Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስን ለመቋቋም ለአፍሪካ አገሮች የዕዳ ስረዛ እንዲደረግ ለቡድን 20 አገሮች...

ኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስን ለመቋቋም ለአፍሪካ አገሮች የዕዳ ስረዛ እንዲደረግ ለቡድን 20 አገሮች ምክረ ሐሳብ አቀረበች

ቀን:

የዓለም ባንክም ተመሳሳይ ጥያቄ በቡድን 20 ጉባዔ ላይ አቅርቧል

የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የአፍሪካና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች መቋቋም እንዲችሉ፣ የቡድን 20 አገሮች የዕዳ ስረዛ እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ ምክረ ሐሳብ አቀረበች።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለቡድን 20 አገሮች የመሪዎች ስብሰባ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል ብሎ ካቀረበው ባለ ሦስት ነጥብ ምክረ ሐሳብ ውስጥ አንዱ፣ የአፍሪካ አገሮችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት የሚያደርስባቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት መቋቋም እንዲችሉ የዕዳ ስረዛና የክፍያ ማራዘሚ እንዲደረግላቸው የሚጠይቅ ነው።

 በዚህ ውስጥ ከተካተቱት ምክረ ሐሳቦች አንዱ የቡድን 20 አገሮች ለአፍሪካ መንግሥታት ለሰጧቸው ብድሮች የሚከፈለው ወለድ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ኢትዮጵያ የጠየቀች ሲሆን፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች የተሰጠው ብድር ደግሞ በከፊል እንዲሰረዝ በተጨማሪ መጠየቋን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የተቀረው የብድር መጠን ደግሞ አነስተኛ ወለድ የሚከፈልበትና የአሥር ዓመት የዕፎይታ ጊዜን አካቶ፣ በረዥም ጊዜ የሚመለስ ብድር ሆኖ እንዲሻሻል ጥያቄዋን አቅርባለች።

የቡድን 20 አገሮች የመሪዎች ስብሰባ ሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በሳዑዲ ዓረቢያ በተካሄደበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ፣ ተመሳሳይ ጥያቄ ለአገሮቹ ማቅረባቸው ታውቋል።

‹‹የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባቸውን የዓለማችንን ደሃ አገሮች ክፉኛ ሊመታ ስለሚችል፣ ለእነዚህ አገሮች የተናጥል ብድር የሰጣችሁ የቡድን 20 አገሮች አፋጣኝ የዕዳ ቅነሳ በማድረግ አገሮቹ ያላቸውን ሀብት የቫይረሱን ወረርሽኝ እንዲከላከሉበት እንድታደርጉ እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል።

የአፍሪካ አገሮች የቫይረሱ ሥርጭት የሚያድርስባቸውን ቀውስ መከላለከል እንዲችሉ የዓለም ባንክ ይፋ ካደረገው የ14 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ፣ ለዕዳ ጫና ቅነሳ የሚሆን የ35 ቢሊዮን ዶላር ፕሮግራም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። የዓለም ባንክ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአፍሪካና ዝቅተኛ ገቢ ባለቸው አገሮች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል፣ በሚቀጥሉት 15 ወራት በአጠቃላይ 150 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል ለቡድን 20 አገሮች ካቀረበችው ምክረ ሐሳብ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የድጋፍ ጥያቄ፣ ራሷን በመወከል ለዓለም ባንክ አቅርባለች። ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥያቄ የመረመረው የዓለም ባንክም ሰሞኑን ይፋ ካደረገው 14 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ተጠቃሚ እንደምትሆን አስታውቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...