Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንፈሳዊ ጉባዔ ማድረግና ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ዕግድ ተጣለ

መንፈሳዊ ጉባዔ ማድረግና ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ዕግድ ተጣለ

ቀን:

በቤተ እምነቶች የምዕመናን መበራከት ሥጋት ፈጥሯል

ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም ተሠራጭቶ ከ17 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውና እየቀጠፈ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲባል፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉባቸውን መንፈሳዊ ጉባዔዎችና ወደ ገዳማትና አድባራት የሚያደርጓቸውን መንፈሳዊ ጉዞዎች ከመጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲያቆሙ ቤተ ክህነት አወጀች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ የሰው ልጆች ከፍተኛ ሥጋት ሆኗል፡፡ የዓለም መንግሥታት አገርንና ሕዝብን ከጥፋት ለማዳን ሕዝባቸው ከቤት እንዳይወጣ፣ ርቀቱን ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ፣ እንዳይጨባበጭ፣ እንዳይተቃቀፍና እንዳይሰባሰብ ማወጃቸውን  አስረድተዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ክቡር የሆነው የሰው ልጆች ሕይወትን ለመታደግ፣ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ ካህናትና የእምነቱ ተከታዮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ፓትርያርኩ መመርያ ሰጥተዋል፡፡

ምዕመናኑ ምንም እንኳን በሰሞነ ሕማማት እርስ በርስ በመተቃቀፍና በመሳሳም ፍቅራቸውንና አንድነታቸውን ይገልጹ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ድርጊቱ በመተው ራስን ዝቅ በማድረግና ርቀታቸውን በመጠበቅ ሰላምታ መለዋወጥ እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡

ወረርሽኙ ሰዎች በተሰባሰቡበት ቦታ የመስፋፋትና የመዛመት ባህሪው ከፍተኛ መሆኑ በሕክምና ባለሙያዎች እየተነገረ መሆኑን የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባዔዎች ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች፣ እንዲሁም ምዕመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች እንዲቋረጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ምዕመናኑ እጃቸውን መታጠብ እንዳለባቸውና ሥርዓተ አምልኮአቸውንም ተራርቀው እንዲፈጽሙም አሳስበዋል፡፡ ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴና በማኅሌት ለጊዜው ታስበው እንዲያልፉም መወሰኑን አክለዋል፡፡

ፓትርያርኩ ጉንፋን ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው እንዲቆዩ፣ ሕክምና እንዲደረግላቸውና ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሥርዓተ ቅዳሴን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈጸመው በቤተ መቅደስ ቀዳሾች ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉና ለአረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት በፈረቃ ቁርባን የሚቀበሉበት ሥርዓት እንደተዘጋጀም አስታውቀዋል፡፡

እነሱም ቢሆኑ በተራራቀ ሁኔታ ወደ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲገቡ፣ ምዕመናኑ ርቀታቸውን ጠብቀው በመቆም በአፀደ ቤተ ክርስቲያን ቆመው እንዲያስቀድሱና ቅዳሴ ፀበልም በግል መጠቀሚያቸው (ኩባያ ወይም ብርጭቆ) በቆሙበት ሆነው እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡ የጠዋት ምሥጋና፣ ሰዓታት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐትና ሌሎች አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልጉ ዲያቆናትና ካህናት ብቻ የሚፈጸሙ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ወረርሽኙ በደስታ፣ በሐዘን፣ በዕድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈጻጸምና በሌሎችም ማኅበራዊ ግንኙነቶች ምክንያት ሊሠራጭ ስለሚችል ቁጥራቸው እጅግ በጣም በቀነሰ ሰዎች እንዲከናወኑም አሳስበዋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ የተጠቁና አገግመው ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ፣ እንዲሁም የውጭ አገር ዜጎችን ከሃይማኖትና ከሥነ ምግባር የወጣ የማግለልና ጥቃት የማድረስ ሁኔታዎች የተወገዙ በመሆናቸው፣ በክርስቲያናዊ ፍቅርና በጨዋነት መንከባከብ እንደሚገባም መክረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆኑ አሳሳች መረጃዎች መቆጠብ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በተለያዩ ቤተ እምነቶች፣ የምዕመናን መበራከት ለብዙዎች ሥጋት ሆኖባቸዋል፡፡ በተለይ ከእሑድ መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ዕኩለ ፆም ወዲህ ባሉት ቀናት በብዙዎቹ ሥፍራዎች ምዕመናን ተጨናንቀው በመታየታቸው፣ የሃይማኖት መሪዎች በፍጥነት የእርምት ዕርምጃ ካልወሰዱ ለወረርሽኙ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጠር አሳስበዋል፡፡ በአንዳንድ አብያተ ክርስትያናት ተራርቀው የቆሙ ሰዎች ቢታዩም፣ በአብዛኛው ግን በተለመደው ሁኔታ መቀጠሉ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡ የእርምት ዕርምጃ በመውሰድ የተደቀነውን አደጋ መመከት እንደሚገባም ሥጋት የገባቸው ወገኖች አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...