የኮሮና ቫይረስ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሥጋት ሆኗል፡፡ በኢኮኖሚያቸው የፈረጠሙ አገሮችን ከመፈታተን አልፎ የበረታ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ በዚህ ቫይረስ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ ተቀዛቅዟል፡፡ ከዚህም በኋላ ጦሱ ብዙ መዘዝ እንደሚኖረው የሚገመት ሲሆን፣ በተጨባጭም እየታየ ነው፡፡ በየዕለቱ ከአራቱም የዓለማችን ማዕዘናት የሚሰማው ዜና በቫይረሱ እየተቀጠፈ ያለውን የሰው ሕይወት ማስቆም አለመቻሉን ነው፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት የሞት ሪፖርት እየቀረበ ነው፡፡ ይህም ማቆሚያውን ለመለየትና ነገንም መተንበይ አለመቻሉን ነው፡፡ የናጠጠ ሀብት ያላቸው አገሮች ይህንን ቫይረስ ማስቆም ባለመቻላቸውና ዜጎቻቸውን ለመታደግ እያደረጉ ያሉትም ጥረት ባለመሳካቱ፣ ጭንቅ ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ከረፈደ አፍሪካን ቀስ በቀስ ማዳረስ ይዟል፡፡ ኢትዮጵያም የቫይረሱ ተጠቂዎች መኖራቸውን ሪፖርት አድርጋለች፡፡ መንግሥት ድንበር ተሻግሮ ኢትዮጵያ የደረሰውን ቫይረስ ለመከላከልና የተጠቂዎችን ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ለ15 ቀናት ትምህርት ቤቶች መዝጋትና ሌሎች ለመከላከል ያስችሉኛል ያላቸውን ውሳኔዎች ላይ ደርሷል፡፡ በተግባር እንዲውሉም እያደረገ ነው፡፡ በመንግሥት የተወሰዱት ዕርምጃዎች ውጤታቸውን ለመተንበይ ባይቻልም፣ ዜጎች በቂ መረጃ እንዲኖራቸው እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ከተገለጸበት ዕለት ጀምሮ፣ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያልተገቡ ድርጊቶች ታይተዋል፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል ያስችላሉ ከተባሉ ቁሳቁሶች ጀምሮ ምግብ ነክና ሌሎች የግብርና ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ለውጥ፣ ሸማቹ በአደባባይ ወጥቶ ድምፅ እያሰማበት ነው፡፡ መንግሥት እንዲህ ያለ ሁኔታ መፈጠሩን በመረዳት አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ የግብይት ሥርዓቱን ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ መንቀሳቀስ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ባለፉት በጥቂት ቀናትም የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ፣ ያላግባብ ምርት ያከማቹ፣ አጋጣሚውን ተጠቅመው ያለ ፈቃድ የተለያዩ ዕቃዎችን ሲሸጡ ነበሩ የተባሉ የንግድ መደብሮች ታሽገዋል፡፡ የተለያዩ ዕርምጃዎችም ስለመወሰዱ እየተገለጸ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃ ገበያውን አረጋግቶታል ወይ የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ አካሄዱ እንዴት ይሆን የሚለውም ይነሳል፡፡ ከዚህ ሰሞናዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ምን እየተሠራ እንደሆነ፣ ከዚህም በኋላ ገበያውን ለማረጋጋትና በአጠቃላይ ከሰሞኑ ዕርምጃ አወሳሰዶች ጋር በተያያዘ ዳዊት ታዬ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሰው ኃይል ዳይሬክተርና የሕዝብ ግንኙነት ተወካይ ከሆኑት አቶ ዳንኤል ሚኤሳ ጋር አጭር ቆይታ አደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡– የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ ከተሰማ በኋላ በገበያ ውስጥ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠርና አጠቃላይ የግብይት ሒደቱን ለመከላከል ተብሎ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የጀመራችሁት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? እንዴትስ እየሠራችሁ ነው?
