ከኳታር የተገኘው የ570 ሚሊዮን ብር የኩላሊት ሆስፒታል ድጋፍ በቨርቹዋል ተፈርሟል
በመላው ዓለም እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ በተጎጂዎች ላይ እያደረሰ ከሚገኘው የጤና እክልና የሞት አደጋ ባሻገር፣ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል ከባድ ኪሳራ እያስከተለ ይገኛል፡፡
በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሰኞ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት ቤቶች፣ ስብሰባዎችና የስፖርት እንቅስቃሴዎች ለሁለት ሳምንት እንዲገቱ መንግሥት መወሰኑን መግለጻቸውን ተከትሎ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባወጣው መግለጫ፣ የትኞቹንም የኢንዱስትሪ ፓርኮች መጎብኘት እንደተከለከለ አስታውቋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንዳለው የትኛውም ዓይነት ጉብኝት መከልከሉ ብቻም ሳይሆን፣ ወደ ፓርኮቹ የተጓዘ ሰው ቢኖር እንኳ ራሱን ለሁለት ሳምንት በማግለል እንዲቆይ አሳስቧል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚንቀሳቀስ ግብረ ኃይል በማቋቋም የማዘዣ ክፍል በእያንዳንዱ ፓርክ ውስጥ እንዲደራጅ እንደሚደረግ ከማስታወቁም ባሻገር፣ በኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ደረጃም ለመረጃ ልውውጥና ግንኙነት ሥራዎች መስተጋብር የሚንቀሳቀስ ማዕከል እንዲያደራጅ ገልጿል፡፡
እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ በመንግሥት ኃላፊዎችና ተቋማት ሲገለጽና ሲነገር ቢሰነብትም፣ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭትና መስፋፋት አጋዥ የሆኑ ምቹ ክንውኖች በመንግሥት አካላት ጭምር ሲፈጸሙ በአደባባይ መታየታቸው መንግሥትን እያስተቸው ይገኛል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የብልጽግና ፓርቲ አባላት በአማራ ክልልና በድሬዳዋ በአዳራሽ ተሰብሰበው የታዩት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የትላልቅ ስብሰባዎች ክልከላ መደንገጉ ከተነገረ በኋላ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲ አመራሮችም በዚሁ መሰል ድርጊት ሲሳተፉ የታዩበት አጋጣሚም ስለበሽታው መተላለፊያ መንገዶች የአመለካከት ችግሮች መኖራቸውን የሚያመላክት ነው፡፡
በአንፃሩ በኳታርና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የ570 ሚሊዮን ብር ወይም የ18 ሚሊዮን ዶላር የዕርዳታ ስምምነት ገጽ ለገጽ የሚፈረምበት ሥነ ሥርዓት ታጥፎ በቨርቹዋል እንዲደረግ ያስገደደው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እንዳይዛመት ከማሰብ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ስምምነቱ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሲደረግ ጋዜጠኞችም እንዳይታደሙ የተደረገው የዓለም ጤና ድርጅት በሚጠይቀው መሠረት የማኅበራዊ ተራርቆትን ለማክበር ሲባል እንደሆነ ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የኳታር መንግሥት የለገሰው ዕርዳታ ለኩላሊት ሆስፒታል ግንባታና የቁሳቁስ ማሟያ የሚውል ሲሆን፣ 77 የተኝቶ መታከሚያ ክፍሎች፣ ስምንት አልጋዎች የሚኖሩት አንድ የጽኑ ሕሙማን ማዕከል እንዲሁም አራት የቀዶ ጥገና ክፍሎች፣ አሥር የተመላላሽ ታካሚዎች ክትትልና ማስተናገጃ ክፍሎችን ጨምሮ በጠቅላላው 106 የኩላሊት ዕጥበት መስጫ ክፍሎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል፡፡
በአንድ ሳምንት ውስጥ በኢትዮጵያ ያሻቀበው የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር፣ በአፍሪካም በተመሳሳይ ወቅት ከ700 በላይ ተጠቂዎችን በ34 አገሮች ውስጥ ያዳረሰው እስካለፈው ዓርብ መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በነበረው አኃዝ መሠረት ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ጽሕፈት ቤት ይፋ እንዳደረገው፣ የ147 ተጠቂዎች ቁጥር የነበረው አኃዝ በቀናት ልዩነት ወደ 700 ሲያሻቅብ በመላው ዓለምም የበሽታው ሥርጭት ከ250 በላይ የደረሰው እስከ መጋቢት 11 ቀን በነበረው የቆይታ ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ከ10,500 በላይ ሟቾች የተመዘገበቡት ይህ የበሽታ ሰሰድ፣ ከ100 ሺሕ በላይ ማገገም የቻሉበትም አጋጣሚ አስተናግዷል፡፡ በመሆኑም ከ250 ሺሕ የበሽታው ታማሚዎች ውስጥ ከ100 ሺሕ በላይ ማገመም መቻላቸው ሲታወቅ፣ በተለይ በቻይና በተመዘገበው መሠረት ከ81 ሺሕ ተጠቂዎች ውስጥ 71 ሺሕ አገግመዋል፡፡ በአንፃሩ ጣልያንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገሮችን እያመሰ የሚገኘው ይህ በሽታ በሺዎች ለሚቆጠሩ ተጠቂዎች ሞት መንስዔም ሆኗል፡፡ በጣልያን ከ3,400 በላይ የሟቾች ቁጥር ሲመዘገብ፣ በኢራን ከ1,400 በላይ እንዲሁም በስፔን ከ1000 በላይ ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለሞት መዳረጋቸው የተመዘገበው እስካለፈው መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