Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በኮሮና አሳቦ ዋጋ ማናር እሳትን ማፋፋም

የገበያና የግብይት ሥርዓታችን፣ የሸመታ ባህላችን የንግድ ‹‹ባህላችን›› ምን ዓይነት ገጽታ እንዳለው ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ከሰሞኑ ክስተት በሚገባ የታዘብን ይመስለኛል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ይፋ በተደረገ ቅፅበት፣ የአገራችን ገበያም እውነተኛ ባህሪውን ገላልጦ አሳይቶናል፡፡ ይህንን በልበ ሙሉነት መናገር የምንችልበት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክስተት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የአገራችንን የንግድ ሥርዓት ብልሹነትና የሥነ ምግባር ጉድፈት በሰፊው ያየንበት፣ ነግ በእኔን እንድንረዳ ዓይናችንን የከፈተ አጋጣሚ እያስተናገድን እንገኛለን፡፡

አጋጣሚ ተጠቅመው ያለፉበትን ትርፍ የማስላት ልምድ ያላቸው፣ ግርግር ሲያመቻቸው በሰው ቁስል እንጨት የሚሰዱትን ዓየናቸው፡፡ አገርና ሕዝብ መደጋገፍና መተባበርን እጅጉን በሚፈልጉበት ወቅት፣ አስደንጋጩ እንግዳው ወረርሽኝ ዓለምን በሚያምስበት በዚህ የብሔራዊ አደጋ ክስትት ወቅት፣ አጋባሽ አመላቸው ገንፍሎባቸው ገበያውን ለማተራመስ ጥረዋል፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ተፈላጊ በሆኑ ምርቶች ላይ ለሸክም የከበደ ዋጋ ሲጭኑበት ማየት ያሳምማል፡፡ ከቫይረሱ መከሰት ባልተናነሰ፣ ዋጋ ሸቅበው፣ ምርት ሸሽገው ለመጠቀም የሚተጉ ነጋዴዎች ማን አለብኝ ማለታቸው ያስተዛዝባል፡፡ ደግነቱ መንግሥትም እንደ ወትሮው በዛቻና ማስጠንቀቂያ አልተዋቸውም፡፡ እየዞረ ማሸጉ ትምህርት ከሆናቸውም አንድ ነገር ነበር፡፡

በየአጋጣሚው እየተጠቀሙ፣ የሰው ቆዳ በመግፈፍ የመበልፀግ ክፉ ጠባይ የተጠናወታቸው ነጋዴዎች ከዚህ ተግባራቸው ይቆጠቡ ዘንድ ከላይ እስከ ታች ቢነገር ቢዘከር ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው የመንግሥትን ነባር አካሄድ የተረዳው ልምዳቸው የሰጣቸው የልብ ልብ ውጤትና ነፀብራቅ ነበር፡፡ በሰው ችግር ከብሮም አትርፎም መኖር የሚቻለው ግን አገር ስትኖር ነው፡፡

በስግብግቦች ተግባር ሁሉም የንግዱ ማኅበረሰብ ሊወቀስ አይችልም፡፡ ክፉ ልማድ የተበተባቸው ነጋዴዎች ግን የበጎዎችና የቅኖችን ስም ማስነሳታቸው ያሳዝናል፡፡ ያውም በዚህ ቀውጢ ወቅት፡፡ እጥረትም ችግርም ቢኖር እንኳ መነጋገርና አቅረቡልን ማለት ሲቻል ያለውን ጥቂት ምርት መሸሸግና ዋጋ መጨመርን ምን አመጣው? ገና ለገና የምርት እጥረት ተፈጥሯል በሚል አወናባጅ ወሬ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ በወረርሽኝ ወቅት የሚታመሰውን ሕዝብ ይባስ ሆድ ማስባስ ከማሳዘንም በላይ ነው፡፡ ከወረርሽኙ ተለይቶ የማይታይ ክፋት ነው፡፡ ወቅትና አጋጣሚ ጠብቀው በሰው ችግር ለመክበር እንቅልፍ የሚነሳቸውን ነጋዴዎች አደባባይ አውጥቶ ይሄን ያየህ ተቀጣ የሚል ዕርምጃ ምነው ዳግም በመጣ ያሰኛል፡፡

ክፉዎችና አመለኞች በማስጠንቀቂያ ስለማይገቱ የቁጥጥር ሥራው በሚገባ መጠናከር አለበት፡፡ ችግሩ በአገር እንደመጣ ዓይተው፣ ሥነ ምግባራዊ ግዴታቸውን በሚገባ የተወጡ መልካሞችን ማመስገን ተገቢ ነው፡፡ የንግድ ሥራ ሐቅና ለሰው ችግርም ደራሽ መሆንን ያሳዩ በርካቶች ታይተዋል፡፡ እነዚህን ያብዛችሁ ማለትም ይገባናል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች መካከል ንክኪና ትንፋሽ ይጠቀሳሉ፡፡ በመሆኑም ዜጎች ንክኪና መተፋፈግን ከሚያስከትሉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠቡ፣ እንደ ከርሞው በአጀብ ከመሰባሰብ፣ ትምህርት ቤት ከመሄድ፣ ስፖርት ማዘውተሪያዎችን ከማጨናነቅ በየቤት መሰንበትን፣ መራራቅን፣ የግል ንፅህናን በሚገባ መጠበቅን፣ አለመጨባበጥና አለመሳሳምን ወዘተ. የሚፈልግ በሽታ ቤታችን በመግባቱ አብሮነታችን ላይ የመጣ፣ ማኅበራዊ ቁርኝታችንን የሚጋፋ ወረርሽኝ መንሰራፋቱ ያስደነግጣል፡፡

