በገነት ዓለሙ
ሁሉንም የልማት፣ የሰላም፣ የፍትሕ፣ የዴሞክራሲ፣ ወዘተ. ጥያቄዎች በአንድ ላይ የሚያስገብር የመኖር ወይም ያለ መኖር ጥያቄ ውስጥ ገብተናል፡፡ ኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ 19 ዛሬ የአገራችን ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የህልውና ጥያቄ ሆኗል፡፡ የሁላችንም፣ የመንግሥትም፣ የሕዝብም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች/ኃይሎችም ዋና ማነጣጠሪያ መሆን ያለበት ይህ ትልቁ የመኖርና ያለ መኖር ጥያቄ ነው፡፡ የሁሉም የትግል አስፈላጊነትና ፋይዳም በዚሁ በትልቁ አደራ ውስጥ የግድ መስተዋል ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ከዚህ የበለጠ አደራ፣ ከዚህ የበለጠ ግዴታ፣ ከዚህ የበለጠ ግዳጅ የለም፡፡
የምንነጋገረው ስለ1966 ወይም 1977 ዓ.ም. ዓይነት ረሃብና ችጋር፣ ስለየአገር ውስጥ የ‹‹እርስ በርስ›› ጦርነት፣ ወዘተ፣ እንዲሁም እነሱም ስለሚያስከትሉት ረሃብ፣ ችጋር፣ ዕልቂት፣ ስደት፣ በዚህም ምክንያትና አማካይነት የሚዘረጋውን የለጋሾችና የዕርዳታ ሰጪዎች እጅና ርብርብ በውጤትነት ስለሚያስከትለው የአደጋ የዕልቂት ዓይነት አይደለም፡፡ ስለምንታወቅበትና እንታወቅበት ስለነበረው ዓይነት ረሃብ አይደለም፡፡ በመላው ዓለም ያንዣበበውን አደጋ በትንሹ ማመላከት ይቻል እንደሆነ ለመሞከር፣ በወዲያኛው ሳምንት ዓርብ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የአሜሪካን የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል (CDC) የውስጥ ማስታወሻ ጠቅሶ ይፋ ያደረገውን መረጃ እንጥቀስ፡፡ ከ300 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ባላት አሜሪካ ውስጥ ከ160 ሚሊዮን እስከ 214 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሊያዙ፣ ከሁለት መቶ ሺሕ እስከ 1.7 ሚሊዮን አሜሪካውያን ሊሞቱ እንደሚችሉ፣ በተጨማሪም 925,000 የተደራጁ የሆስፒታል አልጋዎች ብቻ ባላት አሜሪካ ከ2.4 እስከ 21 ሚሊዮን አሜሪካውያን ሆስፒታል ተኝተው መታከም እንደሚያስፈልጋቸው ይፋ ተደርጓል፡፡
አሜሪካን፣ ጣሊያንን፣ ፈረንሣይን፣ ወዘተ የመሰለ አገር የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት በአጠቃላይ፣ የሕዝብ ጤና ጥበቃ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ፍጥርጥር የፈተነና ያጋለጠ አደጋ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምን አድርጎ ምን ሊያደርገን እንደሚችል መገመት እንኳን ገና አልተቻለም፡፡ ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ይፋ ከተደረገ ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የታየው ምላሽ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡ ‹‹በኪነ ጥበቡ›› እንደምንኖር፣ ዛሬም በዚህ ጉዳይ ጭምር፣ እግዚያብሔር ሳይደግስ አይጣላም እንደምንል፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነታችን ዋነኛው መሠረት ይኸው እንደሆነ ድንብርብሩና ቅጥአምባሩ የወጣው፣ እዚያው በዚያው የሚፈጠሩ ደመነፍሳዊ ምላሾቻችን ያሳያሉ፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት አባል አገር ናት፡፡ በድርጅቱ ዓለም አቀፋዊ የጤና ድንጋጌዎችም ትገዛለች፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተባለ ራሱን የቻለ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተቋቋመው በ1940 ዓ.ም. ቢሆንም፣ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሕጎቿ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ሕጎች ያህል ዘመናዊ ናቸው፡፡ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መቋቋምም የሚቀድሙ ናቸው፡፡
