Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሌላ ዙር እከከኝ ልከክህ. . .?

ሌላ ዙር እከከኝ ልከክህ. . .?

ቀን:

በቁምላቸው አበበ ይማም

አሜሪካ ካሏት አሰላሳዮች ቀዳሚ የሆነው የሀርቫርድናየል ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቅ፣ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሊቅ፣ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ተናጋሪ ፋሪድ ዘካሪያ በእዚያ ሰሞን ዋሽንግተን ፖስት ላይ ባስነበበን መጣጥፉ፣ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ግንኙነት  የሚመራው በስሜት፣ በጥድፊያ፣ በግዴለሽነትና በእንዝህላልነት እንጂ መሬት በረገጠና አበክሮ ተጠንቶ በታቀደ ፖሊሲ አይደለም ሲል ይተቻል፡፡

አሜሪካ የዓለም ፖሊስነቷ ማብቃት አለበት በሚል አመክንዮ ከሶሪያ ድንገት ሦስት ሺሕ የአሜሪካ ጦር አባላትን በማስወጣት ቀጣናውን በኢራን እጅ እንዲወድቅ ካደረገ በኋላ፣ ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ጦር ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ አዝምቷል፡፡ ለምን ሲባል ሳዑዲዎች እጅ በእጅ ስለሚከፍሉን ነዋ ብሏል፡፡ የኢራኑን ጄኔራል ቃሲም ሱሊማኒን በማስገደል ኢራን አጠፋውን ለመመለስ ስትንቀሳቀስ ትራምፕ ሰበብ በማድረግ ወደ የኢራንን መከላከያ ያዳክማል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ኢራቅ በሚገኘው የአሜሪካ ሁለት የጦር ሠፈሮች ላይ ቴህራን ጥቃት ስትሰነዝር እንዳላየ እንዳልሰማ ማለፍን መርጧል፡፡  ለዚህ ነው ጎምቱው የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ጠቢብ ፋሪድ ዘካርያስ ወለፈንድ የሆነውን የትራምፕ የውጭ ግንኙነት መርህ”፣ በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ ስሜትና ግብታዊነት ወርዷል የሚለው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለፈው ወር የተከበረውን የዓለም ሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ይመስላል የቀድሞዋን የዴሞክራት ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ፣ ቀዳማዊ እመቤትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተንን በሲኤንኤን በየሳምንቱ በሚያዘጋጀው ተወዳጁ ‹‹Global Public Square GPS›› ላይ አቅርቧት ነበር፡፡ ለትራምፕ የውጭ ግንኙነት መገበያየት የንግድ ውል መፈጸም (Transactional) ነው ስትል በነገር ወጋ አድርጋዋለች፡፡ የውጭ ግንኙነት  እንደ ሪል ስቴት ሽያጭ አይደለም ማለቷ ነው፡፡

ትራምፕ የሪል ስቴት ባለፀጋ እንደሆነ ያስታውሷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚነደፍበትና የሚመራበት የራሱ ስትራቴጂና ባህል አለው፡፡ ትራም በግብዝነት ራሱን የተዋጣልኝ ተዋዋይና ተገበያይ (Deal Maker) ነኝ ቢልም፣ ከቻይና ጋር ያደረገው የንግድ ስምምነት፣ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የወጠነው የፀረ ኑክሌር ጦር መሣሪያ ስምምነት ኪምንና አገዛዙን እንዳጀገነ ትራምፕንና የውጭ ጉዳይ አካሄዱን እንዳኮሰመነ ከሽፏል፡፡

