Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበዓባይ ጉዳይ ማንም ሊደፍረን የማይችለው በምክንያት ነው!

በዓባይ ጉዳይ ማንም ሊደፍረን የማይችለው በምክንያት ነው!

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ            

ኢትዮጵያ የፃድቃን አገር ነች ሲሉን ቀልድ እየመሰለን በፌዝና በቀልድ የምንመለከት ብዙዎች ነን፣ የምንሳልቀም አንጠፋም፣ አሿፊውም ብዙ ነው። ግን ሳይደግስ አይጣለምና ብዙ መነኩሳት፣ ባህታዊያንና ታላላቅ ነቢያትም በየዕለቱ መጸለያቸውን አላቋረጡም፣ አያቋርጡምም። በፀሎታቸው ቅዱስ ሃይማኖቷን፣ ታሪኳን፣ ባህሏንና ወጓን ሳትለቅ ሕዝቧን ጭምር እነሆ እዚህ አድርሰዋታል። መቼም እንደ እምነታችን እንኑር! ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ እንደዘረጋች ገና አላጠፈችም። ይጠብቃታል ገና ብዙም ያሳየናል እንጠብቅ። ኢትዮጵያን ሊበድሉ ያቀዱ ሁሉ በእግሯ ሥር ሲወድቁ ታይቷል፡፡ እነ ማን ብትሉኝ? እነ ካዲቭ እስማኤል፡፡ የግብፁ መሪ በ1875 ዓ.ም. በማናለብኝነት ኢትዮጵያን ሊያንበረክክ 20,000 ወታደሮች ልኮ፣ የወታደሮቹ መሪ ሙላይ ሐሰን ፓሻ ከእነ ሠራዊቱ ተሸንፎ ሊያመልጥ ሲሞክር ተማርኮ ንጉሡ ፊት ቀርቦ ክንዱ ላይ ሁለት መስቀል ተከትቦበት በእስር ቆይቶ በግብፅ መንግሥት ልመና፣ በኢትዮጵያ መሐሪነት ሐሰን ፓሻ የጦሩ መሪና ተከታይ ወታደሮቹ መለቀቃቸው አንዱ የግብፅ አጉል ምኞትና ማናለብኝ ባይነትን፣ የኢትዮጵያን መሐሪነትና ይቅር ባይነትን ያሳየናል፣ አሳይቷቿዋል።

ዛሬ በማናለብኝነት የዓረብ ማኅበራትን (ሊጎቿን) የሃይማኖት ወዳጆቿንና የፖለቲካ ወገኖቿን በማሠለፍና በጉልበትም የማስፈራራት ታክቲኳን ካላቋረጠች፣ ከኢትዮጵያ ጋር ዓለም አቀግ ሕግ በሚፈቅደውና ሁሉን ጠቀም በሆነ መንገድ የማትስማማና የራሷን ጥቅም ብቻ በበላይነት የማስቀደም ትዕብቷ የማታቆም ከሆነ፣ እኛም የራሳችንን መንገድ መቀየስ ይኖርብናል። ዓባይ ከአንድ ቦታ ተነስቶ የሚፈስ ሳይሆን ከየመጋቢ ወንዞች ተጠራቅሞ ለግብፅ የተረፈ መሆኑን ያልተገነዘቡ ግብፆች እንዲገነዘቡት፣ ኢትዮጵያ መጋቢ ወንዞቿን በየቦታው ለልማት መገደብና ወደ ዓባይ ሙሌት ከመሄዳቸው በፊት አካባቢያቸውን እንዲጠቅሙ መዘጋጀትና የራሳችንን ልማት ማጠናከር የረዥም ጊዜ ችግር በግብፅ ላይ ማምጣት ይቻላል፡፡ ይህ በትክክል ታቅዶበት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ መክረውበት ቢሠራ ለግብፅ የዘለዓለም ችግር፣ መከራና ትምህርት እንደሚሆን መገንዘብ ይቻላልና ይህ በጥብቅ ሊታሰብ የሚገባ ታክቲክ መሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።               