አቶ ዳንኤል፡– ዓርብ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሥራችንን ለመጀመር መነሻ ሆኖናል ማለት ይቻላል፡፡ መግለጫው ከተሰጠ በኋላ የከተማው አስተዳደር የቢሮ ኃላፊዎችና ጠቅላላ ካቢኔው ተሰብስቦ፣ ቅዳሜ ጠዋት ይህንን ተግባር የምንመራበት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ልዩ የሆነ ግብረ ኃይል ተዋቀረ፡፡ ልዩ ግብረ ኃይሉ ከማዕከል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ነው የተዋቀረው፡፡ ግብረ ኃይሉ የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና በየወረዳው ያሉ አመራሮች የተካተቱበት ነው፡፡ ዳይሬክተሮች፣ ባለሙያዎችና የሕግ ባለሙያዎች ጭምር ተካትተውበታል፡፡ የጤና ባለሙያዎችም አሉበት፡፡ በዋናነት ደግሞ ለዚሁ ጉዳይ የተመደቡ ሠራተኞቻችን በሙሉ በዚህ ግብረ ኃይል እንዲሳተፉ አድርገናል፡፡ ይኼ ግብረ ኃይል በወዲያኛው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት በቢሮ ደረጃ በጋራ ሆኖ፣ በወረዳ ደግሞ ሕዝብን አወያይቷል፡፡ ከ9,700 በላይ ከሚሆኑ ሸማቾችና የንግድ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተናል፡፡
ሪፖርተር፡– ውይይቱ ለምን አስፈለገ? ይዘቱስ ምን ነበር?
አቶ ዳንኤል፡– እንዴት አድርገን ነው መሥራት ያለብን የሚለውን ይዘን ለመፍትሔ የሚሆኑ አሠራሮችን ለማመላከት ነው፡፡ ችግሮች ቢያጋጥሙ እንኳን እንዴት መፍታት አለብን በሚለው ላይ ነው፡፡ ይህንን ውይይት ካደረግን በኋላ ከሰኞ ጀምሮ ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ ቀጥታ የንግድ ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ሥራ ውስጥ ገብተናል፡፡ ይህንንም ስንጀምር ከኅብረተሰቡ የደረሰንን ጥቆማዎች መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የዋጋ ጭማሪዎች በተጨባጭ ስለመታየታቸው አስረድቷል፡፡ የተለያዩ ጥቆማዎችንም በመያዝ ወደ ተግባራዊ ሥራ ከገባንበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በ767 የንግድ ተቋማት ላይ ዕርምጃ መውሰድ ችለናል፡፡
ሪፖርተር፡– የዕርምጃ አወሳሰዱ እንዴት ነው? በተጨባጭ እነዚህ የንግድ ድርጅቶች ምን አድርገው ነው? የዕርምጃውስ ዓይነት? ዕርምጃ ለመውሰድ ምን ዓይነት መመዘኛ አላችሁ?
አቶ ዳንኤል፡– ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ ከተገኙት ውስጥ አብዛኞቹ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ያለ ደረሰኝ ግብይት በመፈጸማቸው ነው፡፡ ሲገዙም ሆነ ሲሸጡ ደረሰኝ የላቸውም፡፡ ይኼ ደግሞ ዋጋው እንደይታወቅ በማድረግ ዋጋ ጨምረው ለመሸጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ስለሆነ፣ ዕርምጃ ከወሰድንባቸው አብዛኞቹ ያለ ደረሰኝ በመገበያየት የተያዙ ናቸው፡፡ ሁለተኛው እነዚህ አካላት ከደረሰኙ ባሻገር ያለ ንግድ ፈቃድ ግብይት ይፈጽማሉ፡፡ ፈቃድ ሳይኖራቸው ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ምርት በድብቅም በግልጽም ያለ ንግድ ፈቃድ መሸጣቸው ነው፡፡ በተጨማሪ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ያለ በቂ ምክንያት ያላግባብ ክምችት የፈጠሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ክምችት ደረጃ ያለው በመሆኑ ከዚያ ደረጃ በላይ ክምችት ይዘው በመገኘታቸው ነው፡፡ በተለይ በርበሬና ሌሎች የግብርና ምርቶች ላይ ያላግባብ ክምችት በፈጠሩ ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ እንደ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) ያሉ ምርቶችንም በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ክምችት ያገኘንባቸው አሉ፡፡ ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ ባገኘናቸው ላይም ዕርምጃ ወስደናል፡፡ ከዚህም ሌላ ባልታደሰ የንግድ ፈቃድ ሲሠሩ የተገኙም አሉ፡፡ እነሱ ላይም ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ እስከ ዓርብ ድረስ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ ከ70 በላይ የበርበሬ መደብሮች ይገኙበታል፡፡ በ12 ፋርማሲዎች ላይም ተመሳሳይ ዕርምጃ ወስደናል፡፡
ሪፖርተር፡– እዚህ ላይ በመደበኛ ኃላፊነትችሁ መከናወን የነበረበት ቁጥጥር አልነበረም? አሁን የሚነግሩኝ? ከዚህ ከወቅታዊ ጉዳይ ጋርስ መተሳሰር ነበረበት?
