያት አብዛኞቹ ተርባይኖች እስከ ዘጠኝና ስምንት ወር ድረስ ሊቆሙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ዓመታዊ አማካይ የወንዙ ፍሰት የተወሰነ የተጠጋ የኃይል መጠን እንዲያመነጭ አድርጎ መሥራት ይመረጣል፡፡ በመሆኑም የህዳሴ ግድብ የተርባይኖች ቁጥር የመቀነሱ ሐሳብ የመጣው ግድቡ የሚያመነጨው የኃይል መጠን ወደ አማካዩ በተወሰነ ደረጃ ለማስጠጋት ታስቦ ስለመሆኑ ማየት ይቻላል፡፡
በኃይድሮፓወር ኢነርጂ ማመንጫ ኢኮኖሚ ውስጥ የወንዙ ፍሰት መዋዠቅና የድርቅ ሁኔታ ወሳኝ ፓራሜትሮች ናቸው፡፡ “ስሪ ጎርጅ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው የቻይናው የዓለማችን ትልቁ ግድብ ብንወስድ 24,000 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ግድቡ የተሠራበት የወንዙ ፍሰት በየወቅቱ የሚለዋወጥ በመሆኑ ግን በዓመት 9,800 ሜጋዋት ኃይል ማመንጨት ላይ ይወሰናል፡፡ ይህ ማለት በዓመት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የማይሠሩ ተርባይኖች አሉት ማለት ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በዓለም ሁለተኛው ትልቁ ኢታይፑ የሚባለው ግድብ 14,000 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ግድቡ የተሠራበት የወንዙ ፍሰት አንፃራዊ ወጥነት ስላለው ግን በዓመት 10,900 ሜጋዋት ኃይል ማመንጨት ይችላል፡፡
የህዳሴ ግድብም በየወቅቱ ፍሰቱ በሚለዋወጠው ዓባይ ወንዝ ላይ እንደመሠራቱ በዓመት የሚያመነጨው የኃይል መጠን እስከ 1,900 ሜጋዋት ድረስ ሊወርድ እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም የማመንጨት አቅሙ 6,450 ሜጋዋት መደረጉ ግን ጥቅሙ እንጂ ጉዳቱ ብዙም የሚታይ አይደለም፡፡ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋጋ ከዓለም አቀፍ የኃይድሮፓወር ዋጋ አንፃር እጅግ ርካሹ እንደመሆኑና ግንባታው 70 በመቶ እንደመጠናቀቁ፣ የግድቡ ተርባይን ተቀንሶ የማመንጨት አቅሙ በ1,300 ሜጋዋት መውረዱ ትክክል ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለዚህ ሲባል ፕሮጀክት ዋጋ ቀነሰ የተባለው ገንዘብም ከተቀነሰው የኢነርጂ መጠን አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
የተርባይን ቁጥርና ግድቡ የሚያመነጨው የኢነርጂ መጠን በመቀነስ የፕሮጀክቱ ዋጋ ይቀንሳል የሚባለው ምክንያታዊ አይደለም ማለት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የውኃ ኢነርጂ አስፈላጊነት ከኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ እዚህ ላይ በቀጥታ ቁጥሮችን ከማወዳደር ይልቅ የኢነርጂ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ትንሽ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ኢነርጂ ማለት ሁሉም ነገር ነው፡፡ ኢነርጂ ካለህ ድንጋዩን ወደ ብርቱካን አብቃይ ለም መሬት መለወጥ ትችላለህ፡፡ ጭልጥ ያለ በረሃ ውስጥ ውኃ ማፍለቅ ትችላለህ፡፡ ኢነርጂ በሥልጣኔ ማዕከል ላይ የሚገኝ ውድ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ለሳይንቲስቶች፣ የአንድ ማኅበረሰብ የኢነርጂ ፍጆታ የሥልጣኔ ደረጃ መለኪያም ጭምር ነው፡፡ አንድ አሜሪካዊ የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ዓመታዊ ፍጆታ ከኢትዮጵያዊው አንፃር በ32 እጥፍ የመብለጡ ምስጢርም ይኼው የሥልጣኔ ደረጃ ልዩነት ነው፡፡
አርኪዮሎጂያዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሚሊዮን ዓመታት በፊት የሰው ልጅ የጡንቻው ኢነርጂ እንኳን የማይጠቀም ደካማ ፍጡር ነበር፡፡ ለዚህም እንደ ጥንብ አንሳ የወዳደቁ ነገሮች ይመገብ እንደነበር ሳይንሳዊ ትንበያዎች ያመለክታሉ፡፡ ከበርካታ አዝማናት በኋላ ግን ወደተሻለ ደረጃ ዝግመተ ለውጥ አደረገና የጡንቻዎቹ ኢነርጂ ተጠቅሞ አድኖና ዛፍ ላይ ወጥቶ ትኩስ ነገሮችን መመገብ ጀመረ፡፡ በሒደትም ከነገሮች የሙቀት ኢነርጂ (እሳት) መጠቀም ጀመረ፡፡ በመቀጠልም እንደ ሹል ድንጋይና እንጨት ዓይነት የኢነርጂ ማባዣ ቁሳቁሶች በመጠቀም አዳዲስ ዘዴዎችን መተግበር ቀጠለ፡፡ የእንሰሳት ኢነርጂን (የበሬ፣ የፈረስ፣ የዝሆን ወዘተ) በመጠቀም እንደጀመረም ምርቱን ከማሻሻል አልፎ እንደ አክሱምና አሌክሳንድሪያ ዓይነት ከተሞችን በድቅድቅ ጫካ ውስጥ መገንባት ቻለ፡፡ በሒደትም የእንፋሎት ኢነርጂ በመጠቀም የትራንስፖርትና የማምረቻ መሣሪያዎችን መገንባት ጀመረና ተፈጥሮን የመጠቀም አቅሙ በእጅጉ ማሳደግ ቀጠለ፡፡ እንደ የድንጋይ ከሰልና ነዳጅ ዓይነት የኢነርጂ መልኮች በመጠቀምም ምድር ላይ ገናና ዝርያ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ በተጨማሪም አተሞች ውስጥ የተቋጠረ ኢነርጂንም በመጠቀም የኑክሌር ኢነርጂን ወደተግባር ማምጣቱን ጀመረ፡፡
ይህ የኢነርጂና የሰው ልጅ ሥልጣኔ የቀጥታ ቁርኝት ያሳየናል፡፡ ኢነርጂ ከሁሉም በላይ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ እጅግ ወሳኝ የሆኑ ሳይንሳዊ ምርምሮች በኢነርጂ እጥረት ምክንያት ወደቴክኖሎጂ ማሳደግ ባለመቻሉ መደርደሪያ /ሸልፍ/ ላይ የሚጠባበቁ ብዙ ናቸው፡፡ በእርግጥ ኢነርጂ ማንኛውም ነገር ወደፈለከው የመቀየር አቅም ያለው የቁስ ሌላኛው ገጽታ ነው፡፡
ከላይ የዘርዘርኳቸው የኢነርጂ ዓይነቶች ሁሉ ግን የተፈጥሮ ሥርዓት ማፍረስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፣ ተፈጥሮን የሚፃረሩ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ የኢነርጂ አጠቃቀም በተፈጥሮ አሠራር ላይ ጉልህ መዛባትን እንደሚፈጥርም የታወቀ ነው፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ፈልጎም ይሁን ሳይፈልግ ከበሰበሱ ተክሎች (ነዳጅና የድንጋይ ከሰል) ኢነርጂ መጠቀም ማቆሙ የማይቀር ነው፡፡
የመጭው ሥልጡን ማኅበረሰብ የሚጠቀመው ኢነርጂ ግን ከተፈጥሮ በቀጥታ የሚቀዳ ንጹሑ ይሆናል፡፡ ውኃ የተፈጥሮን ሕግ ለማክበር በራሱ ጊዜ ቁልቁል ሲወርወር፣ ንፋስ የሶላር ሲስተም መስተጋብራዊ የግፊት አቅጣጫ ተከትሎ ሽምጥ ሲጋልብ፣ ሙቀት ከተጨናነቀው ከርሰ ምድር ወደ ቀዝቃዛው የምድር ገጽታ ሽቅብ ሲወጣና የፀሐይ ጨረሮች ከፀሐይ ከርስ ተነስተው ወደ ህዋና ፕላኔቶች ሲሠራጩ… ተከታትሎ ኢነርጂ መቃረም የመጪው ዘመናይ ትውልድ ባህል ይሆናል፡፡ የንፋስ ኃይል፣ የፀሐይ ኃይል፣ የሙቀት ኃይል፣ የውኃ ኃይል ወዘተ የምንላቸው ጽንሰ ሐሳቦች ወደዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመግባታቸው ምክንያትም ይኼው ነው፡፡