ፍልስጤማውያንን ያላሳተፈው የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ዕቅዱ ሒላሪ እንደምትለው፣ የአፍጋኒስታን ቅቡል መንግሥትና ኔቶን (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን) ያላሳተፈው የታሊባንና የአሜሪካ የሰላም ስምምነት ቀለማቸው ሳይደርቅ ከሽፈዋል፣ ጨንግፈዋል፡፡ ወደ 20 ዓመታት የተጠጋው የአሜሪካና የኔቶ  የአፍጋኒስታን ቆይታ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ሕይወታቸውን የገበሩለት፣ የቆሰሉለት፣ አሜሪካውያን ከትሪሊዮን ዶላር በላይ የገፈገፉለት እልህ አስጨራሽ ጦርነት የተነሳለትን ዓላማ ማለትም ታሊባንን፣ አልቃይዳንና አይስን ሳይረታና የአፍጋኒስታንን መንግሥት በሁለት እግሩ ሳያቆም፣ ድንገት በስሜት ተነስቶ ከታሊባን ጋር ለመስማማት ያደረገው ጥረትም ቀናትን ሳይሻገር ጥላ አጥልቶበታል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር በስንት ድካምና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከተፈረመው ባለብዙ ተዋንያን የኢራን ኑክሌርና የአካባቢ ጥበቃ ስምምነት፣ ያለ ምንም አማራጭ የመፍትሔ ሐሳብ መውጣቱን ሒላሪን ጨምሮ የዘርፉ ልሂቃን አምርረው ይተቻሉ፡፡ ትራምፕን በአሜሪካ ታሪክ ሥልጣን ላይ እያለ የተከሰሰ ሦስተ ፕሬዚዳንት (Impeached President) ያደረገው የእከከኝ ልከክህ (Quid Pro Quo) ቅሌትም ሆነ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላልና አለቃቀቅ የሦስትዮሽ ድርድር ድንገት  ዘው ብሎ የገባበት መግፍኤ የከሸፈው፣ በደመ ነፍስ የሚመራው የውጭ ግንኙነቱ ቅርሻ መሆኑን ያሳያል፡፡

የ‹‹Quid Pro Quo›› ሥረወ ሐረግ ላቲን ሲሆን፣ ትርጉሙም ይህን ካደረክልኝ በምላሹ እንዲህ አደርግልሀለሁ ነው፡፡ ‹‹አበው እከከኝ ልከክህ›› እንደሚሉት፡፡
እ.ኤ.አ. ሐምሌ 25 ቀን 2019 ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የቀድሞ ኮሜዲያንና የቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ፣ የአሁኑ አዲስ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዜሌኒስኪ ስልክ ይመታና ‹‹እንኳን ደሳለህ፣ አስተዳደሬ ከአንተ ጋር ተቀራርቦ የመሥራት ብርቱ ፍላጎት አለው፡፡ ዳሩ ግን አንድ ውለታ እንድትውልልኝ እፈልጋለሁ. . .›› ይላል፡፡ እ.ኤ.አ. 2020  የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዴሞክራቶችን የዕጩነት ፉክክር እየመሩ ያሉትንና ተፎካካሪውን የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ባይደን፣ ልጃቸው ሃንተር ባይደንንና የሚሠራበትን ኩባንያ በሪዝማን ላይ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. 2016 ምርጫ አስመልክቶ የዩክሬን መንግሥት ምርመራ እንዲከፍትና ይኼንንም በዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ መግለጫ እንዲሰጥ ይጠይቃል፡፡ ትራምፕ ይኼን ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው የእንደራሴዎችም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዩክሬን መንግሥት ያፀደቀውን 400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወታደራዊ ዕርዳታ በመያዝ ነው፡፡

ዴሞክራቶች፣ ደጋፊዎቻቸውና ልሂቃን ትራምፕ እ.ኤ.አ. 2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪው ባይደን ላይ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ለቅስቀሳ የሚሆነውን ክስ ለማደራጀት ሞክሯል በሚል፣ ‹‹በእከከኝ ልከክህ›› ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የከሰሱት፡፡ እ.ኤ.አ. 2016 ምርጫ ሩሲያ ትራምፕ እንዲያሸንፍ የሒላሪን ኢሜይሎች በመዘርገፍና የዴሞክራቶችን ሰርቨር በመስበር ለትራምፕ መመረጥ ዕገዛ አድርጋለች የሚለውን ክስ በመረጃና በማስረጃ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ሩሲያ ግን ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብላ ሽምጥጥ አድርጋ ከመካዷ አልፎ የሒላሪንም ሆነ የዴሞክራቶችን ሰርቨር ሰብሮ መረጃ የመዘበረው ዩክሬን የሚገኝ ቡድን ነው የሚል የሴራ ልፈፋ አላት፡፡

ትራምፕ ይኼን የሩሲያ የፈጠራ ክስ ደግፎ ነው እንግዲህ፣ ዜሌኒስኪን እ.ኤ.አ. 2016 ምርጫ እንዲያጣራለት ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው፡፡ ሥልጣኑን ያላግባብ በመጠቀም  ዴሞክራቶች ትራምፕ ላይ ባካሄዱት ምርመራ አብላጫ መቀመጫ በያዙበት ምክር ቤት ተከሳሽነቱን በመረጃና በማስረጃ አረጋገጡ፡፡ ሆኖም ሪፐብሊካኖች አብላጫ ወንበር የያዙበት የእንደራሴዎች ምክር ቤት በሁለት አብላጫ ድምፅ ነፃ አውጥቶታል፡፡ ዳፋው ግን ለዘለዓለም ከትራምፕ ሰብዕና ጋር ይኖራል፡፡ አሜሪካውያን በታሪካቸው እንደዚህ በአይዶሎጂ ተከፋፍለውዓይንና አፍን ሆነው አያውቁም፡፡