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እነ እንግሊዝ፣ እነ ጋዳፊ፣ እነ ሳዳም ሑሴን ሳይተኙልን ዋጋቸውን የኢትዮጵያ አምላክ ከፍሎ አይተናል። ግብፅ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ድርጊቶቿ ሳትማር አሁንም እንደ ቀድሞው እየተሳሳተች ነው። ሌሎች በትዕቢት ተመክተው ሊያዋርዱን የፈለጉ ሁሉ ወድቀው መሠረታቸው ወደ መንኮታከት ደርሶ አየን አይደል? ከታላቋ እንግሊዝ ልጀምርላችሁና ልቀጥል፡፡ ጣሊያን አገራችንን በግፍ በወረረችበት ዘመን መጀመሪያ በ1920ዎቹ፣ የኢትዮጵያን በጣሊያን ቅኝ ግዛት መያዟን ያወቀችላትና ያረጋገጥችላት እንግሊዝ ነበረች። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ አምላክ ፍርዱን ሲሰጥ ጀርመን በዓለም ላይ ታላቅና አሸናፊ መስላ ስለታየች፣ ጣሊያን የጀርመን ወገን በመሆን ዳር ቆማ ስትመለከትና ልትጠቀምባት ስትዘጋጅ ጀርመን የአውሮፓ ቁንጮ ገዥ ለመሆን ዴንማርክ፣ ሆላንድ፣ ኖርዌይ፣ ቤልጅግ ለክስንበርግና ፈረንሣይ በጀርመን እጅ ሲወድቁ አልሞት ባይ ተጋዳይነት ፈረንሣይና እንግሊዝ ቆርጠው በጀርመን ላይ በሰኔ ወር 1932 ዓ.ም. ጦርነት አወጁ።

ጣሊያን በዚህ ጊዜ እያመነታች የጦር ሚዛኑ ወዴት እንደሚያጋድል ከዳር ቁጭ ብላ ስትመለከት፣ የፈረንሣይን ድል መሆን ካየች በኋላ ከአሸናፊው ጋር የጦር ጓደኛና የድል ተካፋይ ለመሆን ጓጉታ ነሐሴ 3 ቀን 1932 ዓ.ም. ወደ ጦርነቱ ጥልቅ ብላ ሳታመነታ ገባች። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ በቸሩ አምላካችን የተላከልን ዋናው በር መክፈቻ ሆነና እንግሊዝ ከጣሊያን ጋር መወገኗ ዕዳ እንጂ ጥቅም የማይሰጥ ጨዋታ መሆኑን ተገነዝባ፣ ፊቷን አዙራ ወደ ኢትዮጵያ መለሰች፡፡ በስትራቴጂውም በጦሩም የኢትዮጵያን ጀግኖች ረድቼ ይህንን ሰው በላ ልኩን የማያውቅ የዱቼ ሞሶሎኒን ወታደር ካላስወጣን፣ አድሮ ውሎ የእኛው ዕዳ ነውና እንረዳዳ በሚል መርህ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር ከቆራጡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ጋር ተመካከረች፡፡ በዚህም ጣሊያን በገባችበት ሁኔታ ሳይሆን፣ በምርኮና በእስር ተዋርዳ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ አጎንብሳ ጠይቃ ከኢትዮጵያ ምድረ ገጽ ጠፋች። ልብ በሉ ቀደም ሲል ጣሊያን በተዘዋዋሪ መንገድ አሰብን እንዲይዝ ያደረገች ዋናዋ ተዋናይ የነበረች ራሷ እንግሊዝ ነበረች። ኢትዮጵያም ሁሉንም በልቧ ይዛ ለፈለገችው ዓላማ ደረሰች፡፡ ትዕግሥትና ችሎታ ይሏችኋል ይህ ነው።                                                              

መሃሪና ፈሪኃ እግዚብሔርን አክባሪ ኢትዮጵያዊያንም ትናንትና ገደላችሁን፣ በቁም አቃጠላችሁን፣ በመርዝ ጋዝ ፈጃችሁንና ዘረፋችሁን ሳይሉ በፈጣሪ ትዕዛዝ መሠረት የጣሊያንን ግፍና በደል ትተው በይቅርታ አብልተውና አጠጥተው ሸኙት። ጀርመንም ተዋርዳ በዓለም ታላቅ ከመባል አሽቆልቁላ ወረደች። ይህ ከትናንት ወዲያ የሆነ ሲሆን፣ ትናንትና በእኛ ዘመን ዓለምን ያስጨነቀችው ሩሲያ የኢትዮጵያ የጥንት ወዳጅነቷን ረስታ ወደ ጠላትነት ዞራ ባህል የለሽ፣ ታሪክ የለሽ ኢትዮጵያን ፈጥራለሁ ብላ ከእነ አካቴው ራሷ እንዳልሆነች ሆና፣ እነ ብሬዥኔቭ ጠፍተው፣ በግፍ የገዛቻቸውም ግዛቶች ከእጇ አፈትለከው እነሆ የኢትዮጵያ አምላክ አሳየን፡፡