የውኃ ኃይል ማመንጫ ቢዝነስ ደግሞ ልዩ ነው፣ ከሌሎች ፋይዳዎቹ ባሻገር የግድብ ቢዝነስ አንድ ብር አውጥተህ ሚሊዮን ብሮች የምትሰበስብበት ቢዝነስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስቱም አገሮች የሚሰጠው ጥቅም ቢሰላ ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ይሆናል፡፡ ግብፅና ሱዳን ከመሠረተ ልማት ደኅንነት፣ ከኢነርጂና ከግብርና መስኖ ሥራዎች ብቻ እስከ 5.8 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያገኙ አያሌ ጥናቶች ያሳያሉ፣ በአጠቃላይ ከህዳሴው የሚያገኙት ጥቅም ቢሰላ ደግሞ ከዚህ የበለጠ እንደሚሆን ማየት ይቻላል፡፡
በመሆኑም የህዳሴ ግድብ ኃይል የማመንጨት አቅም ከአማካዩ በብዙ እንዲበልጥ ተደርጎ መሠራቱ ችግር አልነበረውም፡፡ በእርግጥ ለስምንት ወራት አካባቢ የማይሠሩ ተርባይኖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የኃይል ማመንጫው አመራር ወረቀት ላይ ተሰልቶ ባለቀ ሳይንሳዊ እቅድ ላይ ከተመራ በዓመት ውስጥ ከፍ ያለ ኢነርጂ የማመንጨት ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ የግድቡ ቁመት ሳይለወጥና ግንባታው በተገባደደበት እዚህ ግባ የማይባል የገንዘብ መጠን ላይ ዒላማ አድርጎ የግድቡን ኃይል የማመንጨት አቅም መቀነስ ትክክል ነው ለማለት ይከብዳል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢነርጂ በእጅጉ እየናረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሕዝብ ቁጥርና ቴክኖሎጂ በጨመረ ቁጥር ኢነርጂ እየተወደደ መሄዱ የሚጠበቅ ነው፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ሁሉ ያለኢነርጂ ጥቅም ላይ ማዋል የማይታሰብ ነውና፡፡ የአዳጊ አገሮች የኢነርጂ ፍላጎት ዕድገት ደግሞ ካደጉት አንፃር እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አሁንም ህዳሴ ግድብ ወደሥራ ሲገባ የውኃ አለቃቀቁ እንዴት ቢቀናጅ ነው ከፍተኛ የኢነርጂ መጠን ማግኘት የምንችለው የሚለው ላይ ዝርዝር ጥናትና ተሞክሮ ያስፈልጋል፡፡ የሦስቱም አገሮች ድርድር በኢትዮጵያ በኩል ሲታይም በማዕከላዊነት እዚህ ነጥብ ላይ ያተኩራል፡፡
ግብፆች ለድርድር ያቀረቡት የውኃ ሥርዓት ሞዴል ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድብ 1,600 ሜጋዋት በቋሚነት እንደምታመነጭ፣ የግብፅ ዓመታዊ የውኃ ድርሻ (ተፈጥሮ ካልገደበው በስተቀር) ከ55.5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ሊያንስ እንደማይችል፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በዓመት ውስጥ ከፊንጫና ከጣና ዙሪያ ከ1.1 እስከ 1.7 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ እንደምትጠቀም፣ ሱዳኖች ደግሞ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ድረስ እንደሚጠቀሙ መሠረት ያደረገ ሞዴል ነው፡፡ ይህ ከ2011 ዓ.ም. ወዲህ ያሉ የግብፃውያኑ የፍሰት ሥርዓት ሞዴሎች ሁሉ በዚህ መልኩ የተቃኙ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. 1959 የሱዳንና የግብፅ የናይል ስምምነት ላይ ከ55.5 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውኃ የግብፅ ድርሻ ሲሆን አሁንም ትልቁ ጥረትዋ ይህንኑ ለማስጠበቅ ነው፡፡
ከግብፆች ፍላጎት ጋር የሚሄድ፣ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አመራር ከጥቂት ወራት በፊት ሚዲያዎች ላይ ያቀረቡትና በፕሮጀክቱ ድረ ገጽ የተለቀቀው የዓባይ ዓመታዊ ፍሰት በሰከንድ 1,547 ኪዩቢክ ሜትር ድረስ ዝቅ ያደረገው በግድቡ በዓመት ውስጥ የሚያመነጨው አማካይ የኃይል መጠን 16,153 ጊጋጋዋት (1,869 ሜጋዋት በሰዓት) አድርገው በማስቀመጣቸው ነበር፡፡ ይህ አኃዝ ከግብፆች የተፋሰስ ሞዴል የተቃኘበት አኃዝ ጋር ተቃራራቢ (1,600 ሜጋዋት) ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የህዳሴ የማመንጨት አቅም 6,450 ሜጋዋት በሰዓት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከላይ በግርድፉ በተገለጸው መሠረት ዝቅተኛው 1,900 ሜጋዋት በሰዓት ነው፣ ዓመታዊ አማካይ ሊሆን የሚችለው ከነዚህ አኃዞች አማካይ በላይ ነው፡፡ በመሆኑም ዓመታዊ አማካይ በሚል እስከ 1,869 ሜጋዋት በሰዓት ማውረድ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ከሚደረገው ስምምነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ የግድቡ ከፍተኛው የማመንጨት አቅም፣ ዝቅተኛ ከፍተኛው የማመንጨት ሁኔታና አማካይ ዓመታዊ የማመንጨት ስሌት መከለስ አለበት እላለሁ፡፡
የተፋሰሱ ቀጣይ ፈተናዎች
የተለመዱ የአየር ንብረት ምልክቶች ከውኃ ምንጮች ተደራሽነትና አስተማማኝነት ጋር በተያያዘ በመጪው አሠርት ውስጥ በአየር ሁኔታ ላይ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ በሙቀት መጨመርም ሆነ በዝናብ ተለዋዋጭነት ላይ የሚኖረው የአየር ንብረት ተፅዕኖ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በናይል ወንዝ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በእርግጥ የአየር ሙቀት ጨምሯል፡፡ ያም ሆኖ በዝናብና በወንዙ የፍሰት ሁኔታ ላይ በመጠን፣ በወቅትም ሆነ በለውጥ አቅጣጫ ዙሪያ አገሮቹ መግባባት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች ለመገመት አዳጋች ቢሆኑም በአሁኑ ጊዜ ያለው የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውኃ በመሙላትም ሆነ በግድቡ አግልግሎት አሰጣጥ መርህና አስተዳደር ዙሪያ የሚኖረው ተፅዕኖ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ነው፡፡ በተጨማሪም እንደሁኔታው መለዋወጥ የሚችሉና በቀላሉ የሚተገበሩ ስትራቴጂዎችን የሚጠቁሙ ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ፡፡
ኢትዮጵያ የማገዶ ፍጆታዋ በሌላ የኢነርጂ ዓይነት መለወጥ ከሚያስችላት ፍጥነት በላይ እየተጠቀመች በመሆኗ፣ የከፍተኛ ቦታዎች ደኖች መራቆት ተጠናክሮ መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ የደኖች መራቆት ደግሞ የአፈር መሸርሸርና የአፈር ለምነት ማሽቆልቆል እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረግ መቀጠሉም የማይቀር ነው፡፡ ይህ ደግሞ የግብርና ምርቶችን እንዲቀንስ ምክንያት ይሆንና ለግብርና ሥራ አዳዲስ የደን ምንጣሮ ዙሮች ይቀጥላሉ፡፡ በመሆኑም በገጠር ቀበሌዎች የሚደረገው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የከፍተኛ ቦታዎች የደን መራቆትና የመሬት መሸርሸር እንዲቀንስ ወሳኝ ሚና ይጨወታል፡፡