አቶ ዳንኤል፡– አሁን ዋናው ዓላማችን ቁጥጥሩን ማካሄድ ነው፡፡ ቁጥጥሩን ለማካሄድ ወደ ተግባር ስንገባ ግን ከመደበኛ ሕጋዊ አካላት ውጪ እነዚህ በሰፊው ተሰማርተው ነው የተገኙት፡፡ ከመደበኛው ነጋዴ የበለጡ ሆነው በመገኘታቸው ጭምር ዕርምጃ መወሰድ ስላለበት ወስደናል፡፡ እዚህ ውስጥም እኮ ፈቃድ ይዞ ያልተገባ ተግባር ሲፈጽም የያዝነውም አለ፡፡ ለምሳሌ ክምችት የፈጠረው አካል ሕጋዊ ፈቃድ ያለው ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ይህንን ያልተገባ ተግባር ለመፈጸም የተሰማሩ ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህንም ያማከለ ዕርምጃ መወሰዱ ተገቢ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ዕርምጃ ከወሰዳችሁባቸው ወይም እንዲታሸጉ ያደረጋችኋቸው የንግድ ድርጅቶች ምን ዓይነት ስብጥር ያላቸው ናቸው?
አቶ ዳንኤል፡– የታሸጉ የንግድ ድርጅቶችን በየዘርፉ ስናያቸው ብዙ ወፍጮ ቤቶች አሽገናል፡፡ ወፍጮ ቤቶች የግብርና ምርቶች የሚሸጥባቸው ናቸው፡፡ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮችን አሽገናል፡፡ ፋርማሲዎችን አሽገናል፡፡ የበርበሬ መሸጫዎችንና የመሳሰሉትትን አሽገናል፡፡ እነዚህ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ቀደም ብዬ በጠቀስኩልህ ምክንያቶች ነው፡፡ ለምሳሌ የስንዴ ዱቄት ያከማቹ አሉ፡፡ ጓንት፣ አልኮል፣ ማስክ የመሳሰሉትን በብዛት አከማችተው የያዝናቸው አሉ፡፡ እነዚህ ክምችቶችንም ወርሰናቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ወደ 12 ዓይነት የንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ከእነሱ የተወረሱትን ምርቶች መልሰን በሕጋዊ መንገድ በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለኅብረተሰቡ እንዲዳረሱ እያደረግን ነው፡፡
ሪፖርተር፡– እስካሁን የወረሳችሁኋቸው ምርቶች ምን ያህል ዋጋ ይኖራቸዋል ብላችሁ ትገምታላችሁ? ተወርሰው ወደ ኅብረተሰቡ ለሽያጭ ሲቀርብስ የሚገኘው ገቢ የማነው?
