በሔለን ተስፋዬ
በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚውል የንፅህና መጠበቂያ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ማሰባሰብ ተጀመረ፡፡
በከተማዋ ወጣቶችና በበጎ ፈቃደኞች የተቋቋመው ኮሚቴ በመስቀል አደባባይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በተገኙበት የንፅህና መጠበቂያ ማሰባሰቡን በይፋ ሲጀምር፣ ቲቲኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ለግሷል፡፡
ለአንድ ሳምንት የሚሰባሰበውን የንፅህና መጠበቂያ በጎዳና ላይ፣ በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለሚረዱ ሰዎች፣ በማረሚያ ቤቶች ለሚኖሩና መሸመት ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚውል መሆኑን ከአስተባባሪዎቹ አንዱ አቶ ያሬድ ሹመቴ ተናግረዋል፡፡
እኚህን የማኅበረሰቡ ክፍሎች የኮሮና ቫይረስን እንዲከላከሉ መርዳት ካልተቻለ ሥርጭቱ ሊሰፋ ይችላል የሚሉት ሌላው በጎ ፈቃደኛ አቶ መሐመድ ካሳ፣ ቫይረሱ እርስ በርስ ተረዳድተን ካልተከላከልን እጅግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
አቶ መሐመድ እንዳስረዱት ማኅበረሰቡ በነጠላም ሆነ በብዛት የንፅህና መጠበቂያ የመግዛት አቅም ለሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማገዝ ቫይረሱን በጋራ መከላከል ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን በማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡን ቅርርቦሹን ለመግታት በመዲናዪቱ በተለያዩ ቦታዎች ግንዛቤ እያስጨበጡ መሆኑን አቶ ያሬድ አስረድተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስን ቀድሞ ለመከላከል ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በተቻለው መጠን ሰዎች የበዙበት ቦታ ባይሄድ፣ በሰዎች መካከል ክፍት ቦታ በመተው ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