ዓለም በኮሮና ቫይረስ እየደረሰባት ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፣ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ይካሄዳል ማለቱ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባለፈው ዓርብ መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በአምባሳደር ሆቴል በሰጠው መግለጫ፣ አትሌቲክሱን ጨምሮ ለቶኪዮ 2020 የተመረጡ ብሔራዊ አትሌቶች ዝግጅት እንደሚጀምሩ አስታውቋል፡፡
በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አማካይነት ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የተቋቋመው ብሔራዊ የዝግጅትና ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ቶኪዮ 2020 “ተደረገም አልተደረገም” ለብሔራዊ አትሌቶች ጤንነት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በመውሰድ ዝግጅት መጀመር እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ በተለይም በአንዳንድ ወገኖች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መፍትሔ ሳያገኝ ብሔራዊ አትሌቶችን በሆቴል አሰባስቦ ዝግጅት ማድረግ ሥጋት የሚገባቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ቅድመ ግምቱን በመግለጫው ያካተተው ብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴው፣ ሰባት ዶክተሮች የተካተቱበት ብሔራዊ የሕክምናና የሥነ ምግብ ባለሙያ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ በማድረግ አትሌቶች የሚሰባሰቡበት ሚሌኒየም አዳራሽ አጠገብ የሚገኘው አምባሳደር ሆቴል ከአትሌቶች በስተቀር ማናቸውንም አገልግሎት የማይሰጥ ሆኖ ከሐኪሞች በተጨማሪ በጤና ሚኒስቴርና በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካይነት ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበት ይሆናል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ እንዲሁም የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና የኮሚቴው ጸሐፊ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም፣ የሕክምና ቡድኑ አባላትና የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ዝግጅቱን አስመልክቶ ሙያዊ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቀዳሚያውን የወሰደው የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከዋናው ጉዳይ በፊት “በሌላ መንገድ ተከስቻለሁ” በሚል መድረኩን ፈገግ ያደረገ አስተያየት ከሰጠ በኋላ፣ ‹‹ኮሮና ቫይረስ ለእኛ ብቻ ሳይሆን የዓለም ችግር ሆኗል፡፡ የሚነገርለትን ያህል አስፈሪ ነው፣ ሆኖም ግን ችግሩን መቋቋም የምንችለው ጥንቃቄ ሳይለየን መሥራት ያለብንን እየሠራን መሆን ይኖርበታል፡፡ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቶኪዮ 2020 እንደማይሰረዝ ይፋ አድርጓል፣ ይህ ከሆነ ደግሞ እኛም እንደ ሌሎቹ አገሮች ችግሩ እንኳ ቢኖር ከመጥፎ የተሻለውን መጥፎ መርጠን መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ማድረግ ያለብንን አድርገን ቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተቋረጠ እሰየው፣ ካልተቋረጠ ደግሞ እንደማንኛውም ሳንደነባበር እንሳተፋለን፤›› ብሏል፡፡
በችግሩ ምክንያት በርካታ አትሌቶች ከውድድር ውጪ መሆናቸውን ያከለው ኃይሌ የወደፊቱን ትተን እስካሁን የገጠማቸውን እንኳ ብንመለከት፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙባቸው በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በቻይና ብዙ ውድድሮች መሰረዛቸው በሥነ ልቦናው ረገድ ከባድ ነው፡፡ ይህ ችግር አትሌቲክሱን እስከ ወዲያኛው እንዳይጎዳው መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ መፍትሔው ደግሞ አትሌቶች ከልምምድና ዝግጅት እንዳይርቁ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ወረርሽኙን ለመከላከል አትሌቶች በተናጠል መሥራት እንዳለባቸው ይነገራል፡፡ ክፋት የለውም ይሁንና የኢትዮጵያውያን የአኗኗር ዘይቤ ከሚባለው ሁኔታ ጋር ይሄዳል አይሄድም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በግሌ ጥንቃቄው ሳይጓደል እንደወትሮም የተወሰኑት ተቀራርበው ቢሠሩ ነው የሚመረጠው፤›› በማለት ተናግሯል፡፡