አቶ ዳንኤል፡- ይህ የራሱ አሠራር አለው፡፡ የሕግ አካላት ባሉበት እንዲወረስ የተባለው ንብረት መደብሩ ከመታሸጉ በፊት ይወጣል፡፡ ከዚያም ተቆጥሮ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ይሰጥና ምርቱ በገበያ ዋጋ እንዲሸጥ ይደረጋል፡፡ የሚገኘው ገቢም ለብቻው በካዝና ይቀመጣል፡፡ ይህ የሚደረገው በሕገወጥ ተግባር የተከሰሰው ነጋዴ ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄድ በመሆኑ፣ ነጋዴው በምንከሰው ክስ ሊፈረድለት ቢችል እንኳን የሚመለስለት ስለሆነ ነው፡፡ ያለበለዚያ ተወርሶ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ከተወረሰው በተጨማሪ በሕግ ይጠየቃሉ፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ ይህንን በማወቅ ከዚህም በኋላ በአግባቡ ንግዱን ማካሄድ አለበት፡፡ እኛም የቁጥጥር ሥራችንን እንቀጥላለን፡፡
ሪፖርተር፡– ከሰሞኑ የቁጥጥር ሥራ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሕገወጥ ግብይት ፈጽመዋል በሚል በተመሳሳይ የንግድ ድርጅቶች ታሽገዋል፡፡ የእነዚህ የንግድ ድርጅቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አሁንም በዚህ ድርጊት ተሰማሩ በተባሉት ላይ ዕርምጃው መቀጠሉ እየተገለጸ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ የሚታሸጉ ድርጅቶች ውስጥ ምርቶች አሉ፡፡ አሽጎ ዞር ከማለት ምርቶቹ ወደ ገበያ እንዲወጡ የሚደረግበት አሠራር ለምን አይኖርም የሚል አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡ በሌላ በኩልም በመታሸጋቸው የአቅርቦት እጥረት ስለሚፈጠር ይህን እንዴት እየሠራችሁበት ነው? ምርቶቹ ታሽጎባቸው ከሚቀመጡ ገበያ ወጥተው ሕገወጥ ድርጊት የፈጸሙት ግለሰቦች በሌላ መንገድ ቢጠየቁ ይመረጣል የሚልም አመለካከት አለ፡፡ ምክንያቱም በዕቃዎቹ ላይ ማሸግ እጥረት ከመፍጠር ውጪም ለብልሽትም ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ?
አቶ ዳንኤል፡– አሁን በአብዛኛው እየተደረገ ያለው ምርቶችን መያዝ ነው፡፡ ሌሎች በአስተዳደራዊና በሕግ የተያዙ አሉ፡፡ ሌላው ደግሞ በሕገወጥ መንገድ ገበያ ላይ የተገኙትንና የተያዙትን ምርቶች በሙሉ ወደ መንግሥት ገቢ አድርገናል፡፡ በተለይ በሕገወጥ መንገድ እየተገበያዩ ያሉ ምርቶች ከተወረሱ በኋላ ተመልሰው ለኅብረተሰቡ ይቀርባሉ፡፡ እንዲህ ባለ መንገድ የሚወረሱና መልሶ ለገበያ የሚቀርቡበት አሠራር አለን፡፡ በዚህ መሠረት ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– አሁንም ግን በአንዳንድ ቦታዎች የዋጋ ጭማሪዎች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ጤፍ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎበት እየተሸጠ መሆኑ ይነገራል፡፡ በከተማ ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የዋጋ ጭማሪውን ወደ ነበረበት መልሶ ማምጣት ችሏል ብለው ያምናሉ?
አቶ ዳንኤል፡– ዕርምጃ እየወሰድን ባለበት ቦታ ላይ እንዲቆምና ወደ ነበረበት እንዲመለስ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህ ነገር መፍትሔ እየሰጠን ያለነው በተለያየ መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ አንደኛ ቁጥጥሩን ጠንካራ በማድረግና ዕርምጃ በመውሰድ ነው፡፡ አስተዳደራዊ ዕርምጃ በመውሰድ፣ አንዳንዶችም ይቅርታ ጠይቀው ዋጋውን ወደነበረበት እንዲመልሱ በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ውሳኔና በስምምነት የሰቀሉትን ዋጋ የመለሱ በርካቶች አሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ምን ዓይነት ሥራ?
