Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተቋረጠውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ ጫና እንዳይፈጠር ማሳሰቢያ ተሰጠ

የተቋረጠውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ ጫና እንዳይፈጠር ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

የ12ኛ እና የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች መውሰጃ ቀን ይከለሳል

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን አስመልክቶ በጤና ሚኒስቴር መግለጫ ከተሰጠ በኋላ፣ ትምህርት ቤቶች ከመጋቢት 7 እስከ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በመዘጋታቸው የሚፈጠረውን የትምህርት ጊዜ ክፍተት ለማካካስ፣ ተማሪዎች ላይ ጫና እንዳይፈጠር ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታትና ጥንቃቄ ለማድረግ እንዲቻል፣ ከዐፀደ ሕፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች ለ15 ቀናት እንዳይማሩ መወሰኑን ተከትሎ የሚፈጠረውን ጫና አስተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች መውሰድ እንደሚገባቸውም ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በኮሮና በሽታ ምክንያት ለሁለት ሳምንት ትምህርት በመቋረጡ፣ በእነዚህ ጊዜያት በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በታዳጊ ሕፃናት ተማሪዎች ላይ መጫን እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ሞጁሎች አዘጋጅተውና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ተማሪዎቻቸውን እንደሚያገኙ፣ ይህ ማለት ግን ሁሉንም ማኅበረሰብ እንደማይወክል፣ ትምህርት ሲከፈትም መደበኛው የትምህርት ጊዜ እንደሚራዘም ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የባከኑ የትምህርት ጊዜያት የሚካካሱበት፣ ትምህርት የሚጀመርበትና የሚዘጋበትን ጊዜ የቫይረሱን ሥርጭት ዓይቶ እንደሚወስን፣ በትምህርት ሚኒስቴር ቴሌቪዥን ጣቢያም ሆነ በሌሎች ቴክኖሎጂዎች ትምህርት እየተላለፈ ነው ተብሎ የሚታጠፍ የትምህርት ጊዜ እንደማይኖርም አክለዋል፡፡

የ12ኛ እና የ8ኛ ብሔራዊ ፈተናዎች ከዚህ ቀደም ቀን ተወስኖላቸው የነበረ ቢሆንም፣ ዳግም እንደሚከለሱ ዶ/ር ጌታሁን አስታውሰው፣ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በኦንላይን ለመፈተን ከአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ጋር እየሠሩ መሆኑን አክለዋል፡፡

የተማሪዎች ኮምፒውተር የመጠቀም ችሎታ ከፍተት ሊኖረው እንደሚችል ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና  የሞዴል ፈተናን በኦንላይን በመስጠት ቀድሞ እንደሚታይም ተናግረዋል፡፡

ከ42,000 በላይ የትምህርት መስጫ ተቋማት በቅድመ መደበኛ፣ በጎልማሶች ትምህርት፣ በመጀመሪያና በሁለተኛ ትምህርት ቤቶች ከ23 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እስካለፈው ሳምንት ድረስ በትምህርታቸው ላይ የነበሩ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ቤቶች ሲመለሱ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ መምህራንና ትምህርት ቤቶች ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ዝግጅቶች  ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች በሁለት ሳምንት ጊዜው በቤቶቻቸው ሆነው ጤንነታቸው ለኮሮና ቫይረስ እንዳይጋለጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ ትምህርታቸውን ለማጥናት ተጨማሪ ጊዜ እንደሆነ በመገመት፣ መጻሕፍትና ደብተሮቻቸውን ለማጥናት እንዲጠቀሙበት፣ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የሚያገኙ ተማሪዎች በትምህርት ሚኒስቴር የቴሌዥን ጣቢያ ከክልሎች በሬዲዮ የሚተላለፉትን ትምህርቶች እንዲከታተሉ ጠቁመዋል፡፡

የተማሪዎች ወላጆች፣ ልጆቻቸው እንዲያጠኑና መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ዳግም ለሚከፈተው የትምህርት መርሐ ግብር እንዲዘጋጁ እንዲያግዟቸው፣ ገጠራማና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ያሉ ወላጆች ትምህርት  በሚከፈትበት የመጀመሪያው ቀን ልጆቻቸውን መልሰው እንዲልኳቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መምህራን፣ ትምህርት ቤቶች በሚከፈቱበት ጊዜ ትምህርት የተቋረጡባቸውን ሁለት ሳምንታት ለማካካስ በተማሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ጫና እንዳይፈጥሩ፣ ይህ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች የሚመለከት ቢሆንም፣ በተለይ በግል ትምህርት ቤቶች በአፅንኦት እንዲተገበር አሳስበዋል፡፡

ተማሪዎች ተመልሰው ሲመጡ በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመስጠት ላይ ያሉ የተለያዩ ጥንቃቄዎች በተለይም ከግል ንፅህና አጠባበቅ አኳያ በየትምህርት ቤቶች በቋሚነት እንዲተገብሩም አውስተዋል፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በትምህርት ሚኒስቴር አንድ ዓብይ ኮሚቴና ሁለት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው አጠቃላይ ሒደቱን እየመሩ ነው፡፡ አደረጃጀቱ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች እስከ ትምህርት ቤት ድረስ እንዲዘረጋም መመርያ ተላልፏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...