Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየተቀናጀው የመታደጊያ ፕሮግራም ለጋማ ከብቶች

የተቀናጀው የመታደጊያ ፕሮግራም ለጋማ ከብቶች

ቀን:

በአብዛኛው የኢትዮጵያ የገጠር ክፍል መሠረታዊና ዋነኛ መገልገያ የጋማ ከብት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጋማ እንስሳት ሀብቷ በዓለም ከቀዳሚዎቹ አገሮች ተርታ ከመሆኗ አንፃርም ልትንከባከበው የሚገባ ነው፡፡ ይህ ሀብት የገጠሪቱን ክፍል ከከተማው ከተማውንም ከገጠሩ ያገናኛል፡፡

ቆም ተብሎ ቢታሰብ የጋማ ከብት የለም ማለት ከተማና ገጠር አይገናኙም ማለት  ነው፡፡ መኪና የማይገባበት መንገድ ላይ የሚያጓጉዙት እነኚህ ሀብቶች ሰው ከማጓጓዝ ባለፈ ውኃ በማቅረብ ለእናቶችና ሕፃናት ዕፎይታ የሚሆኑባቸው አካባቢዎችም ይታያሉ፡፡

ነገር ግን እነዚህ ባለውለታዎቻችንን በምን መልኩ እየጠበቅናቸው ነው? ተገቢውን እንክብካቤ እያደረግንላቸው ነው ወይ? ከሚሰጡት አገልግሎት አኳያስ ትኩረት ሰጥተናቸዋል ወይ? ብለን ብንጠይቅ ጥያቄዎቹ አየር ላይ ተንጠልጥለው ይቀራሉ፡፡

- Advertisement -

ይህንን የጋማ እንስሳት አገልግሎት የተረዳው ‹‹ብሩክ ኢትዮጵያ›› የተቀናጀ የጋማ ከብት ደኅንነት ትብብር ፕሮግራምም ለአሥራ አራት ዓመታት የጋማ ከብቶች ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዋናነት የሚሠራውም በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ነው፡፡

የብሩክ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ደስታ አረጋ እንደሚሉት፣ የጤንነት ማሻሻል ላይ የሚሠራው በመጀመርያ ኅብረተሰቡን ዕውቀት በማስጨበጡ ላይ ነው፡፡ ይኼም ሲባል እንስሶችን እንዴት መንከባከብ ይቻላል፣ በተጎዱ ጊዜም እንዴት ቁስልን ማከም ይቻላል፣ ቁስል እንዳይፈጠርስ እንዴት ማድረግ ይቻላል የሚለውን ነው፡፡ ግንዛቤው ከተፈጠረ በኋላም ትኩረት የሚደረገው  አገልግሎት ማቅረብ ላይ ነው፡፡ አገልግሎት ማቅረብ ሲባልም የንፁህ ውኃ ማቅረብ፣ የጤና ኬላ መገንባት የከብቶቹን ማረፊያ ማዘጋጀትን ያካትታል፡፡

እስካሁን በአማራ ክልል ሦስት ወረዳዎች ላይ፣ በደቡብ ክልል በጌድኦ፣ በሲዳማና በሃላባ፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሰባት ወረዳዎች ላይ ተደራሽ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

መጋቢት 7 እና 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ንፁህ የውኃ ተደራሽነትን ከማቅረብ፣ የጤና ኬላ ከመገንባትና ለከብቶቹ የማቆያ ቦታ ከማቅረብ አንፃር በምዕራብ አርሲ ዞን አዳባና ዶዶላ ወረዳዎች ላይ የተሠሩ ፕሮጀክቶችን ድርጅቱ አስመርቋል፡፡

የተመረቁት ፕሮጀክቶች ቡጫና የውኃ ፕሮጀክት፣ ሀኮ የጤና ኬላ፣ አዳባ የገበያ ማዕከል፣ ገነታ የውኃ ፕሮጀክት፣ አለንቱ የጤና ኬላ፣ ዶዶላ የገበያ ማዕከልና በሪሳ የውኃ ፕሮጀክት ናቸው፡፡ እነዚህ ተጠቀሱ እንጂ በአጠቃላይ 18 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደገቡ ታውቋል፡፡

ከዶዶላ 20 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ የምትገኘው አዳባ የመጀመርያ መዳረሻችን ነበረች፡፡ ሕዝብ ጥሩ አቀባበል ነበር ያደረገው፡፡ አዳባ ላይ የገበያ ማዕከል እንዲሁም በግብይይት ወቅት ሰዎች ይዘዋቸው የሚመጧቸውን ፈረሶች ማሳረፊያ ሥፍራ ተገንብቷል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ሥራ የገባው ይኸው የማቆያ ሥፍራ በአማካይ በቀን ከ500 በላይ ፈረሶች እንደሚያርፉበት ይነገራል፡፡

ይህ የማቆያ ሥፍራ ከመገንባቱ በፊት ሰው ለመገበያየት ወጥቶ ሸምቶ እስኪጨርስ ድረስ ፈረሱ ዕቃ ተሸክሞ እዚያው ፀሐይ ላይ የሚቆምበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ፈረሱ ይጎዳና ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁን ወደ ገበያው በሚመጡበት ጊዜ እዚያው ማረፊያ ውስጥ ይገቡና ቀዝቅዘው የሚበላም አግኝተው ሻወርም ወስደው የሚወጡበት አጋጣሚ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ማኅበሩ 14 ሰዎች በማቀፍ የሥራ ዕድልም ተፈጥሯል፡፡

ከማኅበሩ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የ45 ዓመቷ ወ/ሮ ረሂማ ከሊፋ ይገኙበታል፡፡ ወ/ሮ ረሂማ የአምስት ልጆች እናት ሲሆኑ ባለቤታቸው አርሶ አደር ናቸው፡፡ ልጆች ማሳደግና የቤቱን ጓዳ ማዘጋጀት የሳቸው የሌት ተቀን ሥራቸው ነው፡፡ አንድ ቀን ባለቤታቸው ወደ ሥራ በሚያቀኑበት ጊዜ በአካባቢው የፈረስ ቤት መገንባቱና ሰዎችንም እያደራጁ ስለመሆኑ እንደሰሙና ሄደው እንዲጠይቁ ያማክሯቸዋል፡፡ ወ/ሮ ረሂማም ከቻልኩ ልሞክረው በማለት ወዳዛው በማቅናት በመመዝገብና በመደራጀት ሥራ መጀመራቸውን ያወሳሉ፡፡ የማኅበሩ አባላት 13ቱ ሴቶች ሲሆኑ አንድ ወንድም እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ቤት ከመዋል እንዲሁም የገንዘብ ምንጭ ከማግኘት አንፃር ይኼ ትልቅ ዕድል መሆኑንም ይናገራሉ፡፡

ይኸው ማኅበር የፈረሶችን ቤት በማፅዳት፣ ፈረሶቹ ሲመጡ ፊኖ በማቅረብ እንዲሁም ፈረሶቹ እንዲታጠቡ በሚፈለግበት ጊዜ የሻወር አገልግሎት በማቅረብ የገቢ ምንጭ ያገኛል፡፡

የሻወር አገልግሎትና የማቆያ (የኮቴ) አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ አምስት ብር ያስከፍላሉ፡፡ እስካሁን በሥራቸው ላይ ምንም ችግር እንዳልገጠማቸውና በጣም ደስተኛ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ ረሂማ ሎሚና ጓደኞቻቸው በመባል የሚጠራው ይኸው ማኅበር የፈረስ ቀለብ (ፊኖ) በኩንታል ከ700 እስከ 800 ብር ከገበያ የሚገዙ ሲሆን ከዚህም የ50 ብር ትርፍ ያገኛሉ፡፡

ወ/ሮ ረሂማ ለመጓጓዧ የሚጠቀሙባቸው ሁለት ፈረሶች እንዳሏቸውና በአቅም እጥረት እንጂ ፈረሶቹን ጋሪ አድርገው የገቢ ማግኛ ዘዴ ቢፈጥሩ ደስ እንደሚላቸው ይገልጻሉ፡፡

አንድ ፈረስ እስከ 4000 ብር እንደሚገዛና ጋሪው ደግሞ 18‚000 እንደሚሸጥ በመግለጽ ይኼን ሁሉ ልጅ እያሳደጉ ግን ጋሪውን መግዛት አለመቻላቸውን አጫውተውናል፡፡