ዓይንህን ለአፈር እየተባባሉ ነው እንግዲህ ወደ 2020 ምርጫ የሚገቡት፡፡
ትራምፕ የገባበትና የነካው ድርድር ሁሉ እርግማን ሆኖ ነው የሚጠናቀቀው፡፡ ምናልባት ከሰሜን አትላንቲክ የነፃ ንግድ ስምምነት (NAFTA)  ውጪ የሆነለት የለም የሚባለው ለእዚህ ነው፡፡ በቅርብ የሚያውቁት ትራምፕ ሽንፈትን መቀበል የማይወድና እልኸኛ ስለሆነ፣ በእዚህም በእዚያ ብሎ የከሸፉበት ድርድሮች ላይ ነፍስ ለመዝራት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ለመመረጥ ካበቁት ነገሮች አንዱ የተዋጣልኝና የለየልኝ ተደራዳሪ ነኝ የሚለው ቅስቀሳ ቢሆንም በተግባር ስላልተሳካለት2020 ፕሬዚዳንታዊ ውድድር ለመራጮቹ አሳካሁት የሚለው ድርድር ፍለጋ ገበያ ወጥቷል፡፡ ይህ ትራም ለራስ ያለው ልዩ ግምት፣ ራስ ወዳድነትና መታበይ ነው እንግዲህ አገራችንን ለመስዋዕትነት ያሳጫት፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወደ አሜሪካ፣ እስራኤልና የዓረቡ ዓለም ፖለቲካ ጎትቶ የዘፈቃት፡፡ አገራችንም ሆነች የለውጥ ኃይሉ ሳይፈልጉ እንደ ገና ዳቦ ከታችና ከላይ የእሳት ላንቃ በሚንቀለቀልበት የመካከለኛው ምሥራቅ ምድጃ የተጣዱት፡፡

መንግሥት ከታች የአገር ቤቱ ፍም ከላይ የእነ ጄርድ ኩሽነርናግብፅ ረመጥ እየነደደበት የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ ሰጠ፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን በደም በአጥንታቸው አስጠብቀው ያቆዩንን ሉዓላዊነት አስደፈረ፣ የከፍታችን ምልክትና ሰንደቅ ዓላማ የሆነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለትራምፕ አመቺ የሰላም ዕቅድ መስዋዕት አደረገ በማለት ብዙ ተብሏል፡፡ እስራኤል በይፋ እንደ አገር ከተመሠረተች እ.ኤ.አ. 1948 አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠር ግን የከሸፉ የሰላም፣ የዕርቅ ውይይቶችና ድርድሮች በአሜሪካ፣ በፈረንሣይ፣ በእንግሊዝ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በዓረብ ሊግ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአውሮፓ ኅብረት አነሳሽነትና ሸምጋይነት ተከናውነዋል፡፡

ሁለት ክፍለ ዘመኖችን ማለትም 20ኛውን ተሻግሮ  21ኛውን የተያያዘ የጂኦ ፖለቲካ ጨዋታ እያሉ ይሳለቁበታል፣ ጠብ የሚል ነገር ያጡበት ልሂቃን፡፡ የጨዋታውን ሕግ የሚያውቁት አሜሪካና እስራኤል ብቻ ናቸው፡፡ ተጫዋችም ዳኛም እነሱ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. 1970 የሮጀርስ የሰላም ዕቅድ አንስቶ በእዚያ ሰሞን ዶናልድ ትራምፕአማቹ ጄርድ ኩሽነር አጋፋሪት የተዘጋጀውና ትራምፕ ‹‹ክፍለ ዘመኑ የሰላም ዕቅድ›› ሲል ያሞካሸው ይጠቀሳል፡፡ ይህ የሰላም ዕቅድ ከጅምሩ ባለድርሻ አካላትን በተለይ ፍልስጤማውያንን፣ የአውሮፓ ኅብረትን፣ የዓረብ ሊግን ያላሳተፈ ስለነበር ገና የኅትመት ቀለሙ ሳይደርቅ፣ ከዋይት ሐውስ እግሩን ሳያነሳ የፍልስጤም ነፃ አውጭ ድርጅት (ፒኤልኦ) ሊቀመንበር መሐመድ አባስና ዋና ተደራዳሪው ሳይብ ኤራካት እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው አውግዘውታል፡፡

