በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ተገንብተው ለነዋሪዎች ያልተላለፉ መኖሪያ ቤቶች በአስቸኳይ የሚገባቸው ማስተካከያ በማድረግ፣ ለለይቶ ማቆያነትና ለጊዜያዊ ሕክምና መስጫነት እንዲዘጋጁ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ጠየቀ፡፡
ፓርቲው ይህን ሐሳብ ያቀረበው ማክሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በራስ ሆቴል፣ ‹‹ሙሉ ኃይላችንን የኮሮና ቫይረስን ጫና ለመቋቋም እናውለው›› በሚል ርዕስ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አማካይነት መግለጫ በሰጠቡት ወቅት ነው፡፡
ወረርሽኙን አገር አቀፍ የደኅንነት ቀውስ በማለት የገለጹት የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ወረርሽኙ የአንድ ጊዜ ክስተት አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ሁላችንም በጋራ ይህንን ነገር መዋጋት ያለብን፡፡ ከዚህ በሽታ ጋር በተያያዘ ብሔራዊ የደኅንነት ስትራቴጂ ያስፈልገናል፤›› ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለአገሪቱ የንግድ ማኅበረሰብ በየእርከኑ ሊደረግ የሚችል ጊዜያዊ የግብር ዕፎይታ ማድረግ ማለትም የተጨማሪ እሴት ታክሶችን መክፈያ ጊዜ ማራዘም፣ የጡረታ መዋጮዎችን መቀነስ፣ ማቆየትና መተው የሚለው አማራጭ በዘርፉ ባለሙያዎችና በንግድ ምክር ቤቶች በጋራ ምክክርና መለስተኛ ጥናት ተደርጎበት በፍጥነት ለውሳኔ እንዲቀርብ ሲልም ፓርቲው ጥሪን አቅርቧል፡፡
መንግሥት እስካሁን የቫይረስ ሥርጭቱን ለመግታት የወሰናቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊነት በተሻለ ትኩረት እንዲከታተል የጠየቀው ፓርቲው፣ ‹‹የቫይረሱን ሥርጭት ሊያባብሱ የሚችሉ ብዙ ሰዎች በአንድ ቦታ መሰብሰብን (በገዥው ብልፅግና ፓርቲ የሚፈጸመውን ጨምሮ) በአስቸኳይ እንዲያስቆም፤›› በማለትም አሳስቧል፡፡
ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሎ የተቆረጠለትን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ደግሞ፣ ‹‹የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራችን እንዳይዛመት መንግሥት ለአጭር ጊዜ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች፣ በምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ላይ ከአሁኑ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆኑን ተገንዝበናል፤›› በማለት አስታውቆ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ መንግሥት ያሳለፋቸው ውሳኔዎችና ወደፊትም የሚወሰኑ ውሳኔዎች የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በግልጽ እያሳወቀ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ምርጫ በሚካሄድበት ቀንም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ማንኛቸውም ማሻሻያዎች፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት እያደረገ እንዲወስንም ፓርቲው አሳስቧል፡፡
ሆኖም ግን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ‹‹ያለ ምንም ማጋነን አሁን ከምርጫም ሆነ ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በአዕምሮአችን አይዞሩም ማለት ይቻላል፡፡ አሁን እያሳሰብን ያለው ጉዳይ እንዴት ነው ከዚህ መዓት ሕዝባችንን ማትረፍ የምንችለው የሚለው ነው፤›› በማለት፣ የኮሮና ወረርሽኝን ለመመለከት ፓርቲው ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ሕዝቡም በሚሰጠው መመርያ መሠረት ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
መረጃ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ ደግሞ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋና በሆሮ ጉድሩ ዞኖች ፀጥታን ከማስከበር አንፃር የስልክና የበይነ መረብ ግንኙነት ከተቋረጠ ወራት መቆጠሩን በማስታወስ፣ ‹‹በአካባቢው የተቋረጠውን የስልክና የበይነ መረብ ግንኙነት ወደ ሥራ እንዲመልስ›› ኢዜማ መንግሥትን አሳስቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም እስካሁን ተቋርጦ በነበረው ግንኙነት ምክንያት የተፈጠረውን የመረጃ ክፍተት ለማካካስም፣ በአካባቢው ከሚሠራጩ የመገናኛ ብዙኃን ጋር በመሆን ሰፊ የግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዲሠራም ኢዜማ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