Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሸቃጮች ገበና

የሸቃጮች ገበና

ቀን:

የኮሮና ኖቭል ቫይረስ በኢትዮጵያ ተገኝቷል ተብሎ በጤና ሚኒስቴር ከተገለጸ ሳምንት አስቆጥሯል፡፡ ሳምንቱ ኢትዮጵያውያን በተለይም በከተማ የሚኖሩትና ስለቫይረሱ አስከፊነት የተረዱት ለነፍሳቸው የተጨነቁበት ለሥጋቸው የዋተቱበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀን እንኳን ሳይፈጅ የሚያልፍ ችግር ሲያጋጥም በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ዋጋ በማናርና በመደበቅ ቀድሞውንም ለተካኑት ነጋዴዎች ፊሽታን የፈጠረ ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን ይረዳዳሉ፣ ይተጋገዛሉ እየተባለ ሲነገር የነበረው ትርክት ልብ ወለድ ነው ወይስ እውነት? ብሎ ግራ እስኪያጋባ ከመድኃኒት አቅራቢዎች እስከ ምግብ ሸቃጮች የኅብረተሰቡን ድንጋጤ ገንዘብ ለማጋበስ ሲጠቀሙበት ተስተውለዋል፡፡

የተፈጠረውን ችግር በጋራ ለመወጣትና የቫይረሱ ሥርጭት እንዳይጎላ አብሮ በመሥራት ሌሎች አገሮች ተፍ ተፍ ሲሉ፣ በኢትዮጵያ ግን በተለይ በነጋዴዎች ዘንድ የተስተዋለው አልጠግብ ባይነትና ጭካኔ ነበር፡፡

ችግር በተከሰተ ቁጥር ሸቀጦችን ማከማቸትና መደበቅ አልያም በናረ ዋጋ መሸጥ ለኢትዮጵያውያን ሸማቾች ብርቅ ባይሆንም፣ አሁን የተከሰተው ኮሮና ኖቭል ቫይረስ ግን ከዚህ ቀደም ከገጠሙ ችግሮች የተለየ  ነው፡፡ የትኛውንም የፍትሕ አካል በማሰማራት አንዱን ከሌላው ጥቃት ለማትረፍ ዕድል የማይሰጥ፣ ደሃ ከሀብታም የማይለይ አገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ አደጋ መሆኑን ያልተገነዘቡና ብቻቸውን ያከማቹትንና በክፋት የሰበሰቡትን ለመብላት የሚችሉ የመሰላቸው፣ የተደናገጠውንና ከችግሩ ለመውጣት ያስፈልጉናል ያሏቸውን ዕቃዎች ለመግዛት ላይ ታች ሲዋቱ የነበሩት ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ፈጽመዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ወረርሽኝ ሲከሰት እንኳን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ያደጉት አገሮችም ቢሆን ይፈተናሉ፡፡ ቫይረሱን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እጥረት ሊያጋጥምም ይችላል፡፡ ሆኖም በዚህ ወቅት ሰው ሠራሽ እጥረት መከሰቱት አልነበረበትም፡፡ ኢትዮጵያውያን ስንሰፈርበት የነበረውን የመተሳሰብ ሚዛን አመጽ ያደረገ ነው፡፡

ይህ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከዓመታት በፊት ጨው የጫኑ መኪኖች መንገድ ተዘግቶ ቆመዋል ሲባል የተስተዋለ ችግርም ነው፡፡ በወቅቱ ሸማቹም አሸማቹም አለቅጥ ተስገብግቦ አንድ ኪሎ ጥሬ ጨው ይሸጥበት ከነበረው ከአሥር ብር ያነሰ ዋጋ፣ እስከ 50 ብርና ከዛም በላይ ሲሸጥ መታዘባችን የቅርብ ዓመት ትውስታ ነው፡፡ ይህ ወቅት ነጋዴው ዋጋ አንሮ ከመሸጥ ባለፈ ክምችት የያዘበት፣ የደበቁት ሸማቹም ሕይወት ያለጨው የማይገፋ ይመስል ከገበያ ገበያ ከሱቅ ሱቅ የተንከራተተበት ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በጨው ያየነው ዛሬ ላይ ከፋርማሲ በሚገዙት ላይ ጭምር ተስተውሏል፡፡ ልዩነቱ የቀደመው ይህንንም ያህል ለማያሰጋ የምግብ ግብዓት መሆኑና የአሁኑ ሕይወትን ለማትረፍ ከቅድመ ጥንቃቄ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊትም ሆነ ከገባ በኋላ ስለቫይረሱ ገዳይነት እንዲሁም በትንፋሽና ንክኪ ምክንያት በፍጥነት ሊዛመት መቻሉና ከኢትዮጵያ ቀድመው በቫይረሱ የተጠቁ አገሮች የሰዎችን  እንቅስቃሴ በከፊልና በሙሉ ማገዳቸው፣ በኢትዮጵያም ይህ ሊመጣ እንደሚችል ሸማቹም ሆነ ነጋዴው በመገመቱ ቫይረሱ ኢትዮጵያ ገባ ተብሎ ሰዓት እንኳን ሳይሞላ ነበር የአዲስ አበባ ገበያዎች በሸማች የተጥለቀለቁት፡፡

ከፋርማሲ ፋርማሲ እያቀያየሩ አልኮል፣ ሳኒታይዘርና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ የሚጠይቁትም በርካቶች ነበሩ፡፡ ዕድል ቀንቷቸው የገዙት ደግሞ ለወትሮው እንደየአካባቢው ከአምስት እስከ ሰባት ብር ይሸጥ የነበረውን ማስክ ከ20 ብር እስከ 50 ብር፣ ሳኒታይዘር ግማሽ ሊትር ቀድሞ ከነበረው ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ 300 ብር፣ አልኮል አንድ ሊትር ከተገኘ 150 ብር ለመግዛት ተገደዋል፡፡ ብዙዎቹ ፋርማሲዎችና ሱፐር  ማርኬቶቹ ደግሞ እነዚህ ዕቃዎች እንደሌላቸው በጽሑፍ ለጥፈው ነበር፡፡

በዕለቱ ቅኝት ስናደርግ ያገኘናቸው ሸማች ለራሳቸው ብለው አልነበረም በየፋርማሲው የተንከራተቱት፡፡ ልጆቻቸው ሰኞ ትምህርት ቤት ሲመጡ ሳኒታይዘርና አልኮል ይዘው እንዲመጡ የሚል ወረቀት ስለተላከላቸው ይህንኑ ፍለጋ ነበር፡፡ እነዚህን ቢያጡም፣ አንድ ማስክ በ20 ብር ሒሳብ ሆኖ አምስት መግዛታቸውን ነግረውናል፡፡

በአንዳንድ ፋርማሲዎች እንደ ገዢ ሆነን ያገኘነው መረጃ፣ በሽታው ገብቷል ተብሎ ከመነገሩ በፊት በግለሰብ መኪና ከየፋርማሲው ሳይኒታይዘር፣ አልኮልና ማስክ በብዛት እየተገዛ ይጫን እንደነበር፣ ከአምራቾች ጭምር በገፍ የሚወስዱ እንደነበሩ ሰምተናል፡፡ ማስክ እንዳለ ካወቅንበት ፋርማሲ ወረፋ ይዘን ባለንበት ወቅት ከፊት የነበሩ ግለሰቦች አንዳንዶች 20 አንዳንዶች 30 እየገዙ ሲወጡ፣ የተሠለፍነው ሳንዳረስ በብዙ ለምን ቁጥር ትሸጣላችሁ ብለን ነበር፡፡ የሚገዙት ግን መልሳቸው ‹‹ለቢሮ ነው›› የሚል ነበር፡፡

ለሸመታ ወጥተው ያነጋገርናቸው ሰዎች ብዙዎቹ በፍርሃትና ጭንቀት የተሸበቡ ነበሩ፡፡ የሚያደርጉት ግራ የገባቸው፣ የፈለጉትን ባለማግኘታቸው የተደናገጡም ዓይተናል፡፡ በየሱፐርማርኬቱ ደግሞ ለወትሮው ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሸማቾች ሲራኮቱ ነበር፡፡

አብዛኞቹ በረኪና፣ ፈሳሽ ሳሙና ላይፍ ቦይ ደረቅ ሳሙና፣ ሶፍት፣ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ዘይትና ሩዝ በገፍ እየሸመቱ ሲወጡ አስተውለናል፡፡ ጓንት ጭነው የሚወጡትም ነበሩ፡፡ ይህ ግርግር ታዲያ የተወሰኑ ነጋዴዎችን ባይጨምርም በርካቶች የተመዘኑበትና የክፋታቸው ጥግ ያደላበት ነበር፡፡ የለንም ብሎ ከመደበቅ በውድ ዋጋ እስከመሸጥ ተስተውሏል፡፡ ይህ በምግብ ነክና በንፅህና መጠበቂያ ሸቃጮች ላይ ብቻ ሳይሆን ስለበሽታው የተሻለ ግንዛቤ አላቸው፣ ሥርጭቱን ለመግታት ሊያግዙ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ የመድኃኒት ቤቶች ላይ ጭምር መሆኑ ኢትዮጵያ የችግር ጊዜ ሰው የላትም ያስብላል፡፡

የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማኅበር በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪ አቶ ገብረ መድህን ቢረጋ፣ እነዚህን አገሪቱ ላይ የተፈጠረውን ችግር የሚያባብሱ የራስን ጥቅም ለማግኘት በመሯሯጥ በለሌሎች ላይ ጉዳት የፈጸሙ ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡

አቶ ገብረ መድህን እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የአቅርቦት እጥረት በተፈጠረ ቁጥር ነጋዴው በኅብረተሰቡ ላይ ያልተገባ ዋጋ ሲጭንና ባዕድ ነገር ከምግብ ቀላቅሎ ሲሸጥ የሚወሰደው ዕርምጃ የማያዳግም ባለመሆኑ በነጋዴውና ሸማቹ መካከል ያለው ግንኙነት ከቁጥጥር እንዲወጣ አድርጓል፡፡

መንግሥት ጠንካራ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ችግር ፈጥረዋል የተባሉት ለጊዜው ታስረው የሚፈቱ፣ ሱቃቸው የታሸገ ደግሞ በማስጠንቀቂያ የሚከፈቱ በመሆናቸው ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም፡፡

ነፃ ገበያ በሚል አካሄድ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ያላው የግሉ ዘርፍ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ ከዚህ ቀደም በነበሩም ሆነ አሁንም ባሉ አስተዳደሮች የግሉን ዘርፍ ሰማይ አውጥቶ ማወደሱ፣ የግሉ ዘርፍ ማን አለብኝ እንዲል አድርጓልም ይላሉ፡፡ ማንም እንደማይነካቸው በማሰብ ዋጋ እንደፈለጉ ሲጨምሩም ኅብረተሰቡ የመናገርና መብቱን የመጠየቅ ባህል ስለሌለው በየጊዜው በሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ ሰለባ ሲሆን ይታያል፡፡

የሸማቹን ፍላጎት ለማሟላት ዘይት፣ ዱቄትና ስኳር በድጎማ የሚያቀርቡ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትም ቢሆኑ፣ በመንግሥት የሚመሩና የሁሉንም ኅብረተሰብ ፍላጎት የሚያሟሉ አይደሉም፡፡

ሸማቹ መብቱን የሚጠይቅበት የተጠናከረ ማኅበርም ሆነ መሥሪያ ቤቱ ጠንካራ አለመሆናቸው ችግሩ በየጊዜው ለመከሰቱ ምክንያት ነው፡፡

መንግሥት ለጉዳዩ የሚጠበቀውን ያህል ትኩረት ሰጥቷል ለማለትም አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ቤት ቢዘጋም፣ ትራንስፖርት ላይ ያለው ችግርም ሆነ በየጎዳናው ተፋፍገው የሚነግዱ ነጋዴዎች ችግር እንዳለ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን 13ኛ ዙር የኮንደሚኒየም ቤት ዕድለኞች በየክፍለ ከተማው ውል ለመዋዋል የሚያደርጉትን ግፊያ፣ በየከነማው ያለውን የተጠጋጋ ሠልፍ ማየቱ በቂ ነው፡፡

በሕዝቡ በኩልም ቢሆን ሌሎች አገሮች አምላክ የሌላቸው ይመስል ‹‹እኛ አምላክ አለን›› በማለት በምድር ላይ ሊወሰድ የሚገባን ጥንቃቄ መተው አግባብ አንዳልሆነም አክለዋል፡፡

በመንግሥት በኩል በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ዋጋ እያናሩ የሸጡና የደበቁ ነጋዴዎች ሱቆችንና መድኃኒት ቤቶችን መዝጋቱ መፍትሔ እንደማይሆን አቶ ገብረ መድህን ገልጸው፣ የታሸጉ ሱቆች ክምችት እንደያዙ ሊሆን እንደሚችል፣ ለአጭር ጊዜ መፍትሔ የፍትሕ አካላት በማቆም አስወድደው የሸጡትን ቀድሞ ይሸጡበት ከነበረው በሁለትና ሦስት እጥፍ ቀንሰው እንዲሸጡ በማስገደድ በረዥም ጊዜ ደግሞ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል መክረዋል፡፡

ኮሮና ቫይረስን ተገን አድርገው ያላግባብ ጭማሪ ባደረጉ 22 መድኃኒት ቤቶች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ምግብ፣ መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለሥልጣን ሲገልጽ፣ የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ በሾላ መርካቶ ቂርቆስና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ከ2,764 በላይ የንግድ ሱቆችን ሰሞኑን አሽጓል፡፡ በኦሮሚያና በባህር ዳር ብቻ ከ1,000 በላይ ሱቆች ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

አቶ ገብረ መድህን፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ፣ ዓለም አቀፍም ሆነ አገር አቀፍ ወረርሽኝ የአቅርቦት እጥረት፣ ግጭትና ሌሎችም በድንገት የሚከሰተቱና የአስቸኳይ ጊዜ ባህሪ ያላቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የሚመራበት የራሱ ሕግ ሊኖረው እንደሚገባና የሕዝብ ተወካዮች ምክር  ቤትም ለአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ ጠርቶ በዚህ ዙሪያ እንዲመከርና ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...