አቶ ዳንኤል፡– የኅብረት ሥራ ማኅበራት በሙሉ ምርቶቻቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ እያደረግን ነው፡፡ በተለይ የግብርና ምርቶችን የሚያቀርቡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ምርቶቻቸውን ይዘው እንዲገቡ በማድረጋችን ገበያውን ለማረጋጋት ተችሏል፡፡ በዚህ ላይ እንደ ምሳሌ የምጠቅሰው ጤፍ ነው፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጤፍ እንዲያቀርቡ በማድረጋችን አንድ ኪሎ ነጭ ጤፍ እየተሸጠ ያለው በ33 ብር ነው፡፡ ቀይ ጤፍ ኪሎው 31 ብር ነው እየተሸጠ ያለው፡፡ ቁጥጥር በጀመርንበት ቀን ግን ገበያ ውስጥ አንድ ኪሎ ነጭ ጤፍ እስከ 40 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ በሻጮቹ ላይ ዕርምጃ ሲወሰድ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ያደረግናቸው አሉ፡፡ እነዚህ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በሰፊው እንዲሳተፉ አድርገን ገበያውን እያረጋጋን ነው፡፡ በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ምርቱን ማስገባታችን በመደበኛ ገበያዎችም የዋጋ ለውጥ እንዲኖር አስችሏል፡፡ ለምሳሌ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ኮልፌ ቀራኒዮን ገበያ ጎብኝቻለሁ፡፡ በአብዛኛው ነጭ ጤፍ ከ33 ብር ባልበለጠ ነው ሲሸጡ የነበሩት፡፡ አሁንም እነዚህ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አቅርቦቱን በሰፊው እንዲያቀርቡ እያደረግን እየገባ ያለ እህል አለ፡፡ ከዚህ ባሻገር ከሰሞኑ ተወደዱ የተባሉት እንደ ነጭ ሽንኩርት፣ ሎሚና የመሳሰሉት ላይም ገበያውን ለማረጋጋት እንዲገቡ እያደረግን ነው፡፡ ገበያው መስተካከሉንም እያጣራን ነው፡፡ አሁንም ኮልፌን ምሳሌ አድርጌ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ገብተው ያመጡትን ምርት ቀጥታ እንዲሸጡ በማድረግ፣ የገበያ ማረጋጋቱን እየተመለከትን ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሔው ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰድ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ምርት ወደ ገበያው እንዲገባ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ከቁጥጥር ባለፈ መነሳት ያለበት ጉዳይ ገበያ በማረጋጋት ሥራ አንዱ ተግባር በቂ ምርት ገበያ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ የእናንተ አንዱ የሥራ ድርሻ በማከማቸትም ሆነ በሌላ ምክንያት እጥረት ተፈጠረባቸው የተባሉ ምርቶችን፣ መንግሥት አሁን ባሉት በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩልም ሆነ በሌላ መንገድ ምርት ለማቅረብ ምን ያህል ዝግጅት አላችሁ?
አቶ ዳንኤል፡– ከሌላው ጊዜ የተለየ አቋማችን ይኼ ነው፡፡ ሌላ ጊዜ አስተዳደራዊ ዕርምጃ በመውሰድ እንለቃለን፡፡ አሁን ግን ፈጣን ዕርምጃ እንወስዳለን፣ እንወርሳለን፡፡ አንደኛው በፍጥነት ጥፋቱን አውቆ መመለስ ከቻለ ወደ ነበረበት ተመልሶ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡
አሁን በርበሬ ላይ በዘመቻ የተወሰደው ዕርምጃ ይህ ነው፡፡ ዋናው ዓላማችን የሚበላሹ ምርቶች ስለሆኑ ምርቶቹ ይወረሱና ተጠያቂዎቹ በፍርድ ቤት ክስ ይመሠረትባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– እንዲህ የሚደረግ መሆኑን አሳውቃችኋል? ለምሳሌ ከዚህ በኋላ በአስተዳደራዊ ዕርምጃ ብቻ ሳይሆን ንብረታችሁ ይወረሳል ብላችሁ አሳውቃችኋል? የተወረሰው ንብረት መልሶ ለኅብረተሰቡ ይቀርባል የሚለው መረጃ አለ? ይህንን እንዴት ነው የምታከናውኑት?
አቶ ዳንኤል፡– መረጃ ለቀናል፡፡ የተወረሱ ንብረቶችን መልሰን ለኅብረተሰቡ እንዲሠራጩ የማድረግ ዕርምጃ እየወሰድን መሆኑን በሚዲያም ገልጸናል፡፡ በግልጽ ተናግረናል፡፡ ይህ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እስካሁን የተወረሱ ንብረቶች እንዴት ወደ ኅብረተሰቡ እንደተላለፉ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በዚህ ላይ ያሉ መረጃዎችን አጠናቅረን ይፋ እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡– በአግባቡ በመነገድ የዋጋ ጭማሪ ሳያደርጉ ኅብረተሰቡን ሲያገለግሉ የነበሩ ነጋዴዎችና ድርጅቶች አሉ፡፡ ሁሉም ነጋዴ አይደለም ዋጋ የጨመረው፡፡ ስለዚህ መልካም የሠሩትን ታበረታታላችሁ?
አቶ ዳንኤል፡– እንዲህ ያሉ ነገሮችንም እንሠራለን፡፡ ፌስቡክ ገጻችንን ብታየው ትረዳለህ፡፡ ለምሳሌ ሸዋ ሱፐር ማርኬትን ቼክ አድርገናል፡፡ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ባለማድረጋቸው አመሥግነን ይህንኑ ሕዝብ እንዲያውቀው በመረጃ መስጫ ገጻችን ላይ አሥፍረናል፡፡ ይህንንም ያደረግነው ሌሎችም እንዲህ በማድረግ ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ነው፡፡ አብዛኛው ነጋዴ ኅብረተሰቡን ለመርዳትና ለማገዝ ላደረገው ጥረት አመሥግነናል፡፡
ሪፖርተር፡– እንደ አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ባልደረባነትዎ በግብይት ሥርዓት ውስጥ ለሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ሸማቹስ አስተዋጽኦ የለውም ይላሉ?
አቶ ዳንኤል፡– አንደኛ በዚህ ረገድ ኅብረተሰቡ ሊያውቀው ይገባል ያልነውን መረጃ እየሰጠን ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ ኅብረተሰቡ ችግር ይፈጠራል በሚል ስሜት አላስፈላጊ ግብይት ይፈጽማል፡፡ ይህ ዓይነቱ ልምድ ደግሞ እጥረት ሊፈጥር ይችላል፡፡ በተለመደው ሸመታ ሥርዓቱን ጠብቆ መሄድ አለበት፡፡ እጥረት ይፈጠርባቸዋል የተባሉ ምርቶችን እንዲቀርቡ እየተደረገ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ማወቅ አለበት፡፡ ሌላ ሥጋት እንዳይገባው ጭምር በተደጋጋሚ እየገለጽን ነው፡፡ አንዳንዴም በሌላ ነገር ኅብረተሰቡ ውዥንብር ውስጥ የሚገባበት ሁኔታ ስላለ፣ በትክክለኛ መረጃ ቢመሩ ይመረጣል፡፡ ገበያ ውስጥ ችግር ካለ ግን ለዚህ የሚሆን የስልክ መስመር ስላዘጋጀን በዚያ በመጠቀም ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይቻላል፡፡ እስካሁንም በዚህ የስልክ መስመር ከ800 በላይ ጥቆማዎች ደርሰውን እየሠራን ነው፡፡ ለኮማንድ ፖስት እያስታወቅን ችግሩ እንዲፈታ እያደረግን ነው፡፡ ስለዚህ ሸማቹ በመደበኛ ግብይት ወቅት ይፈጽም በነበረው ሸመታ መሠረት እጥረት እንዳይፈጠር ማድረግ አለበት፡፡ ከቅዳሜ ጀምሮ በትዕዛዝ እንዲመረት የተደረገውን አልኮል በኅብረት ሥራ ማኅበራት መደብሮች ጭምር እንዲሠራጭ እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡ ለፅዳት የሚሆኑ ዕቃዎችን በአቅራቢያው እንዲያገኝ የሚያስችሉትን አማራጮች እያቀረብንለት መሆኑን መረዳት ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ሌላ ከክልሎች ጋር በመነጋገር ተጨማሪ ምርት የሚቀርብበት ሥራም እያከናወንን ነው፡፡