ከከፍተኛ ቦታዎች እየተጠራረገ የሚወርደው ደለል በግድቡ የአገልግሎት ጥራትና ዕድሜ ላይ የሚኖረው የሥጋት ደረጃ በውል የታወቀ አይመስልም፡፡ በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ዙሪያ ባለፉት አሠርታት ውስጥ የነበረው የመሬት አጠቃቀም፣ በተለይ ደኖችን የማራቆትና የእርሻ መሬትን የማስፋፋት ተግባራት በዓባይ ወንዝ የደለል ጫና ላይ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህን የደለል ጫና በተፋሰሶችና ተራሮች ልማት በኩል መቀነስና ማስቆም የሚቻል ቢሆንም እስካሁን በፖሊሲ የተደገፈ አካሄድ አለመኖሩ አደጋው እየተባባሰ ይገኛል፡፡ (በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥር 2012 ዓ.ም. ውስጥ በፍትሕ መጽሔት “የተራሮች እምባ” በሚል ሰፊ ሀተታ የያዘ አርቲክል ማሳተሜ ይታወቃል፡፡) በመሆኑም በግድቡ የላይኛው ተፋሰስ ዙሪያ ዘመናዊ የአፈርና ደን ጥበቃ ዘዴዎችን መጠቀም ወደ ግድቡ የሚጓጓዘው የደለል ጫናን ስለሚቀንሰው ግድቡ በአገልግሎት ጥራትም ሆነ በአገልግሎት ዕድሜ አስተማማኝ ያደርገዋል፡፡
አሁን ላይ ሱዳን በ1959 ላይ ከተቀመጠላት የውኃ ድርሻ አኳያ ያነሰ የውኃ መጠን እንደምትጠቀም ይታወቃል፡፡ የሱዳን የዕድገት ዕቅድ፣ የአየር ንብረት ለውጥና የህዳሴ ግድብ እውነታ ጋር ተያይዞ በተፋሰሱ ላይ ያለው አሰላለፍ በፍጥነት የሚለወጥበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ ከተደጋጋሚ ጥረት በኋላ ውሳኔዎች የአንድ ወገን ሆነው ብቅ ሲሉ ደግሞ ተጨማሪ ግፊት በጉዳዩ ላይ ለመፍጠር ያመቻል፡፡ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በአንድ ወገን ውሳኔ ወደ ተግባር ባይመጣ ኖሮ ግብፅና ሱዳን ጋር በዓባይ ወንዝ ዙሪያ መወያትም ሆነ መደራደር እንደማይቻል ልብ ይላል፡፡
ምንም እንኳን በህዳሴና በአስዋን መካከል ያለው የውኃ ጉዞ የ30 ቀናት ቢሆንም፣ የትብብር ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ወይም ከፍተኛ የውኃ ፍሰት በሚኖርበት ጊዜ የሁለቱም ግድቦች የአግልግሎት አቅም ለመጨመር እንዲሁም እንደ የመስኖ ግብርናና ጎርፍን የመቆጣጠር ዓይነት ሌሎች ሥራዎችንም ለማጠናከር ያግዛል፡፡
የሚገርመው በሁሉም የተፋሰሱ አገሮች የተፈረመ የውኃ መጋራት ስምምነት አሁን ድረስ አለመኖሩ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ብትን አካሄድ ሌላ ጉድ ከመውለዱ በፊት በፍጥነትና በጥንቃቄ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት መደረግ አለበት፡፡ በናይል ተፈጥሯዊ የፍሰት ሁኔታ 97 ኩዩቢክ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መጠን ያለው ውኃ አስዋን ላይ በዓመት ውስጥ እንደሚገባ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ 84 ኩዩቢክ ኪሎ ሜትር እየተባለ ይገለጽ ከነበረው አንፃር የበለጠ ነው፡፡
የተፋሰሱ አገሮች ስለናይል ውኃዎች ጭብጦችንና መረጃዎችን የሚጋሩበት መርሆዎች እንዲኖሩ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ዓለም አቀፋዊ የውኃ ትብብር መርሆችን መተግበር ምክንያታዊና ሚዛናዊ የተፋሰስ አጠቃቀም ላይ መበረታታት እንዲመጣ ስለሚያግዝ ጥረት ቢደረግ ውጤት ይኖረዋል፡፡
በአጠቃላይ በዓባይ ወንዝም ሆነ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥርት ያሉ ጭብጦችና መረጃዎች (Data) እንዲኖር ጥረት ቢደረግ ለሁሉም የሚበጅ ነው፡፡ የታሪካዊ መረጃዎች ተደራሽነትና ጥራት ላይ ውስንነት ቢኖርም ወይም ከአገር አገር የተለያዩ ቢሆኑም፣ በወቅታዊ የአየርና የውኃ ሁኔታ ነውጦች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤንና ሥሌትን ለማሻሻል በግልጽነት መረጃን መጋራት የሚያስችል የተቋማዊ ማዕቀፍ አስፈላግነት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ማዕቀፍ የተሻለ ውጤታማ የውኃ ሀብት አስተዳደርና ትግበራ በቀጣናው እንዲሰፍንና በተፋሰሱ አገሮች መካከል እውነታን መሠረት ያደረገ ውይይት እንዲኖርና እንዲሳለጥ ያግዛል፡፡