በዚህ መሠረት በተለይም ከ1939 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ፣ ‹‹ልዩነት በሌለው አኳኋን የሕዝብ ጤና መጠበቅና ማበረታታት›› የሕዝብ ጤና ጥበቃ ተብሎ ተቋቁሟል፡፡ ‹‹የሕዝብን ጤና የሚጎዱ በሽታዎች እንዳይነሱ ለመከላከል፣ ለማዳንና ለመቆጣጠር በሰፊው የተቋቋሙ የፅዳትና የሕክምናን ሥራዎች የሚጨምሩ ተግባራት የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሥራዎች ተብለው ተቋቋሙ፡፡›› ከዚህ በመነሳት በርካታ ዝርዝር ደንቦች ወጡ፡፡ ኳራንታይን በሽታ ሲነሳ የማሳወቁ ግዴታን የሚወስኑ ከሌሎች መካከል የሕመምተኛ መለያ ደንቦችን፣ የተላላፊ በሽታ ሕጎችን የመሳሰሉ ሕጎች የወጡት በ1940ዎቹ ውስጥ ነው፡፡ በ1934 ዓ.ም. እና በ1939 ዓ.ም. የወጡት የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሕጎችና በእነሱም አማካይነት የተደነገጉት ሌሎች ዝርዝር ደንቦች እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ፣ የአገር የሕዝብ የጤና ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍ ሆነው ኖረዋል፡፡ ኢፌዴሪ በአዋጅ ቁጥር 200/92 ከ52 ዓመታት በኋላ አዲስ የሕዝብ ጤና ጥበቃ አዋጅ ቢያወጣም፣ በተሻሩት ሕጎች መሠረት የወጡ ደንቦችም ከአዲሱ አዋጅ ጋር እስካልተቃረኑና በሌሎች ደንቦች እስኪተኩ ድረስ ተፈጻሚነታቸው ቀጠለ፡፡
የኢትዮጵያ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሕጎችና በእነሱም መሠረት የተቋቋሙት የሕዝብ ጤና ጥበቃ መሠረተ ልማቶች፣ ታህታይ መዋቅሮች ወይም ተቋማት ግን በተለይም በሕጎች መለዋወጥና ከሁሉም በላይ ደግሞ ወጥ አለመሆን፣ አንዱ በአንዱ ላይ መደራረብና መለጠፍ የተነሳ ጥናትና እርጋታ ሳይኖራቸው ቆይቷል፡፡ በዚህ መካከል ከሁሉም በላይ የተጎዳውና አፍርሶ መሥራት፣ መልሶ መገንባት፣ ሥልጣንና ተግባርን ለተለያዩና አዲስ እየፈረሱ ለሚቋቋሙ አካላት በማደላደል የዕድሜውን ያህል አለኝታ መሆን ያልቻለው የአገሪቱ የሕዝብ ጤና ጥበቃ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ማዕቀፍ ነው፡፡ የተለያዩ የአገሪቱ ሕጎች ‹‹የኅብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር አካል›› ብለው አዲስ የሰየሙትን የመንግሥት መሥሪያ ቤት ዋነኛ ሥራ የሆነውን የአደጋ መከላከል ሥራ የሰጡት፣ አሁን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተባለውና ተጠሪነቱ ለጤና ሚኒስቴር ለሆነው ተቋም ነው፡፡ ሲጀመር የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና እሱ የሚሠራው የተቆጣጣሪነት ሥራ ለምን የሕዝብ ጤና ጥበቃ መሆኑ ቀርቶ፣ መጀመርያ የጤና ጥበቃ አሁን ደግሞ የጤና ሥራ እንደሆነ የነገረን የለም፡፡ የተነገረው የለም፡፡ “Public Health” ለምን የሕዝብ ጤና መሆኑ ቀርቶ የኅብረተሰብ ጤና ተብሎ አዲስ እንደ ተተረጎመም የሚያውቁት የተወሰኑት ብቻ ናቸው፡፡