‹‹ቶኪዮ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ቦታ አለው፣ በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና መንግሥት የራሳቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ አትሌቶቻችን ከሥጋት ነፃ ሆነው እንዲዘጋጁ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ያለው የቴክኒክ ኮሚቴው ጸሐፊ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም በበኩሉ፣ ‹‹ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ መደረግ ያለበት ጥንቃቄ ሳይጓደል ዝግጅት ማድረጉ የተሻለ ነው፡፡ ችግሩ ቢኖርም በሚመጣው ውጤት የሚያዝን እንዳለ ሆኖ የሚስቅም እንዳይኖር ሁሉም በጋራ አድርጎ መሥራት ጉዳት የለውም፡፡ አሁን ባለው ቶኪዮ 2020 ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚደረግ ምልክቶች እያየን ነው፡፡ ሌላውና ዋነኛው ደግሞ በስፖርት ለውጤት ትልቁ ነገር ያለው አዕምሮ ላይ ነው፣ በቁመትና በአካል ግዝፈት ቢሆንማ ኖሮ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ዓለምን ጉድ ባላሰኘ ነበር፤›› ያለው ገብረ እግዚአብሔር ትልቁ ነገር አትሌቶቻችን አዕምሮ ላይ ከተሠራ ችግር እንደሌለው ተናግሯል፡፡
የሕክምና ቡድኑ ዝግጅት በሚመለከት በዶ/ር ቃልኪዳን ዘገዬ አማካይነት እንደቀረበው ማብራሪያ፣ የሕክምና ቡድኑ ከሆቴል መረጣው እንዲሁም ሆቴሉን ፀረ ተሕዋስያን መድኃኒት ከመርጨት ጀምሮ የእያንዳንዱን አትሌት መኝታ ክፍል በልዩ ጥንቃቄ እየተከታተለ መሆኑ፣ ከሆቴል እስከ ልምምድ ቦታ ከዚያም ከልምምድ እስከ ሆቴል ባለው ሁኔታ የአትሌቶቹን ጤንነት የመከታተልና የመለየት ሥራ እንደሚሠራ፣ ቡድኑ ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ባለሙያተኞች ጋር የሕክምና ቡድኑ ከተቋቋመበት ዕለት ጀምሮ በእያንዳንዱ ጉዳይ አብሮ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ስፔሻሊስቶችን ጨምሮ የሕክምና ቡድኑ ሰባት አባላት ያለው እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፣ ‹‹አሁን ዓለም የገጠማት ዓይነት ችግር ሲገጥም፣ አንዳንድ ጊዜ ለመልካም ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፣ ችግር ኖረም አልኖረም ባለበት የሚቆም ነገር ስለሌለ ማድረግ ያለብንን እያደረግን የሚመጣውን መጋፈጥ የሁላችንም ድርሻና ግዴታ ሊሆን ይገባል፡፡ የኦሊምፒክ ፍልስፍና በራሱ የሚለው ኦሊምፒክ ለአንድነት፣ ለሰላምና ለወንድማማችነት ስለሚል አንድ ሆነን መታገልና ይህን ችግር ማለፍ ግድ ይለናል፤›› ብለው ይህ አንድነትና አብሮነት ከቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ባለፈ ለትውልድ የሚሻገር ቅርስ ለማፍራት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሐሳብ አመንጪነት በዕቅድ ለተያዘው የኦሊምፒክ አካዴሚ ግንባታ ዕውን መሆን መረባረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ከዚሁ ኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት እንደሚከናወን፣ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ከአባል አገሮች የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንቶች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረስ ባደረገው ውይይት መገለጹ ይታወቃል፡፡ የአይኢሲ ውሳኔና አቋም ምን ነበር የሚለውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ዝርዝሩን በመግለጫው ተናግረዋል፡፡
አይኦሲ በቪዲዮ ኮንፈረንሱ ካነሳቸው መካከል ኮሮና ቫይረስ አሁን ላይ የዓለም ሕዝቦች በጋራ እየተጋፈጡት የሚገኝ አደገኛ ወረርሽኝ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ለኦሊምፒክ መፈጠር ራሱ መነሻው ችግሮች እንደሆኑ፣ አሁንም ምንም እንኳ ኮሮና ቫይረስ ለሰው ልጆች ደኅንነት አደገኛና አስቸጋሪ ቢሆንም ኦሊምፒክ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት ይከናወናል ማለቱ ተናግረዋል፡፡
ችግሩ ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ፈታኝ ቢሆንም ለዚህ ሲባል ከራሱ ከአይኦሲ፣ ከዓለም የጤና ድርጅት፣ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንና ይህ አካል የሚያከናውናቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን በሚመለከት “አትሌት 360” የሚል ድረ ገጽ ያዘጋጀ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
