Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሰመጉ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በማረሚያ ቤቶች የተጠናከረ ዝግጅት እንዲደረግ አሳሰበ

ኢሰመጉ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በማረሚያ ቤቶች የተጠናከረ ዝግጅት እንዲደረግ አሳሰበ

ቀን:

የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰና ቀለል ያለ ክስ ያላቸው እንዲፈቱ መንግሥት ወስኗል

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለወረርሽኝ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የማረሚያ ቤቶች፣ የፖሊስ ጣቢያዎችና የስደተኞች ወይም ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የቫይረሱ ሥርጭት በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አሳሰበ፡፡

ኢሰመጉ ይህን የማሳሰቢያ መልዕክት ያስተላለፈው ዓርብ መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ ‹‹መንግሥት በማረሚያ ቤቶችና ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ውሰጥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይከሰት አስፈላጊውን የጥንቃቄ ዕርምጃ ይውሰድ›› በሚል ርዕስ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫው አማካይነት ነው፡፡

በሽታው በወረርሽኝ መልክ ቢከሰት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የጥንቃቄ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን መንግሥት በተከታታይ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ማስታወቁን በበጎ ጎን እንደሚመለከት የገለጸው ኢሰመጉ፣ ነገር ግን ‹‹በተለይም በማረሚያ ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያዎችና በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያለው የተጨናነቀ የአያያዝና የኑሮ ሁኔታ በትንፋሽና በንክኪ ለሚተላለፍ የበሽታ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጫ ስለሚያደርግ፣ መንግሥት አደጋውን ለመቀነስ የሚያስችሉ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል፤›› ሲል አሳስቧል፡፡

የበሽታው ወረርሽኝ በተጠቀሱት ሥፍራዎች ቢከሰት በወንጀል ተጠርጥረው በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች፣ ከታራሚዎች፣ ከተፈናቃዮችና ከስደተኞች ጋር የቅርብ ግንኙነት ባላቸው ጠበቆች፣ የቤተሰብ  አባላትና የማረሚያ ቤት ባልደረባዎች፣ እንዲሁም የዕርዳታ አስተባባሪዎች አማካይነት ወደ ብዙኃኑ ማኅበረሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስፋት ሊሠራጭ ስለሚችል፣ ይህንንም በፍጥነት ለመቀልበስ አዳጋች ሊሆን መቻሉ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ኢሰመጉ የሥጋቱን መነሻ አብራርቷል፡፡

በመሆኑም በሌሎች አገሮች ከተወሰዱት ዕርምጃዎች ተሞክሮ በመቅሰም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቶችና የማረሚያ ቤት አስተዳዳር የተቀናጀ የአሠራር ሥርዓት ዘርግተው አስፈላጊውን ሕጋዊ የጥንቃቄ አካሄድ በመከተል ‹‹በዋስ ሊፈቱ የሚችሉ በሕግ የተያዙ ሰዎችን፣ የአመክሮ ጊዜያቸው የተቃረበ ታራሚዎችን፣ ወደ ኅብረተሰቡ ቢቀላቀሉ ጉዳት እንደማያደርሱ የሚታመንባቸው፣ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በመልካም ባህሪያቸው የሚታወቁ፣ እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ታራሚዎችን በመፍታት››፣ ቀሪዎቹም ከጠያቂዎቻቸው ጋር በጥንቃቄ ሊገናኙ የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ በተጨናነቀ ሥፍራ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ የመከላከል ዕርምጃዎችን ከወዲሁ መውሰድ ተገቢ መሆኑን ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የወረርሽኝ ሥጋትን አስቀድሞ ለመከላከል ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ በኅብረተሰቡ መካከል ነፃ የሆነ የመረጃ ልውውጥ መኖር መሆኑን በመጥቀስ፣ ‹‹በኦሮሚያ ክልል በሚስተዋለው የስልክ መስመርና የበይነ መረብ ግንኙነት መቋረጥ ምክንያት ችግሩ የከፋ እንዳይሆን፣ በዚያ አካባቢ ለሚገኙ ማረማያ ቤቶችና መጠለያ ጣቢያዎች መረጃ የሚደርስበትን መንገድ መንግሥት ይቀይስ፤›› በማለት ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ካለው ዝቅተኛ የሆነ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅርቦት አንፃር ታራሚዎች፣ ስደተኞችና ተፈናቃዮች በተጨናነቀ ሁኔታ በሚኖሩባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች፣ ማረሚያ ቤቶችና መጠለያ ጣቢያዎች ችግሩ የባሰ ሊሆን ስለሚችል መንግሥት አስፈላጊውን የንፁህ ውኃ አቅርቦትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ከማሟላት በተጨማሪ፣ ‹‹የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ታራሚዎች ብቻ የሚያድሩባቸው ክፍሎች ማዘጋጀትና መጠለያ ጣቢያዎችንም በአግባቡ ማደራጀት ይጠበቅበታል፤›› ሲል አሳስቧል፡፡

በተያያዘ ዜና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ታራሚዎችን ለመጠበቅ ሲባል ለመጪዎቹ 15 ቀናት ታራሚዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንይገናኙ ዕግድ መጣሉን፣ የማረሚያ ቤቱ ጄነራል ኮሚሽነር ጀማል አብሶ ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጻቸው ይታወሳል፡፡    

ዓርብ መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በማረሚያ ቤቶች ቫይረሱ ከገባ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ሕፃናትን የያዙ፣ የአመክሮ ጊዜያቸው የደረሰና ቀልል ያለ ክስ ያለባቸው እንዲለቀቁ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...