ዓባይን ቢሻቸው ተስማምተው ይጠቀሙ፣ ካልሆነም እንደ ልማዳችን አምላክን ከጎናችን መከታ አድርገን እንተያያለን። በቅኝ ገዥዎች ተዋርደውና እንደ ባሪያ ሲቀጠቀጡ የነበሩት እነ ግብፅ፣ ጌቶቻቸው አዘጋጅተው በሄዱበት መንገድ ኢትዮጵያን ሊሞክሩ ሲነሳሱ እስራኤልን የመሰለ ጀግና ጦር ፈርዶባቸው በማይረሳው የስድስቱ ቀናት ጦርነት ገማል አብዱልናስር ተዋርዶ ሳይሳካለት አረፈው፡፡ ሳዳትም አልተኛልንም ነበር፡፡ ግን ቸሩ ጠባቂያችን ፍርዱን እየሰጠ ሁሉንም በፊቱ አቆመ።                                                      እዩኝ፣ እዩኝ፣ ማን ከእኔ በላይ ባዩ ሳዳም ሁሴንም እንደ አይጥ ከተደበቀበት ጉድጓድ ተይዞ በቃሪያ ጥፊ ፊቱ ደም እስኪመስል እየተደበደበ ሰነባብቶ፣ በአደባባይ ስቅላት ተቀጣ (በክርስቲያን እንኳን ሞተ ባንልም ቅጣቱን ተቀበለ)። የሳዳም ታሪክ ተጽፎ ሳያልቅ ከእኔ በላይ ላሳር ባዩ ሙአመር ጋዳፊ ኢትዮጵያን ሊያጠፋ ለሚችል ሁሉ ረዳትና አጋር በመሆን፣ በማናለብኝነት ሲንቀባረር፣ ዓለም በሙሉ እንዳየው እሱም እንደ አይጥ ከተደበቀበት ተይዞ ፊቱ በደም ተጨማልቆ ማሩኝ፣ ማሩኝ እያለ ሲለምን ምሕረት ሳይደረግለት በውርደት ተሰናበተ። ተመልከቱ የአምላክን ሥራ! ሕጉን አክብሮ ትዕዛዙን ፈጽሞ ለተገኘ ፍርዱን ስለማይነሳ ይኸው አየነው።                                                                           

ሀብታሟ ኢትዮጵያ ሁሉም ቢመኟት የራሷን አትሰጥ የሰውም አትሻምና የአምላክን ዳኝነት ብቻ በመያዝና በልጆቿ ታማኝነት ኖረ፣ ትኖራለችም። ሳዳም ሁሴንና ሙአመር ጋዳፊ ምንም ጊዜም ተኝተውላት አያውቁም ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በሚስጥራዊ መንገዷ ስለምትጠበቅ የአምላኳ ዓይን ሁሌም ከእሷ ጋር ነው፡፡ ማንም ቢዳክር ጠባቂዋ በዋዛ ስለማይለቃት ኖረች፣ ትኖራለችም።                                                           “ኢትዮጵያን አትንኳት! የነካት የተረገም ይሁን!” ነብዩ መሐመድ  ያሉት ነው።                                                                                    የሚገርመው ነገር አሜሪካ አስተናባሪ፣ የገንዘብ ሚኒስትሯ ታዛቢ ወቸጉድ! አዛኝ ቅቤ አንጓች ሆነብኝና ነው። ይህ የአሜሪካ ሕዝብ ሐሳብ ወይስ ግራ የተጋባ ለፖለቲካ ሒሳብ ማወራረጃ የተቀየሰ ይሆን? በ1993 ዓ.ም. ይመስለኛል የኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ወኪል የሆነ ሰው በዓለም ባንክ ውስጥ ነበር፡፡ በዓባይ ጉዳይ በዓለም ባንክ ሕንፃ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሲካሄድ ከፓኪስታን፣ ከህንድ፣ ከግብፅና ከአውሮፓ አገሮች ሳይቀሩ ስብሰባው ውስጥ መግባት ሲፈቀድላቸው፣ የዓባይ አንጡራ ሀብት ልጅ ኢትዮጵያዊ ግን እንዳይገባ ተከልክሎ ሲያዝንና ሲበሳጭ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እኔም በወቅቱ ብስጭቱን ተካፍያለሁ። ታዲያ ማን ነበር ተዋናይ? እንዴት አድርጋ ነው አሜሪካ አስተናባሪ፣ ታዛቢና ገላጋይ ልትሆን የምትችለው? ወገኖቼ ይህንን ቀልድ አቁመን ራሳችንን ራሳችን እንዳኘው።