ሌላው በማስመረቁ ወቅት ያየነው የአሳሌቾ የውኃ ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚህ ወረዳ ውኃ በቀላሉ ማግኘት በጣም ከባድ ፈተና ነበር፡፡ እናቶችና ሴቶች ልጆች ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት በሚፈጅ የእግር መንገድ እየሄዱ ነበር ውኃ የሚቀዱት፡፡ ለዚያውም የወንዝ ውኃ፡፡ ወ/ሮ ጢፉ አሻን የሚባሉ እናት እንደገለጹት በእንስራ የሚቀዱት ውኃ ለቀን በቂ ስላልሆነ እስከ ሦስት ጊዜ ያንን መንገድ መድገም ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለአላስፈላጊ ጉዳቶች ይዳረጉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የሚጠጡት ውኃም ከእንስሳት ጋር እየተቀላቀለባቸው ለሕመም ይዳረጉ እንደነበር አውስተዋል፡፡ ‹‹አሁን ግን ብሩክ ኢትዮጵያ በፈጠረልን ዕድል እዛው ደጃፋችን ላይ ንፁህ የውኃ አቅርቦት ልናገኝ ችለናል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ የውኃ ፕሮጀክት ላይ ለጋማ ከብቶችም ንፁህ ውኃ ማቅረብ መቻሉንም አይተናል፡፡ ይህ የውኃ ፕሮጀክት 5‚000 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ከ10,000 በላይ የጋማ ከብቶችም እንደሚጠቀሙ ተገልጿል፡፡

ኢኮኖሚው በግብርና የተመሠረተ በመሆኑና እስካሁን ሜካናይዝድ ባለመሆኑ ምክንያት እነዚህን የጋማ ከብቶች መጠበቅና መንከባከብ የእኛ ትልቅ የቤት ሥራ ነው ያሉት በፕሮጀክቶቹ ምርቃት ወቅት የተገኙት የምዕራብ አርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ከድር ወሌሞ ናቸው፡፡

እንደ ብሩክ ኢትዮጵያም ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መንግሥት ያልደረሰባቸውን ቦታውን በመሸፈን ትልቅ ሥራ እየሠሩ በመሆኑ ሊመሠገኑ ይገባቸዋል ሲሉም  አወድሰዋቸዋል፡፡

ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ከብሩክ ኢትዮጵያ ጋር አብረው እየሠሩ እንደሆነ በመግለጽ አሁን ላይ የተመረቁት ፕሮጀክቶች ለጋማ ከብቶች ብሎም ለማኅበሰቡ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በብሩክ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አገላለጽ፣ 40.2 ሚሊዮን ብር የፈጁት ፕሮጀክቶች በጣም በአነስተኛ ወጪ የተሠሩ ናቸው፡፡ ይኼም ደግሞ የሆነው ከመንግሥት ጋር በጋራ ስለምንሠራ ነው ብለዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ ‹‹በመጀመርያ በየአካባቢው ስንሠራ የምንጠቀመው የመንግሥት ቢሮ ነው፡፡ በመቀጠል ሥራዎቹን የሚሠሩት የመንግሥት መሐንዲሶች ሲሆኑ፣ ሥራውን ስንሠራ ጥበቃ የሚያደርግልን ደግሞ ማኅበረሰቡ በመሆኑ ብዙ የገንዘብ ወጪዎቻችንን ማቃለል ችለናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አብዛኛው ጊዜ ፈረሶች የሚጠቀሙት የጎማ ጫማዎችን በመሆኑ በብዛት ይንሻፈፋል ሚዛናቻውንም አይጠብቅም፡፡ በዚህም ምክንያት ጉልበታቸው ይንሻፈፍና ከአገልግሎት ውጪ ስለሚሆኑ ይጣላሉ፡፡ ይህ እንዳይሆንም ጫማ የማሻሻል ሥራ እየሠራን ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚጣሉ ፈረሶችና አህዮችንም በተመለከተ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋርና ከከንቲባው ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

እነዚህ እንስሶች በአብዛኛው የሚጣሉት በቁስል ምክንያት ሲሆን ይህንንም ቁስልን የሚያመጣውን የፈረስ በሽታ ለመከላከል ከሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጥናት እያካሄዱ እንደሆነና እንዴት መከላከል ይቻላል የሚለው ላይም በጋራ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...