በመሆኑም ሰዎች ለራሳቸው ደኅንነት ተብሎ አታድርጉ የተባሉትን አድርጉ የተባሉ ይመስል በየጎዳናው የሚሠሩትን ያየ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አይባሉ ነገር ወረርሽኙ አደገኛና ምኅረት የለሽ ነው፡፡ ምክር አለመስማት ግን በገዛ ራስ ላይ ጥፋትን መጋበዝ ነውና የተከለከለውን ባለማድረግ ለሌሎች ዜጎች እናስብላቸው፡፡ ጣልያን ያሳየችን ይህንኑ ነው፡፡ ሕዝቡ በሽታውን ናቀው፣ አናናቀው፡፡ ኮሮና ግን አነቀው፡፡ ሳምንት ባልሞላ ጊዜም ሺዎችን ለሞት፣ አሥር ሺዎችን ለአልጋ ቁራኛነት ዳረጋቸው፡፡ ምድረ ጣልያን የጦር አውድማ መስላ፣ ከመላ አገሩ መውጣትም መግባትም ተከልክሎ፣ ሕዝብ በየቤቱ እሥረኛ የሆነበት መጥፎ ዕድል የገጠመው በገዛ ራሱ መዘናጋትና ቸልታ ነውና እኛም ከሌላው ሰቆቃ በመማር ከችግር ማምለጥ ይጠበቅብናል፡፡

 ወረርሽኙን ያለ ብዙ የከፋ አደጋ ለማለፍ የጤና ተቋማትን ምክር መስማት የህልውና መሠረት ነው፡፡ ከሰሞኑ ቀናት በተለያዩ የሕዝብ ፋርማሲዎች የታዘብነውና የንፅህና ማጠቢያ ቁሳቁሶችን ለመግዛት አንዱ በሌላው ተደራርቦ፣ ሠልፍ ይዞ ሲታይ በሽታ ሊወረው አሰፍስፎ የሚጠብቀው ሕዝብ አይመስልም ነበር፡፡ ይህ አድራጎት ለራስም ለሌሎችም አለማሰብና አለመጨነቅ ያመጣው ግድየለሽነት ነው፡፡

ቫይረሱ በንክኪ ይተላለፋል እየተባሉና በዚህ ጦስም በሽታ እየሸመቱ የንፅህና መጠበቂያ ለመግዛት መገፋፋት ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? መንግሥትም ቢሆን እንዲህ ያለ አጉራ ዘለልነትን መቆጣጠርና ሥርዓት ማስያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ኋላ ዋይታው ለመንግሥትም ጭምር በመሆኑ ሥርዓትና ምክር የማይገዛውን ማስገደድ ለሌላውም ዋስትና ነውና የመንግሥት መዘናጋት ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ መንግሥት ከልፈፋ መውጣት አለበት፡፡ እንደ ምክሩና ማስጠንቀቂያው ሁሉ በተግባር የተደገፈ ዘመቻም መጀመር አለበት፡፡ ሰሞኑን የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች የስም ዝርዝራቸውን ለማየት ሲጋፉና አንዱ በአንዱ ላይ ሲታከኩ ማየትም፣ በአገሩ መንግሥት የለም ወይ ያሰኛልና ይታሰብበት፡፡

ተሳስቦና ተረባርቦ ይህን ፈታኝ ጊዜ ማለፍ፣ ከበሽታው መነሻ ከቻይና ሕዝብ መማር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ሕዝቡና መንግሥት ተባብረው ከባዱን ፈተና በድል እየተወጡት ነው፡፡ እኛ ግን በዚህ ቀውጢ ጊዜ እንኳ ማስቀደም ያለብንና የሌለብን ጉዳይ ሊታየን አልቻለም፡፡ ስብሰባ አቁሙ በተባለ ማግሥት የመንግሥት ኃላፊዎችና የካድሬዎች ጋጋታ ሲታይ፣ ሕዝብና ነጋዴ ላይ ብቻ መጮሁ ውኃ መቸለስ ይሆናል፡፡ ስለዚህ መንግሥትም መዋቅሩን ይመልከት፡፡ ከታች እስከላይ ተናቦ መሥራትና ሕዝብን ማሠራት ላይ ቅድሚያ ይስጥ፡፡

ይህን ካልን በበጎነታቸው ልንጠቅሳቸው የሚገቡ ተግባራትንም ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል፡፡ በየአካባቢው የእጅ ማስታጠቢያ በማሰናዳት ውኃና ሳሙና ለአላፊ አግዳሚው በማቅረብ የሚያስታጥቡ በጎኛዎችን ማየትም ያጽናናል፡፡ አስፈላጊ ዕቃዎችን በነባር ዋጋ ሲሸጡና ከልክ ያለፉ የገፍ ሸማቾችን በመከላከል ግብይቱን ሥርዓት ሲያሲዙ ያየናቸው ፋርማሲዎችና ሱፐር ማርኬቶች አስተማሪዎቻችን ናቸው፡፡ ልብ ላለው ተገቢውን ትምህርት ለግሰዋልና መመሥገን አለባቸው፡፡ የበጎ አድራጎቶች ከዚህም በኋላ ሊቀጥሉ፣ ሊበራከቱ ይገባቸዋል፡፡ ራሳችንን በመጠበቅ ይህንን የእሳት ጊዜ ለመሻገር እንትጋ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት