በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ በመገንባት ላይ የሚገኘው አደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም የመጀመርያ የግንባታ ምዕራፍ ከተጠናቀቀ ሰነባብቷል፡፡ ለሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታና ለማጠቃለያ ሥራው 5.57 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን፣ እስካሁን ለፕሮጀክቱ የመጀመርያ ግንባታ እንዲሁም በሜዳው ዙሪያ የሚነጠፈውን የመሮጪያ ትራክ (መም) እና ለሌሎች ተያያዥ ሥራዎች 2.47 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተነግሯል፡፡
በቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሥራ ተቋራጭና በአማካሪ ድርጅቱ ኤምኤች ኢንጂነሪንግ ከአራት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ብሔራዊ ስታዲየም ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ከተያዘለት ጊዜ አኳያ በጣም የዘገየ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ይሁንና ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ስፖርት ኮሚሽን ባለፈው ሰኞ የስታዲየሙን ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ማስጀመር ይችል ዘንድ ከተቋራጩ ጋር ውል ማድረጉ ታውቋል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩርና የቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሌዩ ጃባህ ብሔራዊ ስታዲየሙን ለማጠናቀቅ በሚያስፈልገው 900 ቀናት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ኮሚሽኑ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ተመልክቷል፡፡
በወንበር ከ62‚000 በላይ ተመልካቾችን እንደሚያስተናግድ የሚነገርለት ይህ ብሔራዊ ስታዲየም፣ በመጀመርያው የግንባታ ምዕራፍ ከተካተቱት ውስጥ ከ30 በላይ የሚዲያ ክፍሎች፣ የጋዜጣዊ መግለጫ አዳራሾች፣ የክብር እንግዶች ማረፊያና አሳንሳሮችን ጨምሮ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች እንዲሁም ከ1‚000 በላይ መፀዳጃ ክፍሎች፣ የፍሳሽ ማስወገጂያ ክፍሎችና ለኤክትሪክ መስመር ዝርጋታ የሚያገለግሉ ነገሮች ተጠናቀዋል፡፡
እንደ መግለጫው ከሆነ በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ የሚካተቱት ደግሞ፣ ዋናውን የመጫወቻ ሜዳ ሳር ማልበስ፣ የመሮጪያ ትራክ (መም) ማንጠፍ፣ የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም፣ እንዲሁም ሰው ሠራሽ ሐይቅና ሄሊኮፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደኅንነት ካሜራዎች ገጠማ፣ ሳውንድ ሲስተም፣ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ፣ የመለማመጃ ሜዳዎችና ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎችን ይሆናል፡፡ ለእነዚህና መሰል ግንባታዎች ማከናወኛ 5.57 ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን በአጠቃላይ ስታዲየሙን ለማጠናቀቅ እስከ ስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱ 48.8 ሔክታር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ስታዲየሙ ብቻውን 95‚000 ካሬ ሜትር የሚሸፍን መሆኑ ተነግሯል፡፡