ከዓለም ጋር፣ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይል ጭምር አስተባብሮና እንደ አንድ ሰው ሆኖ አገራችን ላይ የታወጀውን የበሽታ ጦርነት የምንዋጋው በዚህ ሁሉንም የኢትዮጵያ የልማት የፍትሕ፣ ወዘተ ጥያቄዎች በሙሉ በአንድ ላይ በሚያስገብረው በዚህ የመኖር ያለ መኖር ጥያቄ ውስጥ ሆነን፣ የተቋም ግንባታ ችግሮቻችንንም ጭምር መለስ እያልን እየገመገምንና በዚያም እየተቆጨን መሆን አለበት፡፡
መንግሥት በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን ከማስታወቁ በፊት ኮሮና ቫይረስ የሕዝብ ጤና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ተብሎ በመታወጁ፣ ከተለያዩ ሚኒስትሮች የተውጣጣ ግብረ ኃይል አቋቁሟል፡፡ የትምህርት ቤቶችን ለአሥራ አምስት ቀናት መዘጋትና የመሳሰሉትን ዕርምጃዎች መወሰን የሰማነውም ከዚሁ አካል ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ የተለያዩ ዕርምጃዎች በተናጠልም በጋራም ሲሰጡ እየሰማን ነው፡፡
ሕዝብ የማስተባበር፣ በተለያዩ የፖለቲካ ምክንያቶች የተከታተፈውን ኃይል አንድ ላይ እንዲገጥም የማድረግ፣ ኮሮና ቫይረስን የመሰለ ጠላት የመዋጋት፣ በአገር ላይ ያንዣበበ የሕዝብ ጤና አደጋን የመከላከልና አመራር የመስጠት ግዳጅ ግን ከዚህ በላይ ይጠይቃል፡፡ የአገርን ሀብትና የሰው ኃይል አስተባብሮ ለመምራት፣ የሕጎቻችንን ሙሉ አቅምና ኃይል አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የሕዝብ ጤና ጉዳይ ልዩ ‹‹ፀጋ›› ያለው መሆኑ አንዱ ትልቁ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ሥልጣን ያባልጋልና ፍፁማዊ ሥልጣን ደግሞ ይበልጥ ያባልጋልና ለመንግሥት አገር የሚሰጠው በሽታን የመዋጋት ሥልጣን መረን የወጣ ሊሆን አይገባም፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በዚሁ አጋጣሚ ሰሞኑን እንዳሉት ኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ የተጋረጠ ከፍተኛ የህልውና አደጋ የመሆኑን ያህል፣ በዚያው ልክ ደግሞ መልካም አጋጣሚና በጎ ነገርም አለው፡፡ ሕግ ማስከበርና ሰላም የማስጠበቅ የመንግሥት አቅምና አቋም ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ በምናደርገው ለውጥና ሽግግር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች እክል ቢያጋጥመውም፣ ይህ ክፉ የኮሮና ቫይረስ አጋጣሚ በሕግ አማካይነት አደጋ የመከላከልን፣ ሕዝብ የማስተባበርን፣ ተቋም የመገንባትን ልዩ አጋጣሚ ይዞ መጥቷል፡፡ የሕዝብ ጤና ጥበቃ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን ሕጎቻችንን ወደ መጠቀም የምንገባው ግን ሲጀመር እንዳልነው፣ ሁሉንም የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጥያቄዎች በአንድ ላይ የሚያስገብር የመኖር ወይም ያለ መኖር የህልውና ጥያቄ ውስጥ ስለገባን ነው፡፡
የሕዝብ ጤና በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ውስጥ ልዩም፣ ልዩ ልዩም ቦታ አለው፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና በሌሎችም ሕጎች ውስጥ ያለው ቦታ ተመሳሳይና ከዚያው ምክንያት የተቀዳ ነው፡፡ ጤና በገዛ ራሱ ምክንያት (በሕገ መንግሥቱ በተለያዩ አንቀጾች ለምሳሌ 35፣ 36፣ 41፣ 42፣ 44፣ 89፣ 90፣ 92 እንደ ተደነገገው) መብት ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ጤና በሌሎች መብቶች መገልገል ላይ ጉዳይ አለው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26/3 እንደተደነገገው በግል ሕይወት የመከበር መብት መገልገል ላይ ገደብ ሊጣል የሚችለው፣ የሕዝብ ጤናን በመጠበቅ ዓላማዎች ላይ በተመሠረተ ሕግ ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ ጤና የዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች አንዱ የውኃ ልክ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወንጀል ሕጉ (የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ጀምሮ) በጤና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚደነግግ፣ የሚከለክልና የሚቀጣ ራሱን የቻለ ሰፊ ርዕስ አለው፡፡
በአደጋ ላይ ያለን ሰው አለመርዳትን ጨምሮ (ተራ ሰውንም የሕክምና ባለሙያንም) እስከ የሰው/የእንስሳት በሽታ ማሰራጨት ድረስ የሚቀጣ የወንጀል ሕግ ያለው አገር መንግሥት ሕዝብ የመታደግ ሳይሆን፣ ሕዝብን ከአደጋ መከላከል አሳልፈው ሊሰጡት የማይገባ በቸልተኝነትም ሆነ ሆን ብለው ሊተውት የማይችሉት ግዴታ አለባቸው፡፡
ሕገ መንግሥቱ ከዚህም በላይ ለመንግሥት ከፍተኛና ትልቅ የክፉ ጊዜ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ለአስፈጻሚው አካል የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን የሚሰጠው፣ የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲፈጠር፣ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ሲመጣ ብቻ አይደለም፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ማለት በሽታን አይጨምርም፣ ይጨምራል የሚል ጣጣ ውስጥ እንድንገባም አያደርግም፡፡ የሕዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት ጭምር የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ መደንገግ ይችላል፡፡ በአንቀጽ 93 የተደነገገው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የመንግሥት ሥልጣን ብዙ ዝርዝር ያለው፣ በዓለም አቀፋዊ ሕግ (በዓለም አቀፋዊው የጤና ድንጋጌዎች 2005) ጭምር የሚገዛ ዝርዝር ጥብቅ መጠበቂያና መከላከያ ገደቦች ያሉበት ሕግ ነው፡፡
ዛሬ ዓለምንና ኢትዮጵያን ጭምር ያጋጠማቸው የሕዝብ ጤና ጥበቃ አደጋ እስከ ዛሬ ድረስ ታይቶ የማይታወቅ፣ አምሳያም ተወዳዳሪም የሌለው ስለመሆኑ በግልጽና በይፋ በመላው ዓለም እየተነገረ ነው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ልዩ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ እንደ ተደነገገው ‹‹በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል›› ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ የተለያየ ነው፡፡ በነባሩ የዓለም የጤና ድርጅት አባል ከሆንበት፣ የመጀመርያውን የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ካቋቋምንበት ከ1940 ዓ.ም. ጀምሮ በዘረጋነው የሕዝብ ጤና ጥበቃና የድንገተኛ/የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ዕርምጃና ተቋም ግንባታ ላይ አዛላቂ ሥራ፣ አልሠራንም፡፡ ይልቁንም መንግሥት በተለዋወጠ ቁጥር የተሠራው የአፍርሶ መገንባት ሥራ የውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ከመሆን በላይ ጥፋት የፈጸመ ሥራ ነው፡፡
ከየካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው አዲሱና ከለውጡና ከሽግግሩ በኋላ የወጣው የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2012 ራሱ፣ በአቅሚቲ በሕዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ጉዳይ ላይ የግብር ይውጣ ሥራ ሠርቷል፡፡ በአንቀጽ 72/2 እንደ ተደነገገው የኳራንቲንና የተላላፊ በሽታዎችን ቁጥጥር ሥራ (ለምሳሌ) ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ባለ ተቋም እንዲሠራ ሥልጣንና ተግባር አስተላልፏል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ይህን በመሰለ የሕግ አወጣጥና የተቋም ግንባታ ዝብርቅርቁ የወጣ፣ ቅጣ አንባሩ የጠፋ ሥራ ውስጥ የሕዝብ ጤና ጥበቃ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ወይም የድንገተኛ አደጋ ሥራ ባለቤትና የበለፀገ አሠራር አጥቷል፡፡ ተመሳሳይ ምናልባትም የባሰ አደጋ ውስጥ ገብቶ፣ ከእሱም የባሰ መጫወቻ ሆኖ፣ ፈርሶና ተበትኖ ግብርና ሚኒስቴር ውስጥ ተወሽቆ፣ በስብሶና ሞቶ እንደገና ተነስቶና በከፊል ህልውና አግኝቶ፣ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ኮሚሽን የተባለው ተቋም የቀድሞውን የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን በክፉ ጊዜ በክፉ አጋጣሚ ያካበተውን ልምድና ፍጥርጥር መልሶ ማግኘት አልቻለም፡፡ ከእሱም መማር፣ የእሱንም ልምድ መውሰድ ያልቻልነው በሕዝብ ጤና ጥበቃ የድንገተኛ አደጋ ዘርፍ አኳያም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ሕግና ሰላም ማስከበር ተሳነው በሚባል የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ፣ ሕግ የማስከበር ሥራው አፀፋዊ ፕሮፖጋንዳ እየተሠራበት አስቸጋሪ ሁኔታ በገባበት አጋጣሚ ውስጥ፣ ለሰማይ ለምድር የከበደ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ድንገተኛ አደጋ ውስጥ ገብታለች፡፡ አደጋው የበርካቶችን አንድ መሆን ‹‹ድንገት›› ያመጣ ቢሆንም፣ በዚህ የጋራ የአደራ ግቢ ውስጥ የመገናኘታችንና የመዋል የማደራችን መገለጫ ግን በ‹‹እጅ መታጠብ›› ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም፡፡ ‹‹እጅ መታጠብ›› ለአገር ተቆርቁሮ እንስፍስፍ ብሎ ትግሉ ከዚህ ይጀምራል እያሉ የትግል አጋርነትን መግለጫ ብቻ አይደለም፡፡ መግለጫ ላይሆን ይችላልም፡፡ ‹‹ከደሙ ንፁህ ነኝ›› ብሎ መልዕክት ማስተላለፊያ (አስተላልፌ ነበር የሚሉበት) ቅኔም ሊሆን ይችላል፡፡ እጅ መታጠብ ውኃ ይፈልጋል፡፡ የውኃ ችግራችን በተለመደው የሕግ ማስከበር አሠራር ሊመጣ አልቻለም፡፡ መብራት ከመጋቢት መባቻና ከመርዶው ወዲህ አጋጣሚውን አግኝቶ ብፈልግ እመጣለሁ፣ ብፈልግ እቀራለሁ ማለት ጀምራለች፡፡ ኮሮና ቫይረስ አውሬነትን ከነጋዴው ውስጥ ቀስቅሶ ከማስነሳት አልፎ፣ በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል የሚል አታላይና ዘራፊ አዲስ ነጋዴ ፈጥሯል፡፡
ስብሰባን የሚገድብ፣ ፐብሊክ ስፔሶችን (ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውና የሚገናኝባቸውን ቦታዎች) የሚወስንና መራራቅን የሚያበረታታ፣ ቤት መቆየትን የሚፈቅድ፣ ቀጠሮን የሚያራዝምና የመሳሰሉ ዕርምጃዎች በየቦታውና በተናጠል ቢወስዱም፣ ብዙዎቹ ምናልባትም ሁሉም የየቦታው የቁጥቁጥ ዕርምጃዎች ናቸው፡፡ በዚህ የየብቻ፣ የየግልና የየቅል ዕርምጃ ቢሆን አብዛኞቹ የሕዝብ መገናኛ ሥፍራዎች አልተነኩም፡፡ የትራንስፖርት ሠልፉ፣ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች ውስጥ መታጨቁ፣ የባንክ ወረፋው ገና ያልተነካ የቤት ሥራ ነው፡፡ ይህን የሚያስተባብር አካል መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ኃይል ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በላይ ተጨማሪ አባላትና ሥልጣን ያስፈልገዋል፡፡ መንግሥት ተጨማሪ ሥልጣን ተጨማሪ መላ ተጨማሪ ብልኃት ያስፈልገዋል፡፡