በአፍሪካ በጦር ሥልጠናና በጦር መሣሪያ ግብፅ አንደኛ ነች እያሉ ታላቅነቷን፣ ኃያልነቷንና ተሰሚነቷን የሚያወሩላት ሞልተዋል። ኢትዮጵያስ? ለማንም ያልተገዛች፣ ያልተንበረከከች፣ ለንዋይ ህልውናዋን ያልሸጠች፣ ለነፃነቷ ሟች፣ አልፋ ተርፋ ለዓለም መንግሥታት በጦር ሜዳ አለሁላችሁ የምትል የጀግኖች አገር ናት፡፡ ሽማግሌው፣ ወጣቱ፣ ሴትና ወንዱ ጥቃት የማይወድ ጀግና ሕዝብ እንኳንስ የሚወነጨፍ በሰማይ በራሪ መሣሪያ ይዞ በባዶ እግሩ በዶጋሊ፣ በዓደዋና በሌሎችም የጦር ግንባሮች የተዋደቀና ለጥቁር ሕዝብ ምሳሌ የሆነ ጀግና ሕዝብ ዛሬ ሠልጥኖ ዘመናዊ መሣሪያ አንግቶ ይደፈራል ብሎ ማመን የዋህነት እንዳይሆንባቸው ይጠንቀቁ። ይልቁንስ ለመጣው ሁሉ ተገዥ በመሆን በተቃረመ ውርስ መኩራራትና መዘባነን፣ ለኢትዮጵያዊያን ይህንን ያህል የሚያኮራ አይደለምና ይወቁት፡፡                                                                         

ወገኖቼ በመጀመሪያ ለሰላም መንገድ እንፈልግ፡፡ እምቢ ካሉ ትንሽ፣ ትልቅ፣ ሽማግሌ፣ ጎልማሳ፣ ሴት ወይም ወንድ ሳይባል ተዘጋጅተን እንከላከላለን፡፡ መከላከልን እንደ ፍርኃት የሚቆጥሩም ከሆነ እንዳመጣጣቸው አዋርደን ለመሸኘት እንዘጋጅ።                                                                   የዓለም መንግሥታት ንብረታችሁን አትጠቀሙ የሚል የአድልኦ መስመር የሚይዝ አይመስለኝም፡፡ ከያዘ ግን የዓለም መንግሥታት ወኪል ሳይሆን የግድ መንግሥት ግፊት መሆኑን ተገንዝበን፣ ተገቢው ውሳኔ ላይ ለመድረስ እንዘጋጅ። በውጭ አገርም ቢሆን ያለን ኢትዮጵያዊያን በወኪሎቻችን በኩል ትክክለኛው ፍትሕ እንዲታይ መሞከር ሳይሆን ባለን የዜግነት መብት፣ በምንከፍለው ታክስና ለአገሪቱ በምንሰጠው ግልጋሎት መሠረት ወኪሎቻችንን ለትክክለኛ ፍርድ እንዲቆሙ እንጠይቃለን።                                                                                              የራስህን አንጡራ ሀብት አሳልፈህ ለሌላ ሰጥተህ ለማኝ ሁን የሚል ሕግ ካለ፣ የኮሎራዶን ወንዝ አሜሪካ ሳትጠቀም ለሌላው አሳልፋ ትስጥ የሚል ሕግ ካለ፣ ዶናልድ ትራምፕ ያሳየንና ከዚያ በኋል ሁኔታዎችን በጥናት መልክ ለማየት እንሞክር ይሆናል።                                                                     በቀን አሥር ጊዜ አቋማቸውን የሚለዋውጡ የታላላቅ አገር መሪዎች አገራቸውን ከግምት ውስጥ ባያስገቡ መልካም በሆነ ነበር፡፡ ካልሆነም ራሳችንን በራሳችን ማስከበር ይኖርብናልና። ይህ አስተያየቴ ፍጹም በሆነ ዴሞክራሲያዊ መንገድ የተቀየሰና የታመነ፣ ማንም ማንን ሊጎዳ በማይችል መንገድ መጠቀምን ታላቋ አሜሪካም የምታምንበትና ለተጠቃሚ ወገን የምትቆምበት መንገድ በመሆኑ፣ ሰፊው የአሜሪካ ሕዝብ በተበዳይዋ ኢትዮጵያ በኩል ለእውነት እንዲቆም አሳስባለሁ።                                                                                   