አንዳንዶችም የሰላም ዕቅዱን ከአፓርታይድ የባንቱስታን አገዛዝ ጋር አመሳስለውታል፡፡ ይሁንና የዓረቡ ዓለም እንደ ትናንቱ ዛሬም በአንድነት መቆም ባለመቻሉ፣ እነ ሳዑዲ ዓረቢያም ከኢራን ጥቃት የምትጠብቃቸውን አሜሪካን ላለማስከፋት፣ ግብፅም በየዓመቱ ከአሜሪካ የምታገኘው በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወታደራዊ እርጥባን እንዳታጣ፣ ከሁሉም በላይ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሦስትዮሽ ድርድር ላይ ጫና በማድረግ  እንድታግዛት የፍልስጤማውያንን ህልውና አደጋ ላይ እንደ ጣለ ስለሚነገርለት፣ የትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ኢፍትሐዊ የሰላም ዕቅድ ዝምታን መርጣለች፡፡

ለዚህ ውለታዋም አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት በድርድሩ ለመገኘት ተስማሙ፡፡ እንግዲህ ከዩክሬንእከከኝ ልከክህ” (Quid Pro Qou) በኋላ የተከሰተው ከግብፅ ጋር በዲፕሎማሲያዊ ማኅበረሰብ ኮሪደር ግብፅ ብትችል፣ የትራምፕን የመካከለኛው ምሥራቅን የሰላም ዕቅድ በዓረብ ሊግ አማካይነት እንድትደግፍ ባትችል ተቃውሞውን ከማጋጋል እንድትታቀብ ተስማማች፡፡

በአፀፋው አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተፅዕኖ በማሳደር የግብፅን ጥቅም ማስከበር ጀመረች፡፡ እንዲሁም የዓለም ባንክ የገንዘብ ተቋማትንና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችን ወክሎ የተገኘው፣ ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቃል የተገባውን አሥር ቢሊዮን ዶላር በመያዣነትና በመደራደሪያነት ይዞ ነው ወደ ታዛቢነት የገባው፡፡ የገንዘብ ተቋማቱ በአሜሪካ የሚጠመዘዙና በሪሞት መቆጣጠሪያ ቁጭ ብድግ እንደሚሉ ስንታዘብ፣ ለእነ ትራምፕም በመደራደሪያነት ጥቅም ላይ ለመዋላቸው ጥርጥር የለንም፡፡

ባልተለመደ ሁኔታ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይልቅ፣  የግምጃ ቤቱ ሚኒስትሩ ስቲቨን ምኑችንና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቭድ ማልፓስ በታዛቢነት መሰየማቸው ጥርጣሪያችን ይበልጥ ያጎላዋል፡፡ ይህ የአሜሪካ ስሁት አካሄድ የትራምፕ መንግሥት መጀመርያ ዩክሬን ላይ በማስከተል ግብፅ ላይ በመጨረሻም እኛ ላይ  እከኩኝ ልከካችሁ ማለቱን ልብ ይሏል፡፡ ትራምፕ እንዲከሰስ ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት የነበረው ዴሞክራት የምክር ቤት አባል አዳም ሺፍ በመከራከሪያነት ከፍ ሲልም በማስጠንቀቂያነት ያነሳው ጉዳይ፣ ‹‹ትራምፕ ተመሳሳይ ወንጀል ከመፈጸም ስለማይመለስ ተከሶ ከሥልጣን መባረር አለበት፤›› የሚል ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ ሚዲያ፣ ምዕራባውያንና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቁብ አልሰጡትም እንጂ ትራምፕ በዩክሬን ላይ የፈጸመውን ጥፋት ዓይነት በአገራችንም ደግሞታል ማለት ይቻላል፡፡ በዩክሬን ፕሬዚዳንትና አስተዳደራቸው ላይ ጫና ይደረግባቸው እንደነበረው ሁሉ፣ በአገራችን ተደራዳሪዎችና በመንግሥት ላይ እጅ የመጠምዘዝ ሙከራ ተደርጓል፡፡

የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ እየተደረገ በሚገኘው ድርድር ጫና እንደ ደረሰባቸው ኢትዮጵያን ወክለው የሚደራደሩት የሕግና የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ የካቲት 9 ቀን 2012 .ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ማስታወቃቸውን ይኼው ጋዜጣ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

መደምደሚያ

ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የመመረጥ ህልሙ መሠረት (Constituencies) የሆነትን ወንጌላውያንን፣ የእስራኤል ታማኝ ደጋፊዎችና ቀኝ ዘመም መራጮችን ድጋፍ ለማግኘት ቀደም ሲል የገባውን ቃል ለመፈጸም ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይኼን ድጋፍ ለማግኘት በልጁ ኢቫንካ ባል ጄሪድ ኩሽነር ፊታውራሪነት እየሩሳሌም የማትከፋፈል የእስራኤል መዲና መሆኗን በማወጅ፣ ኤምባሲውን ከቴላቪቭ ወደ እየሩሳሌም በማዛወር ቀደም ሲል የሁለቱ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቶች ለዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድንጋጌዎችና ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም ሲሉ በጥንቃቄ የያዙትን ጉዳይ ለምርጫ ሲል ጭዳ አድርጎታል፡፡

ይህ ትራምፕ ለመመረጥ የሚያግዘው ከሆነ ምንም ከማድረግ የማይመለስ እልኸኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ፍልስጤማውያንን ያላሳተፈው ‹‹የክፍለ ዘመኑ የሰላም ፍኖተ ካርታ›› የዚህ አካል ነው፡፡ ፍልስጤማውያንም ሆኑዓረብ ሊግ የተቃወሙት ቢሆንም፣ ግብፅንና ሳዑዲ ዓረቢያን በመጠቀም የፍልስጤሙን ፒኤልኦን ወደ ድርድር ለማምጣትና የዓረቡን ዓለም ለመከፋፈል ግብፅ ከማንም በላይ ታስፈልገዋለች፡፡ ግብፅ በበኩሏ ከፍልስጤም ይልቅ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ እንቅልፍ ነስቷታል፡፡

ስለሆነም በግድቡ የሦስትዮሽ ድርድር አሜሪካ በታዛቢነት ስም እንድትገባና በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድትፈጥር ሸሩ ቀድሞ ተሸርቧል፡፡ ነጮች የተቀረው ታሪክ ነው ይሉታል እንዲህ ዓይነቱን ሁነተ ቅጥልጥል፡፡ ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሰው ሔሮዶተስ ‹‹ግብፅ የዓባይ ስጦታ ናት›› ሲል ግብፅ የኢትዮጵያ ስጦታ መሆኗን ልብ ያላሉት ግብፃውያን፣ ለናይል ወንዝ 86 በመቶ ከለምለሙ ማህፀኗ እንደሚገማሸርና ተፈጥሯዊ ባለመብትም እሷው መሆኗን ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት የግብፅ ፖለቲከኞች ሟቹ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ የሚመሩት ስብሰባ ላይግድቡ ላይ እንዴት እንደሚያሻጥሩ ሲዶልቱ፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በቀጥታ ሥርጭት ተመለከትን፡፡ አሁን ደግሞ የግብፅ ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባዔ ሶሊማን ዋድሀን፣ ‹‹የኢትዮጵያን ሴራ ግብፅ እጇን አጣጥፋ አትመለከትም፡፡ የናይል ወንዝ ተፈጥሯዊ ተጠቃሚነቷን ለማስከበር ማንኛውንም ዕርምጃ ትወስዳለች፤›› ሲሉ ዝተዋል፡፡

በተዘዋዋሪ ጦርነት አውጀዋል፡፡ የፈርዖኖቹ ግብፅ ይኼ ያዙኝ ልቀቁኝ የትም እንደማያደርሳት ተረድታ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንሚያረጋግጠው ድርድር ላይ ብታተኩር ይሻላል፡፡ ከአራት ኢትዮጵያውያን ሦስቱ መብራት የላቸውም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ዓባይን ጨምሮ የወንዞቻቸውን ዕፍታ ያለ ማንም ቡራኬና ይሁንታ የመጠቀም ተፈጥሮአዊም ዓለም አቀፋዊ መብት እንዳላቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከመንግሥት ጎን ቆመዋል ማለት ይቻላል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የማይታጠፍ ቃል ኪዳናችንና የሉዓላዊነታችን  አሻራ ነው፡፡
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ! አሜን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...