የፊት መሸፈኛ ጭንብል ወደ ውጭ መላክ አቁመናል፡፡ አልኮል (ሲፒርቶ) እጥረት የለም በሚባልበት አገር እጥረትን፣ ጥራትንና ዋጋን በንግድ ሚኒስቴር የተለመደና የዘወትር ተግባር አማካይነት መቋቋም ያስቸግራል፡፡ መንግሥት በሕግ መሠረትና ሕግን ተከትሎ፣ ከሕግም በታች ሆኖ እነዚህን አስፈላጊ ዕቃዎች በዋጋቸውና የተወሰነውን የትርፍ ሕዳግ ጨምሮ ከተካበቱበትና ከተከማቹበት ወስዶ ለሕዝብ የማከፋፈል ሥልጣን ሊኖረው ይገባል፡፡ ያልተገባ ጭማሪ ደግሞ ስግብግብ ነጋዴ፣ ወዘተ እያሉ መጮህ ሕግ ማስከበር አይደለም፡፡ ኮሮና ቫይረስንም አይዋጋም፡፡ መንግሥት ሕዝባዊ እንቅስቅሴም መፍጠር አለበት፡፡ ኮሮና ቫይረስን የመዋጋት የሕዝብ ጤና ጥበቃን፣ አደጋና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን ለመመከት በጎ ፈቃደኝነት ዋናው መሣሪያው ነው፡፡ ማንም ሳይጠራቸው ይህን የመሰለ መለስተኛ አደጋና መፈናቀል የሕዝብ እንባ የሚያሰባስባቸው በጎ ፈቃደኞች፣ ከፓርቲና ከብሔርተኛ ወገንተኛነት ውጭ ሆነው ሊጠሩና ሊደራጁ ይገባል፡፡ ‹‹የሕዝብ ጥቅም›› የሚባል የማይማገጥበትና የማይነገድበት ነገር መምጣት ያለበት ዛሬ ነው፡፡ ይህ ብዙ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያን መላ ሕዝቧን የማዳን ተግባር ነው፡፡
በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የመንግሥት ሥልጣን ግን ከሕግ በላይ መሆን የለበትም፣ በሕግ መደንገግ አለበት፡፡ መሠረታዊ የቁጥጥርና የመንግሥት የሥልጣን አካላትን እርስ በርስ የመቆጣጠርና የመገናዘብ (ቼክ ኤንድ ባላንስ) መጨመር አለበት፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ማለትም ከሕዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ውጪ መውጣት የለበትም፡፡ እጠብቀዋለሁ፣ ከአደጋ እከላከለዋለሁ የሚለውን የሕዝብ ጤናና ሰላም ራሱን የሕዝብ መብትን መጣስና መገሰስ የለበትም፡፡
የሕዝብ ጤና አደጋ ላይ ነው፣ የጤና ባለሙያዎች ከማንም በላይ ለዚህ ጉዳይ ፊታውራሪዎች ሆነው ከመንግሥት ጎን መሠለፍ፣ ሌሎች ከሥራ ውጭም ከአገር ውጭም በሌላ ሥራ ላይ የተሰማሩትን የጤና ባለሙያዎች በዘመቻ መጥራት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ሐሳቦችን የማፍለቅ የእናት አገር ጥሪ አለባቸው፡፡
እስካሁን በበሽታው የተያዙት ሰዎች ብዛት ገና በጣት የሚቆጠር መሆኑ ብቻ የሚያፅናና፣ እውነትም ነው ተብሎ የሚተማመኑበት አይደለም፡፡ አገራችን ገና ምርመራ የሚባል ነገር ያልጀመረች አገር ናት፡፡ በሽታው የተገኘባቸውን ሰዎች ለይቶ የማቆየትና የማከም አቅማችንም ሁለቱም እኩል አወዛጋቢም፣ የሰማይና የምድር ያህል ከባድ ነው፡፡ ከማከሙ ይልቅ ለይቶ የማቆየቱ ደግሞ ሲበዛ የምንታማበት ተግባር ነው፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ ከሰሞኑ እንዳሉት እሳትን በእውር ድንበር ማጥፋት አይቻልም፡፡ ኮሮና ቫይረስን የመታገል ሥራ ‹‹Test‚ test, test,. . .›› ነው ያሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ መርምሮ ለይቶ ማቆየት የበሽታውን ሰንሰለት ይበጥሰዋል፡፡ ተለይተው የታወቁ ሰዎችን የግንኙነት ዱካ ተከትሎ መለየትም እሳት የማጥፋት የአገር ጥሪ ዋነኛ መነሻ ነው፡፡ የመንግሥትም ዋነኛና አጣዳፊ ተግባር ይህንኑ መምራትና ማስተባበር ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