በአፈ ጉባዔው የሚመራ ጉብኝትም ተስተጓጉሏል
ፓርላማው በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ከግብፅና ከሱዳን ጋር በአሜሪካ ተጀምሮ የነበረውን የህዳሴ ግድብ ድርድር አስመልክቶ ማብራሪያ ለመስማት ያቀደ ቢሆንም፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በወጣው የመንግሥት መመርያ ምክንያት ስብሰባው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ከኃላፊዎች ታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መግባቱ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ እስከ ዓርብ ምሽት ድረስ ባሉት ቀናት፣ ዘጠኝ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል። መንግሥትም የበሽታውን ሥርጭት ያግዛሉ የተባሉ የመከላከል ዕርምጃዎችንና መመርያዎችን ቀደም ብሎ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ የትምህርት ተቋማትን በጊዜዊነት መዝጋትን፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ስብሳባዎችንና የቡድን ኩነቶችን መገደብ ያካትታል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መካሄድ የነበረባቸውን ሁለት መደበኛ ስብሰባዎቹን በጽሕፈት ቤቱ አማካይነት፣ ለሁሉም ተመራጭ የምክር ቤቱ አባላቱ መደበኛ ስብሰባዎች እንደማይካሄድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ሪፖርተር ከተለያዩያ የጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ለማወቅ እንደቻለው፣ ከሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለማካሄድ ቀደም ብሎ የተዘጋጁ የቋሚ ኮሚቴዎች መደበኛ ስብሰባዎችና ሁለት አስቸኳይ ስብሰባዎች ተሰርዘው ለሌላ ጊዜ መተላለፋቸው ተረጋግጧል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ሊመክር ታስቦ የነበረው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ትልቅ ግምት ተሰጥቶት ነበር ተብሏል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ስብሰባው በዚህ ሳምንት ለመጥራት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዋናነት የውጭ ጉዳይ፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም በህዳሴው ግድብና በዓባይ ውኃ አጠቃቀም በድርድሩ ተሳታፊ የነበሩ ባለሙያዎችን ለመጥራት ተዘጋጅቶ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች አመልክተዋል፡፡
ይህንኑም መረጃ ሪፖርተር ከቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ተስፋዬ ዳባ በስልክ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ ዕቅዱ እንደተባለው ተይዞ እንደነበረና ባለፈው ሳምንት በወጣው የመንግሥት መመርያ መሠረት ማካሄድ አለመቻሉን ከተረዱ በኋላ፣ ከአፈ ጉባዔው ጋር በመነጋገር ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ መገደዳቸውን አቶ ተስፋዬ አረጋግጠዋል፡፡
ወቅታዊው አገራዊ ሁኔታ የተጠቀሰውን አስቸኳይ ስብሰባ ብቻ ሳይሆን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የዋጋ ጭማሪና የገበያ ሁኔታን በተመለከተ ሊጠራው አቅዶት የነበረው ስብሰባ፣ በተመሳሳይ ምክንያት መሰረዙን አቶ ተስፋዬ አክለዋል፡፡
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ኮሚቴ በዋናነት ከታችኛው ተፋሰስ አገሮች በቅርቡ በዋሽንግተን ተደርጎ ያለ ስምምነት የተጠናቀቀውን የድርድር ሒደት፣ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ያወጡት ትዕዛዝ መሰል አወዛጋቢ መግለጫ፣ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሁለቱ ሚኒስትሮችና የተደራዳሪ ቡድን አባላት ሪፖርት ዕቅድ ተይዞ እንደነበር አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡
ቁሚ ኮሚቴው አስቸኳይ ስብሰባውን ለመጥራት ማሰቡንና ዝርዝር አጀንዳዎችን በተመለከተ ለአፈ ጉባዔው ቀደም ብሎ አሳውቆ እንደነበረ፣ አፈ ጉባዔውም ይሁንታቸውን መስጠታቸውን ያስረዱት አቶ ተስፋዬ ቋሚ ኮሚቴው የራሱን አባላት፣ ለስብሰባው የሚጠሩ ሚኒስትሮችንና የተደራዳሪ ቡድን አባላትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚገኙ ይጠበቅ ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹ምናልባትም ስብሰባው ባቀድነው መሠረት የሚካሄድ ቢሆን እንኳ ከ30 እስከ 40 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ሊገኙ ይችሉ ነበር፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ አሁን በተከሰተው ወረርሽን ለመሰብሰብ ስለማያበረታታ ማካሄድ አንችልም፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የተሰረዘው አስቸኳይ ስብሰባ ሌላ ጊዜ ሊካሄድ እንደሚችል ቢገልጹም፣ ትክክለኛ ተለዋጭ ቀኑ መቼ ሊሆን እንደሚችል ግን እርግጠኛ አለመሆናቸውን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በቀጣይ ለምናካሄደው ተለዋጭ ስብሰባ አሁን መገመት ስለማይቻል፣ በቅርቡ ከአፈ ጉባዔው ጋር በመነጋገርና የሚኖረው ወቅታዊ ሁኔታ ተመሥርቶ ይወሰናል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ከቋሚ ኮሚቴው ስብሰባና ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከተስተጓጎሉት የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባዎች በተጨማሪ፣ የወራርሽኑ ሥጋት ሌሎች ሥራዎችና ተግባራት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ መጪው ሳምንት የሁሉም ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎችንና የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችን ያቀፈ በአፈ ጉባዔው የሚመራ ቡድን፣ ወደ ህዳሴው ግድብ ሊያደርገው የነበረ የመስክ ጉብኝት መሰረዙንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ከ30 በላይ የሚሆኑ የቡድኑን አባላት ግድቡ ወደሚገኝበት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ አጓጉዞ ለመመለስ የሚያስችል የሔሊኮፕተር አገልግሎት እንዲያቀርብ መከላከያ ሚኒስተሩ ተጠይቆ እንደነበር፣ ሚኒስቴሩም በበኩሉ በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎችን መጫን የሚችል ትልቅ መጠን ያለው ሔሊኮፕተር ለማቅረብ መስማማቱን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ ምክር ቤቱ ለእረፍት ባለፈው ወር ከመዘጋቱ ቀደም ብሎ የመንግሥት ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፓርላማ አባላት ሄደው እንዲጎበኙ አሳስበዋቸው የነበረ ቢሆንም፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ጉዞው የተሰረዘ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አረጋግጠዋል፡፡