Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየብዙኃን ሴቶች እናት ካትሪን ሃምሊን (1916-2012)

የብዙኃን ሴቶች እናት ካትሪን ሃምሊን (1916-2012)

ቀን:

‹‹እናት የቤተሰብ ዋና ሀብትና ከፍተኛ ግምት የሚሰጣት መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ ከማህፀን ሕመም (ፊስቱላ) ፈውስ ለማግኘት እጅግ ለሚንከራተቱት ለኢትዮጵያውያን ብርቱ ወጣት እናቶች አገልግሎት ማቅረብም የፍቅር ተግባርን መፈጸም ነው፡፡››

በማዋለድና በሴቶች ሕክምና መደበኛ ሐኪሞች ሆነው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከስድሳ ዓመታት በፊት በልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ባልና ሚስቱ ዶ/ር ካትሪን ሃምሊንና ዶ/ር ሬጊናልድ ሃምሊን፣ በወሊድ ማህፀናቸው የተበላሸ ሴቶችን በመጠገንና በማከም ለፈጸሙት አኩሪ ተግባር የ1965 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የበጎ አድራጎት ሽልማት ሲቀበሉ የተናገሩት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በ1950 ዓ.ም. አዋላጅ ሐኪሞችን ለአዲስ አበባው ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል (የአሁኑ ጦር ኃይሎች) ለመቅጠር ያወጣውን ማስታወቂያ ሰምተው ነው፣ ባልና ሚስቱ ሃምሊኖች ኢትዮጵያ የመጡት፡፡

- Advertisement -

ከዓመት ላነሰ ጊዜ ሠርተው ወደ አውስትራሊያ ለመመለስ አቅደው የነበሩት እነ ሃምሊን አንድ የማህፀን ሐኪም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፊስቱላ ሁኔታ ከነገራቸው በኋላ ግን፣ በአብዛኛው ክፍለ ዓለም የጠፋውን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ሲረዱ ኢትዮጵያውያኑን ከዚህ ደንቃራ በሽታ ለመታደግና ለመፈወስ ቃል የገቡት፡፡

በወሊድ ጊዜ የሚፈጠረው ፊስቱላ እንስቶችን ከማሰቃየቱ ለደዌ ዳኛ ለአልጋ ቁራኛ ከመዳረግ ባለፈ በማኅበረሰቡም መገለል የሚያደርስ በመሆኑ፣ የእነ ሃምሊን ትጋት ሕክምና ከመስጠት ባለፈ ራሱን የቻለ ሆስፒታል ለመገንባት ዕቅዳቸው ማድረጋቸው አልቀረም፡፡

የዶ/ር ሃምሊን ገጸ ታሪክ እንደሚያስረዳው፣ ኢትዮጵያ በመጡ በ15ኛው ዓመታቸው የፊስቱላ ሆስፒታል ለማሠራት ችለዋል፡፡ በኢትዮጵያና በውጭም አገር እየተዘዋወሩ ዕርዳታ ሰብስበው ባገኙት በልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ግቢ ማዕከል ማሠራታቸው፣ በሒደትም በሆስፒታሉ አካባቢ ልዕልት ተናኘ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ በሰጧቸው መሬት ላይ ሆስፒታሉን ዕውን ማድረጋቸው ይወሳል፡፡

ይህም ሆስፒታል 60,000 ገደማ ኢትዮጵያውያትን ከሕመም ፈውሶ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ ከተፈወሱት መካከል ማኅበራዊ ሕይወትን በመቀላቀል ጤናማ ኑሮ ለመኖር ከመታደላቸውም በላይ፣ ዳግም አርግዘው የመውለድን ፀጋና ደስታ ያገኙት ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

የሃምሊን ፊስቱላ ተቋም በሠናይ ተግባሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአርዓያነት በመብቃቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅናን ከማግኘቱ በተጨማሪ፣ ለኖቤል ሽልማት ዶ/ር ሃምሊን ሁለቴ ለማሳጨት በቅቶ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትን ሲያበረክትላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ልዩ የወርቅ ሽልማትም አጥልቀውላቸዋል፡፡

ጥር 15 ቀን 1916 ዓ.ም. በሲዲኒ አውስትራሊያ የተወለዱት ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን በ96 ዓመታቸው መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ያረፉት የፊስቱላ የሕክምና ማዕከል ቅጥር ግቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነው፡፡

ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ፣ ‹‹ካትሪን ሃምሊን ከ60 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ክብራቸው የተነጠቀባቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሬ ሴቶች ዳግም ቀና ብለው እንዲራመዱ ለፍተዋል፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመኖሪያ ቤታቸው በመገኘት ለዶ/ር ሃምሊን ልጅ የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ፣ እሳቸው ያስተማሯቸውና ያሠለጠኗቸው ባለሙያዎች የዶ/ር ሃምሊን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እርግጠኛ ነኝ ማለታቸው ታውቋል፡፡

የሃምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ እንዳስታወቀው ሥርዓተ ቀብራቸው ሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጴጥሮስ ወጳውሎስ በሚገኘው የእንግሊዛውያን መካነ መቃብር ይፈጸማል፡፡

ዶ/ር ሃምሊንና ባለቤታቸው ከ47 ዓመታት በፊት የ1965 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት የወርቅ ኒሻንና ዲፕሎማ ከ10,000 ብር ጋር በተሰጣቸው ጊዜ ባሰሙት ዲስኩር፣ እንዲህ መናገራቸውን የሽልማቱ ድርሳን ያሳያል፡፡

‹‹ፋታ በማይሰጥ ሕመም የተዳከመችና በሕይወት መቆየትን እንኳ ለሌሎች በደል እንደሆነ አድርጋ በመቁጠር ተስፋ የቆረጠች ሴት፣ እንደገና ሕይወት የተሰማት መሆኑን በድንገት ስትረዳውና የዓለም ቤተሰብ አንዱ ዜጋ እንደሆነችም ስትገነዘብ፣ የምታቀርበውን ምሥጋና የሚስተካከል አንድም ነገር ሊኖር አይችልም፤›› ብለው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...