የቀጣናው አገሮች ሳተላይት ላይ መሠረት ያደረጉ ጭብጦችን፣ መረጃዎችንና ውጤቶችን መጠቀም የሚያስችል ሁኔታን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ወጥና ዘላቂ የአሠራር ዘዴን ያስገኝላቸዋል፡፡ የሳተላይት መረጃዎችንና ከቦታው በየጊዜው የሚለቀሙ መረጃዎችን በአንድ ላይ በማቀናጀት የውኃው መጠን፣ ድርቅንና የጎርፍ አደጋዎችን ለመቆጣጠር እንደ ተለዋጭ ምንጮች ሆነው ያገለግላሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት የውኃ ፖለቲካ የተወጠረ ቀጣና ውስጥ፣ የሳተላይት መረጃን እንደግብዓት መጠቀም በአገሮቹ መካከል መተማመንን ያመጣልና ችላ የሚባል አይደለም፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተፋሰሱ አገሮች በግጭትና በትብብር መካከል ሲዋዥቁ የናይል ተፋሰስን ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል፡፡ የተቀናጀና የተባበረ ማዕቀፍ ኖረም አልኖረም፣ የቀጣናዊ እቅድ ግልጽነት እስካለ ድረስ በተፋሰሱ ዙሪያ የወደፊት ዕድገት መነሻ የሚሆን ወለል መፈጠሩ አያጠያይቅም፡፡ ምንም ይሆን የጋራ ጥቅሞች የማደግ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በእነዚህ ጥቅሞች ላይ የጋራ ግንዛቤ ሲፈጠር ደግሞ የበለጠ ጠንካራ ትብብርና ፈቃድ እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ ወጣም ወረደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ “የትብብር ሐውልት” የመሆን እድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ታላቁ ህዳሴ ግድብ በአንድ ወገን ውሳኔ ብቻ ዓለም አቀፍ ወንዝ ላይ እንደመገንባቱ ሥጋትና ተስፋ ማሳደሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች የውኃ እጥረትና አጠቃላይ የሕዝባቸው ኑሮ ላይ ያጋጥማል በሚል ሥጋት መኖሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ብሔራዊ ስኬት ለማስመዝገብ ከተፈለገ ቀጣናዊ የትብብር አማራጭ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ በተፋሰሱ አገሮች ጠንካራ ዝምድና ላይ ማተኮሩ ለኢትዮጵያ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ ጉዳዩን ከግብፅ ጋር ብቻ ማገናኘቱ አያዋጣም የሚል እምነት አለኝ፡፡
አፍሪካ ውስጥ ኢነርጂ ካልለሙት ዘርፎች ውስጥ ቀዳሚው ነው፡፡ ከሰሀራ በታች ባሉት ውስጥ ደግሞ ኢነርጂ ገና ያልተነካ ዘርፍ ሊባል ይችላል፡፡ እ.ኤ.አ. የ2015ቱ የአፍሪካ የልማት ዕድገት ሪፖርት እንደሚያሳየው ከደቡቡ አፍሪካ ውጭ ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮች ሁሉ ከፍተኛ የኤሌክትሪክሲቲ እጥረት እንዳለባቸውና አማካይ ዓመታዊ የግለሰብ የኃይል ፍጆታው 162 ኪሎዋት ሰዓት ብቻ መሆኑን ያትታል፡፡ ይህ ከ7,000 ኪሎዋት ሰዓት ዓመታዊ የዓለም አቀፉ የኃይል ፍጆታ አኳያ ሲታይ በ98 በመቶ ያነሰ በመሆኑ በአስደንጋጭ ደረጃ ዝቅተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የኢትዮጵያ የኃይል ፍጆታም የባሰ ዝቅ ብሎ እናገኛዋለን፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት የዓለም ባንክ ሪፖርት እንዳስቀመጠው የአንድ ኢትዮጵያዊ ዓመታዊ የኤሌክትሪሲቲ ፍጆታ 57 ኪሎዋት ሰዓት ብቻ ነው፡፡ ይህ ሪፖርት የኢነርጂ እጥረት አኅጉሩ ካለው የኢነርጂ እምቅ አቅም አኳያ ምን ያህል በተቃራኒ እንደሚገኝም አስፍሯል፡፡ ይህንን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡
ትልቅ የውኃ ክምችት ምን ያህል ከአንዲት አገር ዕድገት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ሁሉም ደሃ አገሮች ከሕዝብ ብዛታቸው የማይመጣጠን የመጨረሻው ዝቅተኛ የውኃ ክምችት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ለእነዚህ አገሮች የውኃ ክምችትን ማሻሻል ማለት የኢነርጂ ልማታቸው ከማሻሻሉም በላይ በሁሉም ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ያለው አስተዋጽኦ ማሻሻል እንደ ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀጣናው ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ግድቡን ውኃ በመሙላት ሒደት ወቅት ግብፅ መጠነኛ የኢኮኖሚ መቀነስ ልታስተናግድ እንደምትችልና ከዝናብ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ተጨማሪ ጉዳቶች ሊያስከትል እንደሚችል አያሌ ጥናቶች ይጠቁማል፡፡
የህዳሴው ደራሽ ኢነርጂና የተለያዩ የዝናብ ሁኔታዎችን አጣምሮ በመውሰድ፣ የህዳሴው ግድብ አዎንታዊ ተፅዕኖ በሙሌቱ ጊዜም ሆነ ከሙሌት በኋላ በቀጣናው ጂዲፒ ላይ እስከ 5.5 እስከ 8.8 በመቶ ጭማሪ እንደሚያስገኝ የ2008 ዓ.ም. ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የህዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ላይ በሚፈጥረው ተጨማሪ የፍሰት መጠን ሱዳንና ግብፅ ከግብርናና ከኢነርጂ ምርት የሚያገኙት የመጨረሻው ትንሹ ዓመታዊ ጥቅማቸው ከ4.9 እስከ 5.6 ቢሊዮን ዶላር ይጨምራል ይላሉ የ2008 እና የ2007 ዓ.ም. ጥናቶች፡፡
ከላይኛው ተፋሰስ እየተናደ የሚወርደው የደለል ክምችት በዓመት 131 ሚሊዮን ቶን ይጠራቀማል፡፡ ይህ ደለል ህዳሴ ግድብ ውስጥ ሰምጦ ይቀራል፡፡ ይህ ደለል በህዳሴው ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ በጥንቃቄ መጠናት አለበት፡፡ የደለል ጉዞ ህዳሴ ላይ በመቋረጡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ይኖረዋል፡፡ የደለል መጠን ሲቀንስ የሱዳንና የግብፅ ግድቦች ዕድሜ ይጨምራል በመስኖ ቦዮች ይጠራቀም የነበረው ደለልም በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በሱዳን በኩል በቀጥታ ደለል ለማጽዳት ይውል የነበረው 50 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ማዳን ትችላለች፡፡ በተመሳሳይ ደረጃ የመስኖ ቦዮችም የተሻለ ውጤታማ የሚሆኑበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የታችው ተፋሰስ አገሮች የእርሻ ማሳዎቻቸው ለምነት በሒደት የመገርጣትና ምርት የመቀነስ ዕድል ይኖረዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡ ጸሐፊው ሳይንሳዊ ነክ ጽሑፎች ጸሐፊና የምሕንድስና አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