ተመልከቱ እንግዲህ የእግዚብሔርን ነገር፡፡ ከላይ እንደ ጠቀስኩት ያኔ ሶቪየት ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ስታሴር ለራሷም ሳትሆን ተበታተነች። የእነ ጋዳፊን እንተወውና ወደ ግብፅ ብንሸጋገር ገማል አብዱልናስር በስድስቱ ቀናት ጦርነት እንደተዋረደ ሥልጣኔን ለቅቄያለሁ አለ፡፡ ነገር ግን ለምነው መለሱት፡፡ ያ ኃፍረት ሳይለቀው በተቀመጠበት ተሰናበተ። በመቀጠል አንዋር ሳዳትም በአሜሪካ የጊዜው ፕሬዚዳንት ካርተር አማካይነት የኢትዮጵያን ወንዝ መደራደሪያ በማድረግ፣ የእስራኤልን ችግር በኢትዮጵያ ላይ በመደፍደፍ ዕርቅ ወረደ ተባባሉ፡፡ መቼ የላይኛውን ጌታ ፍርድ አዩና? ሳዳትም ሄደ፡፡ ሁላችንም ሂያጅ ነንና መሄዱ አያስደንቀንም፡፡ ግን የምንሠራው ሥራ ነው የሚያስደንቀን። የዛሬው የግብፅ ጄኔራል ለማስፈራራት ቃጣው፡፡ ግን የእኛ አምላክ የት ሄዶ? በበረዶ፣ በአውሎ ንፋሱና በተለያዩ የእግዚአብሔር ቁጣዎች እረፍ፣ ይህችን አገር አትንካት እያለ ነው። ግን ልብ ከየት ይምጣ? ውለው አድረው እንደሚገነዘቡት ተስፋ አደርጋለሁ።                                             

ዛሬ ስለአዲሱ ተውሳክ ኮሮና ቫይረስ ይወራል። የኅዳር በሽታ የሚባል ወረርሽኝ የዛሬ 100 ዓመታት ገደማ በዓለም ላይ ልክ እንደ አሁኑ ተንሰራፍቶ በዓለም 50 ሚሊዮን ሕዝብ ሲያልቅ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለቀው በጣም አነስተኛ ነበር ይባላል። ይህ በቴክኖሎጂ ተራቀን ያቆመነው ወይም የገደብነው ሳይሆን፣ በአንድ አምላክ ቸርነትና አለኝታነት የተጠበቅንበት ሁኔታ ነበር፣ አሁንም አለልን። አሁንም አምላካችን በጥበቡ ይጠብቀናል ለእሱ እንተወው፡፡ የምንችለውን ያህል እንደ ሰው እንጠንቀቅ። ኢትዮጵያዊ የሞተን መቅበር፣ የሟች ወገንን ማፅናናት አንዱ ባህላችን ስለሆነ ታዲያ የሞተን ላንቀብር ነው? ወገኖቼ በአንድ አምላክ እመኑ፣ ምንም አትሆኑምና። በሉ በቸር ይግጠመን። መቼም አንብባችሁ ዝም የማትሉ መልስ መስጠትና መነጋገር ልምዳችሁ ነውና እንገናኝ።  ሁሉም በርሱ ሆነ! ለእሱ እንተወው!                                                                                                     

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...