Friday, May 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮና ቫይረስ ቀውስ 190 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሠራተኛ ቅነሳ ለማድረግ አልታቀደም

ከ20 በላይ አውሮፕላኖች ቆመዋል

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ላይ ባስከተለው ቀውስ ሳቢያ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ 190 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አየር መንገዱ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚያደርገውን በረራ በማቋረጡ፣ ምልልሱን በመቀነሱና የመንገደኞች ፍሰት በማሽቆልቆሉ ምክንያት በየካቲትና በመጋቢት ወር ብቻ 190 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አጥቷል፡፡ ‹‹ይህ ኪሳራ ሳይሆን ማግኘት የነበረብንን ገቢ አጥተናል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፓ ወደ ሚላን፣ ማድሪድ፣ ማርሴይና ጄኔቭ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ተጓዥ መንገደኞች ባለመኖራቸው እንዳቋረጠ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ጂቡቲ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ሱዳንና ካሜሩን ያሉ የአፍሪካ አገሮች የአየር ክልላቸውን ሙሉ በሙሉ ዘግተዋል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያና ናይጄሪያ በሽታው ከተዛመተባቸው አገሮች ዝርዝር በማውጣት በረራ ከልክለዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ህንድና ታይላንድ ቪዛ ከልክለዋል፡፡ አሜሪካና አውሮፓ በበኩላቸው የጉዞ ክልከላ ጥለዋል፡፡

በእነዚህና በሌሎችም ሁኔታዎች አስገዳጅነት አየር መንገዱ እንቅስቃሴውን በ25 በመቶ እንደቀነሰ፣ ከ20 በላይ ትልልቅ አውሮፕላኖቹን ለማቆም እንደተገደደ አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ያስከተለው ቀውስ በአየር መንገዱ ገቢ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ማሳደሩን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ አየር መንገዱ ሠራተኞች ሊቀንስና ሊዘጋ እንደሆነ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚራገበው ዘገባ ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ‹‹ይህ የፈጠራ ወሬ ነው›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ ምንም እንኳ ወረርሽኙ በአየር መንገዱ እንቅስቃሴና ገቢ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ ያሳደረ ቢሆንም፣ አሁን ማኔጅመንቱ የሠራተኛ ቅነሳ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላወጣ ተናግረዋል፡፡ ሠራተኞች ዕረፍት እንዲወጡ መጠየቁን ገልጸው፣ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ጊዜያዊ ሠራተኞችና አውትሶርስ (ከውጭ የሚቀርቡ አገልግሎቶች) ሊቀንሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 14,000 ቋሚና 3,000 የኮንትራት ሠራተኞች አሉት፡፡ ‹‹ይህ አየር መንገድ 24 ሰዓት ሳምንቱን ሙሉ የሚሠሩ ታታሪ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ያሉት የ74 ዓመታት ውጤታማ ታሪክ ያለው ኩባንያ ነው፡፡ በጦርነትና በረሃብ ጊዜ ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ ያለፈ አየር መንገድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ሳርስ፣ ኢቦላና ዚካ ያሉ በሽታዎችን ተቋቁሞ ያለፈ አየር መንገድ ነው፡፡ አሁንም በሠራተኞቹና በማኔጅመንቱ ጥንካሬ በርትቶና ተባብሮ አንድ ሆኖ በመሥራት ይህን ክፉ ቀን ያልፈዋል፤›› ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ቀደም ሲል በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት 113 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያጣ ተንብዮ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ ቁጥሩን ወደ 200 ቢሊዮን ዶላር አሳድጎታል፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶች እስከ መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳጡ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡ ማኅበሩና የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር (AFRAA) አየር መንገዶች በወረርሽኙ የደረሰባቸውን ቀውስ በመመልከት፣ መንግሥታት የተለያዩ ድጋፎች እንዲያደርጉላቸው ተማፅነዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ከመንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳልጠየቀ አቶ ተወልደ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አንገብጋቢ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ፣ እስካሁን በራሳችን ቀውሱን ለመቆጣጠር ጠንክረን በመሥራት ላይ ነን፡፡ ለወደፊት የሚሆነውን አብረን እናያለን፤›› ብለዋል፡፡

የአሜሪካ አየር መንገዶች መንግሥታቸውን 58 ቢሊዮን ዶላር ዕገዛ የጠየቁ ሲሆን፣ አውሮፕላን አምራቹ የቦይንግ ኩባንያ 60 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ጠይቋል፡፡ የአውሮፓ መንግሥታት ለአየር መንገዶቻቸው ምን ያህል ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው በመምከር ላይ ናቸው፡፡ የቻይና መንግሥት ለአየር መንገዶቹ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ቻይና ከራሷ አየር መንገዶች አልፋ ወደ ቻይና ለሚበሩ የውጭ አየር መንገዶች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆነች ታውቋል፡፡

‹‹ቻይና ወደ ግዛቷ ለሚበሩ አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በገንዘብና በዓይነት እየደገፈች ነው፤›› ብለዋል አቶ ተወልደ፡፡ አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በወጪ ቁጠባ ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚያከናውን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች