Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ሚና በፀረ ኮሮና ዘመቻ

ዓለም አቀፍ ደረጃ የሰዎች ሕይወትን በመታደግ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ ማኅበራት ውስጥ ቀይ መስቀል ተጠቃሽ ነው፡፡ ለሰው ልጆች ዘብ የቆመ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋ በሕይወት ላይ አደጋ ከመከሰቱ በፊትና ከተከሰተ በኋላ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚንቀሳቀስ ማኅበር ነው፡፡ በ1927 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በመከላከልና አደጋ ሲከሰት ደግሞ ቀድሞ በመድረስ ከስምንት አሠርታት በላይ ሕይወትን ሲታደግ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ የሰው ልጅ ፈተና የሆነውን የኮሮና ቫይረስ አገሮችን ትንቅንቅ ውስጥ አስገብቷል፡፡ ቫይረሱ ከገባባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው እየሠራ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ እያከናወነ ስላለው ተግባር የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ መሸሻ ሸዋረጋን (ዶ/ር) ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ማኅበሩ ምን ዓይነት ሥራዎችን እየሠራ ነው?

ዶ/ር መሸሻ፡- የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ – 19) በቻይና ተከሰተ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በጎ ፈቃደኞች ግንዛቤ መስጠት፣ በአሥራ አንድ ቅርንጫፎቻችን የሚገኙትን አባሎቻችን ግንዛቤ ስናስጨብጥና እንዴት መከላከል ይቻላል የሚለው ላይ በደንብ እየሠራን ቆይተናል፡፡ ኮሮና ቫይረስ ክስተት ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ከጤና ሚኒስቴር ጋር መሥራት ከጀመርን ሁለት ወራት አልፎናል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል፣ በጤና ሚኒስቴር ቀጥተኛ አመራር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ እንደ ባለድርሻ አካል ከፌዴራል እስከ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በማስተባበር በተቋቋሙ ዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ውስጥ በመሳተፍ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ እስካሁን የሠራቸው ሥራዎች ምን ምን ናቸው?

ዶ/ር መሸሻ፡- በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ200 በጎ ፈቃደኞች ሙያዊ ሥልጠና በመስጠት፣ ለ4‚000 ባለድርሻ አካላትና ተጋላጭ የኅብረተሰብ አካላት ግንዛቤ መስጫ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ስለኮሮና ቫይረስ ምንነት፣ እንዴት እንደሚተላለፍ፣ እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣ የምክር አገልግሎት እንዴት እንደሚሰጥ በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ እየተሠራ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በኋላ በስፋት የምንሄድበት ሆኖ፣ ለትምህርት ቤቶች፣ በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ወገኖችን ጨምሮና ለሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ፈሳሽ ሳሙናና ንፅህና መጠበቂያ ተሠራጭተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የንፅህና መጠበቂያው ምን ያህል ነው? የንፅህና መጠበቂያውን መስጠት ብቻ በቂ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?

ዶ/ር መሸሻ፡- ከአምስት ሺሕ በላይ የሚሆን የንፅህና መጠበቂያዎች አሠራጭተናል፡፡ የንፅህና መጠበቂያ መስጠት ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ በተቻለው መጠን ተፋፍጎ እንዳይሄድ እንዳይንቀሳቀስ ግንዛቤ እናስጨብጣለን፡፡ በሌላ በኩል ትራንስፖርት ላይ በአብዛኛው ሰዎች ለጥቂት ኪሎ ሜትር ብሎ በታክሲ፣ ባስ ከሚጠቀም በእግር መሄድ ራሱንና ወገኑን መታደግ እንደሚቻል ለማስረዳት እየጣርን ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በአዲስ አበባ ከተማ እጅ የማስታጠብና ከተዋስያን እጅን የማንፃት ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የድንኳን አቅርቦት በመደገፍ፣ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያዘጋጀውን የግንዛቤ ማስጨበጫ በማኅበሩ መረጃ መረብ እንዲጫን ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛው ማኅበረሰብ ገጠራማ ቦታዎች ነዋሪ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ቴክኖሎጂ በሌለበት ቦታዎች ስለቫይረሱ ግንዛቤ ያላገኙ ቦታዎችን ማኅበሩ ምን ለማድረግ አቅዷል?

