Sunday, March 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ቀውስ እንዳይፈጠር አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሁሉም ሰው ግዴታ መሆን አለበት!

መላውን ዓለም አዳርሶ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ያለው የኮሮና ቫይረስ ጣሊያን ውስጥ እየገባ በነበረበት ጊዜ መደረግ የነበረባቸው ጥንቃቄዎች ተግባራዊ ስላልሆኑ፣ ጣሊያናውያን በአስደንጋጭ ሁኔታ እያለቁ ነው፡፡ ጣሊያንን እንደ ምሳሌ የምናነሳው ከሌሎቹ የዓለም አገሮች ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ስለደረሰባት ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስን የዕለት ተዕለት መረጃ በማጠናቀር ታዋቂ በሆነው በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የማክሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. የእኩለ ቀን ሪፖርት መሠረት፣ በጣሊያን 64 ሺሕ ሰዎች ሲጠቁ ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ጣሊያናውያን መዘናጋትና ችላ ባይነት የሚያደርሰውን ጥፋት ከእኛ ተማሩ በማለት የቁጭት መልዕክት እያስተላለፉ ነው፡፡ እነሱ አሁን እኛ ዘንድ እንዳለው ሁኔታ ውስጥ ሆነው የጥንቃቄ መልዕክቶች ከማስጠንቀቂያ ጋር ሲነገሯቸው፣ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ በመቁጠር በሬስቶራንቶች፣ በመጠጥ ቤቶች፣ በጭፈራ ቤቶችና በመሳሰሉት ሥፍራዎች በገፍ እየተገኙ ለቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት መሆናቸውን ዛሬ በሰቆቃ እየተናገሩ ነው፣ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› እንደሚባለው፡፡ ችላ ባይነታቸው ምን ያህል አላስፈላጊ መስዋዕትነት እያስከፈላቸው እንደሆነ በቁጭት እያስታወሱ እኛን ያየ ይጠንቀቅ እያሉ ነው፡፡ ‹‹ብልህ ከሌሎች ስህተት ይማራል፣ ሞኝ ግን ከራሱም አይማርም›› የሚባለው ብሂል እንዳይደርስ ከተፈለገ፣ በተቻለ መጠን አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና እንቅስቃሴዎችን በመገደብ ኮሮና ቫይረስ የደገሰውን ዕልቂት በመተባበር ማምከን ይገባል፡፡ ትብብሩ ግን በጥንቃቄ ካልታጀበ በአንድ እጅ ለማጨብጨብ እንደ መሞከር ነው የሚቆጠረው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ፀፀት ውስጥ ከሚከቱን ድርጊቶች እንቆጠብ፡፡ አለበለዚያ በግዳጅ ለበርካታ ቀናት ከቤት የማያስወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ ይችላል፡፡ ይህ አዋጅ በበርካታ አገሮች ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ 

አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨባበጥን በፍፁም በማስወገድ፣ እጅን በሳሙና ሙልጭ አድርጎ በመታጠብ፣ አካባቢን ከማናቸውም ጉድፎች ከማፅዳት በተጨማሪ አካላዊ ርቀትን በሁለት የትልቅ ሰው ዕርምጃዎች በመወሰን፣ በርካታ ሰዎች ከሚገኙባቸው ሥፍራዎች በመራቅ፣ ስብሰባዎችን በማስወገድ፣ ያልተጣሩ መረጃዎችን ማሠራጨትና ማስተጋባትን በማስቆም፣ እንዲሁም ተዓማኒነት የጎደላቸው ትንበያዎች ልፈፋን አደብ በማስገዛት፣ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት የማገዝ ግዴታና ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ የሚተላለፉት የጥንቃቄ መልዕክቶችን ምን ያህል ሰዎች በሚገባ እንደተገነዘቡ፣ ምን ያህሉስ መልዕክቶቹን መገንዘብ እንዳቃታቸውና ቸልተኝነቱስ ምን ያህል እንደሆነ ለመረዳት አዳጋች አይደለም፡፡ በሰዎች መሀል መኖር የሚገባው አካላዊ ርቀት በግልጽ እየተነገረ እያለ መቀራረቡ በጣም ያስደነግጣል፡፡ በቤተ እምነቶች በርካታ ምዕመናን ተፋፍገው ይታያሉ፡፡ በሕዝብ ትራንስፖርት መገልገያዎች አስደንጋጭ መጨናነቆች ይስተዋላሉ፡፡ የቀብር ሥርዓት በሚፈጸምባቸው ሥፍራዎች አሁንም በርካታ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ በምግብና በመጠጥ ቤቶች፣ በጫት መቃሚያዎችና በሺሻ ማጨሻዎች፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶች በሚደረጉባቸው በርካታ ቦታዎች፣ ወዘተ ሳይቀር ለማመን የሚከብዱ መተፋፈጎች አሉ፡፡ በአስገዳጅነት ተግባራዊ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎችን ባለመፈጸም፣ ሁሉንም ነገር ፈጣሪ ትከሻ ላይ የመጫን አዝማሚያዎች በስፋት እየታዩ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችና ሐሳቦች አገር ያጠፋሉ፡፡ እንጠንቀቅ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እጅግ በጣም ፈጣን በሚባል መምዘግዘግ ዓለምን አጥለቅልቋል፡፡ ይህ ፍጥነት ያሠጋው የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስታወቀው የመጀመሪያዎቹ 100 ሺሕ ሰዎች የቫይረሱ ተጠቂ የሆኑት በ67 ቀናት፣ 200 ሺሕ የተደረሰው በ11 ቀናት ሲሆን፣ 300 ሺሕ የተገባው ግን በአራት ቀናት ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የቫይረሱ ሥርጭት ወደ 400 ሺሕ እየተቃረበ ሲሆን፣ ከ17 ሺሕ በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ የቫይረሱ ሥርጭት እንዲህ ክንፍ አውጥቶ እየበረረ ዓለምን ሲረብሽ፣ በአጓጉል አስተሳሰቦች በመጀቦን ታይቶና ተሰምቶ ለማይታወቅ ቀውስ አገርን ማመቻቸት አይገባም፡፡ የአገሪቱ የአደጋ ጊዜ የጤና ምላሽ አቅም፣ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር፣ አደጋው ከቁጥጥር ውጪ ቢሆን የማቀናጀትና የማስተባበር ዝግጅትና አፈጻጸም፣ እንዲሁም የሰው ኃይልና የቁሳቁስ አቅርቦት፣ ወዘተ ደካማና በተግባር ያልተፈተነ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ የእምነት ተቋማት መሪዎች ምዕመናኖቻቸው ከሚመለከታቸው የጤና አካላትና ከመንግሥት የሚተላለፉ የጥንቃቄ ማስጠንቀቂያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አበክረው ከማስገንዘብ ባለፈ፣ ታች ድረስ በመውረድ አፈጻጸሙን መከታተል አለባቸው፡፡ በብዙ ሥፍራዎች እየተስተዋሉ ያሉ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች አገር ከማጥፋታቸው በፊት፣ የእምነት መሪዎች ጣልቃ ገብተው ያስቁሙ፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ካቃታቸው ግን ኢትዮጵያም የሌሎችን መሪር ፅዋ መጨለጧ አይቀርም፡፡ አካላዊ ርቀትን ባለመጠበቅ ብቻ የከፋ አደጋ መድረሱ እንደማይቀር መገንዘብ የግድ ይሆናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን እንደተናገሩት መደረግ ላለባቸው ጥንቃቄዎች ልዩ ትኩረት መስጠት ካልተቻለ፣ በሁለት አኃዝ ያለው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ቀስ በቀስ ወደ ሦስትና አራት አኃዞች ያድጋል፡፡ ችግሩ በጣም የሚያሳስባቸው ወገኖች አደራ እያሉ ያሉት የጣሊያንና የሌሎች ተጎጂ አገሮች ዕጣ ፈንታ በኢትዮጵያ ላይ እንዳይደርስ፣ አሁን በስፋት እየታየ ያለው መተፋፈግና መጨናነቅ በፍጥነት እንዲቆም ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትም በእምነት ተቋማት አካባቢ የሚታየውን አሳሳቢ ድርጊት ለማስቆም፣ ከእምነት ተቋማት መሪዎች ጋር በሚገባ መምከር አለበት፡፡ የእምነት ተቋማት መሪዎችም ያለውን ሥጋት በሚገባ በመገንዘብ አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ አለባቸው፡፡ በየደረጃው ያሉ የእምነት መሪዎችም በዚህ መንፈስ ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ ፀፀትና ቁጭት ውስጥ የሚከት ጥፋት ከመድረሱ በፊት በጋራ ለጥንቃቄ ቅድሚያ ይስጡ፡፡ ምዕመናንም በዚህ መሠረት የሚፈለግባቸውን ያድርጉ፡፡ ዓለም ሁሉ በአንድ ላይ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መግቻ ዘዴዎችን ተግባራዊ እያደረገ ባለበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት፣ በአላዋቂነት አጥር ውስጥ ራስን ከልሎ ለአደጋ መጋለጥ በገዛ እጅ ሕይወትን ከማጥፋት አይተናነስም፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ከሌሎች ስህተት ባለመማር ከዓለም ተነጥሎ ራስን ደሴት ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ አላስፈላጊ ድርጊቶችን በመተባበር ያስወግዱ፡፡

የጥንቃቄ ዕርምጃዎችን ወደ ጎን በማለት አካላዊ ርቀትን በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት ተግባራዊ አለማድረግ፣ የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለማስፋፋት ትልቅ ክፍተት እንደሚፈጥር በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ሌላው ቀርቶ በበጎ ፈቃደኝነት የሚከናወኑ የእጅ ማስታጠብ ሥነ ሥርዓቶች ላይ የታዩ መጠጋጋቶች ያሳስባሉ፡፡ ቫይረሱ ሰውነት ውስጥ ለበርካታ ቀናት ተደብቆ የሚቆይ በመሆኑ፣ በመጠጋጋት ምክንያት የሚጎዱ ሰዎች ካሉ ምርመራ ቢጀመር ተጠቂዎች ብዛታቸው ከሚታሰበው በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት ማጓጓዣዎች እስከ 65 ሰዎች ተጭነው በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች የሚጓዙ መንገደኞች፣ በየቀኑ በአምስቱም በሮች ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎችም ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በተቻለ መጠን እንዲገታ መንግሥት መወሰን አለበት፡፡ የተለያዩ አቅርቦቶችን ከሚያመላልሱ የጭነት ተሸከርካሪዎች በስተቀር ሕዝብ እንደ ሰርዲን ተጠቅጥቆ የሚጓዝባቸው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ተሸከርካሪዎች ለጊዜው እንቅስቃሴያቸው ቢገታ፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ይረዳል፡፡ እጅን በመታጠብ ብቻ ከአፍ እስከ ገደፋቸው የሞሉ አውቶቡሶች ላይ ተፋፍጎ ተጭኖ ቀኑን ሙሉ መጓዝ አደጋው የከፋ ነው፡፡ አካላዊ ርቀትን ባለመጠበቅ የሚፈጠሩ መጨናነቆችንና መተፋፈጎችን በአስቸኳይ ማስቆም ካልተቻለ፣ ራስንም አገርንም መቀመቅ ውስጥ መክተት ይከተላል፡፡ አስከፊው ቀውስ ከተከሰተ ደግሞ እንኳን ግለሰብ አገርም ጥርቅም ተደርጋ ትዘጋለች፡፡ ቀውሱ እንዳይከሰት ግን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ግዴታ መሆን አለበት!        

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...