ቶኪዮ 2020 ችግር ሊሆንበት እንደሚችል ከተገለጹት መካከል ለኦሊምፒክ ተሳትፎ መሥፈርት (ሚኒማ) በሚመለከት እስካሁን ባለው አብዛኛው መሥፈርቱን ያሟሉ ከመሆኑ ባሻገር፣ የሚቀር ካለ ግን አትሌቶች ቀደም ሲል በነበራቸው ውጤት (ፐርፎርማንስ) መሠረት የመወዳደር ዕድል ይኖራቸዋል ማለቱም ተነግሯል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ሥጋት የተሳታፊ እጥረት እንደሚገጥመው ቅድመ ግምቱን ያስቀመጠው አይኦሲ፣ በመፍትሔነት ከዚህ ቀደም በሚኒማ ምክንያት የተሳትፎ ዕድል ያልነበራቸው አገሮች ተጨማሪ አትሌቶችን ያለሚኒማ እንዲያሳትፉ የሚያደርግ አሠራር “አመቻችቻለሁ” ስለማለቱ ጭምር ዶ/ር አሸብር ተናግረዋል፡፡
ከመግለጫው በኋላ የተነሱት ጥያቄዎች ብዙዎቹ ከኮሮና ቫይረስ ይልቅ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል በተባለው ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር፡፡ በተለይም ከአሠራርና ከአካሄድ እንዲሁም ከትጥቅ አጠቃቀምና እደላን በሚመለከት ግልጽ የሆነ አሠራር እንደሌለ፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ ያለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኦሊምፒክ አመራሮች ትኩረት እየተሰጠው አለመሆኑ፣ ከብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ምርጫ ጋር ተያይዞ ሴቶችን ያገለለ ምርጫ ስለመደረጉ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በሁለቱ ተቋማት ማለትም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል በተለይ ስፖርቱን በሚመለከት ምንም ዓይነት ግጭት እንደሌለ፣ ሆኖም ተቋማቱን በመጠቀም የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ችግር የሚፈጥሩ ግለሰቦች ስለመኖራቸው የኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ተናግረዋል፡፡
ትጥቅን በሚመለከት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ዓለም አቀፍ ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች በስፖንሰርነት የሚሰጧቸው ትጥቆች ለአትሌቶችና ለሚመለከታቸው አካላት አግባብ ባለው መልኩ ይሰጣል፣ ወደ ፊትም ይቀጥላል፡፡ ይህ ሲባል ግን ቀደም ሲል እንደነበረው ለአትሌቶች በሚል የሚወጣ ትጥቅ ለንግድ አገልግሎት እንዲውል ፈፅሞ አንፈቅድም፤›› ብለዋል፡፡ የሴት አሠልጣኞችን ምርጫ በተመለከተ ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን እንደገና ተመልክቶ የማስተካከያ ምርጫ ያደርጋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ተቋማት መካከል ተፈጥሯል ስለተባለው ውዝግብ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ‹‹በግሌ ይህን ትልቅ ብሔራዊ ኃላፊነት ከተቀበልኩበት ጊዜ አንስቶ አሁን የምሰማቸውን አለመግባባቶች አላስተዋልኩም፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ፀብ ለአትሌት አይደለም ለፖለቲከኛም እየጠቀመ አይደለም፣ የኦሊምፒክ ፍልስፍና ራሱ ከዚህ ጋር ፍፁም የሚቃረን ነው፡፡ ጋዜጠኛም ከዚህ መሰሉ ወገንተኝነት የፀዳ መሆን ይጠበቅበታል፣ ካልሆነ ግን አደገኛ ነው፡፡ በአሠራር የማኮርፍባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩ እንኳ ለአገር ጥቅም እስከሆነ ድረስ እኔ ያልኩት ካልሆነ አገር ይፍረስ የምልበት አሠራር ሊኖር አይገባም፣ ስህተትም ነው፤›› ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ጸሐፊው ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም በበኩላቸው፣ ይህን ጉዳይ ይህን ያህል እንዲሰፋ ያደረገው መገናኛ ብዙኃኑ እንደሆኑና በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በኦሊምፒክ ዝግጅቱ ላይ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹የሁላችንም እምነት የጋራ ስፖርትና የጋራ አገር እንዳለን ነው፣ ተቋማት የግለሰቦች ፍላጎት ማሟያ መሆን አይገባቸውም፡፡ ተቋማቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው፣ መሥራትና ማድረግ ካለብንም እነዚህን ነገሮች ከግምት አስገብተን ካልሆነ ከባድ ነው፤›› ያሉት ሁለቱ የቀድሞ አትሌቶች ተቋማትን ተገን አድርገው አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦች ሊጠነቀቁ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