138 ቶን እሴት የተጨመረበት ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቧል
በዓመቱ ስምንት ወራት ውስጥ ለውጭ ከቀረበ ከ167 ሺሕ ቶን በላይ የቡና ወጪ ንግድ ከ465 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘቱን፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ ከታቀደው የገቢ መጠን ከ100 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡
ባለሥልጣኑ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መሠረት ለውጭ ገበያ የቀረቡት ቡናን ጨምሮ የሻይና የቅመማ ቅመም ምርቶች ሲሆኑ፣ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ውስጥ 176,249.80 ቶን የቡና፣ የሻይና ቅመማ ቅመም ውጤቶችን በመላክ 577.70 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የዕቅዱን መቶ በመቶ ያሳካበትን የ176,360.82 ቶን ምርት አፈጻጸም በማስመዝገብ የምርት አቅርቦቱን ቢያሳካም፣ በገቢ ረገድ ግን ከሁሉም ምርቶች ውጤት ከ478 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 81 በመቶ ያህል ገቢ አስገኝቷል፡፡
ከዚህ አፈጻጸም ውስጥ የቡና ድርሻ በምርት ብዛት መጠን 167,132 ቶን ነበር፡፡ ከዕቅድና ከአፈጻጸም አኳያ ሲመዘን ከ2011 ዓ.ም. ስምንት ወራት አኳያ፣ በመጠን ረገድ የ37,893.22 ቶን ወይም የ27.37 በመቶ፣ በገቢ በኩልም የ28.2 ሚሊዮን ዶላር ወይም 6.3 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡ ተጠቁሟል፡፡
የቡና የየካቲት ወር እንቅስቃሴ በተቃኘበት የባለሥልጣኑ የስምንት ወራት ሪፖርት መሠረት፣ 20,472 ቶን የቡና ምርት አቅርቦት በመፈጸም 71.86 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቅ ነበር፡፡ ከዚህ ዕቅድ ውስጥ 17,455 ቶን ቡና ለውጭ ቀርቦ የዕቅዱን 85 በመቶ በመፈጸም፣ 57.3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት ወሩን አገባዷል፡፡
በስምንት ወራት ከተላከው የቡና ምርት ውስጥ 138 ቶን ቡና እሴት ተጨምሮበት ለውጭ ገበያ ሲቀርብ፣ ከገቢ አኳያም 900 ሺሕ ዶላር ገደማ አስገኝቷል፡፡ ከ8,534 ቶን በላይ የቅመማ ቅመም ምርት ውስጥ 4,811 ቶን እሴት ተጨምሮበት ተልኳል፡፡ ቅመማ ቅመም ዘርፍ ካስገኘው 11,653 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ 4.44 ሚሊዮን ዶላር እሴት ተጨምሮበት ከተላከ ምርት የተገኘ ነው፡፡
የቡና ምርት መዳረሻ ገበያ ከሆኑ አገሮች መካከል በመጠንና በገቢ ድርሻ ጀርመን ቀዳሚ ሆናለች፡፡ 39,822 ቶን ቡና በመረከብ የ24 በመቶ ድርሻ ስትይዝ በገቢ 94 ሚሊዮን ዶላር አስገኝታለች፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ 28,906 ቶን ቡና ግዥ በመፈጸም የ80.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት ሁለተኛዋ ከፍተኛ የቡና መዳረሻ ገበያ ሆናለች፡፡ ጃፓን 17,804 ቶን ድርሻ በመያዝ 46 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት በቅደም ተከተል ሦስተኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ ቤልጅየም፣ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ፈረንሣይ፣ ሱዳን፣ ጣሊያን፣ እንዲሁም ዮርዳኖስ ከአራተኛ እስከ አሥረኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በላከው መግለጫ በዓለም ገበያ የሚታየው የቡና ዋጋ ለውጥ እምብዛም መሻሻል ባያሳይም፣ ለኢትዮጵያ የቡና ወጪ ንግድ ገቢ መሻሻል ዕድል እንደሚፈጥር የሚጠበቀውን የቡና ቅምሻ ውድድር ተስፋ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳ ባለሥልጣኑ የቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድሩ ከፍተኛ ውጤት እንደሚገኝበት ቢጠብቅም፣ ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው መረጃ ግን ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› የተሰኘው የቡና ጥራት ውድድር በአዲስ አበባ የመካሄዱ አዝማሚያ በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ሥጋት ሳቢያ ሊራዘም ወይም በታሰበው ጊዜ የመካሄዱ አዝማሚያ አጠራጣሪ እንደሆነ፣ የልዩ ጣዕም ቡና ተዋንያን የሚሳተፉበት አሶሲዬሽን ኦፍ ስፔሻሊቲ ኮፊ ያወጣው መረጃ አመላክቷል፡፡