ዶ/ር መሸሻ፡- አሁን ያደረግነው እንደ ጅማሮ እንጂ ሥራችን በዚህ ያበቃል ማለት አይደለም፡፡ ማኅበሩ የሰው ሕይወትን ለመታደግ ያለንን አቅም አሟጠን እንጠቀማለን፡፡ እንደ ማኅበርም በዚህ ጉዳይ ላይ እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙ ተቋሞች ተሳትፎ ስለሚያደርጉ ችግሩ ይቀረፋል ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም በሕክምና አሰጣጥ የተሻሉ የተባሉ አገሮች መቋቋም እንዳቃታቸው እየታየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ በቂ የሕክምና ባለሙያና የሕክምና ግብዓት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ አሁን አገሪቱ ባላት አቅም ቫይረሱን ለመከላከልም ሆነ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ለመንከባከብ በቂ የሕክምና ሀብት አለ ማለት ይቻላል?

ዶ/ር መሸሻ፡- አሁን ባለው ነገር መንግሥት ሆነ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ቫይረሱ ከመሠራጨቱ በፊት ባለው አቅም እየሠራ ነው፡፡ እርግጥ ያለን የሕክምና አሰጣጥም ሆነ በቂ የማገገሚያ ቦታዎች እጥረት ቢኖርም እንደ ማኅበር የሰውን ሕይወት ለመታደግ የትኛውንም ዓይነት ዕርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አንልም፡፡ እንደ ማኅበር ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽንና እህት ማኅበራት ጋር በመሆን 5‚000 የፊት ማስክ፣ 6‚000 ሰርጀሪካል ጓንት፣ 1‚500 የሕክምና ጫማዎች፣ 1‚000 የፕላስቲክ የፊት መከላከያና 5‚000 መለያ ጋውኖችን ለመግዛት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መድቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ500 በላይ የሚሆኑ አምቡላንሶችን አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶላቸው ለማገልገልም ዝግጁ ሆነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የአውሮፕላን መዳረሻዎች ላይ ምን ዓይነት ሥራ እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር መሸሻ፡- ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት በጎ ፈቃደኞችን በአዲስ አበባና በክልል አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ከአጎራባች አገሮች ወደ ኢትዮጵያ መግቢያ ኬላዎች ላይ የሙቀት ልየታ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል በከተማ  አስተዳደሩ አማካይነት ከተዋህስያን ማንፃት የሚችል ዲተርጀንት በከነማ ፋርማሲዎች አማካይነት ማሠራጨት ጀምሯል፡፡ የነበረውን ወረፋ ለመቀነስ በየ ፋርማሲዎቹ ከ100 በላይ በጎ ፈቃደኞችን አሠማርተናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አምቡላንሶች ላይ ለሚሠሩ ሙያተኞችም  ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ግንዛቤ አስጨብጠናል፡፡ ይህ ማለት በቂ ነው ማለት ሳይሆን በየጊዜው ክፍተቶች ለመሙላት ማኅበሩ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኅብረተሰብ ያለጥንቃቄ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ምን መደረግ አለበት?

ዶ/ር መሸሻ፡- አሁን ባለው ነገር የኢትዮጵያ  ቀይ መስቀልና መንግሥት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብቻ መከላከል እጅግ ይከብዳል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ በዚህ ወቅት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም ራሱን፣ ቤተሰቡንና ማኅበረሰቡን ከቫይረሱ መጠበቅ አለበት፡፡ በጎ ፈቃደኞችም ሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች መጀመርያ ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ አለበለዚያም ሥራችን ውኃ ቅዳ ቅኃ መልስ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በሰው ልጆች ላይ የመጣውን ፈተና መቋቋም የሚቻለው ሁሉም ተረባርቦ መከላከልና ግንዛቤ ለሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ነው፡፡ በተለይም በየክልል ከተሞች ያሉ ወጣቶች በገጠራማ ቦታዎች እየሄዱ ኅብረተሰቡን መታደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም አገሪቷ ባላት አቅም አነስተኛ በመሆኑ ሁሉም መረባረብና ራሱን ከቫይረሱ በመጠበቅ ማኅበራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...