ካለፉት ሁለት አሠርታት ወዲህ የኮሮና ቫይረስ የተለያዩ ዝርያዎች በተለያዩ ወቅቶች እየተከሰቱ ሰዎችን እያጠቁ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል በ2003 ዓ.ም. ተከስቶ ለተወሰነ ጊዜ አሸብሮ የጠፋው ‹‹ሳርስ››፣ ከርሱም ቀጥሎ የመጣው ‹‹መርስ›› እና ለዓለም ሥጋት የሆነው የአሁኑ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ይገኙበታል፡፡ የቫይረሶቹ መነሻም ከእንስሳት ወደ ሰው (ዞኖቲክ ትራንስሚሽን) ነው፡፡
የሃሌ ሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል መሥራችና ባለቤት ጌታቸው አደራዬ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፣ የአብዛኞቹ መተላለፊያ መንገዶች በመተንፈሻ አካል በሳልና በማስነጠስ ሲሆን፣ በንክኪም ይተላለፋል፡፡ ሳርስና መርስ የተባሉት ቫይረሶች በፍጥነት ተደርሶባቸው ቶሎ የከሰሙ ሲሆን፣ ኮሮና ቫይረስ ግን ልዩ የሚያደርገው የሥርጭት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ150 አገሮች በላይ ማዳረሱ ነው፡፡
ፍጥነቱን ለማቆም በጣም የሚያስቸግር መሆኑን ገልጸው፣ ኮሮና ቫይረስ ከያዛቸው ሰዎች ውስጥ ሕይወታቸው የሚያልፉ ወይም ጽኑ የሳምባ ችግርና ኒሞንያ፣ የመተንፈሻ አካልና የውስጥ አካል (ኦርጋን) ድክመት፣ ኩላሊታቸው የሚደክምባቸው በጣም ጥቂቶቹ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
የሚሞተውም ሰው ከአራትና ከአምስት በመቶ በላይ እንደማይበልጥ፣ ይኼ በመቶ ሲሰላ ትንሽ እንደሚመስል፣ ትልቁ ችግር ግን ከመቶ ሰዎች መካከል አራቱ፣ እንደሆነና የሚያስፈራውም ይኸው እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡
‹‹አንዳንዴ ምንም ሳይታወቀን ቫይረሱን ተሸክመን እንሄዳለን፣ ብዙ ጊዜ በሳል መልክ ይከሰታል፡፡ ጠንከር ያለ ጊዜ ትኩሳትና ትንፋሽ ማጠር ይመጣል፡፡ በጣም የከፋ ጊዜ ደግሞ የውስጥ አካላት ድክመት ይከሰታል፡፡ ከዚህም ወደ ልዩ ክትትል ክፍል መግባት ይመጣል፣ ሞትም ሊከሰት ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ ለአንድ በሽታ ፈውስ የሚሆን መድኃኒት በሳይንሳዊ መንገድ ለማግኘት ቢያንስ ስምንት ዓመት ይፈጃል፡፡ ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ግን ቀደም ብለው የነበሩ የቫይረስ መድኃኒቶችን መጠቀም ወይም ትንሽ የሞዴል ለውጥ በማድረግ ለማምረት የሚያስችል ጥናት በጃፓንና ቻይና በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ቃለ አብ ደረጀ (ዶ/ር)፣ የኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት ሆስፒታሉ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየ፣ በዚህም ዝግጅት 11 ባለሙያዎች ያሉበት ኮሚቴ እንዲዋቀርና ራስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ሲያስገቡ እንደቆዩ፣ የትኩሳት መለያ ዕቃዎችን፣ ተገቢ የሆኑ የመከላከያ አልባሳትን፣ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችንና ሳኒተራይዞችን ሲያሟሉ እንደቆየ ተናግረዋል፡፡
በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ ከታወጀ በኋላ ግን ሆስፒታሉ ከመንግሥት ጎን በመቆም የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ጥረት አድርጓል፡፡
በመጀመርያ የተደረገው ነገር ቢኖር ወደ 400 ለሚጠጉ የሆስፒታሉ ሠራተኞች በቫይረሱ ዙሪያ ያተኮረ አጠር ያለ ሥልጠና መሰጠቱ፣ ራሳቸውን መከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ለሁሉም ሠራተኛ ማዳረሱ፣ ለአገልግሎት ለሚመጡ ታካሚዎቹና ሌሎችም የኅብረሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱ ከጥረቶቹ መካከል ተጠቃሾች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